የፍቅር ትርጉሙ

ከእለታት አንድ ቀን፥ በአንድ የስደት አገር ምሽት፣ ጥቂት ኢትዮጵያውያን ወጣቶች እራሳቸውን በሞቀ ክርክር መሃል ያገኛሉ። ክርክሩ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሲሆን፤ የአንድ የዝግጅት ክፍላችንን አባል ትኩረት የሳበው ርእስ በሁለት ወጣቶች መካከል የተካሄደው ልውውጥ ነው።

ወጣት ቁጥር 1፥ በአሁኑ ሰዓት አገራችን ያለችበት ሁኔታ አንገብጋቢ ስለሆነ፤ ማንኛውም ሊወሰድ የሚገባው እርምጃ ፈጣን፣ ጠንካራ እና ያለውን አደገኛ ሁኔታ የተረዳ ሊሆን ይገባዋል ይላል። ወጣት ቁጥር 2 ደግሞ፥ አይ ማንኛውንም እርምጃ ከመውሰዳችን በፊት ረጋ ብለን እየተካሄደ ያለውን ሁኔታ ልንመረምር እና ለምንስ እየተካሄደ እንደሆነ እራሳችንን ልንጠይቅ ይገባል ይላል።

በዚህ ወቅት ወጣት ቁጥር 1 ለወጣት ቁጥር 2 ጥያቄ ያቀርብለታል። “እስኪ ይህንን ሁኔታ አስብ” ብሎ ጀመረ፥ ወጣት ቁጥር 1። “ከስራ መጥተህ፣ እቤትህ ደጃፍ ትደርሳለህ። ያላስብከው ሁኔታ ይጠብቅሃል። በሩ ተሰብሯል። ትገባለህ። አንድ ወንበዴ እናትህን ሲደፍራት ታገኛለህ። መጀመሪያ የምታደርገው ነገር ምንድን ነው? የተቻለህን መንገድ ሁሉ ተጠቅመህ ወንበዴውን ማስቆም አይደለም?” ይለዋል።

ወጣት ቁጥር 2 እንዲህ ሲል መለሰ፥ “አይ! ‘ሰውየውስ እንደዚህ የሚያደርገው ለምንድን ነው?’ የሚለውን ጥያቄ መጠየቅ እና መመለስ አለብን።”

በዚህ ወቅት ወጣት ቁጥር 1 በመገረም እንዲህ አለ፥ “ይኸውልህ ወንድሜ፥ ይቅርታ አድርግልኝ እንጂ…የእብድ ሰው ትርጉሙ ይህ ነው። ጤናማ ሰው እናቱ አይደለችም ማንኛውም ሰው እንደዛ እፊትለፊቱ እየተጠቃ ዝም አይልም። ወይም አንተ እንደምትለው መቀመጫ ፈልጎ ተቀምጦ ወንበዴው ምን ሆኖ ይሆን እንዲህ ያለ ነገር ሰው ላይ የሚፈጽመው ብሎ አይመራመርም። ጤናማ ሰው በዙሪያው ያለውን ነገር ፈጥኖ በማሰስ ወይ ዱላ ወይ ቢላዋ አንስቶ አጥቂውን በማጥቃት ተጠቂዋን ያድናል፤ ወደ ህክምናም ይወስዳታል። ህግ አስከባሪ ሃይል ጠርቶም ወንጀለኛውን ያስረክባል። ወደፊት እንዲህ አይነት ወንጀል እንዳይፈጸም ለመከላከል በሚል በወንበዴው ስነ-ልቦና እና ታሪክ ላይ መመራመር እና መፈላሰፍ ካስፈለገ፤ እሱን ኋላ ላይ ነገሮች በቁጥጥር ስር ከዋሉና ሰላም ከሰፈነ በኋላ ያደርጋል።” አለው።

በዚህ ጊዜ ወጣት ቁጥር 2 እና በክፍሉ ውስጥ የነበሩ ሌሎች ከመሳቅ ውጪ ምንም አልተባለም።

“የ1960ዎቹ ትውልድ” ተብለው የሚጠሩት ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ስር ነቀል ለውጥን ለማምጣት በነበራቸው የጋለ ስሜት በመነዳት በወቅቱ ያካሄዱት ትግል እና በሂደት ፈጽመውታል የሚባለው ስህተት፤ ጥቂት የማይባሉ የዚህ ዘመን ወጣቶችን በፍርሃት አደንዝዟል። “እኛም ለውጥን ለማምጣት እንፈልጋለን፤ እኛም መስዋእትነትን አንፈራም፤ ነገር ግን የአባቶቻችን ትውልድ የፈጸመውን ስህተት መልሰን እንዳንደግም ምን ዋስትና አለ?” ብለው የሚጠይቁ ጥቂቶች አይደሉም።

ይህ አደንዛዥ ፍርሃት ምክንያታዊነታቸውን የቀማቸው እና ግራ መጋባት ውስጥ የከተታቸውም ጥቂቶች አይደሉም። በመግቢያችን ላይ በጠቀስነው ታሪክ ውስጥ እንደነበረው ወጣት ቁጥር 2 እናታቸው ስትጠቃ ቢያዩ እንኳ አጥቂዋን አጥቅተው ማባረሩ ትክክለኛው እርምጃ ላይሆን ይችላል ብለው የሚጠራጠሩ፤ የተልፈሰፈሱ እና እረኛ እንደጠፋቸው በጎች በሃሳብ ጫካ ውስጥ የሚንከራተቱ አሉ። ዝምተኛነትን እንደ ሰላማዊነት የሚያዩ እና የፍቅርን ትርጉም የሚያዛቡም ብዙ ናቸው።

ይህ ደግሞ ይኸው በመግቢያችን የጠቀስነው የዝግጅት ክፍላችን አባል በአንድ ወቅት ከሌላ እጁን ከሰጠ ወጣት ጋር ወዳደረገው ውይይት ይወስደናል። የኛው ልጅ፥ “ወያኔን ድል መንሳት የሚቻለው እንዴት ነው?” ብሎ ወጣቱን ይጠይቀዋል። ወጣቱም እንዲህ ሲል መለሰ፥ “ወያኔን ማሸነፍ የሚቻለው በፍቅር ብቻ ነው። እኔ ከዚህ በኋላ በጦርነት እና በሌላ ምንም አላምንም። በፍቅር ብቻ ነው።” አለው።

እኛ፥ ወያኔንም ሆነ ማንኛውንም አጥፊ ሃይል በፍቅር ማሸነፍ እንደሚቻል ቅንጣት ታህል ጥርጣሬ የለንም። ፍቅር አሸናፊ ሃይል ነው። ነገር ግን የኛ የፍቅር ትርጉም እንደዛ እንደተንበረከከ ወጣት የተዛባ አይደለም። ፍቅር ማለት የወደድከው ሰው በጭንቅላትህ ላይ እንዲረማመድብህ መፍቀድ ማለት አይደለም። ፍቅር ምክንያታዊ የሆነ ስሜት እንጂ፤ እውርነት አይደለም። ፍቅር ያከብራል፤ መልሶ እንዲከበርም ይጠብቃል። ፍቅር ቸርነትን ያደርጋል፤ ይቅርም ይላል። ከልክ ባለፈ መንገድ ሲጠቃ ግን ቆሞ አያይም፤ ይልቁንስ እንደ እሳት ነበልባል ሆኖ ደግሞ ይባላል።

ፍቅር እናቱ ስትጠቃ ቆሞ አያይም። በሃያ ሁለት ጥይቶች ተበሳስቶ ሰውነቷ እንደ ወንፊት ሲሆን ያጠቋትን ወድቆ አይለማመጥም። ፍቅር የሰባት አመት ልጁ አይን በጥይት ሰደፍ ሲመታ ቆሞ አያይም። ፍቅር የአስራ አራት አመት ልጁ ተንበርክኮ እየለመነ ልቡ በጥይት ሲቀደድ ዝም አይልም። ፍቅር አገሩ የዘረኞች እና የወንበዴዎች መሳለቂያ እና መጨፈሪያ ሲሆን ቆሞ አያይም። ፍቅር ደንቆሮና እውር አይደለም። ፍቅር አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ተቆጪና ተናዳጅም ነው። እንደዛ ያልሆነ ፍቅር፣ ፍቅር አይደለም፤ ድንዛዜ አንጂ።

አገሩን የሚወድ፣ እናቱን የሚወድ፣ ልጁን የሚወድ፣ ወንድሙን የሚወድ፣ እህቱን የሚወድ ቢኖር፤ ተቆጥቶ የመነሻው ዘመን አሁን ነው።

ከድንዛዜ እና ከግራ መጋባት ያድነን…የፍቅር ሰዎችም ያድርገን ብለን እየተመኘን፣ የዛሬዋን ሃተታችንን ባጭሩ እንቋጫለን።