ፓትርያርኩ ያነሷቸው አራት መሠረታዊ ነገሮች

የዘንድሮው የርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ሲከፈት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ጉባኤው ሊያተኩርባቸው ብሎም ውሳኔ አሳልፎ ሊፈጽማቸው ይገባል ያሏቸውን አራት መሠረታዊ ነገሮች አንሥተዋል፡፡
1.         ብልሹ አሠራርን ማረምና ማስወገድ
2.       አስተዳደሩን በአዲስ መልክ ማዋቀር
3.       የፋይናንስ አያያዝን ማስተካከል
4.       የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን እንደገና ማዋቀር
በመጀመርያ ፓትርያርኩ ከተለመደው መወድሳዊና ቢሮክራሲያዊ ንግግር ወጣ ብለው በቤተ ክርስቲያኒቱ ወቅታዊና አሳሳቢ ጉዳዮች ላይ ማተኮራቸው የሚያስመሰግን ነው፡፡ ከተሰየሙ በኋላ የመጀመርያቸው በሆነው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ላይ ያቀረቡት መክፈቻ ከሁለት ነገሮች አንጻር ተገቢም ተመስጋኝም ነው፡፡

1.       ከወቅታዊነት 
ብልሹ አሠራር፣ የመዋቅር ማሻሻያ፣ የፋይናንስ ሥርዓቱን ማሻሻልና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሁኔታ በቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት ላይ ቅርብ የሆነ አደጋ የደገኑ ናቸው፡፡ በተለይም ሙስና ዛሬ ዛሬ የቤተ ክህነቱ ዋና መለያ ጠባይ እየሆነ ነው፡፡ ሲሞናዊነት ቤተ ክህነቱን ጥፍንግ አድርጎ በመያዙ ከጵጵስና እስከ ዲቁና ያለው መዓርግ በገንዘብ እስከ መሰጠት ደርሷል፡፡ የደብር አስተዳዳሪነት፣ የሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅነት፣ የመመሪያ ኃላፊነት፣ የውጭ የትምህርና የሥራ ዕድል ያለ ጉቦና መማለጃ የማይሆኑ ሆነዋል፡፡ ዛሬ ዛሬ በቤተ ክህነቱ ሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንና አምስቱ አዕማደ ምሥጢራት ትርጉማቸው ተለውጦ ሰባት ሺና አምስት ሺ ብር ሆነዋል፡፡ ‹ከሐዋርያት ጋር ና› ማለት አሥራ ሁለት ሺ ብር ይዘህ ና፤ ‹ሰባው አርድዕት የሉም ወይ› ማለት ሰባ ሺ ብር ያስፈልግሃል፤ ሠላሳ ፣ ስድሳና መቶ ማፍራት ሰለሳ፣ ስድሳና መቶ ሺ ብር መስጠት ሆነዋል፡፡ ስለዚህም ፓትርያርኩ በዚህ ጉዳይ ላይ ሥር ነቀል የሆነ ለውጥ በማምጣት የሙስናንም ምንጭ ማድረቅ አለብን ማለታቸው ተገቢ ነው፡፡ 
የቤተ ክህነቱ መዋቅር ከተዘረጋ ግማሽ ማዕተ ዓመት ያለፈው፣ የመዋቅር ማሻሻያ ሲያልፍም ያልነካው፣ መምሪያዎችና ክፍሎች፣ ድርጅቶችና ተቋማት  ያለ ጥናት በአንድ ቀን ውሳኔ ሲከፈቱና ሲዘጉ የሚኖሩበት፣ ሀገሪቱ ቢፒ አር ና ካይዘንን ስትተገብር ከቦታው ያልተነቃነቀ መዋቅር ነው፡፡ ምን ያህል የሰው ኃይል አላችሁ? በምን ደረጃ የሠለጠነ የሰው ኃይል ያስፈልጋችኋል? በአንድ ደብር ስንት ሰው መኖር አለበት? ቢባል ቤተ ክህነት መልስ የለውም፡፡ ኮምፒውተር በሌለበት አጥቢያ የኮምፒውተር ጸሐፊ፣ ለአንድ አጥቢያ አራት የስብከተ ወንጌል ኃላፊ፣ የአብነት ትምህርት ቤት ለሌለበት ደብር የአብነት ትምህርት ተቆጣጣሪ የሚመደበው መዋቅሩ ያልተጠና የዘመድ አሠራር የተበተበው ስለሆነ ነው፡፡
የቤተ ክህነቱ የፋይናንስ አሠራር አሁን ዓለም ከደረሰበት ሳይሆን ሀገሪቱ ከደረሰችበት እንኳን ቢመዘን ለቅርስ መቀመጥ ያለበት ነው፡፡ ያልጠፉ ሞዴላ ሞዴሎች መገኛ፣ አንዳች የአካውንቲንግ ኮርስ ያልወሰደ ሰው ሚሊዮኖችን የሚያንቀሳቅስበት፤ በዘመነ ኮምፒውተር በአሮጌ መዝገብ በሠንጠረዥ የሚሠራበት፣ ያለ በጀት ወጭ የሚፈቀድበት፤ ዕቅድና መርሕ የማይመራው፣ ለሙስና እጅግ የተጋለጠ፣ የፋይናንስ ሕግ የሌለው ቤት ነው ቤተ ክህነቱ፡፡ ቤታቸውን ከፍተው እየሄዱ ሰው ሌባ ይላሉ እንዳለቺው ሴት በሩን ለሙስና ከፍቶ ሙስናን መታገል አይቻልምና የፋይናንስ ሥርዓቱ ማሻሻያ ያስፈልገዋል መባሉ ዘገየ ይባል እንደሁ እንጂ ለምን የሚያሰኝ አይደለም፡፡
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የተከፋፈለበት መንገድ ፈጽሞ ጥናት የሚጎድለው ነበር፡፡ በወቅቱ ብጹዐን አባቶች የአቡነ ጳውሎስን ሥልጣን ለመቀነስ ሲሉ ብቻ ያደረጉት ነው፡፡ አማራጭ ጥናቶች ቀርበው አልተገመገሙም እንጂ በአንድ ጉሮሮ ይገባ የነበረውን ጉቦ በአራት ጉሮሮ እንዲገባ ማድረግ ባላስፈለገ ነበር፡፡ ቢያንስ ዐሥሩን ክፍለ ከተሞች በአውራጃ ደረጃ አዋቅሮ፣ በሥራ አስኪያጅ በመምራት፣ የሥልጣን ክልላቸውን ወስኖ በመስጠት ለሕዝብ ቅርብ እንዲሆኑ ማድረግ ይገባ ነበር፤ ከዚህም በላይ የሰው ኃይል ምደባና ዝውውርን በማዕከል ደረጃ በሰው ኃይል ቅጥርና ዝውውር ኮሚቴ በኩል በማየት፣ የቅሬታ ሰሚ ቦርድ በማቋቋም፣ የዘመድ አሠራሩን መቀነስ ይቻል ነበር፡፡ ከዚህም በላይ በጋራ ሊሠሩ የሚገባቸውን ጉዳዮች ለማቀናጀት እንዲቻል ሀገረ ስብከቱን በአንድ ሊቀ ጳጳስ መምራት፣ ከሊቀ ጳጳሱ ጋር የሚሠራና በጉባኤ የሚወስን ዐቢይ ኮሚቴ በማቋቋምም ውሳኔዎችን ከግል ወደ ቡድን መውሰድና ሀገረ ስብከቱን በተሻለ መምራት በተቻለ ነበር፡፡ ይህንን ሁሉ ከማድረግ ግን ሀገረ ስብከቱን ከአራት ከፍሎ አራት ሥራ አስኪያጅና ሁለት ጳጳስ በመሾም እንደ ከነዓን በዕጣ ነው ያከፋፈሏቸው፡፡ ያውም ከተመደቡት ጳጳሳት አንዱ አራት ሀገረ ስብከት የሚያስተዳድሩ ነበሩ፡፡
እነዚህ ሁሉ ችግሮች ቤተ ክርስቲያኒቱን አላላውስ ስላሏት ነው በዚህ ጊዜ ለመፍትሔው እንነሣ ብለው ፓትርያርኩ ማቅረባቸው ወቅታዊ ነው የምንለው፡፡
  1. የግድ ነው
ለሌላው አርአያ ትሆናለች ተብላ የምትጠበቅ ቤተ ክህነት እርሷ ራሷ በችግር መጠቀስ የለባትም፡፡ ከዚህ በፊት የፍትሕ አካላቱ ቤተ ክህነትን የሚመለከቱ ክሶች እየበዙ መምጣታቸውን ለቅዱስ ሲኖዶስ ማሳሰቢያ ሰጥተው ነበር፡፡ የሰብአዊ መብት ኮሚሽንም ከሚደርሱት አቤቱታዎች አብዛኞቹ ቤተ ክህነቱን የሚመለከቱ መሆናቸው ይሰማል፡፡ የቤተ ክህነቱ ግቢም ሥራ በሚሠሩ ሰዎች ሳይሆን አቤቱታ ይዘው ከመላዋ ሀገሪቱ በሚመጡ ባለጉዳዮች የተሞላ ነው፡፡ በየአጥቢያውም ተአምርና ገድል ሳይሆን የገንዘብ መበላት፣ የቦታ መሸጥ፣ የዘመድ ቅጥር፣ የሙዳየ ምጽዋት መሰረቅ ሆኗል የሚሰማው፡፡ በአዲስ አበባና በታላላቅ ከተሞች የሚገነቡትን ሕንጻዎች የሚያጠና ቢኖር ከቤተ ክህነቱ ጋር በተያያዙ ሰዎች የሚገነቡት የአንበሳው ድርሻ ይኖራቸዋል፡፡
ይህን ሁሉ ይዞ ወንጌለ መንግሥትን መስበክ፣ የነፍስ ድኅነትን ለማምጣት መሮጥና ሐዋርያዊ አገልግሎት መፈጸም የማይታሰብ ነው፡፡ በቤተ ክህነቱ የሚከበሩትና የሚፈሩት፣ ሰው የሚፈልጋቸውና የሚሟሟትላቸው መምሪያዎች ከገንዘብ ጋር የተነካኩትን እንጂ ከስብከት፣ ከክህነት፣ ከሊቃውንት ጉባኤ፣ ከሰንበት ትምህርት ቤት፣ ከገዳማት ጋር የተያያዙትን አይደለም፡፡ ዋናው የቤተ ክርስቲያኒቱን ተልዕኮ የሚያስፈጽሙት መምሪያዎች፣ የቅጣት ቦታዎች ሆነዋል፡፡ ዛሬ ዛሬ እገሌ በሊቃውንት ጉባኤ ተመደበ ማለት የዕውቀት ማሳያ ሳይሆን ‹ተወረወረ› ማለት ሆኗል፡፡
የሬዲዮና የጋዜጣ፣ የመጽሔትና የፊልም ጀማሪ የነበረች ቤተ ክህነት ሚዲያዋን ሁሉ ዘግታ ዘግታ ዛሬ ሕዝብ የማያውቃቸው፣ ሕዝቡንም የማያውቁ ሚዲያዎችን ይዛ ቀርታለች፡፡ ስንት አጥቢያ አለሽ? ስንት ምእመን አለሽ? ስንት ካህን አለሽ? ስንት ገዳም አለሽ? ስትባል ቤተ ክህነት በግምት ነው የምትናገረው፡፡ ዛሬ ምእመኑ ጥያቄውን የሚመልስለት አባት ይፈልጋል፡፡ በቤተ ሰብ ምጣኔ፣ በልጆች አስተዳደግ፣ በትዳር ጉዳዮች፣ ከአዳዲስ አስተሳሰቦች አንጻር በመጡ ማኅበራዊና ሳይንሳዊ ጉዳዮች ዙሪያ ጥያቄ አለው፡፡ በዚህ ዘመን ቢሮ የሚቀመጡ፣ መንበረ ጵጵስናቸው ውስጥ መኖራቸው ሳይታወቅ ዓመት የሚያሳልፉ አባቶችን ሳይሆን እንደ እረኛው ከበጎች ጋር የሚሆኑ አባቶችን ሕዝቡ ይፈልጋል፡፡
ታድያ ይህንን ሁሉ በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ይዞ ከመጓዝ በላይ ምን አሳዛኝ ነገር አለ፡፡ የግድ ነው፤ ቤተ ክህነት የግድ ነው፤ ራሷን መፈተሽ፣ ራሷን ማረምና ራሷን ማንቃት አለባት፤ በጊዜ ካልታከመች በሽታው ገዳይ ነው፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ የራሱን መዋቅርና አሠራር ከማስተካከል፣ በሊቃውንትና በባለሞያዎች የሚታገዝበትን መንገድ ከመፍጠር፣ ውሳኔዎቹን የሚያስፈጽምበትን ዐቅምና አሠራር ከመዘርጋት መጀመር አለበት፡፡ ዛሬ ሁሉን ዐውቃለሁ የሚባልበት ጊዜ አይደለም፡፡ አዲሱ የሮማው ፓፓ ስምንት አማካሪዎችን በቅርቡ የሾሙት የዓለምን ሂደት ተገንዝበውት ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ በሊቃውንት መደገፍ አለበት፡፡ ሃሳቦች በአንድ ቀን ጉባኤ ተጀምረው ማለቅ የለባቸውም፡፡ አስቀድሞ በሊቃውንትና በባለሞያዎች የተመከረባቸው መሆን አለባቸው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ የለውጡን ሥራ ከራሱ በመጀመር ለሌሎች አርአያ እንዲሆን ይጠበቃል፡፡‹ ባለ መድኃኒት ሆይ…› እንዲል፡፡
አሁን በፓትርያርኩ የቀረቡትን ሃሳቦች ቅዱስ ሲኖዶሱ መሠረት ያለው፣ ለምእመኑ ተስፋ የሚፈነጥቅና የነገውን መንገድ የሚያቀና ውሳኔ ያሳልፍባቸዋል፤ አፈጻጸማቸውም ከወረቀት ይዘላል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ችግሮችን አፍረጥርጦ መፍታት እንጂ እንደ ቆጵሮስ በጎን አልፎ መሄድ መድኃኒት አይሆንም፡፡ ያለበለዚያ ግን ፓትርያርኩ እንዳሉት ‹በሁላችንም ላይ ታሪክና እግዚአብሔር ይፈርዱብናል፡፡›