አማርኛ ከሠላሳ ዓመት በኋላ
የዛሬ ሠላሳ ዓመት በ2035 ዓም በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች መካከል የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ውድድር ይደረጋል፡፡ በውድድሩም ከዚህ በታች የማቀርብላችሁ ወግ ‹እኔና ትምህርት ቤቴ› በሚል ርእስ ተወዳድሮ አንደኛ ይወጣል፡፡
ይህ ኦፖርቹኒቲ ስለ ተሰጠኝ ታንክዩ፡፡ አቦ ይመቻችሁ፡፡ ሀገራችን ኢቶጲያ ሚራክልየስ ሀገር ናት፡፡ አይ ሚን ነፍስ ነገር ናት፡፡ ይህንን ስል ግን ሙድ እንዳትይዙብኝ፡፡ እዚህ ሀገር ብዙ ነገር ነፍ ነው ማለቴ ነው፡፡ ዋተር ነፍ ነው፣ ኦፕን ኤይር ነፍ ነው፣ ሰን ሴትና ሰን ራይዝ ነፍ ነው፡፡ ማዩንቴይን ነፍ ነው፤ የሚደብረው ነገር ሮዶቹና ቪሌጆቹ ምልክት የላቸውም፡፡ ፎር ኤግዛምፕል የኛን ቤት ለሰው ስንነግር ‹ኒር እንትና ጫት ቤት› ነው የምንለው፡፡ ቢኮዝ እዚህ ሀገር ጫት ቤት ነፍ ነዋ፡፡ አት ዚስ ፖይንት ኤክስፕሌይን ማድረግ አለብኝ፡፡ የአያቴን ካፕ ቦርድ ስሾፍ አዲስ ዘመን የሚባል አንድ የድሮ ኒውስ ፔፐር አገኘሁና፡፡ ኮለመኑ ላይ ‹በምግብ ራስን መቻል› የሚል ነገር ሾፍኩ፡፡ ነገሩ ክሊር አልሆነልኝም ነበር፡፡ ዋት ኢዝ ‹ራስን መቻል›? ራስ ማለት ‹ሄድ› አይለደም እንዴ? መቻልስ ምንድን ነው? አንዱን ፍሬንዴን አስክ ሳደርገው ‹መቻል የሚባል ኦልድ ውሻ ጎረቤታችን አለ› አለኝ፡፡ ስለዚህ ራስን መቻል ሚን ‹የመቻል ራስ› ማለት ነው፡፡
ሶ፣ ዋት ኢዝ ዘሚኒንግ ኦፍ በምግብ ራስን መቻል? የመቻል ምግብ ማለት ነው? ማዘርን ስነግራት ለፒፕሉ ሁሉ ነፍ ምግብ ማቅረብ ነው አለችኝ፡፡ ዛት ኢዝ ጉድ፡፡ እዚህ ግን ጫት ሾፕ ብቻ ነው ነፍ ያለው፡፡ ግራንድ ማዘሬ ወደ ሰኩል ስትወስደኝ ‹እዚህ አፈር ፈጭተን አደግን› ትላለች፡፡ አም ሰርፕራይዝድ፤ ለምን አፈር ይፈጫሉ፡፡ ወይኔ ወፍጮ የለም እንዴ በእነርሱ ጊዜ? ደግሞስ አፈር ከየት አገኙ? አይ ወንደር፡፡ ግራንድ ማዘሬ ግን ይኼ አሁን ፎቅ ቢዩልት የተደረገበት ፕሌስ ሁሉ ሜዳ ነበር አለች፡፡ እኔ ግን በቴሌቭዥን ከማየው የስታዲዮም ሜዳ በቀር ሌላ ሜዳ አላውቅምና አይ ዶንት ቢሊቭ ኸር፡፡ እርሷ ግን ‹አሁን እናንተ በተገዛ አሸዋ የምትጫወቱት አፈር ስለሌለ ነው› ትላለች፡፡ ዌል ዌር ኢዝ ዘአፈር? አይ አስክድ ኸር፡፡ ‹አፈሩን ሁለት ነገር ሸፈነው፤ ሕንጻና ኮብል ስቶን› አለችኝ፡፡ ኢት ኢዝ አሜይዚንግ፡፡ ኦልዱ ቲቸር ደግሞ ‹ፈረንጆች ተራራ ሊያዩ እዚህ ሀገር ሲመጡ፣ እኛ ሜዳ ልናይ ውጭ ሀገር እንሄዳለን› ይላሉ፡፡
የምጽፈው ኤሎት ኦፍ ነገር ነበረኝ፤ ግን ፕሮብሌሙ ያኛው የአምሐሪክ ቲቸር ይቆጣሉ፡፡ ለምን ግን ይቆጣሉ፡፡ ቲቸርየን ጠይቀነው ነበር፡፡ ‹የአማርኛን ትምህርት በኮሌጅ የተማሩ የመጨረሻው ሰው ናቸው፤ ከእርሳቸው በኋላ ቆመ፡፡ እኛ በትርፍ ጊዜያችን ነው የተማርነው›› አለን፡፡ ለካስ ኦልድ ሆነው ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሐግ ልንሰጣቸው ሄደን ‹ቲቸርየ ፒስ ነዎት› ስንላቸው ‹ፕስ ለድመት ነው›፣ የሚሉን ለካስ ኦልድነት ይዟቸው ነው፡፡ወይኔ ሲያሳዝኑ፡፡ የኛ አምሐሪክ ቲቸርማ የጨሱ ናቸውኮ፡፡ሞርኒንግ ላይ ሲገቡ ‹ጪሶቹ ፒስ ናችሁ› ይሉናል፡፡ ደግሞ ሐርድ አይበጥሱም፡፡ ሆሞርክ ብንሠራ ባንሠራ እርሳቸው ‹ቴክ ኢት ኢዚ› ነው የሚሉን፡፡ ኦል ፒፕሉ ይወዳቸዋል፡፡ የኢቫሉዌሽን ፖይንት ሲሞላ ሀንድረድ ነው የምናሽራቸው፡፡ ኦልዱ ቲቸር ግን ከዳይሬክተሩ ሃርድ ዋርኒንግ ተሰጥቷቸዋል አሉ፡፡ ‹አምሐሪክን ሲምፕሊፋይድ ማድረግ ካልቻሉ ይጫራሉ› ተብለዋል፤፤
ኦልዱ ቲቸር ስትሪክት ናቸው፡፡ ሆምወርክ ካልሰራህ ሂ ዊል ኪል ዩ፡፡ ግሥ፣ ዐረፍተ ነገር፣ መልመጃ፣ ምንባብ የሚባሉ ዎርዶች ያሉት እርሳቸው ጋ ብቻ ነው፡፡ አቤት እነዚህ ወርዶች ሲደብሩኝ፡፡ የኛ ቲቸር ግሥ ምንድን ነው? ስንለው ሳቀ፡፡ የክላሳችን ልጆች ግን በሌላ ተረጎሙት፡፡ አያቴ ስትሰማ ብልግና ነው አለችኝ፡፡ ዐረፍተ ነገር የሚለውን ግን ቲቸርየም አልገባቸውም፡፡ የድሮ ቃል ነው አሉኝ፡፡ አንድ ጂኒየስ ልጅ እንዲያውም ኦልድ ቲቸራችን ጋ ያሉት ወርዶች ሙዝየም ተሠርቶ ይቀመጡ አለ፡፡ ቢኮዝ የርሳቸውን ወርዶች ለፓረንቶቻችን ስንነግራቸው ‹ከማን ጋር ነው የዋላችሁት ዛሬ?› ብለው ሐርድ ይሰጡናል፡፡ እነርሱም አያውቋቸውም፡፡ አንዲት ቺክ እንዲያውም ‹ኦልድ ቲቸራችንን እርሳቸው የሉሲ ግራንድ ሰን ናቸው› ብላ አስቃናለች፡፡
ላስት ዊክ ፎር ኤግዛምፕል ለክላሳቸው ልጆች ‹በአዲስ አበባ በእንግሊዝኛ የማይጠሩ የት/ቤት ስሞችን አምጡ› ብለው ሆም ወርክ ሰጡ፡፡ ልጆቹ ዘይ ኦል ክራይድ፡፡ ዘይ ኩድንት ጌት ኤኒ ኔም በአማርኛ፡፡ ፊውቸር፣ ቱሞሮ፣ ፋንታሲ፣ዴንቨር፣ ካሊፎርኒያ፣ ሆላንድ፣ ኦክስፎርድ፣ ካምብሪጅ፣ ቢል ጌት፣ አንስታይን፣ ሼክስፒር ነው ኔማቸው፡፡ የአማርኛ ኔም ከየት ያምጡ፡፡ በኋላ አንዲት የስኩላችን ታይፒስት ገቨርመንት ስኩል ሂዱ አለቻቸው፡፡ ዛት ኢዝ ናይስ አይዲያ፡፡ ኦልሞስት ኦል ጎቨርመንት ስኩልስ ስማቸው አማርኛ ነው፡፡ ሶ ዊ ካን ዲቫይድ ዘ ስኩልስ ኢን ቱ ቱ ፡፡ በአማርኛና በእንግሊዝኛ የሚጠሩ፡፡
ኖት ኦንሊ ዚስ፣ ኦልዱ ቲቸር ብዙ የማያርፉባቸው ነገሮች አሉ፡፡ ክላሱን ለሁለት ዲቫይድ አድርገው ሃፎቹ አምስት የኢትዮጵያ ሊደሮች ስም፣ ሃፎቹ ደግሞ አምስት የአሜሪካ ሊደሮች ስም ጻፉ አሉ፡፡ የአሜሪካ ሊደርስ የተሰጣቸው ዘይ አር ቬሪ ግላድ፡፡ የኢትዮጵያ የተሰጣቸው ግን ዘይ አር ቢካም ክሬዚ፡፡ ‹ፕሊስ ቲቸርዬ ወደ አናዘር ግሩፕ ቀይሩን› እያሉ አለቀሱ፡፡ ፎር ዮር ሰርፕራይዝ ሁለቱ ፋዘራቸውን አመጡ፡፡ የአንዷ ፋዘርማ ለቲቸር ሐርድ ነው የሰጧቸው፡፡ ‹ልጆቹ ኢትዮጵያን ሂስትሪ ሳይማሩ እንዴት የኢትዮጵያን ሊደር ትጠይቋቸዋላችሁ› ብለው ነቀሉ፡፡ ኦልድ ቲቸር ደግሞ አስገቡላቸው ‹ልጆች ታሪካቸውንና ማንነታቸውን እንዲያውቁ ማድረግ የወላጆችም ግዴታ ነው› አሉ፡፡
መፋጠጡ የመጣው አት ላስት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሊደር የተሰጣቸው ልጆች ‹እኛ የኢትዮጵያ ሊደር ሊሞላልን ስላልቻለ በእንግሊዝ አሟልተነዋል› ብለው ሁለት የኢትዮጵያ ሦስት የእንግሊዝ ሊደርስ አመጡ፡፡ ኦልዱን ቲቸር ማድሊ ያሳቃቸው ግን የኢትዮጵያ ሊደር ብለው ያመጡት የሁለት የፊልም አክተሮችና የአንድ ቤስት ሲንገር ስም መሆኑ ነው፡፡ ኦልዱ ቲቸር ከኛ ቲቸሮች ጋር አይስማሙም፡፡ እርሳቸው ያከራሉ፡፡ የኛ ቲቸር ግን ‹ሲከርር ይበጠሳል› ይላሉ፡፡ ላስት ሳተርደይ በአምስቱ ክላሶች መካከል ሰልፍ ላይ የአማርኛ ኮምፒቲሽን ይደረግ ብለው ፐርፎርም አድርገን ነበር፡፡ ኳስሽኑን ያወጡት የኛ ቲቸር ናቸው፡፡
‹ያለው› በሚለው ዐርፍተ ነገር ሥራ? ይላል የፈርስቱ ኳሽን፡፡ ልጁ ይብራራልኝ አለ፡፡ ማለቴ ኤክስፕሌይን ይደረግልኝ፡፡ ‹ያለው በሚለው ቃል ሴንቴንስ ሥራ› አሉት ቲቸራችን፡፡ ገባው፡፡
‹ሁኔታ ነው ያለው› የሚል ነገር ሲናገር ተጨበጨበለት፡፡ ኦልዱ ቲቸር ግን አዘኑ፡፡ ‹ይህ ብክነት ነው፡፡ እንዲህ ሆኗል፣ ተደርጓል ብሎ ማጠቃለል ሲቻል፡፡ የተደረገበት ሁኔታ ነው ያለው እያሉ ሦስት ግሥና አንድ ገለጫ ማባከን ምንድን ነው? ብለው ተቆጡ፤ ግን አሞንግ አስ ግስና ገላጭ የገባው አልነበረም፡፡ አንት የኛ ክላስ ልጅ ግን ግሥና ገላጭ ‹የድሮ ቲቸሮች ኔሞች ናቸው› አለችን፡፡
አንዱ ደግሞ ‹ትናንት› በሚለው ዐረፍተ ነገር ሥራ ሲባል፡፡ በስንት ኤክስፕላኔሽን ‹የፋዘሬ ፋዘር ትናንት ደየመ› ብሎ ሴንቴንስ ሠራ፡፡ የኛ ቲቸር ሲያጨበጭቡ ኦልዱ ግን ነኩት፡፡ እንዲያውም ሊበጭጩ ነበር፡፡ ነቅለው ተነሡና ‹ደየመ ምንድን ነው?› አሉና አፋጠጡት፡፡ ልጁም ‹ጫረ ነዋ› አላቸው፡፡ እንደገና ጨሱ፤ ‹ጫረስ ምንድን ነው?› አሉት ‹ተነጠፈ ነዋ› ልጁ ሳቀ፡፡ ወላጆቹ ግን ‹ሀግ› ሰጡት፡፡
የአማርኛ ቲቸር ቀጠሉ፡፡ አንድ የአምሐሪክ ዲክሽነሪ አወጡና ‹ለሚከተሉት ወርዶች ሚኒንጋቸውን ተናገር› አሉ፡፡ ኦልዱ ቲቸር ሲቲ ስካን አደረጓቸው፡፡
መስጠት፡- መንፋት ነዋ፤ አለ ልጁ ‹ራይት› አሉት መምሩ፡፡
መፈንከት፡- ብር መዘርዘር
ምስኪን፡- ነፍስዋ ጀለስ
ቡርቴ፡- ቀሽት
ፍሬው ኃይሉ፡- ባለ ተሳቢው አውቶቡስ
አልመጣም ቀረሁኝ፡- የቧንቧ ውኃ
አየሁሽ፡- መብራት ኃይል
በልጆቹ ጂኒየስነት ተጨበጨበ፡፡
‹የመጨረሻው ኮምፕቲሽን ዕንቆቅልሽ ነው› ሁሉም ኮምፕልኬትድ ሆነበት፡፡ የአንዱ ልጅ እናት ‹የምን ቋንቋ ነው ይኼ› ብላ አስክ አደረገች፡፡ ኦልዱ ቲቸር ‹አማርኛ ነዋ› አሏት፡፡ ‹ኦልድ አምሐሪክ መሆን አለበት፤ እናንተ እንደ ዋልያ ኢንደሚክ የሆኑትን ዎርዶች ብቻ ነው እንዴ የምታመጡት፤ ኢዝ ኖት ፌይር ›› አት ላስት ኢንግሊሽ ቲቸር ኢክስፕሌይን አደረጉልን፡፡ ለካስ ኢት ሚንስ ‹ ሪድል›
‹ስሄድ አገኘኋት ስመለስ አጣኋት›
‹የኛ መንደር› አለች አንዲት ጂነስ፤ እንደ ጉድ ተሳቀ፤ እንደ ጉድ፡፡
‹ቤቷን ዘግታ የምትዘፍን›
ናይት ክለብ
‹ዓባይ ማደርያ የለው ግንድ ይዞ ይዞራል›
ቤት የሌለው ባለ መኪና
እኔ በኮምፕትሽኑ አንደኛ ስለወጣሁ አንድ ሚሊዮን ብር ተሸለምኩ፡፡ የተሰበረውን የሩሜን በር አሠራበታለሁ፡፡ ካርፔንተሩ በናይን ሀንድረድ ታውዘንድ እሠራልሻለሁ ብሎኛል፡፡ ግራንድ ማዘሬ ሰርቲ ይርስ ኤጎ ቤቷን በአንድ ሚሊዮን ብር መግዛቷን ነግራኛለች፡፡ ናው ኢት ኢዝ ዘ ፕራይስ ኦፍ ኤ ዶር፡፡
በዚህኛው የአምሐሪክ ኮምፒቲሽን ኮምፒት ያደረግኩትም ለዊንዶው የሚሆን ነገር ዊን ባደርግ ብዬ ነው፡፡
(ሁሉም ቆሞ በተማሪዋ የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ችሎታ አጨበጨበ፡፡ ዳይሬክተሩም የልጂቱ ሥነ ጽሑፍ አማርኛ ባለፉት ሠላሳ ዓመታት ያስመዘገበውን ፈጣን ዕድገት ያሳያል ሲሉ ደሰኮሩ፡፡)
© ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ነው፤ በሌላ ሚዲያ ማውጣት ክልክል ነው