በአዲስ አበባ የታክሲ ሾፌሮች አደሙ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ በታክሲ እጦት እየታመሰ ነው

የአዲስ አበባ ከተማ ታክሲ ሾፌሮች ባለፈዉ ሰኞ የስራ ማቆም አድማ በመጀመራቸዉ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪና በስራና በተለያዩ ምክንያቶች ከተማዋን የሚጎበኘዉ ህዝብ ከፍተኛ የመጓጓዣ ችግር እንደገጠመዉ የግንቦት ሰባት ዘጋቢ ከስፍራው ባስተላለፈልን ሪፖርት ገለጸ። እንደዘጋቢያችን አባባል የዘረኛው አገዛዝ የጸጥታ ኃይሎች የታክሲ ሾፌሮች አድማዉን አቁመዉ ስራ እንዲጀምሩ ከማስገደዳቸዉ ባሻገር አንዳንዶችን ከማሰገደድ አልፈዉ ያስሩ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ኢሳት በትናንትናው እለት ባሰራጨው ዜና “ተነስ ምን ትጠብቃለህ? ” የሚል ወረቀት ሲበተን እንደነበርና በአዲስ አበባ ከተማም ከፍተኛ ውጥረት ይታይ እንደነበር ከፍጠኛ ቁጥር ያላቸዉ የታክሲ አሽከርካሪዎች ለኢሳት ዘጋቢ መግለጻቸውን አስታዉቋል። የዘረኛው አገዛዝ ደህንነት አባላት የቆሙ ታክሲ ባለቤቶችን እየጠሩ ስራ እንዲጀምሩ ቢጠይቁም ባለንብረቶቹ እኛ የምናዉቀዉ ነገር የለም ሾፌሮችን ጠይቋቸው የሚል መልስ መስጠታቸው የታወቀ ሲሆን በዚህ የተበሳጩት የወያኔ ደህንነት አባላት አንዳንድ ሾፌሮችን መያዝና ማሰር የጀመሩ መሆናቸው ተገልጿል።

ኢሳት ከውስጥ አዋቂ ምንጮቹ ባገኘው መረጃ መሰረት እነመለስ ዜናዊ በአዲስ አበባ ያለውን የታክሲ ትራንስፖርት እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ በወያኔ የንግድ ኩባኒያዎች ለማስያዝ ባላቸው እቅድ መሠረት የስራውን አዋጭነት ለማስጠናት ከዚህ ቀደም በተለያዩ የአረብ አገሮች የታክሲ የአሰራር ስርአት እንዳጠና ለሚነገርለት አንድ ህንዳዊ ኤክስፐርት ኮንትራት ስጥተው ያስጠኑ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

የአዲስ አበባ ታክሲ ባለንብረቶችና አሽከርካሪዎች በምርጫ97 ወቅት ቅንጅት ጠርቶት የነበረውን ህዝባዊ ሰልፍ በማስተባበር፣ነጻ የታክሲ አገልግሎት በመስጠትና፣ቅንጅትን በመደገፍ ከስራቸው ጋር ጎን ለጎን ከፍተኛ ቅስቀሳ በማካሄድ ድጋፍ ይሰጡ ስለነበር ከአሁን ቦኋላ ተመሳሳይ አጋጣሚ እንዳይፈጠር ወያኔ የከተማውን የታክሲ ንግድ ለመቆጣጠር ውሳኔ እንዳደረገ ታውቆአል።

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙት የታክሲ ባለንብረቶችና አሽከርካሪዎች ከሰባ በመቶ በላይ የሚሆኑት የጉራጌና የኦሮሞ ተወላጆች በመሆናቸው ማንኛውም አይነት ተቃውሞ ከተነሳ ተቃዋሚ ድርጅቶችን ከመደገፍና በአድማ ተሳታፊ ከመሆን ወደኋላ አይሉም ብለዉ የሚያምኑት መለስ ዜናዊ፤ የአዘብ መስፍንና በረከት ስምዖን ከዚህ ስጋት ለመዳን ብቸኛዉ አማራጭ የታክሲ ንግድን ሙሉ በሙሉ እነርሱ በሚቆጣጠሩት የኢህአዴግ የንግድ ድርጅቶች ማስያዝ መሆኑን ይስማማሙበታል።

 ወያኔ ስልጣን ከተቆጣጠረበት 1983 ጀምሮ ከሱ ቁጥጥር ነጻ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲቋቋሙ እነሱን የሚመስል ተለጣፊ በማበጀት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንዳቀጨጨ ሁሉ በንግዱም ክፍለ ኢኮኖሚም የተሰማራውን ህብረተሰብ ለማዳከምና ከዉድድር ዉጭ ለማድረግ በሚያደርገዉ ጥረት እሱ እራሱ በሚቆጣጠራቸው የንግድ ድርጅቶች ስም ወይም ለሱ ታማኝ የሆኑ ተለጣፊ ባለሀብቶችን በማሰማራት የአገሪቱን ሃብት በየመስኩ እየተቆጣጠረ እንደሆነ ይታወቃል።

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የተጀመረው የታክሲዎች የሥራ ማቆም አድማ ያስደነገጠው ወያኔ ታክሲዎች በአስቸኳይ ሥራ ካልጀመሩ እርምጃ እንደሚወስድ እየዛተ እንደሚገኝ የገለጸው ዘጋቢያችን – አዲስ አበባ ውጥረት አርግዛለች መች እንደምትገለገል ግብ ለጊዜዉ ምንም የታወቀ ነገር የለም ብሏል።