የአንደኛ ዓመት ማስታወሻ፤ ሽቅቡም ቁልቁሉም!
‹ዞን ዘጠኝ እንዴት ተመሠረተ? ለምን ተመሠረተ? ለምን ዞን ዘጠኝ ተባለ?…› እና ሌሎችም ተመሳሳይ ጥያቄዎች ባሳለፍነው ዓመት በዞን ዘጠኝ የፌስቡክ ገጽ በብዛት ያስተናገድናቸው ጥያቄዎች ናቸው፡፡ እነሆ ‹ዞን ዘጠኝ› የሚለውን ስም አውጥተን ጦማሩን (ብሎጉን) የፈጠርንበትን ቀን (ግንቦት 5/2004) አንደኛ ዓመት በማስመልከት ለነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት እንሞክራለን፡፡
በመጀመሪያ እንዲህ ነበር
በሊባኖስ ቤይሩት በአሠሪዎቿ ድብደባ የደረሰባት የዓለም ደቻሳ ሞት ብዙ የማኅበራዊ አውታር ኢትዮጵያውንን አስቆጣ፡፡ ይህ ምሬት ፌስቡክን እንደማህፀን ተጠቅሞ ‘ደጉ ኢትዮጵያዊ’ የተሰኘውን ቡድን ወለደ፡፡ በአጋጣሚ የተወሰኑ የዞን ዘጠኝ አባላት እነዚህ ስብስብ ውስጥ ተገኘን፤ እንዲሁ አጋጣሚ! አንዳንዱ ለሰላምታ፣ አንዳንዱ ሲያልፍ ሲያገድም አንዱ ደግሞ የዓለም ጉዳይ አስቆጭቶት፡፡
የዓለምን ደቻሳን ቤተሰቦች (ልጆች) ለመርዳት የገንዘብ ማሰባሰብና የመሳሰሉት ሥራዎች ሲጠናቀቁ የደጉ ኢትዮጵያ ቡድን አባላት መካከል ጥቂቶቹ ከሌሎች የፌስቡክ ወዳጆች ጋር ወትሮም አየር (በይነመረብ) ላይ በተመሳሳይ ሐሳብ ዙሪያ ሲያወሩ የሚተዋወቁት ሰዎች ነበሩና እየተገናኙ መወያየታቸውን ቀጠሉ፡፡ ይህ መቀራረብ ተጨማሪ ቀጠሮዎችን ወለደ፡፡ በጠፋችው ከተማ አዲስ አበባ እንደመስቀል ወፍ አልፎ አልፎ የሚካሄዱ የፖለቲካ ውይይቶች መከታተል ጀመርን፡፡ ይህ ተከታታይ ግንኙነት ሌላ ሐሳብ ይዞ ብቅ አለ፡፡ በጣም ትንሽ፣ ግን መሰባሰብ የሚፈልግ ሐሳብ፡፡ ለምን በየቦታውን በየብሎጉ የምናወራውን ሰብሰብ አድርገን ወደ አንድ ቦታ አናመጣውም፤ የሚለው ሐሳብ የታሰሩ ጋዜጠኞችን በመጠየቅ ወደ ቃሊቲ በመሄድ ታገዘ፡፡ የቃሊቲው ጉዞ ብዙ መነቃቃትንና የዞን 9ኝን ስም ወለደ፡፡
ስሙ የተገኘው እንዲህ ነው፤ በወቅቱ ከእስረኞች መሐል በማንኛውም ሰው መጠየቅ የሚችሉትን ርዕዮት ዓለሙንና ከእርስዋ ጋር በተመሳሳይ ክስ የተከሰሱ እስረኞችን ለነርሱ በተከለለው ዞን 8 ስናዋራቸው ሒሩት ክፍሌ ‹‹እናንተስ፣ ዞን 9 እነዴት ነው?›› ብላ ጠየቀችን፡፡ በተደናገረ ስሜት ደህና ነን ብለን ስንመልስ ርዕዮት ‹እኛ እዚህ ያለነው እኮ ውጪ ያላችሁትን ትልቁ እስር ቤት ዞን 9 ውስጥ ነው ያላችሁት ነው የምንላችሁ› ብላ አብራራችልን፡፡ ከሰዓታት በኋላ ስም ስንፈልግለት የነበረው የጦማሪዎች ቡድን ስም ተገኘለት – ‹‹ለምን ዞን 9 አንለውም?›› አለ ከመካከላችን አንዱ፤ በፈገግታ አፀደቅነው፡፡ ከዚያ ተጀምረው ወደ ነበሩት ምንና እንዴት እናድርግ ውይይቶች ተመለስን፡፡
የዓለምን ደቻሳን ቤተሰቦች (ልጆች) ለመርዳት የገንዘብ ማሰባሰብና የመሳሰሉት ሥራዎች ሲጠናቀቁ የደጉ ኢትዮጵያ ቡድን አባላት መካከል ጥቂቶቹ ከሌሎች የፌስቡክ ወዳጆች ጋር ወትሮም አየር (በይነመረብ) ላይ በተመሳሳይ ሐሳብ ዙሪያ ሲያወሩ የሚተዋወቁት ሰዎች ነበሩና እየተገናኙ መወያየታቸውን ቀጠሉ፡፡ ይህ መቀራረብ ተጨማሪ ቀጠሮዎችን ወለደ፡፡ በጠፋችው ከተማ አዲስ አበባ እንደመስቀል ወፍ አልፎ አልፎ የሚካሄዱ የፖለቲካ ውይይቶች መከታተል ጀመርን፡፡ ይህ ተከታታይ ግንኙነት ሌላ ሐሳብ ይዞ ብቅ አለ፡፡ በጣም ትንሽ፣ ግን መሰባሰብ የሚፈልግ ሐሳብ፡፡ ለምን በየቦታውን በየብሎጉ የምናወራውን ሰብሰብ አድርገን ወደ አንድ ቦታ አናመጣውም፤ የሚለው ሐሳብ የታሰሩ ጋዜጠኞችን በመጠየቅ ወደ ቃሊቲ በመሄድ ታገዘ፡፡ የቃሊቲው ጉዞ ብዙ መነቃቃትንና የዞን 9ኝን ስም ወለደ፡፡
ዞን9 ስሙን ከማግኘቱ ቀደም ብሎ ስናነሳቸው ከነበሩት ጉዳዮች መካከል አንዱ በአገሩ ጉዳይ ያገባኛል የሚል ወጣት መቀነስ ነበር፡፡ ያገባኛልን ማምጣት በእኛ አቅም የማይሳካ የማይታሰብ እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ነገር ግን ባቅማችን እንደሚያገባን በመናገር የድርሻችንን ለመሞከር ስንነሳ የመጀመሪያው ዓላማ ተበታትኖ የሚታየውን የበይነ መረብ ውይይት መልክ ወዳለው ተዋስኦ ለማምጣት የሚሞክር አለፈመደብ (‹ፕላትፎርም›) ለመፍጠር መሞከር ነበር፡፡ ይህ ሙከራ የተለያዩ ጦማሮች እና የማኅበረሰብ ሚዲያ ገጾች ላይ የሚንጸባረቁትን ሐሳቦቻችንን ወደ አንድ ማምጣት ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ ይህ የመጦመር ሒደት ግን ከግል አራማጅነት ባሕርያችን ተነጥሎ ሊታይ እንደማይችል ገባን፡፡ ዞን9 ላይ ጦማር የሚጽፉ ዘጠኛውያን በግላቸው የየራሳቸውን ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት የሚጠቀሙ አራማጆች መሆናቸውን አልቀየረውም፡፡
በጣም በተገደበ አቅምና በትርፍ ጊዜ የሚዘጋጁት እነዚህ ጦማሮች ከዞን ዘጠኛውያን ውጪ አንባቢዎችንም ጭምር ወደ ጽሑፍ ማምጣት ችለው ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በግላችን ሐሳባችንን እንደፈለግን ከምንገልጽባቸው የግል መንገዶቻችን ወጥተን በከፊል ተቋማዊ እና ቡድናዊ ሐሳቦች ማምጣትን አስለምደውናል፡፡ ኃላፊነት የምንወስድባቸው ሲያሰኘን የማናጠፋቸው እና ከግል ቁጥጥር ውጪ የሆኑ ጽሑፎችን እና ሐሳቦችን ማንፀባረቅ ምንም ደካማ ጎናችን ቢሆንም ሙከራው አስተምሮናል ብለን አናምናለን፡፡ በተለያዩ ተግዳሮቶች የተነሳ እየተቆራረጡ ዓይን አልገቡም እንጂ የሚዲያና የጦማሮች ዳሰሳ ሙከራዎቹም እንደሙከራ የተማርንባቸው ነበሩ፡፡ የግል ኑሮ ውጣ ወረድና ዕቅድ ወደኋላ ያንጓተተው የአንድ ዓመት የጦማሮች ዕቅዳችን በዘመቻዎች ላይ ግን የተሻለ ውጤቶችን አስመዝግቧል ማለት ይቻላል፡፡
ዘመቻዎች
ጥያቄዎችና ትችቶች
የመነቃቃት (‹ኢንስፓይሬሽን›) እጥረት የእኛም ድካም ምንጭ ነበር፡፡ መነቃቃት ማጣታችንን ለመገዳደር ብዙ ሞክናል – የወደቅንበት ትልቁ ፈተናችን ሆኖ ዓመቱ አለፈ እንጂ፡፡ የጦማሮች መቆራረጥ፣ የውይይት ሐሳቦቸን አንስቶ በጋራ ለማውራት መሞከር ጀምረን የወደቅንባው ፈተናዎች ናቸው፡፡ ጠፍተን ብቅ ስንል ፊት የማይነሱን ወዳጆች ባይኖሩን ኖሮ ደግሞ አንድ ዓመት መቆየትም አስቸጋሪ ይሆንብን ነበር፡፡ የተለያዩ የተሰፉ ሐሳብን የማካፈል ሙከራዎችንም ጀምረን አልዘለቅንባቸውም፣ የ‹‹መክሸፍ››ን ተከታታይ ጽሑፍ ጅማሬዎች፣ ተከታታይ የሚዲያና የጦማር ዳሰሳዎች… ጨምሮ ሌሎችንም ማስታወስ ይቻላል፡፡ ታቅደው ባደባባይ ባይወሩም በኛው ድካም የትም ያልደረሱ ሥራዎችም ብዙ ናቸው፡፡ ቋሚ በአንድ ጉዳይ ዙሪያ የሚያጠነጥኑ መጽሐፍትን አሳጥሮ በዳሰሳ መልክ ማቅረብም የታሰበበት ነገር ግን ያልተነገረና የወደቅንበት ፈተና ነው፡፡ ሳንናገር የወደቅንበት ከነብዛቱ ያለፉትን 12 ወራት መዝለቃችን የወዳጆቻችንን ደግነት ያሳያል፡፡ ምስጋና ለዞን ዘጠኝ ነዋሪዎች!
በመጀመሪያው ጽሑፋችን ‹‹የሚያገባውን ትውልድ ፍለጋ…›› ያገባናል ብለን ጀምረናል፡፡ ይህች ሙከራ ትንሽ መሆኗ አያጠራጠርም፡፡ ጥቂቶችን ካስወራች፣ አንዳንዶችን ካወያየች፣ ሌሎችን በየፍላጎታቸው ዙሪያ እንደኛው ዓይነት ኢ-መደበኛም ይሁን መደበኛ ቡድን ለመፍጠር ካነሳሳች ስኬት አጠገብ ባትደርስም ከስረናል ብለን እንዳናስብ ይረዳናል፡፡ አንዱን ዓመት ያያችሁንን፣ ያነበባችሁንን፣ ያበረታታችሁንን ሁሉ እናመሰግናለን፡፡ በአካሄዳችን የተከፋችሁብንም ጥያቄ የሆነባችሁን ሐሳብ ጭምር እንድታካፍሉን ተጋብዛችኋል፤ መልስ ካለን እንመልሳለን፣ መልሱ መሻሻል ከሆነም ለመስተካከል እንጥራለን፡፡ በድጋሚ እናመሰግናለን!
