ዕሩቅ ብእሲ
<ዕሩቅ ብእሲ> በግእዙ ሰው ብቻ፣ ሥጋ ብቻ፣ የተራቆተ፣ ምንም ነገር የሌለው እንደ ማለት ነው፡፡ ቃሉ ከነገረ መለኮት ትምህርት ጋር ተያይዞ የመጣ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ አይደለም፣ ሥግው ቃል አይደለም፣ ሰው ብቻ ነው የሚለውን ትምህርት ለመቃወም በተሰጡ ትምህርቶች ላይ ነው ቃሉን የምናገኘው፡፡ እዚህ ግን ሌላ ትርጉም ነው የምንሰጠው፡፡ ‹ዕሩቅ ብእሲ› ምንም ነገር የሌለው፣ ሥጋ ብቻ ያለው ሰው፣ ሌላ አንዳች ነገር ያልተዋሐደው፣ እንዴው ሥጋና ደም የሆነ ሰው ማለታችን ነው፡፡
ዕሩቅ ብእሲ የራሱ የሆነ ሞያ፣ ሞራል፣ ሀብት፣ ጸጋ፣ ክብር፣ ዝና የለውም፤ ዕሩቅ ብእሲ ራሱን ችሎ አይቆምም፣ እንደ ሐረግ መደገፊያ፣ እንደ እንሽላሊት መታከኪያ ይፈልጋል፡፡ እንደ ሙጫ መጣበቂያ እንደ አልጌ መሸሸጊያ ይሻል፡፡ እንደ ገደል ማሚቱ የሚያስተጋባው፣ እንደ በቀቀን የሚቀዳው ነገር ይፈልጋል- ዕሩቅ ብእሲ፡፡
‹ዕሩቅ ብእሲ› ችግሩ ምንም የሌለው መናጢ መሆኑ አይደለም፡፡ ነገር ግን መናጢነቱን አለማመኑ ብሎም ሊሸውደው መሞከሩ ነው፡፡ ጉድለቱን ሊሞላ፣ ድካሙን ሊያበረታ፣ ስሕተቱን ሊያርም፣ ብቃቱን ሊያሳድግ፣ ዐቅመ ቢስነቱን ሊያበረታ አይፈልግም፡፡ አንዳንዴም አይችልም፡፡ ነገር ግን መሸሸጊያ፣ መጠጊያ፣ መንጠልጠያ፣ መመሸጊያ ይፈልጋል፡፡ በመልኩ አይኮራምና በቀለማ ቀለም ውስጥ፣ በዕውቀቱ አይተማመንምና በብዙ መዓርጋት ውስጥ፣ በግሉ አይቆምምና በብዙ ማኅበራት፣ ፓርቲዎችና ክበቦች ውስጥ፣ በሰውነቱ አይቆምምና በብሔሩ፣ በብሔረሰቡና በጎሳ ውስጥ፣ በአስተሳሰቡ አይገዳደርምና በእምነት ተቋሙ ውስጥ፣ በራሱ አልታወቅም ብሎ ያስባልና በታዋቂዎች ኪስ ውስጥ፣ ሀብት የለኝም ብሎ ያማርራልና በሀብታሞች ሞሰብ ውስጥ፣ ሥልጣን አላገኝም ብሎ ይሠጋልና በባለ ሥልጣናት ሳምሶናይት ውስጥ፣ ዕውቀት ያጥረኛል ብሎ ይጨነቃልና በዐዋቂዎች ብርዕ ሥር፣ የራሱ ድግስ የለውምና በደጋሾቹ ዳስ ውስጥ ይመስጋል፡፡
ዕሩቅ ብእሲ ማነህ? ሲሉት ‹ፈረስ አባቴ ነው› ይላል፣ ስሙን ሲጠይቁት እገሌ ዘመዴ ነው፣ ይላል፣ ሲተዋወቁት እገሌንኮ ዐውቀዋለሁ ብሎ ይተርካል፣ የሚኖርበትን ቤት ከጠየቁት እገሌ የተባለው ሰው ቤት ውስጥ ቤተኛ መሆኑን ይናገራል፣ ቀበሌውን ከጠየቁት ቀበሌ የሚያውቀው ባለ ሥልጣን መኖሩን ያወራል፤ የተማረበትን ከጠየቁት ስለሚያውቀው ምሁር ይዘረዝራል፣ የሚሠራበትን ከጠየቁት የሚያውቃቸውን መሥሪያ ቤቶች ይናገራል፡፡ ያነበበውን ከጠየቁት የተዋወቃቸውን ደራሲዎች ስም ያቀርባል፡፡ የሄደበትን ሀገር ከጠየቁት የሚያውቃቸውን የውጭ ዜጎች ይደረድራል፡፡ ስለ ሀብቱ ከጠየቁት እገሌና እገሌ የተባሉ ሀብታሞችን እንደሚቀራረብ ይደሰኩራል፡፡ ካነበበው ጋዜጣ ይልቅ በተዋወቃቸው ጋዜጠኞች ይኩራራል፤ ከተመለከተው ፊልም ይልቅ እጃቸውን በጨበጣቸው ተዋንያን ይጎርራል፤ ከተሳለመው ቤተ ክርስቲያን ይልቅ ስልካቸውን በመዘገባቸው ሰባክያንና ዘማርያን ይደሰታል፡፡ ስለገዛው መኪና የሚያወራው የለውም፤ መኪና ስለገዙ ሰዎች ግን ብዙ ነገር ይላል፡፡ ሳይጠራ ይመጣል፣ ሳይመደብ ያስተናግዳል፣ ሳይመረጥ ኮሚቴ ይሆናል፡፡ ሳይታሰብ ቤተኛ ይሆናል – ዕሩቅ ብእሲ፡፡
ለዕሩቅ ብእሲ የተለያዩ ስብስቦች በጣም ይመቹታል፡፡ ራሱን ከማጋለጥ ይታደጉታልና፡፡ለራሱም የሚለጥፈው ስም ያገኛል፡፡ ዕሩቅ ብእሲ በገዥው ፓርቲ ውስጥ አለ፤ በተቃዋሚውም ውስጥ አለ፡፡ ገዥው ፓርቲ ውስጥ ያለው ዕሩቅ ብእሲ ርዕዮትም፣ ዓለምም የሌለው ነው፤ ብቃትና ችሎታ በጎኑ ያላለፈ ነው፤ መፍጠር አይችልም፣ ማነብነብ ግን ተክኗል፤ መምራት አይችልም፣ ለማጀብ ግን ማንም አይችለውም፤ መሥራት አይችልም፣ ለመሞዳሞድ ግን ነፍስ ነው፤ ለፓርቲው ምንም አይሠራም፣ በፓርቲው ግን ይሠራል፤ የፓርቲው ፕሮግራም አይገባውም፣ ስለ ፓርቲው ፕሮግራም ግን ከእርሱ በላይ የሚያወራ የለም፤ ስለ ፖሊሲው አያውቅም፣ ሁሉንም አመራሮች ግን ያውቃል፤ ወደ ፓርቲው አልቀረበም፣ ወደ ጥቅሞቹ ግን በጣም ተጠግቷል፡፡ በራሱ ስም መቆም ስለማይችል በፓርቲው ስምና በባለ ሥልጣናቱ ስም ይነግዳል፡፡ የሚያውቀውን ሳይሆን የሰማውን ያወራል፡፡ ድሎትን የሚመገብበት ሆድ እንጂ መከራን የሚችልበት ትዕግሥት ስለሌለው ለድግሱ ከፊት ለሰማዕትነቱ ግን ከኋላ ነው የሚሰለፈው፡፡
ዕሩቅ ብእሲ ወደ ገዥው ፓርቲ የሚመጣው ዓለማው ፖሊሲው፣ ስትራቴጂው ገብቶት፣ በርዕዮተ ዓለሙ ተስማምቶ፣ በዚህ መሥመር ታግዬ ለውጥ አመጣለሁ ብሎ አይደለም፡፡ ጥገት ላም ላገኝ እችላለሁ ብሎ እንጂ፡፡ በራሱ መንገድ፣ በራሱ ችሎታ፣ ከሌሎቹ ጋር ተወዳድሮ፣ በራሱ ተራምዶ፣ በራሱ ታግሎ ለመጓዝና ያሰበበት ለመድረስ ዐቅም የለውም፣ ልብም የለውም፣ ትዕግሥትም የለውም፡፡ ስለዚህ የተሻለው አማራጭ መጠጋት ነው፡፡ ሲጠጋ የፓርቲው ‹የስሙ ቀዳሽ የክብሩ ወራሽ› ይሆናል፡፡ የፓርቲውን ስም ለስንፍናው መደበቂያ፣ ለድክመቱ መሠወሪያ፣ ለዐቅመ ቢስነቱ ማገሚያ ያደርገዋል፡፡ ቀጥ ብሎ መቆም የማይችለው ሐረግ፣ በብዙ ቋሚዎች መካከል ይገባና የቆመ መስሎ ይታያል፡፡
የፓርቲ ሽፋን ባያገኝ ኖሮ በዕውቀቱ ማን ይሾመው ነበር? በየት ተወዳድሮ የውጭ ዕድል ያገኝ ነበር? በምን ዐቅሙ ቤትና መኪና፣ ክብርና ዝና ያገኝ ነበር? ‹ቅዳሴው ቢያልቅበት ቀረርቶ ሞላበት› እንደሚባለው ‹ዕውቀትና ችሎታ ቢያልቅበት አባልነት ሞልቶበት ነው እንጂ፡፡ ‹ዓሊ ለተዳረ ሲራጅ በግ አረደ› እንዲሉ ሌሎች በታገሉ፣ ሌሎቹ በደሙ፣ ሌሎች ሌት ተቀን በለፉ፣ ዕሩቅ ብአሲ ተቀለጣጥፎ እፍታ እፍታውን ይወስደዋል፡፡ እርሱ እቴ ከመታወቂያው እንጂ ከትግሉ የለበትም፡፡
ዕሩቅ ብእሲ በተቃዋሚው ውስጥም አለ፡፡ መቃወም እንጀራው የሆነ፡፡ ከአንዱ ፓርቲ ወጥቶ ወደ ሌላው ፓርቲ ሰይጣን እንዳሳተው መነኩሴ በኣት ሲለውጥ የሚኖር፤ ከኮሚኒስትነት ወደ ሶሺያሊስትነት፣ ከሶሺያሊስትነት ወደ ሊበራልነት፣ ከሊበራልነት ወደ አብዮታዊነት ሲቀያየር፣ ከኅብረ ብሔር እስከ ብሔር፣ ከብሔር እስከ ብሔረ ሰብ፣ ከብሔረ ሰብ እስከ ጎሳ ፓርቲ ሲገባና ሲወጣ ስቅ የማይለው፡፡ በሄደበት ሁሉ ወይ ሊቀመንበር፣ ወይ ጸሐፊ፣ ወይ የፖሊት ቢሮ፣ ወይ ማዕከላዊ ኮሚቴ፣ ወይ ሥራ አስፈጻሚ፣ ወይ ኦዲት ኮሚሽን፣ ወይ ቃል አቀባይ እንደሆነ የሚኖር፡፡
የተቃዋሚው ጎራ ውስጥ ባይኖር ኖሮ፣ ራሱንም ‹ተቃዋሚ› በሚባል የንግድ ምልክት ውስጥ ባይከትት ኖሮ ማንም ሊሰማው፣ ሊያየው፣ ሊመርጠው የማይችል ነው- ዕሩቅ ብእሲ፡፡ ጋዜጣ ላይ ለመውጣቱ፣ ሬዲዮ ላይ ለመቅረቡ፣ የውጭ ዕድል ለማግኘቱ፣ መግለጫ ለመስጠቱ ዋነኛው ምክንያት ተቃዋሚ መሆኑ ብቻ የሆነ፡፡ ስለ ዕውቀቱ፣ ስለ ብስለቱ፣ ስለ አመራር ክሂሎቱ፣ ስለ ትግል ስልቱ፣ ስለ አእምሮ ምጥቀቱ ተብሎ ሊነገርለት የማይችል፣ የህልውናው ምንጭ ተቃዋሚነት የሆነ ነው- ዕሩቅ ብእሲ፡፡ እነዚህ አነስተኛና ጥቃቅን ፓርቲዎች ባይኖሩ ኖሮ እርሱን ማን ሊቀ መንበር ያደርገው ነበር?
ለዕሩቅ ብእሲ ማኅበራት ምቹ ናቸው፡፡ በራሱ ሠርቶ፣ በራሱ መታወቅ ለማይችለው ዕሩቅ ብእሲ አንድ ቀን ስብሰባ ላይ መጥቶ በአፈ ጮሌነት ለመመረጥና ወንበር ለመያዝ ይመቹታል፡፡ እኔ እንዲህ ነኝ ማለት ስለማይችል እኔ የዚህ አባል ነኝ፣ የዚህ ሰብሳቢ፣ የዚህ ዋና ጸሐፊ፣ የዚህ አመራር የሚለውን ካባ ይደርበዋል፡፡ ከዚያ ውጭ ህልው ስለማይሆንም ካባውን ላለመገፈፍ ይሟሟታል፡፡ ለእርሱ ማኅበር የመሥሪያ ቦታ አይደለም፤ በኅብረት የማገልገያ መንገድም አይደለም፡፡ ለእርሱ ማኅበር ካባው ነው፡፡ ‹ዕሩቅ ብእሲ› ዎች የሞሉበት ማኅበር መጀመርያ በዓላማ ይቋቋምና በኋላ ዓላማውን ረስቶ ማኅበሩ ብቻ ይቀራል፡፡
ዕሩቅ ብእሲ ‹ዕሩቅ› ነውና ምንጊዜም ሽፋን ይፈልጋል፡፡ ዕራቁቱን መሆኑን ያውቀዋልና እንደ አዳም በለስ ውስጥ ገብቶ መሸሸግ አለበት፡፡ ሀብታም እንደማይሆን ለራሱ ያሳምንና የሀብታም አጫዋች ይሆናል፡፡ ሲስቁ ይስቃል፣ ሲሸታቸው ያስነጥሳል፣ ሲበሳጩ የርሱ ጨጓራ ይነዳል፤ ሲያማቸው እርሱ መርፌውን ይወጋል፤ ያልሆኑትን ነዎት ብሎ፣ ያልሠሩትን ሠሩት ብሎ፣ የሌላቸውን ሰጥቶ፣ ከሰው ተራ አውጥቶ ከመላእክት ተራ ይከታቸዋል፡፡ የእገሌ ጋሻ ጃግሬ፣ የእገሌ ቀራቢ እንዲባል ያደርጋል፡፡ የሚቀጥርበት ድርጅት የለውም አስቀጥራችኋላሁ ብሎ ግን ይጎርራል፣ የሚሰጠው ገንዘብ የለውም አሰጣችኋላሁ ብሎ ግን ይሰበስባል፤ የሚያወራው ነገር የለውም እገሌ እንዲህ ሲል ከጎኑ ነበርኩ ብሎ ግን ይዘባነናል፡፡ ሴቶችን ወደራሱ መሳብ እንደማይችል ያውቃል፣ ወደ ሚሳቡበት ግን ያስጠጋል፡፡
ዕሩቅ ብእሲ ብዙ ታዋቂ ሰዎችን ይቀርባል፡፡ እርሱን የሚያውቀው አያገኝም፤ በታዋቂዎች ደረት ላይ ልጥፍ ብሎ ግን ትንሽ መታወቅን ቆረስ ያደርጋል፡፡ ከታዋቂዎች ጋር የተነሣው ብዙ ፎቶ አለው፡፡ ስለ ታዋቂዎቹ ሲነሣ ያንን እየመዠለጠ ‹እርሱማ ወዳጄ ነው፣ እርሱማ አብሮ አደጌ ነው፣ እርሱማ ጓደኛዬ ነው፣ እርሱማ በእጄ ነው፣ ከእርሱ ጋርማ ሁሌ ነው የምንገናኘው› ይላል፡፡ ካስፈለገም ሞባይሉን መዥረጥ አድርጎ ‹ልደውልለት› ይላችኋል፡፡ ዕሩቅ ብአሲ የግብዣ ወረቀት ከየትም ብሎ አያጣም፡፡ ወረቀቱን ከታተመበት ዓላማ በላይ የሚጠቀምበት ጋባዡ ሳይሆን ዕሩቅ ብእሲ ነው፡፡ ለርሱ የታላቅነቱ ምንጭ ነው፡፡፡ ‹ቀላል አይደለሁም› ለማለት ወጣ አድርጎ ያሳያችኋል፡፡ ወይም ልክ በአጋጣሚ እንዳደረገው አድርጎ ጠረጲዛችሁ ላይ ጣል ያደርገዋል፡፡ ሌላ የሚያወራው ቁም ነገር የለውማ፡፡
ዕሩቅ ብእሲ በእምነት ተቋማትም ውስጥ ሞልቷል፡፡ ውስጣቸውን የማያጠሩ፣ ለአገልጋዮቻቸውና ለተከታዮቻቸው ጥብቅ መመዘኛ የሌላቸው፣ ለንጽሕናና ቅድስና ትኩረት የማይሰጡ፣ ጠባቡን በር ያሰፉ የእምነት ተቋማት የዕሩቅ ብእሲ መሸሸጊያ ናቸው፡፡ ዕሩቅ ብእሲ እዚያ የሚሄደው አምኖ ለመጽደቅ፣ ተጋድሎ ድል ለማድረግ፣ አገልግሎ በረከት ለማግኘት፣ በጎ ሠርቶ ዋጋ ለመቀበል አይደለም፡፡ የሃይማኖትን ሽፋን ለማግኘት እንጂ፡፡ ድክመቱን፣ ዐቅመ ቢስነቱን፣ አላዋቂነቱን፣ ስንፍናውንና ጎደሎነቱን ታግሎ ከማሸነፍ ይልቅ የሃይማኖት ስም ይሰጠዋል፡፡ ሌሎች ሰዎች እንዲታረም፣ እንዲስተካከልና እንዲሞረድ ሲነግሩትም ‹የዚህ እምነት ተከታይ በመሆኔ ነው› የሚል ታርጋ ይለጥፍለታል፡፡
አንዳንዱ ሰው ሰባኪ ባይሆን ኖሮ ምን ይሆን ነበር? ዘማሪ ባይሆን ኖሮ ምን ይሆን ነበር? አገልጋይ ባይሆን ኖሮ ምን ይሆን ነበር? ለመሆኑ ዓለምን ንቆ ነው ወይስ ዓለም ንቃው? ዕሩቅ ብእሲ ዓለምን አይንቅም፤ ዓለም ግን ትንቀዋለች፡፡ ዕሩቅ ብእሲ ዓለምን በቤተ እምነት ውስጥ ይፈልጋታል፡፡ ዕሩቅ ብእሲ ቤተ እምነቱ መዳኛው ሳትሆን እንጀራው ናት፡፡ ‹አብላ› የሚለውን ሕግ ‹ብላ›፣ ‹አጠጣ› የሚለውን ሕግ ‹ጠጣ›፣ ‹እርዳ› የሚለውን ሕግ ‹ተረዳ›፣ ‹አክብር› የሚለውን ሕግ ‹ተከበር›፣ ስጥ የሚለውን ሕግ ‹ተቀበል› ብሎ የሚተረጉመውም ለዚህ ነው፡፡ እርሱ ወደ ቤተ እምነቱ መጥቷል እንጂ ወደ እግዚአብሔር አልመጣም፡፡ ቀርቧል እንጂ አልገባም፡፡
ዕሩቅ ብእሲ በየመሥሪያ ቤቱም አለ፡፡ እንደምንም ብሎ እዚያች ቦታ ተቀጥሯል፡፡ ከዚያች ከወጣ ግን መውደቂያ የለውም፡፡ የሚተማመንበት ዕውቀትም፣ ችሎታም፣ ብቃትም፣ ክሂሎትም፣ ሞራልም፣ ትጋትም የለውም፡፡ ስለዚህ ያችን ወንበር መልቀቅ የለበትም፡፡እርሷን ላለመልቀቅ ሁን ያሉትን ሁሉ ይሆናል፡፡ እሺም ይላል፣ እምቢም ይላል፡፡ ሳያምን አንገቱን ይነቀንቃል፣ ሳይገባው ያጨበጭባል፣ ሳይመለከተው ሃሳብ ይሰጣል፣ ሳይረዳው ቃል ይገባል፣ የእርሱ ዓላማ ኮከብ ሠራተኛ መባል አይደለም፤ የእርሱ ዓላማ በባለ ሥልጣናቱ ፊት ሞገስ ማግኘት ነው፡፡ ይህን ካረጋገጠ በቃው፡፡
ዕሩቅ ብእሲ ዕውቀት ከመጨመር መዓርግ መጨመር ይወዳል፤ ዕሩቅ ብእሲ ከስሙ ይልቅ ዝነኛው፣ ታዋቂው፣ ታላቁ፣ ቅዱሱ፣ ምርጡ፣ የሚለው ቅጽል ያስደስተዋል፡፡ ዕሩቅ ብእሲ የሥራ ስሞችን ሁሉ የመዓርግ ስሞች አድርጓቸዋል፡፡ ተማሪ፣ አርሶ አደር፣ አርቲስት፣ ድምጻዊ፣ ጋዜጠኛ፣ ገጣሚ፣ ኢንቨስተር፣ ወዘተ መዓርግ የሆኑት ዕሩቅ ብእሲ አስገድዷቸው ነው፡፡ ዕሩቅ ብእሲ በሚዲያ እንዴት እንደሚቀርብ ምን እንደሚናገር አይጨነቅም፡፡ ውስጡ አንዳች የለምና ‹እ እ እ› እያለ ማዜም ነው፡፡
ዕሩቅ ብእሲ ብቻውን ሊቆም የማይቻለው፣ መደበቂያ የሚያስፈልገው፣ መንጠላጠያ የሚሻ፣ መመሠጊያ የሚፈልግ፣ መደገፊያ የሚቧችር፣ በሌላው ጌጥ የሚያጌጥ፣ በሌላው ትጋት የሚያተርፍ፣ በሌላው ስም የሚመካ፣ ውስጡን በውጩ የሚደብቅ አስገራሚ ፍጡር ነው፡፡ የሌለበት ቦታ የለም፤ የሌለበት ፓርቲና ድርጅት፣ እምነትና ተቋም፣ ማኅበርና ስብስብ የለም፡፡ ዕሩቅ ብእሲ – ያው ተንጠላጥሎና፣ ተከልሎ፣ ያው በሰው ትከሻ ላይ ሲራመድ፣ ያው በጀግኖች መካከል ተደብቆ፣ ያው ተለጥፎና ተጣጥፎ ይታያል- ያው!