ችግር ፈቺ ዜጋ

በቀደም ዕለት ከመገናኛ ወደ ሲኤም ሲ በሚወስደው መንገድ ላይ እየተጓዝን አንድ አይ ሱዙ መኪና ከጎናችን መጣ፡፡ እኛ ወደ መንገዱ ጠርዝ ተጠግተን ነበር የምንነዳው፡፡ አይ ሱዙ መኪናው የመጣው ከመንገዱ ጠርዝ ቀጥሎ በስተ ቀኝ ከሚገኘው መሥመር ነው፡፡ ወደ መንገዱ ማቋረጫ ላይ ሲደርስ ወደ ግራ ለመጠምዘዝ ፍሬቻ ማብራት ጀመረ፡፡ የነበረበት መሥመር በቀጥታ ለመንዳት እንጂ ለመጠምዘዝ የሚያስችል አልነበረም፡፡ ምክንያቱም በስተግራው ሌሎች መኪኖች ማለፍ ይችላሉና፡፡ አይሱዙው ግን መሐል መንገድ ላይ ቆሞ ፍሬቻ እያበራ አሳልፉኝ ማለት ቀጠለ፡፡ በግራ መንገዱ በኩል የማለፍ መብት የተሰጣቸው መኪኖች ከቁብ ሳይቆጥሩት ጥለውት ያልፋሉ፡፡ ከአይሱዙው ኋላ የነበሩ ብዙ መኪኖች በመቆማቸው ምክንያት መንገዱ ተጨናነቀ፡፡ ይህንን ያየ ከፊታችን የነበረው ባለመኪና ቆመና አይሱዙው እንዲያልፍ አደረገው፡፡ ያን ጊዜ መንገዱ ተከፍቶ መጨናነቁ ተፈታ፡፡ የአይሱዙው ሾፌር ግን ላሳለፈው ሰው ምስጋናም ሳያቀርብ ፈትለክ አለ፡፡

ይህ ቀላል አጋጣሚ ልዩ ልዩ ጥያቄዎችን እንድናነሣ ቢያደርገን መልካም ነው፡፡ የአይ ሱዙው ሾፌር ለምን ለመጠምዘዝ በማይቻልበት መሥመር በኩል መጣ? ከኋላው ቆመው ጊዜና ነዳጅ ለሚያባክኑ ሌሎች ሰዎች ለምን አላሰበላቸውም? የአይሱዙው ሾፌር በተሳሳተ መሥመር ለመታጠፍ ቢመጣም በግራው በኩል የሚያልፉት ሌሎች ሾፌሮች አንዳቸው እንኳን በመቆም ለምን አላሳለፉትም? እነዚያ ሁሉ ሾፌሮች እንደነርሱ ያሉ ሌሎች መኪና ነጅዎች በአንድ አይሱዙ ምክንያት መቆማቸው እንዴት አላስጨነቃቸውም? በመጨረሻስ ከፊታችን የነበረው ሾፌር ለምን አይሱዙውን አሳለፈው? የአይሱዙው ሾፌርስ ለምን አላመሰገነውም?
ይህ ቀላል ችግር እንዲሁ የተፈጠረና እንዲሁም የተፈታ አይደለም፡፡ ሌሎች በሀገሪቱ ውስጥ የሚፈጠሩ ከባድና ታላላቅ ችግሮች በሚፈጠሩበትና ሊፈቱም በሚችሉበት ምክንያትና መንገድ የመጣና የተፈታ ነው፡፡ ችግር ፈቺ ዜጋ ባለመሆን የሚመጣ፣ በመሆንም የሚፈታ ነው፡፡ ችግር ፈቺ ዜጋ የአንዲት ሀገር የሥልጣኔዋ መሠረት፣ የዕድገቷም አቀላጣፊ፣ ብሎም የነጻነቷ አስገኚና የሉዓላዊነቷም ጠባቂ ነው፡፡ አንዲት ሀገር ገንዘብም፣ ነዳጅም፣ በቂ መሠረተ ልማትም፣ የተማረና የሠለጠነ የሰው ኃይልም ባይኖራት ችግር ፈቺ ዜጋ ካላት እነዚህን ነገሮች በአጭርና በተቀላጠፈ መንገድ ልታገኛቸው እንደምትችል ጃፓንና ኮርያን ያየ ያውቀዋል፡፡
ችግር ፈቺ ዜጋ ማለት አሳቢነት ያለው፣ ኃላፊነት የሚሰማውና ራሱን ላመነበት ተልዕኮ የሚመድብ ዜጋ ማለት ነው፡፡  አንድ ሰው ያስባል ሲባል አስገራሚ ነገር ነው፡፡ ምክንያቱም ሰውን ከእንስሳት ከለዩት ነገሮች ዋናው ለማሰብ መቻሉ ነውና፡፡ ስለሚያስብ ዜጋ መናገር የማያስብ ዜጋ መኖሩን በጎንዮሽ ማሳየት ስለሚሆን ነው አስገራሚ የሚሆነው፡፡ የማያስብ ሰው አለን? የሚል ጥያቄ ስለሚያስነሣ፡፡ ማሰብን ከአእምሮ የዕለት ተዕለት ሥራ አንጻር ካየነው፣ ማሰብን ከሰው ተፈጥሮ ጋር ብቻ ካመዛዘነው የማያስብ ሰው የለም፡፡ የሚያስብ ዜጋ ማለት ግን ከዚህ ይለያል፡፡ እዚህ ላይ አሳቢነት ያልነው በእንግሊዝኛው Thoughtfulness የሚለውን ነው፡፡ አሳቢነት አንድ ሰው ማንኛውንም ነገር ሲወስን፣ ሲያደርግና ሲከውን ለአካባቢው፣ ለሌሎች ሰዎች ብሎም ለሀገሩና ለቀጣዩ ትውልድ እያሰበ፣ ለእነዚህ ሁሉ መልካም ሊያደርግ በሚችልበት መንገድ ሲወስን፣ ሲያደርግና ሲከውን ነው፡፡ የአይሱዙው ሾፌራችን ከጎደሉት ነገሮች አንዱ ይኼ ነበር፡፡ እርሱ ራሱ መንገድ ማግኘቱን፣ ታጥፎ ለመሄድና የራሱን ጉዳይ ለመፈጸም መቻሉን እንጂ በአካባቢው፣ በሌሎችና በሀገሩ ላይ የሚያስከትለውን ችግር ለማሰብ ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ ለምሳሌ እንዲህ ማሰብ ይችል ነበር፡፡ ከኋላዬ መንገድ የተዘጋበት አምቡላንስ አለ፤ በአምቡላንሱ ውስጥ ደግሞ ልትወልድ ምጥ የተያዘች ሴት አለች፤ ከኋላዬ ልጆቹ አደጋ ውስጥ ናቸው ተብሎ ከቢሮው የተጠራ አባት አለ፤ በአስቸኳይ ነድቶ ልጆቹን መታደግ ይፈልጋል፤ ከኋላዬ የቆሙት መኪኖች ያለ አግባብ ቆመው የሚለቅቁት ጢስ አካባቢውን እየበከለው ነው፤ እኔ መንገዱን በመዝጋቴ አውቶቡስና ታክሲ የሚጠብቁ ሰዎች በፀሐይ እየተንቃቁ ነው፤ አሳቢነት ከሌለ እነዚህን ነገሮች የሚያስበውን ልቡና ስግብግብነት ስለሚጫወትበት ችግር ፈጠሪ እንጂ ችግር ፈቺ መሆን አይቻልም፡፡ አሳቢነት በሌለው ሰውና በሌላቸው ወገኖቹ ዘንድ በሌሎች ሰዎች መብት ላይ መጫወት፣ ሌሎችን ሰዎች ማታለል፣ የሌሎችን ሰዎችን ሰልፍ ጥሶ መቅደም፣ ቆሻሻን ከግቢ አውጥቶ መንገድ ዳር መድፋት፣ጊዜው ያለፈበት ምኃኒትና ምግብ መሸጥ፤ በዘመድ ቅድሚያ ማግኘትና ሌሎችም እንደ አራድነት ይቆጠራሉ፤ አድራጊዎችም ይሞገሳሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ለጊዜው የራሳቸውን ችግር እየፈቱ ይመስላቸዋል እንጂ ውስብስብ ችግር በራሳቸውም ላይ እየፈጠሩ ይሄዳሉ፡፡ አራዳነት የሚሠራው የበለጠ አራዳ እስኪመጣ ድረስ ነው፡፡ አራዳነትን የችግር መውጫ የሚያደርጉት የበለጠ አራዳ ሲመጣ ችግር ላይ ይወድቃሉ፡፡
ሰውየው ከጓደኛው ጋር ወርቅ ሊዘርፉ ይሄዳሉ፡፡ አንድ ሀብታም ሰው ቤት ገብተው ወርቅ ይዘርፉና ወደ ጫካ ገቡ፡፡ እዚያ ጋደም ብለው በየራሳቸው እንዲህ ሲሉ በየራሳቸው አሰቡ፡ ዛሬ ይኼ ሰው ባይኖር ኖሮ ይኼ ሁሉ ወርቅ የእኔ ብቻ ይሆን ነበር፡፡ እንዴት ብቻቸውን ሊወስዱ እንደሚችሉም አውጠነጠኑ፡፡ አንደኛው ለሌላኛው ‹እባክህ ከተማ ገብተህ በምታውቀው መንገድ ምግብ ግዛ› አለው፡፡ ያም ብቻውን ለማሰብ ጊዜ ማግኘቱን ሲያይ እሺ ብሎ ከተማ ሄደ፡፡ ጫካ የቀረውም ‹‹አሁን እንደመጣ በዚህ ጩቤ ሆዱን እዘረግፈውና ብቻዬን ወርቁን እወስዳለሁ› ብሎ ተዘጋጀ፡፡ ምግብ ሊገዛ የሄደውም ‹እዚህ እንጀራ ላይ መርዝ ነስንሼ እሰጠዋለሁ› ብሎ አዘጋጅቶለት መጣ፡፡
እንደተገናኙ ጫካ የቀረው ጓደኛ የወዳጁን አንጀት በጩቤ ዘረገፈና ወርቁን ወረሰ፤ ከዚያም መሬት ላይ አረፍ ብሎ ጓደኛው ገዝቶ ያመጣውን እንጀራ ብቻውን በላ፡፡ ከደቂቃዎች በኋላም እርሱም በሞት ተከተለው፡፡ ወርቁም ጫካ ውስጥ ብቻውን ቀረ፡፡ ይህ ነባር ተረት ምንጊዜም ከአራዳ የሚበልጥ አራዳ መኖሩን እንድናስብና ራሳችንን ብቻ እንዳናይ የተተረተ ነው፡፡
ከአይሱዙው በስተግራ በኩል ያልፉ የነበሩ ባለመኪኖች ይህ ጎድሏቸው ነበር፡፡ ለሰከንዶች ቆመው አይ ሱዙው የፈጠረውን ችግር ቢፈቱት አያሌ የማያውቋቸውን ችግሮች ሊፈቱ እንደሚችሉ አላሰቡም፡፡ ከኋላ ታግተው የተያዙ ከሠላሳ በላይ መኪኖችን ችግሮች እንደሚፈቱ፤ ምናልባትም ደግሞ ሳያስቡት የእነርሱንም ችግሮች አብረው እንደሚፈቱ የሚያገናዝቡበት ዐቅም አልነበራቸውም፡፡ ከኋላ ማን እንዳለ ማን ያውቃል? ሚስት? ልጅ? ወንድም? እናት? አባት? ጎረቤት?
አንድ ወዳጄ እንዲህ አጫውቶኝ ነበር፡፡ አንድ ሐኪም በሥራ መካከል ለሻሂ በሄደበት ጊዜ በድንገት ከሐኪም ቤቱ ይደወልለታል፡፡ ስልኩን ማንሣት ግን አልፈለገም፡፡ በአንድ በኩል ከጓደኞቹ ጋር ሻሂ መጠጣት ፈልጓል በሌላ በኩልም ትንሽ ሞቅ ያለ ወሬ ይዟል፡፡ ከአንድ ሰዓት በኋላ ወደ ሕክምና ጣቢያው ሲመለስ ግን ጆሮ ጭው የሚያደርግ ነገር ነበር የገጠመው፡፡ የገዛ ወንድሙ በመኪና አደጋ ተጎድቶ በድንገተኛ ነበር የመጣው፡፡ ደም ይፈስሰው ነበር፤ ነርሶቹ ማድረግ የሚችሉትን ሁሉ አደረጉ፤ ነገር ግን ሕይወቱን ሊታደጓት እልቻሉም፡፡ ማን ያውቃል የሐኪሙ መምጣት የሚፈጥረው ነገር ይኖር ነበር፡፡ አሳቢነት ያለው ሰው ምንጊዜም ነገሮችን አርቆ አያስባቸውም፤ ያቀርባቸዋል፡፡ በራሱ ላይ፣ በወገኑ ላይ፣ በቤተ ሰቡ ላይ እንደተፈጸሙ አድርጎ ይቆጥራቸዋል፡፡
ችግር ፈቺ ዜጋ አሳቢነትን ገንዘብ ከማድረጉም በተጨማሪ ኃላፊነትም ይሰማዋል፡፡ ራሱን ተጠያቂ ያደርጋል፡፡ ይህን መሥራት ግዴታዬ ነው ብሎ ያስባል፡፡ ለነገሮች የኦሪት ፍየል አይፈልግም፡፡ የኦሪት ፍየል ፍለጋ ማለት ለአንድ ነገር የሚጠየቅ፣ የሚቀጣ ሌላ አካል ፍለጋ ማለት ነው፡፡ አይሱዙውን ያሳለፈው ሰው ይህ ነገር ሳይኖረው አይቀርም፡፡ ይህንን የተወሳሰበ የትራፊክ መጨናነቅ መፍታት ያለበት የትራፊክ ፖሊሱ ነው ብሎ አላሰበም፤ ወይም ለዚህ ሁሉ ችግር ተጠያቂው ይህ የአይ ሱዙ ሾፌር ነው ብሎ የሚያመካኝበት አካል አልፈለገም፡፡ ከዚያ ይልቅ ይህንን ችግር መፍታት የእኔ ድርሻ ነው፤ እችላለሁም ብሎ አሰበ፡፡ ስለዚህም መኪናውን አቁሞ አይሱዙውን አሳለፈው፤ ችግሩም ተፈታ፡፡ በየመሥሪያ ቤቱ ይህንን መሰል ሰዎች ብናገኝ ኖሮ ‹አለቃዬ የሉም፣ መመሪያ የለም፣ እኔን አይመለከትም፣ ሌላ ጊዜ ና› የሚሉ አታካችና አድካሚ መልሶች አይኖሩም ነበር፡፡ አንድ ሰው እርሱ ራሱ ሊወስን ባይችል እንኳን ለሚወስነው ሰው ሃሳብ መስጠት፣ ወደሚወሰንበት ቦታ በትክክል ማስተላለፍ፣ መከታተል፣ መረጃ መስጠት ይችላል፡፡ መቼም ፋይሉ ራሱ ተነሥቶ ወደ አለቅዬው ዘንድ አይሄድም፡፡
ሚኒያፖሊስ የሚኖር አንድ ወዳጄ እንዲህ አጫውቶኝ ነበር፡፡ ከሥራ በምትተርፈው ጊዜ በግል መኪናው ኢትዮጵያውያንን  መኪና ያለማምድ ነበር፡፡ ሥራው  ፈቃድ ያስፈልገዋል፡፡ እርሱ ግን ፈቃድ የለውም፡፡ ፈቃድ ስለሌለውም ከአካባቢው ራቅ ብሎ በከተማ ጥግ ባሉ መንደሮች መንገድ ላይ ነበር የሚያለማምደው፡፡ ለብዙ ጊዜ ከሠራ በኋላ አንድ ቀን ስለ መኪና ማቆም አንዲትን ልጅ ለማሳየት ወደ አንድ መንገድ ዳር ይወጣል፡፡ በዚያ መንገድ አጠገብ አንድ ቤት አለ፡፡ አንዲት በእድሜ ገፋ ያለች ሴት ከቤቱ ወጣችና ወደ እርሱ መጣች፡፡ መኪናውን ተጠግታም ‹አንተ ሰው እዚህ ሠፈር ምንድን ነው የምታደርገው? የተለያዩ ሰዎች እየያዝክ ትመጣለህ፣ እዚህም ለጥቂት ጊዜ ትቆማለህ፣ በዙ ጊዜ ተከታትዬሃለሁ፣ ፎቶ ግራም አንሥቼሃለሁ፣ የተፈጠረ ችግር ስለሌለ ግን ዝም ብያለሁ፤ ለመሆኑ ምን እያደረግክ ነው?› ብላ ጠየቀችው፡፡ እርሱም ደንግጦ እኅቶቹን መኪና እያለማመደ መሆኑን ነገራት፡፡ ‹ስንት እኅቶች ናቸው ያሉህ?› አለችው ተገርማ፡፡ ከዚያ በኋላ እዚያ አካባቢ ሄዶ አያውቅም፡፡
ኃላፊነት የሚሰማው ዜጋ እንደዚህ ነው፡፡ አንድን ነገር ለመከታተል፣ ለማድረግ ወይም መረጃ ለመያዝ፣ በአንድ ጉዳይ ላይ የሚችለውን ለማድረግ የማንንም ማነሣሣት፣ ውክልና፣ ሹመት ወይም መመሪያ አይጠብቅም፤ እርሱ ለማድረግ መልካም የመሰለውንና፣ ሕግም የሚፈቅደውን ያደርጋል፡፡ ሀገሬን፣ ሕዝቤን፣ ወገኔና የመታደግ ኃላፊነት አለብኝ ብሎ ያምናል፡፡ ኃላፊነቱንም ራሱ ከራሱ ይቀበላል፡፡ በአምስት ዓመቱ የጣልያን ወረራ ጊዜ በየጫካው ገብተው ጠላትን ፋታ የነሡት አርበኞች ይህ ነገር ነበራቸው፡፡ የመከላከያ ሚንስቴር እንዲያሠማራቸው አልጠበቁም፣ ለሀገራቸው ነጻነት ራሳቸው ኃላፊነቱን ወስደው ተዋጉ፡፡ ምንም አልሾማቸውም፣ ራሳቸውን ሾሙ፤ ማንም አልቀጠራቸውም፣ ራሳቸውን ቀጠሩ፡፡
ይህ ኃላፊነት የመውሰድ ችሎታ ነው ራስን ለተልዕኮ የሚያሠማራው፡፡ ሰው ማሰብ ከቻለ፣ ኃላፊነትንም ከወሰደ ራሱን ለአንዳች ተልዕኮ ያሠማራል፡፡ የሁለቱም ነገሮች መገለጫቸው ተግባር ነውና፡፡ ያ ከፊታችን የነበረው ሾፌር ስለሌሎች አሰበ፣ ችግሩን የመፍታት ኃላፊነትንም ወሰደ፡፡ እነዚህ ሁለቱ በሦስተኛው ነገር ባይታጀቡ ኖሮ ጥቅም አይኖራቸውም ነበር፡፡ ተልዕኮን በመውሰድ፡፡ ያ ሾፌር መኪናውን አቁሞ አይሱዙውን የማሳለፍ ተልዕኮን ራሱ ወሰደ፡፡ ከፊታችሁ ቀድመዋችሁ ከገቡ በኋላ በሩን ይዘው የሚያሳልፏችሁ ሰዎች፣ እናንተ የጣላችሁትን ቆሻሻ አንሥተው ቅርጫት ውስጥ የሚጨምሩ ሰዎች፣ ደክሟችሁ መምጣታችሁን አይተው ወንበር የሚለቁላችሁ ሰዎች፣ ታክሲ ውስጥ ሽማግሌዎች ሲመጡ የፊት ወንበራቸውን ለቅቀው ወደ ኋላ የሚጠጉ ሰዎች፣ ለነፍሰ ጡር ሴቶች ቅድሚያ የሚሰጡ ሰዎች፣ ቤታችሁ መጥተው ቁጭ ሳይሉ ቤታችሁን ማስተካከል የሚጀምሩ ወዳጆች፣ በአንዳች ነገር ተቸግራችሁ ሲያዩ የመፍትሔውን አቅጣጫ የሚያመለክቷችሁ ሰዎች፣ ለነጻነትና እኩልነት፣ ለፍትሐዊነትና ለሰብአዊ መብት ተቆርቁረው የሚታገሉ ሰዎች ሌሎች አይደሉም፣ አሳቢነትን ገንዘብ አድርገው፣ ኃላፊነትንም ወስደው ለራሳቸው ተልዕኮ የሰጡ ሰዎች ናቸው፡፡
ራሳቸውን ለተልዕኮ ያሠማሩ ችግር ፈቺ ዜጎች ናቸው የዓለማችንን ችግሮች ያቃለሉ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ሃሳቦችን ያመነጩት፣ የፖለቲካና የማኅበራዊ እሳቤዎችን ጽንሰ ሃሳቦች የቀረጹት፣ ለሰላም ላይ ታች ያሉት፣ እንደ ጧፍ ነድደው እንደ መብራት ያበሩት፤ ራሳቸውን ለተልዕኮ ያሠማሩ ችግር ፈቺ ዜጎች በመኖራቸው ነው በየቢሮው፣ በየተቋማቱ፣ በየጤና ጣቢያው፣ በየቴሌ ቅርንጫፉ ቢያንስ የባሰ ችግር እንዳይፈጠር ያደረጉት፤ እነዚህ ዜጎች ናቸው ሀገራችንን የተሸከሙት፤ እነርሱ ሲበዙ ዕድገታችንና ብልጽግናችን፣ ዴሞክራሲያችንና የፖለቲካ ባህላችን፣ ማኅበራዊ መስተጋብራችንና የኑሮ ደረጃችን ይሻሻላል፡፡ እነርሱ ሲያንሱ ደግሞ ሙስናና ብልሹ አሠራር፣ አምባገነንነትና ስግብግበነት፣ ችግርና ጠኔ፣ ቀጠናና ችጋር፣ ቢሮክራሲና የዘመድ አሠራር፣ ትብትብና ውስብስብነት፣ ምሬትና ሮሮ፣ ኋላ ቀርነትና ድህነት፣ ድንቁርናና ማይምነት ሀገርን እጅ ተወርች አሥረው ይይዟታል፡፡
ችግር ፈቺ ዜጋ ባልበቀለበት ሀገር ችግር ፈቺ ፖለቲከኛ፣ ችግር ፈቺ መሪ፣ ችግር ፈቺ፣ ምሁር፣ ችግር ፈቺ የሃይማኖት አባት፣ ችግር ፈቺ  ነጋዴ፣ ችግር ፈቺ ቢሮክራት፣ ችግር ፈቺ የፍትሕ ሰው፣ ችግር ፈቺ ፖሊስ፣ ችግር ፈቺ ሐኪም፣ ችግር ፈቺ ጋዜጠኛ፣ ችግር ፈቺ ደራሲ፣ ችግር ፈቺ መሐንዲስ ማሰብ ሕልም ነው፡፡
ለዚህም ነው ጥቂቶች ችግር ፈቺ ዜጎቻችንን ‹ችግር ፈቺ ዜጎች ሆይ፣ እንደ ምድር አሸዋ እንደ ሰማይ ከዋክብትም ያብዛችሁ፤ እንደ ምድር አፈርና እንደ ሰማይ ጠል የበዛውን ችግራችንን ታስወግዱልን ዘንድ› ብለን መመረቅ ያለብን፡፡
© ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ስለሆነ በተመሳሳይ ሚዲያ መጠቀም ክልክል ነው