ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ከዓመት ከስድስት ወር እስር በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ቃሊቲ ሰው ገብቶ እንዲጠይቀው ተፈቀደ
ከሕግ ውጪ መታሰሩን ተረድተው በያሉበት ድምፃቸውን ለሚያሰሙ ምስጋና አቅርቧል
“ስላደረጋችኹልኝ እና ስለምታደርጉልኝ ኹሉ አመሰግናለሁ!” እስክንድር ነጋ
“እስክንድር ለዚህን ያህል ወራት እስር ቤት መቆየቱን ተጠራጠርኩ፤ ጥንካሬው አሁንም አብሮት አለ” ጋዜጠኛ ጽዮን ግርማ

Ethiopia Zare (ዓርብ ሰኔ 7 ቀን 2005 ዓ.ም. June 14, 2013)፦ ላለፉት አስራ ስምንት ወራት በእስር ላይ ያለው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ለመጀመሪያ ጊዜ ከባለቤቱ ከጋዜጠኛ ሰርካለም ፋሲል እና ከልጁ ከናፍቆት ሌላ ሰው እንዲጠይቀው በዚህ ሣምንት መፈቀዱን ለመረዳት ችለናል። ዛሬ ጠዋት ቃሊቲ ሄደው ከጠየቁት ውስጥ ጋዜጠኛ ጽዮን ግርማ አንዷ ስትሆን፤ አላግባብ ከሕግ ውጪ መታሰሩን ተረድተው በያሉበት ድምፃቸውን ላሰሙና ለሚያሰሙ ሁሉ በያሉበት ምስጋናዬ ይድረሳቸው ብሏታል።