ብሔራዊ ውርደት በቃ በዳኛቸው ቢያድግልኝ

እንደ ሀገር እየፈረስን እንደ ሕዝብ እየተዋረድን ነው። እያንዳንዳችን በነቂስ የግብዞች መጫወቻ ሆነናል። ተንቀናል፣ ታግተናል። የእምነት ቤቶቻችን በከሀዲዎች ተጠለፉ፤ ፍትህ መስጫዎች ውርደት ማሸከሚያዎች ዜና ማሰራጪያዎች ደግሞ ውሸት መርጫዎች ሆኑ። ነፃነት ያልን እስርን ንብረት እናፍራ ያልን መከራን አተረፍን። የትግራይ ሽፍቶች ከሆዳሞች ጋር ሆነው መዘበሩን፣ በችጋር ጠበሱን። እኛ የሚላስ የሚቀመስ አጥተን ለም ሀገራችንን ለባዕድ ሸጡብን። አርሰን የምንበላ ሞፈራችንን ሰቅለን ባርያ እንድንሆን ፈረዱብን። በረሀብ እየተቆላንም ሆዳሞችን መሸከም ተገደናል። ምሁራን የሌቦች ባለሟል ወታደሮች ደግሞ ዘበኞቻቸው እንዲሆኑ ተገደዋል። ወጣቶች ለእለት ጉርሻቸው ቅጥረኛ ሰላዮች እንዲሆኑ ተመልምለዋል። የልብ ልብ በማግኘታቸው በሁላችንም አንገት ውስጥ ገመድ አጥልቀው ባሻቸው ጊዜ ሊያንቁን ተዘጋጅተዋል። አንድ መሆን ስላልቻልን አንድባንድ ያንቁናል። እናም በብሔራዊ ኩራታችን ምትክ ብሔራዊ ውርደትን እንቀበል ዘንድ እየተገደድን ነው።

ወንጀለኞችን አንገሰን ለራሳችን ግን ታግተናል። ከመንደራችን እየተነቀልን በየአቅጣጫው ስደት ይዘናል። ለራሳችን ተዋርደን ልጆቻችንንም ተስፋቢስ የበዩ ተመልካቾች አድርገናቸዋል። ከዚህ በላይ ሞት፣ ከዚህ በላይ ቅሌት የለም። እንደ ሰው ተፈጥረን ከቤት እንስሳ እንኳን አንሰን መሞት ውርደት ነው። የተነጠቅነውን ክብር አስመልሰን በምንወዳት አገራችን ላይ ኮርተን መረማመድና ለመጪው ትውልድም አኩሪ ታሪክ ሰርቶ ለማለፍ ግን የመጨረሻ ዕድል አለን። በምድር ላይ ለምናደርገው ሁሉ የመዳን መንገድ በእጃችን ይገኛል። ማንም ሊያድነን ማንም ሊያስጥለን አይመጣም። መፍትሄው ብሔራዊ ውርደት በቃ ብሎ መነሳት ነው። በእውቀት፣ በማስተዋልና በጋራ መነሳት የሀገር ማዳኛ ብቸኛው መንገድ ነው። እንደ ኢትዮጵያዊ በግል ካሰብንበት ለመድረስ የምንችለው በጋራ የምንኖርባትን ሀገር በነፃነት መገንባት ስንችል ብቻ ነው። እፍኝ የማይሞሉ ወሮበሎች ታላቋን ኢትዮጵያን ሲያፈርሱ ዳር ቆሞ መመልከት የትውልድ ንቅዘት ነው፣ ሀፍረት ነው፣ ሽንፈት ነው።ማንንም ከማንም የማይለይ ብሔራው ውርደታችንም ነው። የነቀዘና ውስጡ ባዶውን የቀረ የዱርዬ ስብስብ ሊገዛን አይገባም። የፈራን ፈርተን ለደነበረ በርግገን የስቃይ ቀናትን ማርዘም አይገባንም። ወያኔን ተጠግቶ የጠረቃ ሆዳም እንኳ ጊዜው ሲደርስ ያርዱታል ወይም ያዋርዱታል። የማፊያ ወግ እንደዚያ ነው። ከዚህ ስርዓት ውርደት እንጂ ክብር አይጠበቅም። እንደ ቀደሙቱ በግልም ይሁን በጋራ፣ ባደባባይም ይሁን በመንደር፤ በሀገር ውስጥም ይሁን በውጪ ብሔራዊ ውርደት በቃ! ብለን ልንነሳ ይገባል። አዎን ብሔራዊ ውርደት ይብቃን!!!

ዳኛቸው ቢያድግልኝ
[email protected]