የሐረር የታሪክ አባት
የሐረር ሰውም ሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን እኒህን ሰው የሚያውቃቸው በአካውንታንትነታቸውም ሆነ በኦዲተርነታቸው አይደለም፡፡ እርሳቸው ከዚያም በላይ ከብረዋል፤ ከዚያም በላይ አገልግለዋል፣ ከዚያም በላይ ታምነዋል፣ ከዚያም በላይ በሕዝቡ ልብ ውስጥ ነግሠዋል፡፡
አብዱላሂ ሸሪፍ በታሪካችን መጥፋት፣ በቅርሶቻችን መበላሸትና ሳይሰበሰቡ ባክነው መቅረት፣ ትውልዱም ታሪኩንና ባህሉን የሚያውቅበት ዕድል ሳይፈጠርለት በመቅረቱ ያዝናሉ፡፡ እንደብዙዎቻችን ግን አዝነው ብቻ አልቀሩም፡፡ የሺ ኪሎ ሜትር ጉዞ በአንድ ርምጃ ይጀመራል፤ የብዙ ዓመታት ገድል በአንዲት ሰዓት ይወጠናል ብለው አሰቡ፡፡ የአካባቢውን ሕዝብ ቅርሶች፣ ባህላዊና የወግ ዕቃዎች፣ መጻሕፍትና መዛግብት፣ ሥዕሎችና ፎቶዎች፣ ሙዚቃዎችና አልባሳት መሰብሰብ ጀመሩ፡፡ አንዳንዱን በልግሥና ያገኛሉ፤ ሌሎቹን ምግብ እየተውም ቢሆን ይገዛሉ፡፡ ቤታቸው ከ1980ዎቹ መጀመሪያ አንሥቶ በቅርሶች፣ ባህላዊና የወግ ዕቃዎች መሞላት ጀመረ፡፡
‹‹የዛሬ 23 ዓመት ራስን ማጣት የፈጠረብኝ ቁጭት ነው መነሻዬ›› ይላሉ አብዱላሂ ሸሪፍ፡፡ ይህንን ቁጭት አብዱላሂ ሸሪፍ ‹የማንነት ነውጥ› ሲሉ ይጠሩታል፡፡ ‹ታሪክ እያለህ፣ ባህል እያለህ፣ ቅርስ እያለህ፤ ለዚህ ደግሞ በቂ ማስረጃ እያለህ ግን እንደሌለህ ስትቆጠር አትናደድም፣ አታብድም›› ብለው ይጠይቃሉ፡፡ ‹‹ማንነትህ ሲፈተን ምን ይሰማሃል?›› ይሉና ተጠያቂውን አፍጥጠው ያያሉ፡፡ አስተያየታቸው ልቡናን ሠርሥሮ ይገባና የደም ዝውውርን ሊያቆም ይዳዳዋል፡፡ ‹‹የምትፈተነው ስለሌለህ አይደለም፣ የምትፈተነው ያለህን ማቅረብ ባለመቻልህ ብቻ ነው፡፡ ለፈተና ያቀረበን የታሪክና የቅርስ ድህነታችን አይደለም፤ ለፈተና ያቀረበን ስንፍናችን ነው፡፡ ይህን ስንፍናችንን ማስወገድ ከቻልን የምናቀርበው ሞልቶናል›› ይላሉ ሼክ አብዱላሂ ሸሪፍ፡፡
አብዱላሂ ሸሪፍን ሙስሊም ክርስቲያኑ ያምናቸዋል፡፡ ቅርሱንና የወግ ዕቃውን አደራ ብሎ የሚሰጠው ለእርሳቸው ነው፡፡ እንደ ወርቅ ተፈትነው ያለፉ ሰው ናቸው፡፡ አደራ የምይነኩ፡፡ ቃልን የማይበሉ፤ ለምድር ለሰማይ የከበዱ፡፡ ሼክ አብዱላሂ ሸሪፍ ለ17 ዓመታት በቤታቸው ነበር ቅርሶችን፣ የወግና የባህል ዕቃዎችን ይሰበስቡ የነበሩት፡፡ መጀመሪያ ከመደበኛ ሥራቸው ጋር ጎን ለጎን ነበር የሚሠሩት፣ከ12 ዓመታት ወዲህ ግን ይኼው ሆኗል ሥራቸው፡፡ ‹‹የምሠራው ለገንዘብ ብዬ አይደለም፤ ከማገኘው ይልቅ ለቅርሶቹ የማወጣው ይበልጣልና፡፡ የምሠራው ለእርካታ ነው፡፡ የኔ ዋናው ጥያቄ ምን አገኛለሁ? አይደለም፤ ዛሬ ማታ ምን እሠራለሁ? ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ሥራዬን የምሠራው ማታ ማታ ነው፡፡ በሚያልፍ ምድር የማያልፍ ሥራ እየሠራሁ መሆኔን ለራሴ እነግረዋለሁ፣ በየጊዜው ራሴን አሳምነዋለሁ፡፡ ልጄ አንተም የኅሊና ርካታ የማታገኝበትን ሥራ አትሥራ፡፡ የማይረካበትን ሥራ የሚሠራ እንስሳ ብቻ ነው፡፡ እንስሳ የታዘዘውንና ሌሎችን የሚያስደስተውን ብቻ ነው የሚሠራው፤ አንተ ግን የሚያረካህንና ስታስበው ነፍስህን የሚያስደስታትን ነው መሥራት ያለብህ›› ይላሉ ሼክ አብዱላሂ ሸሪፍ ሲመክሩ፡፡
በአሁኑ ጊዜ ከ1200 በላይ ጥንታውያን መጻሕፍትን፣ ከ400 ሰዓት በላይ የድምጽ ቅርሶችን፣ ጥንታውያን ሳንቲሞችን፣ ከመካከለኛው ዘመን ጀምረው የነበሩ የጦር መሣርያዎችን፣ ከሁለት መቶ ዓመታት በላይ እድሜ ያስቆጠሩ ፎቶዎችን፣ የሐረርን የንግድ ግንኙነት የሚያሳዩ ሳንቲሞችን፣ መዛግብትን፣ የወግ ዕቃዎችን ሰብስበዋል፡፡ እነዚህ ቅርሶች በዋናነት የሐረሪ፣ የአርጎባ፣ የአማራ፣ የኦሮሞና የጉራጌ ቅርሶች ናቸው፡፡ በሐረርና አካባቢው በተደረጉ ቁፋሮዎች የተገኙ መስቀሎች፣ የአንገት ማተቦች፣ የነገሥታት ማኅተሞች በአብዱላሂ ሸሪፍ ሙዝየም ውስጥ አሉ፡፡ እንዲያውም ከ100 ዓመት በላይ እድሜ ያለው መጽሐፍ ቅዱስም አሳይተውኛል፤
ሼክ አብዱላሂ ሸሪፍ መሰብሰብ ብቻ ሳይሆን ለጎብኚዎች፣ ለአጥኚዎችና ለሚዲያ ሰዎች መረጃ የሚሰጥበትን መንገድም አመቻችተዋል፡፡ ለዚህም ነበር በመኖሪያ ቤታቸው የመጀመሪያውን ሙዝየም በራሳቸው ወጭ የከፈቱት፡፡ በቤታቸው ውስጥ ለ17 ዓመታት ሲሠሩ ቆዩ፡፡ በ1990/91 ዓም የሼክ ሸሪፍ መኖሪያ ቤት በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የግለሰብ የቅርስ ስብስብ ሥፍራ ተብሎ በመመዝገብ ወደ ‹‹ሸሪፍ የግል ሙዝየም›› ተለወጠ፡፡ የክልሉ መንግሥትም የአብዱላሂ ሸሪፍን ጥረት ሲያይ በቅርስነት የተመዘገበውን የራስ ተፈሪ (ዐፄ ኃይለ ሥላሴ) ቤት ሰጣቸው፡፡ ዛሬ በቦታው ‹ሸሪፍ የሐረር ከተማ ሙዝየም›› የሚባል ታላቅ ሙዝየም ከፍተዋል፡፡
ቅርሱን በማሰባሰብ፣ በመመዝገብና በመጠበቁ ሥራ የሼክ አብዱላሂ ቤተሰብ በነቂስ ነው የሚሳተፈው፡፡ ለዚያውም ከመሥዋዕትነት ጋር፡፡ ‹‹ሦስቱ ልጆቼና ባለቤቴ እነዚህን ዘመን የተጫናቸውን መዛግብት ሲያገላብጡ የአስም ሕመምተኞች ሆነዋል፡፡ እንደዚያም ሆኖ ግን ሥራውን አላቋረጥንም›› ይላሉ በኩራት፡፡
አብዱላሂ ሸሪፍ በተለይም ጥንታውያን የብራና መጻሕፍትን፣ መዛግብትን፣ ፎቶዎችንና ሥዕሎችን ወደ ዲጂታል ቅጅ የመገልበጡን ሥራም እያከናወኑት ነው፡፡ ‹‹ጎብኚዎችና ተመራማሪዎች ቅርሶቹንና መዛግብቱን ሳይጎዱ የሚፈልጉትን መረጃ በቀላሉ ያገኛሉ፡፡ ከዚህም በላይ ዋናው ቅጅ ቢጠፋ በውስጡ ያለውን ነገር ለታሪክ ማቆየት ይቻላል፡፡ ቢዘረፍም ቅጅውን በማስረጃነት በመያዝ ለመከራከርም ይመቻል›› ይላሉ- ሼክ አብዱላሂ ሸሪፍ፡፡
ሼክ አብዱላሂ ሸሪፍ ‹‹አባቶችችን ለመሥራት ያልደከሙትን እንዴት እኛ ለመጠበቅ ይደክመናል› የሚለው ሃሳብ ቀንና ሌሊት እንዲተጉ አድርጓቸዋል፡፡ እርሳቸው ለመሰብሰብ፣ ለመመዝገብ፣ ዲጂታል ለማድረግና ለማሳየት ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ታሪክን ለመተንተን፣ ለማስረዳትና በቀላል ቋንቋ ለመግለጥም የታደሉ ናቸው፡፡ እርሳቸውን ማነጋገር የጀመረ ሰው ቀጠሮውን ይሠርዛል፤ የቆመ ይቀመጣል፤ የሄደ ተመልሶ ይመጣል፤ ማዳመጥ የጀመረ ማስተዋሻና መቅጃ ማውጣት ይቀጥላል፡፡ መተረክ ይችሉበታል፤ ቁጭት መፍጠር ያውቁበታል – የሐረር የታሪክ አባት- አብዱላሂ ሸሪፍ፡፡
ከሠርጸ ፍሬ ስብሐት ጋር ጉብኚታችንን ፈጽመን ልንወጣ ስንል አብዱላሂ ሸሪፍን እንዲህ ብዬ ጠየቅኳቸው ‹‹አሁን ይህንን ቅርስ ይሽጡልኝ የሚል አካል ቢመጣ ምን ይሉታል››
ቆጣ አሉ፡፡
‹‹ይህ ማንነቴ ነው፤ ማንነቴን አልሸጥም፤ እንደ ሰው ተወልጄ እንደ እንስሳ ልሞት አልችልም››