ግንቦት 20 ሠልፍ ያልወጡ የመንግስት ሠራተኞች ሪፖርት እንዲያደርጉ ታዘዙ
ኃይሌ ሙሉ | ሪፖርተር
ግንቦት 20 ቀን 2003 ዓ.ም. በተካሄደው የድጋፍ ሰላማዊ ሠልፍ ያልተገኙ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ሠራተኞች በሦስት ቀን ውስጥ ማስረጃ እንዲያቀርቡ ታዘዙ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የሰው ኃይል አስተዳደር ደጋፊ የሥራ ሒደት መሪ ስምና ፊርማ አርፎበት ግንቦት 22 ቀን 2003 ዓ.ም. በመሥሪያ ቤቱ የማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ በተለጠፈው ማስታወቂያ ላይ እንደተገለጸው፣ ግንቦት 20 ቀን በተደረገው አገር አቀፍ ጥሪ ያልተገኙ ሠራተኞች ያልተገኙበትን ምክንያት የሚገልጽ ማስረጃ በሦስት ቀን ውስጥ ማቅረብ አለባቸው፡፡
በድጋፉ ሰላማዊ ሠልፍ ላይ የተገኙ 79 ሠራተኞች ሙሉ ስም ከማስታወቂያው በታች የተዘረዘረ ሲሆን፣ የሰው ኃይል አስተዳደር ደጋፊ የሥራ ሒደት በዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤቱ ስም በሠልፉ ለተገኙ ለእነዚህ ሠራተኞች ያለውን የላቀ አክብሮት ገልጿል፡፡
በመሥሪያ ቤቱ ማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ የተጻፈው ማስታወቂያ እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹መሥሪያ ቤታችን ግንቦት 20 ቀን 2003 ዓ.ም. ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን አስመልክቶ በተደረገው የድጋፍ ሰላማዊ ሠልፍ ላይ ጥሪያችንን አክብራችሁ የተገኛችሁ ከዚህ በታች የተዘረዘረው የመሥሪያ ቤታችን ሠራተኞች አገራዊ ግዴታችሁን በመወጣታችሁ የላቀ አክብሮታችንን እየገለጽን፣ የሰው ኃይል አስተዳደር ደጋፊ የሥራ ሒደት በመሥሪያ ቤቱ ስም ከፍተኛ ምስጋናችንን እያቀረብን ከዚህ በታች ስማችሁ ያልተጠቀሰው ሠራተኞች ግን በዕለቱ በተደረገው አገር አቀፋዊ ጥሪ ያልተገኛችሁበትን ምክንያት በሦስት ቀን ውስጥ ማስረጃ ይዛችሁ እንድታቀርቡ እናሳስባለን፡፡››
ግንቦት 20 ቀን በተካሄደው ሰላማዊ ሠልፍ ያልተገኙ ሠራተኞች ሪፖርት እንዲያደርጉ የተጠየቁበትን ምክንያት እንዲያብራሩልን የጠየቅናቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ኦዲተር ጄነራል ወይዘሮ አባይነሽ ገብረ መድህን እንደገለጹት፣ በሰላማዊ ሠልፉ ላይ ያልተገኙበትን ምክንያት እንዲያሳውቁ የተጠየቁት ጉዳዩ ከሥራ ዲሲፕሊን ጋር የሚገናኝ በመሆኑ ነው፡፡
መሥሪያ ቤቱ ከግንቦት 20 ቀን በፊት ቀደም ብሎ በነበረው የሥራ ቀን በለጠፈው ማስታወቂያ የቢሮው ሠራተኞች የህዳሴ ግድብ ግንባታን አስመልክቶ በሚደረገው ሰላማዊ ሠልፍ እንዲሳተፉ ጥሪ ያደረገ መሆኑን የጠቆሙት ወይዘሮ አባይነሽ፣ በዕለቱ በሠልፉ ላይ ያልተገኙ ሠራተኞች እንደ መንግሥት ሠራተኝነታቸው የቀሩበትን ምክንያት የመግለጽ ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
‹‹አንድ ሠራተኛ ከቀረ ምክንያቱን መናገር አለበት፡፡ ምክንያቱም ይኼ የሥራ ዲሲፕሊን ነው፡፡ መሥሪያ ቤቱ ነው ጥሪውን ያስተላለፈው፡፡ እንደ መንግሥት ሠራተኛነቱ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ጥሪ ሲያስተላልፍ በዚህ ምክንያት አልተመቸኝም ማለት አለበት፤›› ብለዋል፡፡
እርሳቸው እንደሚሉት፣ ሠራተኞቹ ግንቦት 20 ቀን ሰላማዊ ሠልፍ እንዲወጡ መሥሪያ ቤታቸው ጥሪ ያስተላለፈው ግንቦት 20 በዓልን ለማክበር ሳይሆን ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ድጋፍ ለመስጠት ነው፡፡
‹‹አንድ የመንግሥት ሠራተኛ በብሔራዊ በዓል ቀን በሚካሄድ ሰላማዊ ሠልፍ የመሳተፍም ሆነ የመቅረት መብት አለው፡፡ በዕለቱ የቀረ ሠራተኛ ለምንድነው ሪፖርት እንዲያደርግ የተፈለገው?›› በሚል ላቀረብንላቸው ጥያቄ ወይዘሮ አባይነሽ ሲመልሱ፣ ‹‹ጥሪው በአገር አቀፍ ደረጃ ቢተላለፍ ትክክል ነው፡፡ ነገር ግን ጥሪውን ያስተላለፈው መሥሪያ ቤቱ ነው፡፡ [የዓባይ ግድብ ግንባታ] መልዕክት በትክክል እንዲተላለፍ እንፈልጋለን፡፡ ስለዚህ ሠራተኞች ያልተገኙበትን ምክንያት ከዲሲፕሊን አኳያ ማስረዳት ይጠበቅባቸዋል፤›› ብለዋል፡፡