የደረጃ ዕድገት

የዚህ መ/ቤት ሠራተኞች ዘንድሮስ አምርረዋል፡፡ ባለ ስንት አሐዝ እንደፈለጉ አይታወቅም እንጂ ዕድገት ዕድገት ይላሉ፡፡ ‹ላለፉት ጥቂት ዓመታት የደረጃ ዕድገት አላገኘንምና እንደገና ሊታይልን ይገባል› እያሉ አንዴ በስብሰባ አንዴ በደብዳቤ ይጯጯሃሉ፡፡ ለነገሩ ባለቤት ካልጮኸ ጎረቤት አይረዳም የሚለውን የሚያውቁ አዲስ ሠራተኞች ናቸው አሉ ጉዳዩን የሚገፋፉት፡፡ አንዳንዶች ነባር ሠራተኞች ግን ‹ነባይነ ነባይን ከመ ዘኢነባይነ ኮነ- ጩኸን ጩኸን እንዳልጮህን ሆንን› የሚለውን በመተረክ ነው ያለፈ ልምዳቸውን የሚያካፍሉት፡፡
ኃላፊዎቹ ደግሞ ጥያቄው በተደራጀ መልኩ እንዲቀርብ ነው ያሳሰቡት፡፡ በአነስተኛም ይደራጁ በከፍተኛ የቢሮው ሠራተኞች ግን አንዳች አደረጃጀት ይዘው ጥያቄዎችቸውን ቢያቀርቡ የተሻለ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ ‹አንድነት ኃይል ነው› የሚለው መፈክር ከሠርቶ አደር ጋዜጣ መቆም በኋላ በብዛት ባይታይም የአደረጃጀቶች የውስጥ ፋይል ውስጥ ግን ሊኖር እንደሚችል አንዳንድ አስተያየት ሰጭዎች ገልጠዋል፡፡ 

ሠራተኞችም ‹ምክር ሠናዪት ለእለ ዘይገብራ – ምክር ለሚፈጽማት መልካም ናት› የሚለውን አስታውሰው ተደራጁና የደረጃ ዕድገት ጥያቄያቸውን እነሆ አቀረቡ፡፡ ባቀረቡበት ቀን በተደረገው ስብሰባም ተደራጅተው መብት መጠየቅ መብታቸው መሆኑን፣ ይህንን አሁን ለደረጃ ዕድገት ጥያቄ የሰበሰቡትን የተደራጀ ኃይል ወደ ሌሎች የልማት ተግባራትም በማዞር የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንዳለባቸው፡፡ ይህ አሁን የቀሰሙት ተሞክሮም ተጠናክሮ እንዲቀጥል፡፡ ለዚህም እያንዳንዱ ሠራተኛ እንዲረባረብ ከኃላፊው ማሳሰቢያ ተሰጠ፡፡ በርግጥ አንዳንድ ሸርዳጅ የመሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች መደራጀት፣ መረባረብ፣ ኃይል፣ ተሞክሮ፣ ፈጣን፣ ቀጣይነት፣ የሚሉት ቃላት በዚህ አዳራሽ ውስጥ ከመብዛታቸው የተነሣ ግድግዳው ሲፈረፈርም እነርሱ ናቸው አሉ የሚወድቁት፡፡
‹የዛሬው ስብሰባ የተዘጋጀው› አሉ የመሥሪያ ቤቱ ኃላፊ ‹ባለፈው ለጠየቃችሁት የደረጃ ዕድገት ጥያቄ በጥናት የተደገፈ በቂ ምላሽ ለመስጠት ነው፡፡ ሁሉም ነገር ጥናት ይጠይቃል፡፡እንዲሁ በግብታዊነት የሚደረግ ነገር የለም፡፡ ረጋ ብሎ፣ ጊዜ ወስዶ፣ ተቀምጦ፣ ተሰብስቦ፣ ከሌሎች ተሞክሮ ቀስሞ፣ ነው፡፡ በዚህ መሠረት መ/ቤቱ ኮሚቴ አቋቁሟል፡፡ አሁን የኮሚቴው ሪፖርት ይቀርባል› አሉና ለኮሚቴው ሊቀ መንበር መድረኩን ሰጡት፡፡
‹ይህ ኮሚቴ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የሠራተኛውን ጥያቄ ዲሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊና ሕጋዊ በሆነ መንገድ ለመመለስ ተንቀሳቅሷል፡፡ ለዚህም እንዲረዳው እስኪ የሌሎች ሀገሮች ልምድ ምን ይመስላል? ብሎ የሦስት ሀገሮችን ልምድ ለመቅሰም ወደ ሀገሮቹ ተጉዟል› [ይህንን ሲል አሽሟጣጮቹ ‹ከሄዳችሁት ውስጥ እርስዎ ብቻ ነው የተመለሱት› አሉና አሽሟጠጡ፡፡] በዚህም መሠረት የቻይና፣ የሞንጎልያና የዚምባቡዌ ልምድ ተወስዷል፡፡ ተሞክሮው ከተቀሰመ በኋላም ዓለም ዐቀፍ ነባራዊ ሁኔታው ምን ይመስላል? የሚለውን ለማየት እንዲቻል አራት ኮምፒውተሮች ተገዝተው፣ ብሮድ ባንድ ኢንተርኔት ገብቶ ከመረጃ መረቦች እየተፈለጉ ተወስደዋል፡፡ ለዚህም ይረዳ ዘንድ ድርጅቱ የ‹አይ ቲ› ማዕከል ያቋቋመ ሲሆን የኮሚቴው አባላትም የሦስት ወር ሥልጠና ከታዋቂ ተቋም ወስደዋል፡፡ መረጃውን እየፈለገ ለማምጣትም አንድ ከፍተኛ ኤክስፐርት ተቀጥሯል፡፡[አሁንም አሽሟጣጮቹ አላቆሙም ‹ኮምፒወተሩ የተገዛው ከኃላፊው እኅት ሱቅ ነው፤ ሥልጠናውንም የሰጠው የኮሚቴው ሊቀ መንበር ወንድም ነው፤ ተቀጠረ የተባለውም ኤክስፐርት የምክትል ኃላፊው ዘመድ ነው› የማናውቅ መሰልናቸው፡፡
መናገርስ እናውቃለን
ግን ብንናገር እናልቃለን ብለን እንጂ‹ አሉና ከታተፉት]
‹ከዚህ በኋላ ኮሚቴው ወደ ጥናትና ምርምር ገባ፡፡ ብዙ ነገሮችን አገናዘበ፣ በአማካሪ ድርጅቶችም ሁኔታውን አስገመገመ፡፡ በመጨረሻም የደረሰበትን ዛሬ ይኼው ሊያቀርብ ነው፡፡› ብሎ ቀና ሲል የሚያፈጥ ዓይን እንጂ የሚያጨበጭብ እጅ አጣ፡፡
‹ኮሚቴው ጉዳዩን ከሥር ከመሠረቱ ነው ያየው፡፡ በዚህም መሠረት ከፋፍሎ ያቀርበዋል፡፡ [‹ቆይ ሁሉም ነገር በዚህ ዘመን መከፋፈል አለበት እንዴ› አለ አንድ አሽሟጣጭ]
1.1       የደረጃ ዕድገት ምንድን ነው?
የደረጃ ዕድገት ከሁለት ቃላት የተመሠረት ሐረግ ነው፡፡ ደረጃ እና ዕድገት፡፡ ደረጃ የሚለው ቃል ‹ደረጃ፣ ተደረጀ፣ አደራጀ፣ ተደረጃጀ፣ ድርጅጅት፣ ድርጅት› ከሚለው ግስ የመጣ ሲሆን ብዙ ትርጉም እንዳለው መዛግብተ ቃላት ያስረዳሉ፡፡ የቤት መወጣጫ መሰላል ደረጃ ይባላል፡፡በሌላ በኩልም ደረጃዎች መዳቢ የሚያወጣው ደረጃም አለ፡፡ ሌሎች ደረጃዎች መኖራቸውንም ምሁራን ይገልጣሉ፡፡ የኛ ደረጃ ግ ከሁሉም የተለየ ነው፡፡ ዕድገት የሚለውም ‹አደገ፣ ተመነደገ› ከሚለው የመጣ ሲሆን ማደግ መመንደግ ማለት መሆኑን ከልዩ ልዩ ሀገሮች ልምድ ለማወቅ ተችሏል፡፡
1.2     የደረጃ ዕድገት አመጣጥ ታሪካዊ ዳራ
የደረጃ ዕድገት በዓለም ላይ ከመጣ ብዙ ዘመናት አልፈውታል፡፡ መዛግብት እንደሚገልጡት በአውሮፓ የኢንዱስትሪ አብዮት ጊዜ ሳይጀመር አይቀርም ይባላል፡፡ የደረጃ ዕድገት እንደየሀገሩ ርዕዮተ ዓለም ይለያያል፡፡ ልዩነቱን እንደሚከተለው ከፋፍለን ማየት እንችላለን፡፡
የደረጃ ዕድገት በካፒታሊስት ሥርዓት
የደረጃ ዕድገት በኮሚኒዝም ሥርዓት
የደረጃ ዕድገት በታዳጊ አገሮች፣
የደረጃ ዕድገት በገለልተኛ ንቅናቄ ሀገሮች
የደረጃ ዕድገት በአፍሪካ
1.3     የደረጃ ዕድገት በልዩ ልዩ ሀገሮች
የደረጃ ዕድገት በዓለም ላይ አንድ ወጥ የሆነ አሠራር እንደሌለው በሦስት ሀገሮች ባደረግነው ጥናት ታውቋል፡፡ በቻይና የደረጃ ዕድገት ‹ቹ ቻግ ቺግ› የሚባል ሲሆን በኮሙኒስት ፓርቲው ውስጥ በሚኖር ተሳትፎ መጠን ይወሰናል፡፡ በሞንጎልያ እጅግ ብርድ ስለነበረ ተዘዋውረን መዛግብቶቻቸውን ለማየት አልቻልንም እንጂ የደረጃ ዕድገት መኖሩን ዐውቀናል፡፡ በዚምባብዌ ከሀገሪቱ ኢኮኖሚ የተነሣ የደረጃ ዕድገት ቆሟል [አንድ አሽሟጣጭ ‹ሞንጎልያ ብርድ ከሆነ፣ ዚምባቡዌ የደረጃ ዕድገት ከሌለ ለምን ሄዳችሁ?› አሉ]
1.4     የደረጃ ዕድገት በኢትዮጵያ
  • የደረጃ ዕድገት በዐፄው ዘመን
ባለፈው በነፍጠኛው ሥርዓት ጊዜ ዕድገትና ደረጃ የሚታሰቡ አልነበሩም፡፡ ቢታሰቡም ለሥርዓቱ ቁንጮዎች እንጂ ለብሔር ብሔረሰቦች የሚሆን አልነበረም፡፡ሥርዓቱ ዘውዳዊ በመሆኑ ዕድገትና ደረጃም ዘውዳዊ ነበሩ፡፡ ያም ቢሆን እንኳን የደረጃ ዕድገትን የሚመለከቱ መዛግብትን ማግኘት አልቻልንም፡፡[ይኼኔ አንዱ አሽሟጣጭ ‹ ግእዝ አላውቅም አትልም፤ አላገኘንም ከምትል› አሉት]
  • የደረጃ ዕድገት በደርግ ጊዜ
የደርግ ሥርዓት ሰው በላ ሥርዓት ነው፡፡ ጦርነት ናፋቂ የሆነ ሥርዓት ነው፡፡ ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር ተብሎ ስለነበር ደረጃና ዕድገትም ራሳቸው ጦር ግንባር ዘምተው ነበር፡፡
  • የደረጃ ዕድገት በሽግግሩ ጊዜ
በሽግግሩ ዘመን ገና ኢኮኖሚያችን ስላልጠነከረ የደረጃ ዕድገትም የተጠናከረ አልነበረም፡፡ የደረጃ ዕድገት ፈጣን ዕድገት ከማስመዝገባችን በፊት ያን ያህል የተጠናከረ ዕድገት አልነበረውም፡፡ ቢሆንም ግን ተስፋ ሰጭ ጅምሮች ታይተው ነበር፡፡
  • የደረጃ ዕድገት ፈጣን ዕድገት ካስመዘገብን በኋላ
በአሁኑ ጊዜ የደረጃና ዕድገት ጉዳይ ትኩረት አግኝቶ በመሠራት ላይ ይገኛል፡፡ የሠራተኛውን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት መሠረት ባደረገ መልኩ በተቀየሰው አቅጣጫ መሠረት ፖሊሲ ተቀርጾ ወደ ተግባር ተገብቷል፡፡ በርግጥ ወደ ተግባር ሲገባ አፈጻጸም ላይ ችግሮች መከሰታቸው አልቀረም፡፡
የተከሰቱ ችግሮች
·         የሠራተኛው የግንዛቤ ማነስ
·         ስለ ደረጃ ዕድገት የሚገልጡ በቂ ሥልጠናዎች አለመሰጠታቸው
·         የጠባቂነት መንፈስ
·         የኪራይ ሰብሳቢነት መንፈስ
·         የደረጃ ዕድገትን ከሀገር ዕድገት ነጥሎ ማየት
·         የደረጃ ዕድገትን አመካኝቶ ሌሎች እንቅስቃሴዎች ማድረግ
·         በመ/ ቤቱ ውስጥ የደረጃ ዕድገትን ትክክለኛ ግንዛቤ የሚያስጨብጡ መፈክሮች አለመኖር
·         የደረጃ ዕድገትን አስመልክቶ ችግር ያለባቸውን ጥቂት ሠራተኞች ለመለየት አለመቻል፡፡
የመፍትሔ ሃሳብ
ኮሚቴው ላለፉት ሦስት ወራት ባደረገው ርብርብ ይህንን ጥናት ከፍጻሜ ለማድረስ ችሏል፡፡ የዚህ ጥናት ዓላማም የመፍትሔ አቅጣጫ ማመላከት ነው፡፡
1.         ስለ ደረጃ ዕድገት ሠራተኛው ተገቢ ግንዛቤ እንዲጨብጥ የሚያስችሉ ሲምፖዝየሞች፣ ወርክሾፖችና ስብሰባዎች ማድረግ
2.       የተሻለ ተሞክሮ ካላቸው ሌሎች ድርጅቶች ልምድ መቅሰም
3.       በመ/ቤቱ ውስጥ የደረጅ ዕድገትን የሚያስገነዝቡ መፈክሮችን መስቀል
4.       የደረጃ ዕድገትን የሚያስገነዝቡ በራሪ ወረቀቶች፣ ፖስተሮችና ባነሮችን ማዘጋጀት
5.       የደረጃ ዕድገትና የሀገር ዕድገትን ለይቶ የሚያውቅ ሠራተኛ ለማፍራት እንዲቻል በዚህ ረገድ ሥልጠና ማዘጋጀት፡፡
6.       የደረጃ ዕድገትን የሚያራግቡትን ኃይሎች ለይቶ ሠራተኛው ራሱ እንዲዋጋቸው ማድረግ
በሠራተኛው ያላሰለሰ ጥረት የደረጃና ዕድገት ናፋቂዎችን ጠንክረን እንዋጋለን፡፡ አመሰግናለሁ፡፡ ›
አቅራቢው ጥናቱን ሲጨርስና በመስኮቱ በኩል ከድርጅቱ ክበብ የተከፈተ ሙዚቃ ‹ልመደው ልመደው ሆዴ፣ ከእንግዲህ እደር በዘዴ› ሲል አንድ ሆነ፡፡
© ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት የወጣ ስለሆነ በሌላ ተመሳሳይ ሚዲያ ማውጣት የተከለከለ ነው
በፒዲ ኤፍ ቋቱ መበላሸት ምክንያት የ ፒዲ ኤፍ ጽሑፍ ለማቅረብ አልቻልኩም፤ እስኪስተካከል ታገሡ