የተሳሳቱ ስልኮች


click here for pdf

‹‹አንድ ቀን ነው፤ ባለቤቴ ከበረራ የምትመለሰው ሌሊት ስለሆነ በግማሽ ልቤ ተኝቼ ስልኳን እጠብቅ ነበር፡፡ እኩለ ሌሊት ላይ ስልኬ ጮኸ፡፡ እኔም ቁጥሩን ሳላይ እንዴው በዳበሳ ስልኩን አነሣሁት፡፡ ‹ሃሎ አያ ግርማ› አለኝ የደወለው ሰው፡፡ ‹ተሳስተዋል ጌታዬ፤ ይህ የአያ ግርማ ስልክ አይደለም› ስል መለስኩለት፡፡ ‹ኧረ እባክዎን ፈልጌያቸው ነው› አለኝ፡፡ እኔም መሳሳቱን ደግሜ አስረዳሁትና ስልኩን ዘጋሁት፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በምሽት እየደወለ ‹አያ ግርማ የሉም› የሚለኝ ሰውዬ ሊያቆም አልቻለም፡፡ እየቆየሁ የስልክ ቁጥሩን ሳውቀው ማንሣት አቆምኩ፡፡ ነገር ግን ልጆቼ ወይም ባለቤቴ ስልኩን ሲያነሡት አሁንም ‹አያ ግርማ የሉም› ይለኛል ያ ሰው፡፡ ደጋግሜ መሳሳቱን ነግሬዋለሁ፡፡ ግን የሚሰማ አልሆነም፡፡ እንዲያውም ጓደኞቼ መቀለጃ አድርገውት ሲያገኙኝ ‹አያ ግርማ› ይሉኝ ነበር፡፡
አንዳንዴ ቀን፣ ብዙ ጊዜ ግን ሌሊት ይደውላል፡፡ አላነሣ ስለው በሌላ ስልክ ቀይሮ መደወልም ጀምሮ ነበር፡፡ እኔ ደግሞ ባለቤቴ ከበረራ የምትመለሰው ሌሊት ስለሆነ ስልኬን አልዘጋውም፡፡ ሰውዬው አሰለቸኝ፡፡ አንድ ሌሊት በሰባት ሰዓት አካባቢ በሌላ ስልክ ደወለና እንደለመደው ‹አያ ግርማ የሉም› ሲለኝ ድምፄን አስተዛዝኜ ‹አያ ግርማኮ ዐረፉ› አልኩት፡፡ ጩኸቱን ለቀቀው፡፡ ቤቱን ሲያደባልቀው ይታወቀኛል፡፡ ከዚያ አንዲት ሴትዮ ስልኩን ተቀበሉና ‹መቼ ዐረፉ› አሉኝ ‹ትናንት ዐረፉ› አልኩ በተሰበረ ድምጽ፡፡ እርሳቸውም ‹በሉ አይዟችሁ እግዚአብሔር ያጽናችሁ› ብለው ዘጉት፡፡ ከዚያ በኋላ ዐረፍኩ፡›› ብሎ ያጫወተኝ አንድ ወዳጄ ነው፡፡

 የሞባይል ስልክ ከተስፋፋ ወዲህ የተሳሳቱ የስልክ ጥሪዎች የዕለት ተዕለት ገጠመኞቻችን ሆነዋል፡፡ አንዳንዱ ሰው የደወለበት ቦታ ትክክል መሆኑን እንኳን ለማረጋገጥ አይፈልግም፡፡ ልክ ስልኩ እንደተነሣለት ወደ ጉዳዩ ይገባና ይዘከዝከዋል፡፡ የተደወለለት ወገን ግራ ገብቶት ‹የት ነው የደወሉት› ሲለው ነው ‹እገሌ አይደለህም እንዴ› ማለት የሚጀምረው፡፡ እንዲህ ያለው ነገር ይበልጥ የሚወሳሰበው ደግሞ የሚደወልለት ወገን ተመሳሳይ ጉዳይ ካለው ነው፡፡

አንዳንዱም የደወለበትን ቦታ ሳያውቅ ምሥጢሩን የሚዘከዝክ አለ፡፡ አንዱ ይደውልልኛና ‹እኔ የምልህ የቤቱን ዋጋ በምን ያህል ልቀንሰው? ከፍ ካደረግነው ቀረጥ እንበላለን፡፡ እንትናን ስጠይቀው እነርሱም በግማሽ ቀንሰው እንደ ተዋዋሉ ነግሮኛል፡፡ እና በሰባት መቶ ሺ ብናደርገውስ?› አለና ዘከዘከልኝ፡፡ ግራ ገባኝ፡፡ ‹ማን ጋ ነው የደወሉት?› ብዬ ጠየቅኩት፡፡ ‹እንትና አይደለህም እንዴ› ሲል በድንጋጤ ድምጽ መለሰልኝ፡፡ ‹አይደለሁም ተሳስተዋል› ስለው ይቅርታ እንኳን ለመጠየቅ ልብ ሳያገኝ በድንጋጤ ዘጋው፡፡ እርግጠኛ ነኝ ለጥቂት ሰዓታት ‹ምናልባት ሀገር ውስጥ ገቢ ይሆን የደወልኩት? አሁን በስልክ ተከታትለው ቢይዙኝስ› እያለ ሳይጨናነቅ አይቀርም፡፡
የተሳሳቱ ስልኮች ያጣሏቸው ፍቅረኛሞችና ባለትዳሮችም አሉ፡፡ አንዳንድ ደዋይ የደወለበትን ቦታ ሳያጣራ ለፍቅረኛ ወይም ለትዳር አጋር የሚባለውን ሁሉ ያወርደዋል፡፡ አንድ ጓደኛዬ አንድ ማለዳ ልብሱን እየለበሰ ሞባይሉ ይጮኻል፡፡ እርሱም ሸሚዙን ለመልበስ እንዲያመቸው ስልኩን ‹ስፒከሩ› ላይ ያደርግና ‹ሃሎ› ይላል፡፡ ከወዲያ የደወለችው ሴት ‹አንተ ምን ብትንቀኝ ነው ቀጥረኽኝ የምትቀረው? ሚስትህ እንዳትሰማብህ ብለህ ነው አይደል? እርሷ የምትሄድ መስሎህ ቀጠርከኝ፣ ስትቀር ዘግተህኝ አደርክ፡፡ ባለጌ ነህ ባለጌ› ብላ ጮኸችበት፡፡ እርሱም ሚስቱም አመዳቸው ቡን አለ፡፡ ‹የት ነው የደወልሽው› አለና ጠየቃት፡፡ ‹አንተ ጋ ነዋ፤ አንተ ጋ፡፡ ልትሸውደኝ ፈለግክ፡፡ ሚስትህ አጠገብህ አለች መሰል› አለችውና ጠረቀመችበት፡፡
እውነትም ሚስቱ ትናንት ፊልድ ልትወጣ ነበረ፡፡ በአጋጣሚ የአውሮፕላን ትኬት ጠፍቶ ነው የቀረችው፡፡ ሚስቱ ግራ ገባት፡፡ ባሏን ታምነዋለች፡፡ ግን ይህች ሴት እንዴት የርሷን መሄድ ዐወቀች፡፡ እንዴትስ አሁን ከአጠገቡ መሆንዋን ዐወቀች፡፡ ልቧ እየተምታታባት ፈዝዛ ቀረች፡፡ ባል ደዋይዋ በስሕተት መደወሏን ለማስረዳት ማለ ተገዘተ፤ ሚስትም ለማመንም ለመካድም ተቸገረች፡፡ ወደ ደዋይዋ ዘንድ መልሶ ሲደውል ስልኳን አታነሣውም፡፡ ይህ ችግር የተፈታው የእርሷ እኅት ለሴትዮዋ ደውላ ካገኘቻትና ደዋይዋ የደወለችው በስሕተት መሆኑን፤ እርሱንም ፈጽማ እንደማታውቀው ካረጋገጠች በኋላ ነበር፡፡ የደወለችበትን ሰው ስሙን እንኳን አታውቀውም፡፡
ሰው የደወለበትን ቦታ ሳያረጋግጥ እንዴት መርዶ በስልክ ያረዳል? አንዳንዴኮ አጋጣሚዎች የሚፈጥሩት መገጣጠም አለ፡፡ አንድ የታክሲ ደንበኛዬ እንዲህ አጫውቶኛል፡፡ አንድ ቀን ለታክሲ ተራ ይዞ እያለ በሞባይሉ ይደወልና፡፡ ‹የሳሙኤል ጓደኛ ነህ አይደል› ይለዋል፡፡ ‹አዎ፣ ደኅና አይደለም እንዴ› ይላል ደንግጦ፡፡ ‹‹አይ እርሱስ ደኅና ነው፤ አባቱ ስላረፉ ጓደኞቹ ቀስ ብላችሁ እንደታረዱት ነው›› ይለዋል፡፡ እርሱም ስለደነገጠ የደዋዩን ስም እንኳን አልጠየቀም፡፡ ሌሎቹን ባለ ታክሲዎች ሰብስቦ ይነግራቸዋል፡፡ እነርሱም ተመካክረው በጠዋቱ ቤቱ ይሄዳሉ፡፡
በማለዳ ባለ ታክሲዎች በቤቱ የተሰበሰቡበት ሰው ግራ ይገባዋል፡፡ ደግሞም ሁሉም ጋቢ ለብሰዋል፡፡ ‹ምን ችግር ተፈጠረ?› ይላል ሳሙኤል፡፡ መጀመርያ መርዶውን የሰማው ባለ ታክሲም ‹አይ አባትህ ስላረፉ ልናጽናናህ መጥተን ነው› ይለዋል፡፡ ሳሙኤል ግራ ገባው፡፡ ‹የኔ አባት› ብሎ ይጠይቃል፡፡ ‹አዎ ትናንት ተደውሎ ተነግሮን ነው› ይላል ባለ ታክሲው ጓደኛው፡፡ ሳሙኤል በግርምት ሁሉንም ያያቸዋል፡፡ ከዚያም ተነሥቶ ወደ ውስጠኛው ክፍል ሲገባ ተከትለውት ይገባሉ፡፡ በድንጋጤ በራሱ ላይ አደጋ የሚፈጥር መሰላቸው፡፡ ሳሙኤል አንድ በር ሲከፍት አንድ አረጋዊ ሰው ጋቢያቸውን ለብሰው ዳዊት ይደግማሉ፡፡ ‹አባቴኮ ይኼውና› ይላቸዋል፡፡ መርዶ አርጂዎችም ይደነግጣሉ፤ ግራም ይጋባሉ፡፡
ያ መጀመርያ ወሬውን ያመጣውን ባለ ታክሲ ይጠይቁታል፡፡ እርሱም በርግጠኛነት መስማቱን ይምላል፣ይገዘታል፡፡ የሰውዬውን ስምና ስልክ ግን አልያዘውም፡፡ ክፋቱም ከሰውዬው ስልክ በኋላ ብዙ ስልክ ስላስተናገደ ለመለየት አልቻለም፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ድንጋጤው ወደ ጨዋታ፣ ከዚያም ወደ ቀልድ ተቀይሮ ቁርስ በልተው መውጣታቸውን ነግሮኛል፡፡ እዚህ ያለ መርዶው የደገጠ ሰው እንዳለ ሁሉ፤ ሌላ ቦታ ደግሞ ተደውሎለታል ተብሎ በመቅረቱ የሚታማ ይኖራል፡፡
ደውሎ ‹ማነህ› የሚልም አለኮ፡፡ ‹አንተ ማን ብለህ ደወልክ› ሲሉት ‹አንተ ራስህ ማነህ› ብሎ የሚያፋጥጥ፡፡ ኧረ ከዚህ የከፋውም የደወለበትን ቦታ ሳያረጋግጥ ቀልድ ይቃጣዋል፡፡ የተደወለለት ሰው ግራ ሲገባውና ሲናደድ ‹እኔን አታውቀኝም› ብሎ የልጅ ቀልድ የሚቀልድ ሞልቷል፡፡
የደወልነው ስልክ በቴክኒክ ምክንያት ወይም በራሳችን ስሕተት ምክንያት ያልታሰበ ቦታ ሊገባ ይችላል፡፡ ስሕተቱን በጊዜ ለማረምም ሆነ በተሳሳተ ስልክ ላይ ብዙ ወጭ ላለማውጣት፤ ከዚያም አልፎ በሌላው ሰው ሕይወት ውስጥ ችግር ላለመፍጠር የስልክ አጠቃቀም ሥነ ምግባር ወሳኝ ነው፡፡
እስኪ ስንቶቻችን ከደወልን በኋላ ሰላምታ እናቀርባለን? ስንቶቻችንስ የደወልንበት ቁጥር ትክክል መሆኑን እናረጋግጣለን? በስልክ ግንኙነት ውስጥ ‹ሃሎ› ማለት ብቻ አይበቃም፡፡ ቢቻል ‹ጤና ይስጥልኝ› ብሎ ‹የእገሌ ስልክ ነው?› ብሎ ማረጋገጥም ያስፈልጋል፡፡ ስልኩ እንደተነሣ ‹እገሌ ወይም እገሊት የለችም› ብሎ ማፋጠጥ ‹እገሌ ነህ አይደል› ብሎ ማንጓጠጥም ሥነ ምግባራዊ አይደለም፡፡ አንዳንዱ ሰውም ያለጠበቀው ሰው ሲያነሣው ይቅርታ እንኳን አይጠይቅም፡፡ ጆሮ ላይ ድርግም ያደርገዋል፡፡ ይህም አንዳንድ ሰዎችን የማያውቁትን ስልክ እንዳያነሡ እያደረጋቸው ነው፡፡
ሰው በተናደደ ጊዜ ስልክ ባይደውል ይመረጣል፡፡ በአካል ግንኙነት ወቅት በእጅ ስንዛሬ፣ በፊት ገጽታና በዓይንና ጥርስ ሁኔታ ብዙ መልእክቶችን አብሮ ማስተላለፍ ይቻላል፡፡ በስልክ ግን ድምጽ ብቻ ነው ያለው፡፡ እንዲህ ሲሆን ደግሞ ደዋዩ በቁጣ ስሜት ምክንያት ሊሳደብ፣ ክፉ ቃል ሊወጣው ወይም አላስፈላጊ ነገር ሊናገር ይችላል፡፡ ይህንን ያደረገው የተሳሳተ ስልክ ላይ ከሆነ ደግሞ በተቀባዩ ላይ የባሰ ንዴት ይፈጥራል፡፡ ማን ያውቃል አንዳንድ ጊዜ የምንፈልገውን ቁጥር ከስልክ መዝገባችን ነክተን ስንደውል በስሕተት የላይኛውን ወይም የታችኛውን ነክተን እንደውል ይሆናል፡፡ ታድያ ያ ወዳጃችንን እንዲያ በስድብና በቁጣ አጥረግርገነው መልሰን እንዴት ፊቱን እናያለን?
ፈረንሳዮች በባህላቸው ከምሽቱ 3 ሰዓት እስከ ንጋቱ 3 ሰዓት ሰው ጋር ስልክ አይደውሉም ይባላል፡፡ የኛ ባህል ምን ይላል? ዕረፍት ማለት የቢሮን ሥራ ወደ ቤት ማምጣት አይደለም፡፡ ዕረፍት ማለት የኩነት ለውጥ ነው፡፡ ገዳም ወርደንም፣ መዝናኛ ቦታ ገብተንም፣ ቅዳ ውስጥ ሆነንም፣ አልጋ ላይ ተጋድመንም፣ ከቤተሰብ ጋር ከብበንም አሁንም ሞባይሎቻችን ሥራቸውን ካላቆሙ ዕረፍት ምኑ ላይ ነው? በተለይ ደግሞ በምሽት ለሚደወሉ ስልኮች አንዳች የእግድ የመግባቢያ ጊዜ ያስፈልጋቸዋል፡፡ የሌሊት ስልኮች የትዳር አጋርን፣ ልጆችንና አልፎ አልፎም መላ ቤተሰብን የሚበጠብጡ ናቸው፡፡ እንደ እኔ እንደ እኔ፣ አደጋ ተከስቶ ካልሆነ በቀር ከምሽቱ አራት ሰዓት እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት ሰው ጋር ስልክ መደወል በባህላችን ነውር መሆን አለበት፡፡
ግድግዳቸው ከሰንበሌጥ የማይሻል አንዳንድ ቤቶች ደግሞ አሉላችሁ፣ ጎረቤት የሚያወራውን ሁሉ እንደ መዳብ ሽቦ የሚያስተላልፉ፡፡ ቀን እንኳን ብዙ ጩኸት ስላለ ብዙም አይሰማም፡፡ ሌሊቱ ግን ጸጥ ስለሚል በስልክ የሚወራው ሁሉ ጎረቤት ተሻግሮ በማግስቱ የቡና አጀንዳ ይሆናል፡፡ አንዱም ለዚህ ነው በስልኮች ላይ የሰዓት እላፊ መጣል ያለበት፡፡
ምንም እንኳን ስልክ ሀገራችን ከገባ ከመቶ ዓመት በላይ ቢሆነው፣ የስልክ ሥነ ምግባራችን ግን ገና ያልለየለትና የተደባለቀ ነው፡፡ ለፊት ለፊት ግንኙነት ብዙ ወጎችን በዘመናት ቀምረናል፡፡ ስልክ ግን ገና አልተቀመረለትም፡፡ ምን ተብሎ ንግግር ይጀመር? ምን ተብሎ ያብቃ? ስሕተት ሲፈጠር ምን እንበል? የትኛውን ጊዜ ከስልክ ነጻ እናድርገው? ልጆቻችን ስልክ መያዝ ያለባቸው ከስንት ዓመት ጀምረው ነው? ስልክ እና ዕረፍት እንዴት ይስማሙ? ስልክና የእምነት ቦታዎችስ? እና መሰል ጉዳዮች ማኅበረሰባዊ ውይይቶችን ይፈልጋሉ፡፡
© ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ በመሆኑ በሌላ ሚዲያ ማውጣት ክልክል ነው