በውጪ ሃገር የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በቶሮንቶ የተሳካ ስብሰባ አካሄዱ

ባለፈዉ ቅዳሜ ሚያዚያ 29 ቀን 2003 ዓም ካናዳ ቶሮንቶ ዉስጥ ከተለያዩ ማህበረሰብ የተወጣጡ ኢትዮጵያዊያን አወያዮችና ተሳታፊዎች የተገኙበትበት የተሳካ የ“በቃ” ንቅናቄ ስብሰባ መካሄዱንና የስብሰባዉ ተሳታፊዎችና እንግዶቹ አብሮ መስራትንና ለአንድ ዓለማ በጋራ መታገልን የሚያሳይ የአቋም መግለጫ ማውጣታቸውን ቶሮንቶ ዉስጥ የሚገኘዉ የግንቦት 7 ዘጋቢ ከስፍራው ባስተላለፈልን ሪፖርት ገልጿል።

 በእለቱ ስብሰባ በመቶዎች የሚቆጠሩ የኦጋዴን፤ የአፋርና የኦሮሞ ብሄረሰብ አባላት እንዲሁም ሌሎች ኢትዮጵያዊያን የተገኙ ሲሆን፡ በጋራ ያወጡትም መግለጫ “ኢትዮጵያ አንድ ናት”፡ “አንድነታችን በተለያዩ ማህበረሰቦች የተገነባ አንድነት ነው፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሁሉም ነገር በፊት የሰውነትና የተፈጥሮ ነጻነታችንና መብታችን መከበር ከምንም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር ነው” የሚል እንደነበረ የግንቦት ሰባት ዘጋቢ ካስተላለፈልን ሪፖርት ለማወቅ ተችሏል።

በእለቱ ስብሰባ በመጀመሪያ የተናገሩት፡ ከአፋር ብሄረሰብ የተወከሉት አቶ አሎ አይደሂስ ሲሆኑ እሳቸዉም- “ሕወሀት/ኢህአዴግ በማሳ ውስጥ እንደበቀለና፡ እህል እንደሚያቀጭጭ አላስፈላጊ ዛፍ ከመሰሉት በኋላ፤ አንድ ላይ አይቀመጡም፡ አይወያዩም፡ ብለዉ ለያይተዉ የሚያዩን ተቃዋሚዎች ዛሬ መሰባሰባችን እጅግ አስደንግጧቸዋል ካሉ በኋላ ይህ የህብረትና የአንድነት መንፈስ ወደፊትም መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል። በመጨረሻም ይህ ዛፍ መርዘኛ ስለሆነና እህሎቹን ስላቀጨጫቸው ከስሩ ለመንቀልና በአገራችን ፍትህና ርትእ ለማስፈን አብረን መስራት ይኖርብናል በማለት ማሳሰባቸውን ተገልጿል።

ሁለተኛዉ ተናጋሪ የኦጋዴን ማህበረሰብ ተወካይ የሆኑት አቶ መሀመድ ሀሰን ደግሞ፡ “እድሜ ልካችንን በማይረቡ ነገሮች እየተጨቃጨቅን ከመኖርና፡ በቋንቋና በሀይማኖት ዙሪያ ተሰባስበን ከምንለያይ የአላማና የትግል አንድነት ፈጥረን፡ አገራችንን እያጠፋ ያለውን ስርአት ማስወገድ አለብን ማለታቸውን ዘጋቢያችን አያይዞ ገልጿል። አቶ መሃመድ በመቀጠልም ሕወሀት/ኢህአዴግ ላለፉት አመታት በተለይም በኦጋዴን አካባቢ ከፍተኛ የሆነ እልቂት ሲፈጽም ገና ለገና ተገንጣይ ቡድኖች ናቸው ብሎ በማሰብና በመፍራት፡ በውጭ የምንገኝ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ በኦጋዴን የተፈጸመውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ተቃውመን በአንድነት አለመውጣታችን እጅግ እንደጎዳን ገልጸዋለ፡ አሁንም ወያኔ ለምእራባዊያን የሚሸጠውን የፈጠራ ፖለቲካ ተባብረን ካልደመሰስነው በስተቀር፡ እርስ በርሳችን ስንባላ ያቺ የምንወዳት አገር ልትጠፋ እንደምንችል አሳስበው የጋራ ዓላማ ይዘን ልንቀሳቀስ ይገባል ሲሉ ጥሪ ማቅረባቸዉን ዘጋቢያችን ገልጿል።

ሶስተኛ ተናጋሪ የሆኑት አቶ አበበ በለውም፡ አሁን የስራ ጊዜ ነው፡ ጠላቶቻችን እያንዳንዱን ሰዓት ለአፈናም ይሁን ለዝርፊያ በስራ ነዉ የሚያሳልፉት፡ እኛ ግን እስካሁን ወሬ ከማዉራት ፈቀቅ እንዳላልን ገልጸው፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የአንዱ ብሄር ችግር የዚያ ብሄር ብቻ ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያዊ ችግር ስለሆነ ችግራችንን ለማስወገድ ተባብረን መስራት እንዳለብን አሳስበዋል። አራተኛው ተናጋሪ ነበሩት ወጣት ጃዋር መሐመድ ደግሞ በበኩላቸዉ ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲን ለማስፈንና፡ የመፈረካከስ አደጋን ለማቆም ህዝቡና ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ማድረግ ስለሚገባቸው ነገሮች በዝርዝር መናገሩን የግንቦት 7 ዘጋቢ አክሎ ገልጿል። ወጣት ጃዋር፡ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ህዝቡን ቀድመው በመሄድ የማስተባበር ስራ መስራት እንዳለባቸዉ ካሳሰበ በኋላ የፖለቲካ ድርጅቶች ደጋፊ እናጣለን በሚል ፍራቻ ብቻ ተፈራርተውና ተራርቀው ከሚኖሩ ፡ ተጠጋግተዉ በመተማመንና በመተባበር በመስራት፡ የአንድነትና የነጻነት አራማጆችን፡ ወደመሀል አምጥተዉ አብሮ የመሄድ ባህል ማዳበር እንደሚገባቸዉ በጥብቅ አሳስቧል።

 በመጨረሻም አቶ ኦባንግ ሜቶ ከራሱ ልምድና ከአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር ሰፊ ማብራሪያ አሰምቶ፡ ሁላችንም ነጻ ካልወጣን አንዳችንም ነጻ እንደማንወጣና፡ ከብሄር ግኑኝነት በፊት ሰብዓዊነት መቅደም እንዳለበት አሳስቦ የአብሮ መስራትን አስፈላጊነት አበክሮ ከገለጸ በኋላ ጠላታችን ይሄ ብሄር ወይንም ያኛው ብሄር ሳይሆን፡ የመለስ ዜናዊ ስርአት እንደሆነ ገልጾ፡ ይህንን ስርአት ለመጣል በጋራ እንድንታገል አደራ ማለቱን ዘጋቢያችን ጠቅሷል።

“አንድነት ሀይል ነው” በሚል መፈክር የተጀመረው የእለቱ ስብሰባ፡ አምስቱም ተናጋሪዎች በጋራ ባወጡት “አንድነት ሀይል ነው” እንዲሁም መለያየት በቃ በሚል መግለጫ መጠናቀቁ ታውቋል።