የኢሳት 3ኛ አመት ክብረ-በዓል የሙስሊሞች ብቻ ነው እንዴ? ልጅ ተክሌ
1-ጽሁፍ ካላበሳጨ ወይ ካላስጨበጨበ አይመቸኝም። ላለፉት ጥቂት ሳምንታት የሚያበሳጭ ወይ የሚያስጨፍር ርእስ ስጠብቅ ሳልጽፍ ቆየሁ። የኢትዮጵያውያን፤ በተለይም የአማርኛ ተናጋሪዎች ከቤንሻንጉል መባረር በራሱ በቂ አናዳጅና አሳዛኝ ክስተት በመሆኑ፤ እንዲሁም ሌሎች ስለጻፉበት እሱ ላይ ብዙ አልደክምም። ስለዚህ ሌላ አናዳጅ ርእስ ናፈቅኩ። ባለፈው ሰኞ፤ ከአድካሚው ውሎዬ እረፍት ለመውሰድ ወደኢሳት ድረ-ገጽ አመራሁ። የደንቡን አድርሼ ከኢሳት ድረገጽ ወጥቼ ለመሄድ ጣቴን ጠቅ ለማድረቅ ስንቀለቀል፤ በአይኔ የቀኝ ጠርዝ፤ በኢሳት ድረገጽ የግራ ማእዘን ላይ፤ ስድስት ሰባት ወንዶች የተደረዱበት ምስል አየሁና ተመለስኩኝ። አንዳንዶቹ የተለመዱ ፊቶች ናቸው። “ሲሳይ አጌና፤ ታማኝ በየነ፤ ሻምበል በላይነህ፤ ሄኖክ የሺጥላ …” ከኢሳት ጋር በተያያዘ አንዳንዶቹ አዳዲስ ናቸው። የኢሳት ሶስተኛ አመት ዝግጅትን ለማድመቅ የተመረጡ እንግዶች ናቸው። የሚያበሳጭም ባይሆን፤ እነሆ የሚያወያይ ርእስ ተደግሶልኝ አየሁ።
2-ከኤፕሪል 13 እስከ ሜይ 26 የኢሳት 3ኛ አመት ክብረበዓል ይካሄዳል። ነጂብ ሞሀመድ፤ ከታማኝ በየነና ሄኖክ የሺጥላ ጋር ቅዳሜ ሎስ አንጀለስ ይገኛል። እሁድ እዚያው ሳንዲየጎ ይጓዛሉ። እነዚሁ ሰዎች።ታማኝ በየነና ሻምበል በላይነህ ካሊድ ኦማርን ይዘው እሁድ ዜፕሪል 20 ሳን ሆዜ ይገኛሉ። ታማኝ በበነጋው እሁድ ኤፕሪል 21 መንሱር ኑርን ይዞ ሲያትል ይታያል። ነጂብና ታማኝ እንደገና እሁድ ኤፕሪል 28 ናሽቪል ይገኛሉ። ጃክሰንቪል ፍሎሪዳ ታማኝና ሻምበል ሜይ 18 ይገኛሉ። በስድስት ከተሞች በሚካሄዱ የኢሳት ዝግጅቶች ላይ አምስት የሙስሊም የሀይማኖት መሪዎች የመጋበዙ አንክዮ ትንሽ ግራ ያጋባል? በኔ አስተያየት፤ ኢሳት የሁሉም ኢትዮጵያውያን ከሆነ፤ ነውም፤ በኢሳት ሶስተኛ አመት ዝግጅቶች ላይ ከስድስቱ ከተሞች ውስጥ በአምስቱ የሙስሊም ሀይማኖት መሪዎች ዋንኛ ተጋባዥ እንግዶች መሆናቸው ብልሀት ያነሰውና ያልተጠና ውሳኔ ነው። ይሄ አካሄድ ያለውን ፖለቲካዊ አንድምታ የኢሳት አስተዳደር የተረዳው አልመሰለኝም።
3-ሙስሊም ኢትዮጵያዊያን፤ በተለይም በአገር ቤት ያሉቱ የሚያደርጉትን ሰላማዊና በሳል ትግል ብደግፍም፤ የኢሳት ዝግጅት አሰላለፍ ሀይማኖትን መሰረት ያደረገና ሀይማኖታዊ አንድምታ በሚኖረው መልኩ ይሁን የሚል እምነት የለኝም። ባንድ በኩል ሙስሊሞች ለመብታቸው መታገላቸው የሚደገፍ፤ የሚያስቀና፤ የሚኮረጅ ቢሆንም፤ ሙስሊሞች ግን በኢትዮጵያ ውስጥ እንደአንድ ፖለቲካዊ ጎራ ወይም ቡድን ይታዩ ወይንም እንደ አንድ ፖለቲካዊ ቡድን ሆነው እንዲወጡ እናበረታታቸው ወይንም እውቅና እንስጣቸው የሚለውን ሀሳብ አልደግፈውም። እንደዚያ ብለው የሚያስቡ ሙስሊሞችም ሌሎች ኢትዮጵያዊያንም ሊኖሩ ይችላሉ። እኔ ግን ሙስሊሞችንም ይሁን ማናቸውንም የሀይማኖት ድርጅት ፖለቲካዊ ሀይል አድርጎ በሚያወጣ ጉዞ ውስጥ አባል አልሆንም።
4-ዜግነትን መሰረት አድርጎ የሚንቀሳቀስ እንደኢሳት ያለና ብዙዎቻችን በሀይማኖታችን ሳይሆን በዜግነታችን የተከተልነው ተቋም አንዱ ላይ አይደለም፤ ሁለቱም ላይ አይደለም፤ አምስት ዝግጅቶች ላይ የሙስሊም ሀይማኖት መሪዎችን ነጥሎ መጋበዙ ምን ማለት እንደሆነ አልገባኝም።ብዙዎቻችን በኢሳትም በኩል ይሁን በሌላ መስመር የሙስሊሞቹን ትግል ብንደግፈም፤ ድጋፋችን የሚቀጥለው ግን የኛን የጋራ ትግል እስካገዘና፤ በመጨረሻ እንደ ሀይማኖት ቡድን የሚያደርጉት ትግላቸው በኛ የጋራ ጥቅም ላይ ችግር እስካልጋረጠ ድረስ ነው። የሙስሊሙ አንድ ወጥ ፖለቲካዊ ሀይል ሆኖ መውጣት፤ ሀይማኖታችንን ሳይሆን ዜግነትን ብቻ መሰረት አድርገን ለምንንቀሳቀስ ሀይሎች ጠንቅ ነው።
5-የሙስሊሞቹን ትግል ስንደግፍና ከሙስሊሞቹ ጎን ስንቆም፤ ሀይማኖትና መንግስት የተለያዩ ናቸው፤ መንግስት ሴኪውለር ይሁን፤ የሚለውን መሰረታዊ የመንግስት መርህ አምነንበት፤ የመንግስትን ጣልቃገብነት በኦርቶዶክሱም ሆነ በእስልምናው ሀይማኖት ስለቀመስነው ነው እንጂ፤ የሙስሊሞች አንድ ፖለቲካዊ ሀይል ሆኖ መውጣት ጉዳያችን ሆኖ አይመስለኝም። መንግስት በማናቸውም ሀይማኖቶች ጉዳይ ገብቶ መፈትፈት የለበትም ከሚለው መሰረታዊ ሁላችንንም ከሚያስማማ የሰለጠነ ሀሳብ በመነሳት ነው። እንጂ ሙስሊሞች ተደራጅተው፤ አንድ የፖለቲካ ሀይል እንዲሆኑ የማድረግ ፖለቲካዊና አገራዊ ግዴታ አለብን ከሚል የሀላፊነት ስሜት በመነሳት አይደለም የሙስሊሙን ትግል የምንደግፈው።
6-የኢትዮጵያ ልሂቃን መንግስትና ሀይማኖት ይለያዩ ሲሉ ትግል የጀመሩት ከ50 አመት በፊት ነው። አሁንም መንግስት በሙስሊሞች ጉዳይ ጣልቃ አይግባ ስንል ያንን ማለታችን ነው። ያ ብዙ ወጣት ኢትዮጵያውያን የሞቱለት መርህ ይከበር ማለታችን ነው። መንግስት በኦርቶዶክሱም ይሁን፤ በመጅሊስም ይሁን በሲኖዶስ፤ ጣልቃ አይግባ ማለታችን ነው። በሙስሊሙም አይግባ ስንል፤ መንግስትና ሀይማኖት አይለያዩ ማለታችን ነው እንጂ ሙስሊሞች ፖለቲካዊ ሀይል ሁነው ይውጡ ማለታችን አይደለም። አሁን ኢሳት የያዘው አካሄድ ግን፤ በሙስሊሞች ላይ የሚደርሰውን በደልና ግፍ ከመዘገብና ከማጋለጥ አልፎ፤ ሙስሊሞች ተጽአኖ መፍጥር የሚችሉ አንድ ትልቅ የፖለቲካ ቡድኖች አድርጎ የመፍጠር አዝማሚያ የያዘ ነው። ያ አንደኛ መንግስትና ሀይማኖት ይለያዩ የሚለውን መርህ ይሽራል፤ ምክንያቱም ሀይማኖት በመንግስት ጣልቃ እንዲገባ ሊያደርግ ይችላልና። ሁለተኛ፤ ያንን ሚዛናዊ የሚያደርግ ወይም የሚፎካከር ጠንካራ የኦርቶዶክስም ይሁን የፕሮቴስታንት ድርጅት በሌለበት ሁኔታ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የሙስሊሞች ብቻ ጠናካራ የፖለቲካ ጎራ ሆኖ መውጣት ለኢትዮጵያ አደጋ ይጋብዛል።
7-መንገስት ሴኩላር ይሁን ስንል፤ ይሄንን መንግስት ለመጣል የምፈልግ ሀይሎችም ሴኪውላር መሆን አለብን። እንጂ፤ የምንሰራው ስራ በሀይማኖታዊ አንድምታ እንዲተረጎም አድርገን መሆን የለበትም። የኢሳት ሶስተኛ አመት ክብረበኣል ስግጅቶች ላይ ከስድስቱ ከተሞች በአምስቱ የተጋበዙት፤ ከታወቁቱ መደበኛ እንግዶች በስተቀር፤ በአትሌትነት፤ በሯጭነት፤ በሙዚቀኛነት፤ በደራሲነት፤ የማንንም ሀይማኖት በማይወክል በፖለቲካ መሪነት አይደለም የተጋበዙት። በጎበዝ የሀይማኖት መሪነታቸው የምናውቃቸው ሙስሊሞች ከሚኖሩበት ከተማ ውጪ በክብር እንግድነት ኢሳትን ወክለው መጋበዛቸው ብዙዎችን ግራ ሊያጋባ፤ ሊያሸሽም ይችላል። እነዚህን ሰዎች በመጋበዝ ልናመጣ ያሰብነው ትርፍ፤ በግልጽ ላንሰፍረው የማንችለው ትልቅ ኪሳራ እንደሚያመጣብን፤ አደገኛ አካሄድ እንደሆነም አላስተዋልንም የሚል ራእይ ተገልጾልኛል።
8-የሳዲቅ መጋበዝ አይከነክነኝም። በጋዜጠኝነት ኢሳትን ሲረዳ የቆየ ሰው ነውና፤ ልክ ሲሳይ በአጋጣሚ ለኢሳት የሚሰራ ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ጋዜጠኛ እንደሆነው ወይንም ታማኝ ለኢትዮጵያ የቆመ ኢሳት ውስጥ የሚሰራ ክርስቲያን እንደሆነው፤ ሳዲቅም በቅጥርም ባይሆን በፈቃደኝነት ለኢሳት የሚያገለግል ጋዜጠኛ ነው። የነጂብና የኦማር፤ እንዲሁም የመንሱር ሁኔታ ግን ግራ ገብቶኛል። በግሌ ከነጂብም ይሁን ከማናቸውም ሙስሊሞች ጋር ምንም ችግር የለብኝም። ዞሮ ዞሮ ግን ነጂብና ካሊድ የሀይማኖት መሪ ናቸው። ነጂብ የፈርስት ሂጅራ ፋውነዴሽን። ከዚህ ቀደም የሚጋበዙትም ይሁን አሁን እነሱን የሚያጅቡት የኢሳት ሰዎች ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ወክለው ነው የሚመጡት ከሚል ግምት ካልተነሳን፤ ወይንም እነታማኝና ሜይንስትሪም የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ኦርቶዶክሱን ይወክላሉ የሚል ያልተጻፈ ግምት ከሌለ በስተቀር፤ ታማኝም ይሁን ሻምበል አበበ ገላውም ይሁኑ አበበ በለው ለኢሳት ዝግጅቶች የሚገኙት በዜግነት እንጂ በሀይማኖት አይደለም። ኦርቶዶክስን ወክለው አይደለም።
9-ወዳጄ ታማኝ፤ ከዚህ ቀደም በስህተት ሙስሊሞቹን የካሰ መስሎት የኛ በኣል ሲከበር ስለሙስሊሞች በአል አለመከበር የተናገረው ንግግር በየዋህነት ቢታለፍለትም፤ በምንም መልኩ ግን የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮችን ወክሎ የሰነዘረው የይቅርታ ንግግር አይመስለኝም። እኔና ታማኝ ኦርቶዶክሶች ብንሆንም ኦርቶዶክሶችን አንወክልም። እኔ እስከማውቀው ድረስ፤ እነ ነጂብ ትናንትም ዛሬም የሀይማኖት መሪዎች ናቸው። የሀይማኖት መሪዎች ከጋበዝን ደግሞ ቢመጡም ባይመጡም የኦርቲኦዶክሱንም የፕሮቴስታንቱንም፤ የይሁዲውንም፤ የካቶሊኩንም ነው እንጂ፤ በምን መስፈርት ነው የሙስሊሞቹን ብቻ የምንጋብዘው? ይሄ አደገኛ አካሄድ ነው።
10-ብዙዎች የነቁም ያልነቁም የሙስሊሙን እንቅቃሴና አካሄድ በጥርጣሬ የሚመለከቱ ስጋት የገባቸው ኢትዮጵያዊያን አሉ። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንደ ኢሳት ያለ ለሁሉም ኢትጵያዊያን በእኩልነትና ፍትሀዊነት ላገለግል ቆሜያለሁ የሚል ተቋም፤ ዝግጅቶችን ሲያዘጋጅ በክብር እንግድነት ስለሚጋብዛቸው ሰዎች ማንነት ጥንቃቄ ማድረግ አለበት። ከስድስት ዝግጅቶች በአምስቱ ላይ እነ ነጂብን ሲጋብዝ ሊፈጥር የሚችለውን አንድምታ፤ ሊያሸሽ የሚችለውን ህዝብ ማሰብ አለበት። ኢሳት ደግሞ የሙስሊሞችና የኦርቶዶክሰቶች ብቻ ሳይሆን፤ ስለአገር ያላቸው ተቆርቋሪነት ጎዶሎ ቢሆንም እንኳን፤ የጴንጤዎችም ጭምር ነው። ወይም ነው ብለን ነው ማሰብ ያለብን። ዝግቶቹ በተለያየ አጋጣሚ የተዘጋጁ ቢሆኑ አይገርምም። ነገር ግን ሆን ተብሎ ባንድ ላይ ታስቦበት ይሄንን ቅርጽና አንድምታ እንዲይዝ የተዘጋጀ ይመስላል።
11-በመሰረቱ የሀይማኖት ስራ በሰውና በእግዚአብሄር መካከል ያለውን ግንኙነት የሚመለከት ነው፤ የፖለቲካ ዓላማ ደግሞ በሰውና በሰው መካከል ያለውን ግንኙነት የሚመለከት ነው። ሀይማኖት በሰውና በሰው መካከል ያለውን ግንኙነት የሚዳኘው ፖለቲካ ላይ ተጽእኖ ማሰደር ሲጀምር ነው። ተጽእኖ አሳዳሪውን ሀይማኖት (እስልምናን ሊሆን ይችላል) የሚገዳደር ወይም የሚያርቅ በሌላ ሀይማኖት ዙሪያ የተደራጀ ሀይል (ምሳሌ ኦርቶዶክስ ወይንም ፕሮቴስታንት) ከሌለ፤ የዚያ ተጽእኖ ፈጣሪ ሀይማኖት (እስልምና) አንድ ወጥ በሀይማኖት ዙሪያ የተሰባሰበ ሀይል ወይም ቡድን ሆኖ መውጣት ለሁላቸንም አደጋ ነው። ኢሳት ያንን አደጋ መከላከል እንጂ ማበረታተት የለበትም።
12-መቼም የሆነ ሆኗልና፤ የተጋበዙት ሰዎች ይሰረዙ ብለን አንጣራም። ይሁን እንጂ፤ ለወደፊቱ ይሄ እንዳይደገም ጥንቃቄ ያስፈልጋል። ያለበለዚያ የምንቆጣም እንኖራለን። ለነገሩ፤ እሁን እነ ሌንጮ ይሄን የመሰለ ፖለቲካዊ ጮማ አዋጅ ይዘው አንድነታችን ደጅ ላይ ቆመው፤ እጣ ፈንታችን የሚወሰነው ከኢትዮጵያዊነት ታዛ ስር ነው ሲሉ፤ ሲሆን ሲሆን ለቀጣዮቹ ወራት እነሱን ብቻ፤ ካለበለዚያም ከሌሎች ጋር እየቀየጥን የአገራችንን ነገር መምከር ነበር እንጂ፤ ሀይማኖታዊ መሪዎች ላይ ማተኮር አልነበረብንም። ለወደፊቱ ጥንቃቄ ይደረግ። የኢሳት አስተዳደርን ለዛሬ ምረነዋል።
ልጅ ተክሌ ነን። ቶሮንቶ፤ ሚያዚያ፤ 2005/2013