እየበሉ መራብ

ሁለተኛው ጉዳይ
(ባለፈው ሳምንት ከወላጆች ጋር በሁለት ጉዳዮች ለመነጋገር ተነሥቼ ነበር፤ የመጀመሪያውን ሳምንት አቅርቤአለሁ፤ በየቦታው መወያያ መሆኑን ፍንጭ አግኝቻለሁ፤ እስኪ ሁለተኛውን ዛሬ ላቅርብ)
አንዲት እኅት እንዲህ አወጋችኝ
ለዶክትሬት ጥናቷ ከአሜሪካ ትመጣና አጎቷ ቤት ታርፋለች፡፡ አጎቷ ‹አላቸው› ከሚባሉት የከተማችን ባለ ሀብቶች አንዱ ነበር፡፡ ሁለት ወንዶች ልጆች አሉት፡፡ ልጆቹ የሰባትና የዐሥር ዓመት ልጆች ናቸው፡፡ ልጆቹ በተደጋጋሚ ይታመማሉ፡፡ በሳምንት ቢያንስ አንድ ጊዜ ከሐኪም ቤት አይጠፉም፡፡ ‹‹አንድ ጊዜ እኔ ምሳ ስበላ ልጆቹን ጠራኋቸውና አብረን እንድንበላ ጋበዝኳቸው፡፡ እንጀራ እንደማይበሉ ነገሩኝ፡፡ ምንድን ነው ታዲያ የምትበሉት? አልኳቸው፡፡ ከሱፐር ማርኬት የሚገዛ አንድ የምግብ ዓይነት ነገሩኝ፡፡ ሞግዚታቸውም ያንን ይዛላቸው መጣች፡፡ በዚያ ጊዜ አንዳች ነገር ከነከነኝና ምሳዬን ከጨረስኩ በኋላ ወደ ማዕድ ቤቱ ገብቼ ሞግዚቷን ጠየቅኳት፡፡ ምንድን ነው እነዚህ ልጆች አዘውትረው የሚበሉት? እስኪ አሳይኝ? አልኳት፡፡ መደርደሪያውን ስትከፍተው ሁሉም ከሱፐር ማርኬት የሚገዙ የተፈበረኩ ምግቦች ናቸው፡፡ እጅግ በጣም ገረመኝ፡፡ 

በቀጣዩ ቀን ከልጆቹ ጋር ብስክሌትና ኳስ አብሬ ተጫወትኩ፡፡ ብዙ ጊዜ ወላጆቻቸውን ስለማያገኙ ከእኔ ጋር በመጨዋታቸው ደስ አላቸው፡፡ ከሰዓትም አብሬያቸው እንድጫወት ለመኑኝ፡፡ እኔም ይህንን አጋጣሚ ተጠቅሜ ከእኔ ጋር አብረው ምሳ ከበሉ ብቻ እንደምጫወት ነገርኳቸው፡፡ ቅር እያላቸው ለጨዋታው ሲሉ ተስማሙ፡፡ ቋቅ እያላቸውም በምሳ ሰዓት እንጀራውን በወጥ አብረውኝ በሉ፡፡ ቃል እንደገባሁትም አብሬያቸው ተጫወትኩ፡፡ በቀጣዩ ቀን ከባልትና ቤት የገንፎ እህል ገዝቼ መጣሁ፡፡ ከዚያም ገንፎ ሠራሁና አብረን እንድንበላ ጋበዝኳቸው፡፡ እንደምንም በሉልኝ፡፡ ቆሎ የሚባለውን ነገርማ ነክተውት ቀርቶ አይተውት አያውቁም፡፡ እኔ ግን ቆሎ ለጥርሳቸው ጥንካሬ እንደሚጠቅም፤ ኳስ ተጫዋች መሆን ከፈለጉ ደግሞ መጠንከር እንዳለባቸው፤ ለዚህም ከልዩ ልዩ ጥራጥሬ የተሠራው ቆሎ እንደሚጠቅም ነገርኳቸው፡፡ አብሬያቸው እየተጫወትኩ ስለምነግራቸው ተቀበሉኝ፡፡
በመጀመሪያው ቀን ለጥርሳቸው እንዳይከብዳቸው ለዘዝ ያለ ቆሎ እንዲበሉ አደረግኩ፡፡ ኳስ እንጫወትና በዕረፍት ሰዓት ቆሎ በልተን ውኃ እንጠጣለን፡፡ የተሰጠውን ያህል ያልበላ ይቀጣል እያልን ጨዋታ አደረግነው፡፡ ቂጣውንም በዚህ መልክ ነበር ያስለመድኳቸው፡፡ ማር የተቀባ ቂጣ መብላት አልለመዱም፡፡ ብስክሌት ለመንዳት ግን ቂጣ አስፈላጊ መሆኑን ነገርኳቸውና በብስክሌታቸው ጭኜ ስንነዳ እንበላ ነበር፡፡
እንዲህ እያደረግኩ ሰምተዋቸውም ተመግበዋቸውም የማያውቋቸውን ምግቦች አስለመድኳቸው፡፡ የሚገርምህ ነገር በየሳምንቱ ሐኪም ቤት መሄዱ ቀረ፡፡ ለካስ የእነዚህ ልጆች ችግር የምግብ ችግር ነበር፡፡ ከሱፐር ማርኬት የሚመጡ ምግቦችን እንጂ በባህላችን የሚዘጋጁና ለልጆች የሚያስፈልጉ ነገሮችን የያዙ ተፈጥሯዊ ምግቦችን አይመገቡም ነበር፡፡ ለካስ ልጆቹ እየበሉ የሚራቡ ነበሩ፡፡
ወላጆቻቸው ገንዘብ አላጡም፤ መግዛት የማይችሉም አይደሉም፡፡ ነገር ግን ልጆቻቸውን የወደዱ የሚመላስቸው፣ ልጆቻቸውንም የተከባከቡ የሚመስላቸው ከየሱፐር ማርኬቱ የሚገዙ የተፈበረኩ ምግቦችን በመግዛት፣ በጣፋጮች በማንበሽበሽ፣ ለልጆቹ ስሜት እንጂ ለልጆቹ ጤንነት የማይጠቅሙ የተፈበረኩ ምግቦችን በመስጠት ነው፡፡ ለእነርሱ ዘመናዊነት ማለት የታሸገ ምግብ ነው፣ ጣፋጭ ምግብ ነው፤ የሚገዛ ምግብ ነው፡፡ ርግጥ ነው ልጆቹ ደስ ይላቸዋል፡፡ ‹‹ማሚ እወድሻለሁ፤ ዳድ እወድሃለሁ›› እያሉ ደስታቸው እንዲጨምር ያደርጉታል፡፡ ደጋግመውም እንዲገዙላቸው የሚፈልጉት ይህንኑ ይሆናል፡፡ እነርሱም ብላ አትብላ ከሚለው ጭቅጭቅ ይድኑ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ልጆቹን እየገደልናቸው ነው፡፡ በሁለት መንገድ፡፡
በአንድ መልኩ ማኅበራዊነትን እናሳጣቸዋለን፡፡ አንድ ልጅ ሀገሩን እንዲወድድ፣ ለሀገሩ እንዲያስብና ማኅበረሰቡን ዐውቆ የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣ ‹ማኀበር› socialization ያስፈልገዋል፡፡ ከማኅበረሰቡ ጋር መግባባት፣ መላመድና ማኅበረሰቡን መሆን፡፡ ከማኀበሪያ መንገዶች አንዱ ደግሞ አብሮ መብላትና መጠጣት ናቸው፡፡ እነዚህ ልጆች ሠርግ፣ ማኅበር፣ ተዝካር፣ ግብዣ እንዴት ነው የሚቀበሉት?  ነገስ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እንዴት ነው የሚሠሩት? በሌላም በኩል እዚህ ሀገር የሱፐር ማርኬት ምግቦች በዘላቂነት አይገኙም፡፡ ይቀያየራሉ፡፡ ዛሬ ወደ ሀገር ውስጥ ገብቶ ልጆችህ የለመዱት ምግብ ነገ የለም ትባላለህ፤ ያን ጊዜ ልጆቹን ሌላ ነገር ማስለመድ ችግር ይሆንብሃል፡፡
ምን ይሄ ብቻ፡፡ ብዙ ጊዜ የታሸጉ ምግቦች የሚሠሩባቸው ነገሮች ልጆችን ያቃዥቧቸዋል፡፡ ስሜታውያን አድርገው ዕረፍት አልባ ያደርጓቸዋል፡፡ ያን ጊዜ ልጆቹ ረባሾች፣ ቀዥቃዣዎች፣ የማይሰሙ፣ ቀልበ ቢሶች ተደርገው በወላጆቻቸው፣ በቅርብ ዘመዶቻቸውና በሌላው ማኅበረሰብ እንዲነወሩ ያደርጋቸዋል፡፡ ይሄም ለልጆቹ ከማኅበረሰቡ ጋር አለመቀላቀል አንዱ ምክንያት ይሆናል፡፡
ሁለተኛው ጉዳት ደግሞ ልጆቹን የቅንጦት ረሃብ ውስጥ መጣሉ ነው፡፡ ዛሬ ዛሬ በምዕራቡ ዓለም ተፈጥሯዊ ምግቦችን መመገብ የሥልጣኔና የጤንነት ምልክቶች ናቸው፡፡ ውድ ምግቦችም ተፈጥሯዊ ምግቦች ናቸው፡፡ እኛ ሀገር እነዚህን ተፈጥሯዊ ምግቦች ብዙ ጊዜ የሚያገኙት ‹ድኾች› ናቸው፡፡ እስኪ ዝም ብለህ እይ በከተሞቻችንኮ የተጠበሰ በቆሎ መብላት፣ ቆሎ መብላት፣ ንፍሮ መብላት እየቀረ ነው፡፡ እነዚህ ምግቦችኮ ያልያዙት የንጥረ ነገር ዓይነት አልነበረም፡፡ ገንፎ እንኳንስ ከምግብ ዝርዝራችን ከአራስ ቤትም እየጠፋ ነው፡፡ እኔ የጃፓኖች ምግብ ቤት ገብቼ ከዶሮ ሥጋ ጋር የተቀቀለ በቆሎ ነበር ያቀረቡልኝ፡፡ አሁን እኛ ሀገር እንግዳ ጠርተህ የተቀቀለ በቆሎ ብታቀርብ ስምህ ነው የሚጠፋው፡፡ አንተ ራስህ ግሪክ ሀገር የተጠበሰ በቆሎ በሰባት ዶላር መግዛትህን ስትናገር ሰምቼሃለሁ፡፡ እኛ ሀገር ግን የተጠበሰ በቆሎ ምብላት የድህነት ምልክት ነው፡፡
ልጆቻችንኮ የተመጣጠነ ምግብ እየተመገቡ አይደለም፡፡ ይህ የሆነው በማጣታችን ምክንያት ብቻ አይደለም፡፡ ርግጥ ነው በምግብ እጥረት የሚጎዱ ሚሊዮን ልጆች አሉን፡፡ እኔ ግን የማወራህ በቅንጦት ረሃብ ውስጥ ስላሉት ልጆች ነው፡፡ ድንች እንደ ልብ በሚገኝበት ሀገር፣ በርካሽ ገዝቶ ቀቅሎ ማብላት ሲቻል እንዴት የታሸገ ድንች ጥብስ እናበላቸዋለን፡፡ እኛ በውድ ዋጋ ገዝተን ከምናበላቸው የታሸገ የድንች ጥብስ ይልቅ እነዚህ መንገድ ዳር የተቀቀለ ድንች ገዝተው (እምቦቲቶ) የሚበሉት ይበልጣሉ፡፡ እነርሱ ጋር ችግሩ ንጽሕናው ነው፡፡ በይዘቱ ግን ትክክለኛውና ጤነኛው የእነርሱ እምቦቲቶ ነው፡፡ ቡላና የገብስ ቂጣ እንደልብ በሚገኝባት ሀገር እየኖርን እንዴት ልጆቻችንን በታሸገ ዱቄት እናሳድጋቸዋለን?
ይኼ ፈጽሞ ልጅን መውደድ ሊሆን አይችልም፡፡ የማይሆኑ ምግቦችን እየመገብን ልጆቻችን በትምህርታቸው ሰነፍ ሆኑ ብለን ደግሞ እናማርራለን፡፡ እኔ ድሮ ድሮ የገጠር ልጅ ለምን ጎበዝ እንደሚሆን አሁን ነው የገባኝ፡፡ ገጠርኮ ልጆች ሁሉንም ዓይነት ምግብ ይበላሉ፡፡ የሚዘሩትንና የሚያበቅሉትን ተወው፡፡ ከጫካ የሚገኙ፣ ጤናማ የሆኑና በንጥረ ነገሮች የበለጸጉ ስንት ምግቦች ነበሩ፡፡ እነዚህ ምግቦች እኔ ሕጻን እያለሁ ከገበያ በቀላሉ እናገኛቸው ነበር፡፡ አሁን እንኳን ከተማ ገጠር መገኘታቸውንም እንጃ፡፡ እነ እንኮይ፣ እነ ሾላ፣ አነ ባምባ፣ እነ ኮሽም፣ እነ ግብጦ፣ የት ሄዱ፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የምታገኛቸው ከ500 ዓመት በላይ የኖሩት አበውኮ እነዚህን ተፈጥሯዊ ፍራ ፍሬዎች ነበር የሚመገቡት፡፡
የገጠሩም ሰው ዛሬ ዛሬ ሥልጣኔ የሚመስለው ልክ እንደ ከተማው ያለ አመጋገብ ነው፡፡ እነርሱ የሚያወጡት ቅብዐ ኑግ እኛ ከዱባይ ከምናስመጣው ዘይት እንደሚበልጥ ልንነግራቸው ይገባል፡፡ ልጅን መውደድ ማለት የሱፐር ማርኬት ምግብ መመገብ ሳይሆን በአካባቢው የምናገኛቸውን ምግቦች እያፈራረቁ እያመጣጠኑ መመገብ ማለት መሆኑን መንገር አለብን፡፡ ይህ አስተሳሰብ በመዛባቱ የተነሣ ቤተሰቦቻቸው በትክክለኛ መንገድ የሚያሳድጓቸው ልጆች እንኳን እንደ ሌሎቹ የተፈበረኩ ምግቦችን ስላልበሉ እያማረሩ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ሬዲዮውና ቴሌቭዥኑ በእነዚህ ምግቦች ማስታወቂያዎች የተሞሉ ናቸዋ፡፡
ሲሆን ሲሆን በየብሔረሰቡ ያሉትን ምግቦች አጥንተን ወደ ሀገራዊው ባህል እንክተታቸው፡፡ አንደኛ በቀላሉ ይገኛሉ፡፡ እኛው ጋ ነዋ የሚበቅሉት፤ ሁለተኛ የተፈጥሮ ናቸው፡፡ ከጎጂ ነገሮች ነጻ ይሆናሉ፡፡ ሦስተኛ አሠራራቸው ቀላል ይሆናል፤ በባህል ተሞክረውና ተፈትነው የወጡ ናቸውና፡፡ እነ ጣልያንኮ ፒዛን ከኤርትራ ነው የወሰዱት፡፡ የትግራይ ሰዎች ቂጣውን በቅቤና በአዋዜ የመብላት የቆየ ባህል ነበራቸው፡፡ ጣልያኖች አዋዜውን በቲማቲም ተኩትና ፒዛን አመጡት፡፡ ዛሬ ልጆቻችን ፒዛ ነው እንጂ ቂጣ አንወድም ሲሉ ዝም እንላቸዋለን፡፡
ባይሆን ባህላዊ ምግቦችን ለልጆች በሚጣፍጣቸውና በሚስባቸው መንገድ እንዴት እናቅርባቸው? ብለን ወላጆች መምከር አለብን፡፡ እንደ ምዕራባውያኑ ልጆቹ ከተጎዱና ለአደጋ ከተጋለጡ በኋላ ጉዳዩ ሀገራዊ ጉዳይ እንደሚሆን ጥርጥር የለኝም፡፡ እንዲያውም ከከተማው ይልቅ የገጠሩ ሕዝብ በባለሞያዎች የሚሰጠውን ሃሳብ እየተቀበለ የልጆቹን አመጋገብ እያስተካከለ መሆኑን አንዳንድ ቦታዎች አይቻለሁ፡፡ ጭብጦውን እንዲቀይሩ አይደለም፡፡ ጭብጦውን ከልዩ ልዩ እህሎች በተፈጨ ዱቄት እንዲሠሩት ነው ያስተማሯቸው፡፡ ካገኙ ትንሽ ወተት እንዲያደርጉበት፣ ከተቻለ ደግሞ ቅቤ እንዲጨምሩበት ነው የሚያስተምሯቸው፡፡ ክክ ወጡን እንዲተውት አይደለም የነገሯቸው፤ ክኩን የአተር ብቻ ከማድረግ የሌሎችንም ጥራጥሬዎች እንዲያደርጉት ነው፡፡ ››
ለእኔ እያብራራችልኝ በሄደች ቁጥር ንዴቷ እየጨመረ መጣ፡፡ ሞያዋም፣ ትምህርቷም ስቧት ብዙ ነገር ታዝባለች፡፡ ነገር ግን ከዘመዶቿ ጋር እንኳን በዚህ ጉዳይ መስማማት አልቻለችልም፡፡
‹‹ምናልባትኮ ወላጆች ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት ሲልኩ አልበላም ስለሚሏቸው ይሆናል›› አልኳት፡፡
‹‹ልጆችኮ አልበላም የሚሉት ከብዙ ነገር አንጻር ነው፡፡ የምግቡ አዘገጃጀት፣ የጓደኞቻቸው ተጽዕኖ፣ የመመገቢያው ዕቃ፣ ሌሎችም አብረው መታየት አለባቸው፡፡ እንዲያውም እነዚህ ከሱፐር ማርኬት የሚገዙ ምግቦች ልጆቹን ለሌሎች ምግቦች ማለማመጃ ሊሆኑን ይችላሉ፡፡ ሌሎች ምግቦችን ለሚመገቡ ልጆች እንደ ሽልማት በመስጠት፡፡ በሌላም በኩል ልጆቻችን በራሳቸው እንዲተማመኑ ማስተማርም አለብን፡፡ ማሳመን አለብን፡፡ ራሳቸውን እንዲሆኑ፡፡ ይሄ ባህሌ ነው፤ ይህንን እወዳለሁ እንዲሉ፡፡››
ሃሳቧ እጅግ አብዝቼ እንዳስብ አድርጎኛል፡፡ በተለይም ‹የቅንጦት ረሃብ›› ያለችው ነገር ልክ ነው እያልኩ ከራሴ ጋርም ከቤተሰቤ ጋርም ብዙ ሰዓታት ተነጋግሬበታለሁ፡፡ እስኪ ወላጆች ተነጋገሩበት፡፡ ወቅቱ ትምህርት ቤቶች የተዘጉበት በመሆኑ የልጆቻችንን አመጋገብ ለማስተካከል ምቹ ጊዜ ላይ ነን፡፡  ለመሆኑ በየቤታችን የቅንጦት ረሃብ የለም? በየቤታችን የልጆቻችን አመጋገብ የታሰበበት ነው? ስለምንገዛላቸው እንጂ ስለሚመገቡት ነገር እናስባለን፡፡ እኛ ገዛን፣ ሞግዚቶቻቸውስ ይመግቧቸዋል? እስኪ የሰሞኑ የቤተሰብ አጀንዳ ይኼ ይሁን፡፡