የአ/አ ሀ/ስብከት በደብረ ጽጌ ቅ/ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል የተባለውን የከፋ ሙስናና ብልሹ አሠራር ሊያጣራ ነው
- ደብሩ በተጭበረበረ የሕንጻ ኪራይ ውል ከ2 ሚልዮን ብር በላይ ገቢ ማጣቱ ተነግሯል
በቋሚ ሲኖዶስ አሻሽሎ ባጸደቀው ውስጠ ደንብ አስተዳደራዊ መዋቅሩን እያደራጀ የሚገኘው የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት በደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ‹‹የፋይናንስ እንቀስቃሴና አሠራር›› ጋራ በተያያዘ በደብሩ ጽ/ቤት ተፈጽሟል የተባለውን ሙስናና ብልሹ አሠራር ሊያጣራ ነው፡፡
ከሀ/ስብከቱ ዐበይት አድባራት አንዱ በኾነው የደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል የተባለውን የከፋ ሙስናና ብልሹ አስተዳደር የመመርመሩ ሥራ የሚካሄደው፣ በደብሩ ከፋይናንስ እንቅስቃሴና አሠራር ጋራ በተያያዘ ሥር የሰደደ ችግር በመኖሩ የሒሳብ ምርመራ እንዲደረግ የሰበካ ጉባኤ አባላትና ምእመናን ለሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስና ዋና ሥራ አስኪያጅ ሲያሳስቡ በቆዩት መሠረት እንደኾነ ተዘግቧል፡፡
ይህንኑ የሒሳብ ምርመራ ሥራ የሚያከናውን የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የቁጥጥር አገልግሎት ዋና ሓላፊና ሁለት የሀ/ስብከቱ ልኡካን የሚገኙበት ልኡክ በሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ መሠየሙ ተሰምቷል፡፡
በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ሲፈጸም የቆየው የአስተዳደር ችግርና የገንዘብ ምዝበራ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን የአጥቢያው ምእመናንና የደብሩ ካህናት ለሐራዊ ምንጮች አስታውቀዋል፡፡
በሀ/ስብከቱ በርካታ የገቢ ምንጮችና ከፍተኛ ገቢ ካላቸው ገዳማትና አድባራት በቀዳሚነት በሚጠቀሰው በቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ምዝበራው የተባባሰው፣ ደብሩ ለሁለገብ አገልግሎት ባሠራው የሕንጻ ኪራይና ከሙዳየ ምጽዋት ከሚሰበሰቡት የገቢ ምንጮች ላይ መኾኑ ተገልጧል፡፡
‹‹በሕንጻው የኪራይ አገልግሎት የሚፈጸመው ዐይን ያወጣ ምዝበራ ሕንጻው ባለቤት የለውም ወይ የሚያሰኝ ነው?›› የሚሉት ካህናቱና ምእመናኑ፡-
- የሕንጻው ክፍሎች ከአካባቢው ሕንጻዎች የኪራይ ተመን ዝቅተኛ በኾነ ዋጋ እንደሚከራዩ፣
- ከተከራዮች ጋራ የጊዜ ገደብ የሌላቸው ውሎች እንደሚፈጸሙ፣
- በተጭበረበረ ማኅተምና ቲተር የተደረጉ ሕገ ወጥ ውሎች መኖራቸውን፣
- ባለፈ የኪራይ ተመን በተፈጸሙ የውል ማራዘሞች ደብሩ ከፍተኛ ገቢ ማጣቱን፣
- ከአንድ ሚልዮን ብር በላይ ውዝፍ ክፍያ ያለባቸው ተከራዮች መኖራቸውን፣
- ያለወቅታዊ የዋጋ ማስተካከያ በዝቅተኛ ክፍያ ለረጅም ጊዜ ውል የፈጸሙ ተከራዮች እንዳሉ፣
- ፈጽሞ ውል የሌላቸው ተከራዮች መኖራቸውን፣
በመዘርዘር ያስረዳሉ፡፡
የሕንጻውን የኪራይ ውል አሰጣጥ ለመመርመርና የኪራይ ተመኑን ከአካባቢው ዋጋ ጋራ ለማጣጣም በደብሩ ጽ/ቤት እና ሰበካ ጉባኤ የተቋቋመው አጣሪ ኮሚቴ ለአስተዳደሩ ያቀረበውን ሪፖርት በመጥቀስ አቤቱታ አቅራቢዎቹ እንደሚያስረዱት÷ የውል ጊዜያቸው ካለቀ ሁለት ተከራዮች ጋራ ብቻ በተጭበረበረ መንገድ በተፈጸሙ የውል ማራዘሞች ደብሩ ከሚያዝያ ወር ፳፻፬ ዓ.ም ጀምሮ ማግኘት የሚገባውን 2,637,603.30 /ሁለት ሚልዮን ስድስት መቶ ሠላሳ ሰባት ሺሕ ስድስት መቶ ሦስት ከሠላሳ ሳንቲም/ እንዲያጣ ተደርጓል፡፡
ኮሚቴው አሻሽሎ ካቀረበው ወቅታዊ የኪራይ ዋጋ ተመን ይልቅ ባለፈ የክፍያ ተመን ላይ በመመሥረትና ከተከራዮች ጋራ የጥቅም ተካፋይ በመኾን አላግባብ እንዲራዘም የተደረገው ሕገ ወጥ ውል፣ ‹‹የደብዳቤ ውል ቁጥር በሌለውና ከሓላፊነት በተነሡት የደብሩ አስተዳዳሪ ፊርማ›› የተሰጠ እንደኾነ ተመልክቷል፡፡ የደብሩን ንብረት የመጠበቅ፣ የኪራይ ውሎችን በመከታተል የደብሩን ጥቅሞች ማስጠበቅ የሚገባቸው ጸሐፊውና ቁጥጥሩ የሕገ ወጥ ውሉ ‹‹አዘጋጆችና ምስክሮች›› መኾናቸው ምዝበራውና ሙስናው በምን ደረጃና በእነማን እየተፈጸመ እንዳለ አረጋጋጭ ነው ተብሏል፡፡
በሕንጻ ኪራይ ውል አሰጣጥ ለሚፈጸሙ ምዝበራዎች የማያዳግም መፍትሔ ለመስጠት÷ ሀ/ስብከቱ በዋና ጸሐፊውና ተቆጣጣሪው ላይ የእርምት ርምጃ እንዲወስድ፣ አግባብነት የሌላቸውን ውሎች የፈጸሙ ሓላፊዎች በሕግ እንዲጠየቁና ደብሩ ያጣቸውን ገቢዎች እንዲያገኝ፣ ተከራዮች በኪራይ ውል ውስጠ ደንቡ መሠረት እንዲስተናገዱና ደንቡን የማያከብሩ ተከራዮች ጋራ ውል እንዲቋረጥ ኮሚቴው ሐሳብ አቅርቦ የነበረ ቢኾንም አንዱም ተግባራዊ ሳይደረግ ‹‹ጸሐፊው በይቅርታ፣ ቁጥጥሩ በዝውውር መታለፋቸውን›› ነው ምእመናኑ የሚናገሩት፡፡
የደብሩ ጽ/ቤት በበኩሉ ከኪራይ ውሎች ጋራ በተያያዘ ከተጠቀሱት ስሕተቶች አብዛኞቹ በቀድሞው የደብሩ አስተዳደር የተፈጸሙ መኾናቸው ገልጾ፣ ደብሩ ከሚያከራያቸው 47 ሱቆች መካከል የ35 ሱቆችን ውል እንደ አዲስ የማስተካከል ሥራ መሠራቱን፣ በሕገ ወጥ መንገድ ከሁለት ተከራዮች ጋራ የተፈጸሙት ውሎችም ከስድስት ወራት በፊት እንዲቋረጡ ተደርጎ ጉዳዩ በፍርድ ቤት መያዙን አስረድቷል፡፡
በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑ በወር ሁለት ጊዜ የሙዳየ ምጽዋት ቆጠራ የሚካሄድ ሲኾን በእያንዳንዱ ወር በአማካይ ከግማሽ ሚልዮን ብር በላይ ገቢ እንደሚደረግ ተመልክቷል፡፡ በ2003 ዓ.ም ሐምሌ ወር የተመረጠው የደብሩ ሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባኤ በሥራ ላይ በቆየባቸው ባለፉት 22 ወራት ለ44 ጊዜያት በተካሄደው የሙዳየ ምጽዋት ቆጠራ ከ12 ሚልዮን ብር በላይ እንደሚሰበሰብ ቢታመንም በደብሩ የባንክ ሒሳብ ያለው ተቀማጭ ግን ከአምስት ሚልዮን ብር እንደማይበልጥ የደረሱን ማስረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ከአምስት ሚልዮን ብሩ ውስጥ 3.5 ሚልዮን ብሩ ካለፈው ሰበካ አስተዳደር ጉባኤ የዞረ ሒሳብ እንደኾነ የሚያሰሉት ካህናቱና ምእመናኑ፣ በ2003 ዓ.ም የተመረጠው ሰበካ ጉባኤ ወደ ደብሩ ካዝና ያስገባው ገቢ ከ1.5 ሚልዮን ብር የማይበልጥ መኾኑ የምዝበራውን መጠን በጉልሕ እንደሚያሳይና አሳሳቢ እንደሚያደርገው በምሬት ይናገራሉ፡፡
በሙዳየ ምጽዋት ቆጠራ ወቅት የቆጠራውን ሂደትና የገባውን የገንዘብ መጠን በዝርዝር የሚያሳዩት የ22 ወራት 44 የቆጠራ ቃለ ጉባኤዎች፣ በቀድሞው የአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት አስተዳደራዊ መዋቅር ደብሩ ከተካለለበት የምሥራቅ አዲስ አበባ ሀ/ስብከት ጽ/ቤት በተላኩ ልኡካን ለሒሳብ ምርመራ በተፈለጉበት ወቅት የደብሩ ጸሐፊ፣ ‹‹የቆጠራው ቃለ ጉባኤዎች የጠፉ ስለኾነ አናስመረምርም›› በማለታቸው ማጣራቱ ሳይካሄድ መቅረቱን ካህናቱና ምእመናኑ አስታውሰዋል፡፡
የቀድሞው የምሥራቅ አዲስ አበባ ሀ/ስብከት ለሒሳብ ምርመራ የላካቸው መርማሪዎች ‹‹የቆጠራ ቃለ ጉባኤዎች ስለጠፉ አናስመረምርም፤ ከዚህ ቀደም ስላስመረመርን በድጋሚ አናስመረምርም፤ የሰበካ ጉባኤ አባላት ባሉበት አናስመረምርም›› በሚሉ የተለያዩ ሰበቦች ሥራቸውን ሳይፈጽሙ እንዲመለሱ መደረጋቸው ‹‹በሙስና የዘቀጠው›› የደብሩ አስተዳደር ጽ/ቤት፣ ደንብና አሠራርን በመጣስ የፈጸመው ምዝበራ ከሚያስከትልበት የሕግ ተጠያቂነት ለማምለጥ የሚያደርገውን ሙከራ በግልጽ እንደሚያሳይ ካህናቱና ምእመናኑ አብራርተዋል፡፡
የሕንጻውን ኪራይና ሙዳየ ምጽዋቱን ጨምሮ በሌሎች የደብሩ ዘጠኝ የገቢ ምንጮች ላይ በአስተዳደር ጽ/ቤቱ አባላት የሚፈጸመውና ከዕለት ወደ ዕለት እየከፋ መምጣቱ የተገለጸው ምዝበራ፣ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎቷን ለመፈጸም ያላትን መንፈሳዊ ሥልጣንና ፋይናንሳዊ አቅም እየተፈታተነው እንዳለ የሰበካ ጉባኤ አባላቱ አስረድተዋል፡፡ ‹‹የአስተሳሰብና የምግባር ብልሽቱን›› በእነርሱ ደረጃ ለማስተካከል ከሚቻለው በላይ ስለኾነባቸውም ጉዳዩ ተጣርቶ አስቸኳይ የእርምት ርምጃ እንዲወሰድ ለአዲሱ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስና ለዋና ሥራ አስኪያጁ መጋቤ ሐዲስ ይልማ ቸርነት በሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት በአካል ቀርበው ማስረዳታቸውን አስታውቀዋል፡፡
ከሳምንታት በፊት በብዙ መቶ የሚቆጠሩ የአጥቢያው ምእመናንና የደብሩ አገልጋዮች በሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት ሁለት ጊዜ ከሊቀ ጳጳሱና የሀ/ስብከቱ የሥራ ሓላፊዎች ጋራ ተገናኝተው በችግሩ ላይ ግልጽ ውይይት አካሂደዋል፡፡ ሊቀ ጳጳሱና ዋና ሥራ አስኪያጁ በአካል በቤተ ክርስቲያኑ ቅጽር በተገኙበት ተመሳሳይ ውይይት የተደረገ ሲኾን ካህናቱና ምእመናኑ የአሠራር ብልሽቱንና ምዝበራውን ባጋለጡባቸው በእኒህ መድረኮች፣ በደብሩ ጸሐፊ ‹‹ጠፍተዋል›› የተባሉት ቃለ ጉባኤዎችና ለምርመራው የሚያስፈልጉ ሌሎች ሰነዶች በአስቸኳይ ቀርበው የማጣራቱ ሥራ እንዲካሄድ ሊቀ ጳጳሱ ጠንካራ የቃል ትእዛዝና ቀነ ገደብ ለአስተዳደር አባላቱ መስጠታቸው ተዘግቧል፡፡