አባድሮች፣ እናመሰግናለን


ከሀገር ወጣ ብዬ የተለያዩ ሀገሮች ስዘዋወር ከምቀናባቸው ነገሮች አንዱ የደንበኞች አያያዛቸው ነው፡፡ ‹ደንበኛ ንጉሥ ነው› የሚለው እዚያ በገሐድ ይታያል፡፡ ምናልባት ደንበኞች አገልጋዮቻቸውን ሲያመናጭቁ እንጂ አገልጋዮቹ ደንበኞቹን ሲያመናጭቁ ብዙ ጊዜ አታዩም፡፡ እኛ ሀገር ብዙ ቦታ ከፍላችሁም ለምናችሁም ነው፡፡ ከምግብ ቤት ዐቅም እንኳን ጥሩ ምግብ ቶሎ ለማግኘት የወይ ባለቤቱን ወይ አስተናጋጁን ማወቅ አለባችሁ፡፡ መክፈላችሁ ብቻ በቂ አይደለም፡፡
የደንበኞች መኖር ነው የነጋዴዎች የህልውና ምንጭ፡፡ ደንበኞችን መከባከብ ራስን መከባከብ ነው፡፡ አንድን ደንበኛ በሚገባ መያዝ ብዙ ደንበኞችን ያለ ማስታወቂያ ለመሳብ ያስችላል፡፡ አንድን ደንበኛ ማስቀየም ደግሞ ለብዙ ደንበኞች ክፉ ስም እንዲያወጣ ዕድል ይሰጣል፡፡ 

ይህንን በብዙ ሀገሮች ታዩታላችሁ፡፡ የደንበኛነት ካርድ ይሰጧችኋል፤ ልዩ ቅናሽ ያደርጉላችኋል፡፡ አዲስ ነገር ሲመጣ ይነግሯችኋል፡፡ ቅድሚያ ይሰጧችኋል፡፡ እንዲያውም የእንግሊዝ ነጋዴዎች ታማኝ ደንበኞቻቸውን ውድ የሆኑ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን  በነጻ እስከ መጋበዝ ይደርሳሉ፡፡ በዚህም የተነሣ ታላላቅ ኮርፖሬሽኖች የእግር ኳስ ትኬቶችን አስቀድመው በመግዛት ለደንበኞቻቸው በስጦታ ያበረክታሉ፡፡

አውሮፓ ሳንሻገር እዚህ ጎረቤታችን ኬንያና አለፍም ብሎ ኡጋንዳ የደንበኞች ክብካቤ ልዩ ነው፡፡ ስማችሁን መዝግበው ከማስቀመጥ ጀምሮ በደንበኝነታችሁ ርዝማኔ ልክ የቅናሽ አገልግሎትና የነጻ ስጦታ እስከ መስጠት ይደርሳሉ፡፡ እጅግ ታማኝና ከእነርሱ ጋር ለዘመናት ለዘለቁት ደንበኞቻቸው ደግሞ የአውሮፕላን ትኬት ችለው የቱሪስት ቦታዎችን ያስጎበኛሉ፡፡
ይህንን ማየት ነበር እኛ ሀገር የሚናፍቀኝ፡፡ ያልፈለጋችሁትን ምግብ አምጥቶ ‹አንድ ጊዜ ትኬት ተቆርጦበታል ምንም ማድረግ አልችልም› የሚለውን መልስ የማይሰጥ፤ አስተያየት ስትሰጡት ‹ይቅርታ› ብሎ ለማረም የሚጥር፣ ያላችሁትን ሳያመጣ የማይረሳችሁ፣ አስጠብቆ የለም የማይል፣ ‹ተበላሽቷል ለውጠው› ስትሉት ‹ከደመወዜ ነው የሚቆርጡት› የማይል፤ ደንበኞቹን የማያውቅ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ የማያስተዳድረው፣ ከዚያም አልፎ ደንበኞቹን ‹እግዜር ይስጥልኝ› የሚል ነጋዴ የማየት ምኞት፡፡
ትናንት አዘውትረን ወደምንጎበኘው አባድር ሱፐር ማርኬት የጉርድ ሾላ ቅርንጫፍ ሄድን፡፡ አባድርን የማውቀው አራት ኪሎ በሚገኘው ቅርንጫፋቸው ከዛሬ ሃያ ዓመት አካባቢ ጀምሮ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ በኋላ ግን የጉርድ ሾላው ቅርንጫፍ ደንበኛ ነኝ፡፡ አንድ ጊዜ ‹ለምን ደንበኞቻችሁን አትመዘግቡም› የሚል ሃሳብ ሰጠን፡፡ በደስታ ተቀበሉት፡፡ በሳምንቱ ምዝገባውን ጀመሩ፡፡ አስተናጋጆቹ ደንበኞቻቸውን በቅርበት ያውቃሉ፡፡ በስም ይጠራሉ፤ ይከባከባሉ፡፡ ባለቤቶቹ በየጊዜው ይከታተሉትል፤ የምትሰጧቸውን አስተያየቶች በደስታ ይቀበላሉ፡፡ ደግሞም ያርማሉ፡፡
እጅግ የሚገርመኝ ነገር የሱፐር ማርኬቶቹ ባለቤቶች ሙስሊሞች ሆነው የክርስቲያኖች በዓል ሲሆን ‹እንኳን አደረሳችሁ› ብለው ለክርስቲያን ደንበኞቻቸው ስጦታ ያዘጋጃሉ፡፡ እኔ እንዲህ የሚያደርጉ ክርስቲያን ነጋዴዎች አልገጠሙኝም፡፡ ለምሳሌ የገና በዓል ዕለት ቤቱ የክርስቲያን ቤት እስኪመስል ድረስ በገና ዛፍና ስጦታ ያሸበርቃል፡፡ ኢትዮጵያዊው የእምነት መከባበርና መገናዘብ የሚታይበት ቤት ነው – አባድር፡፡
ታድያ ትናንት ማታ ከሱፐር ማርኬቱ ስንወጣ አንድ ፖስታ ሰጡን፡፡ ፖስታውን ስንከፍተው የስጦታ ካርድ ነው፡፡ ደንበኞቻችን ስለሆናችሁ ይህንን ካርድ ሰጥተናችኋል ብለው ከሱፐር ማርኬቱ በነጻ ዕቃ የምንወስድበት ካርድ ሰጡን፡፡
 የገረመኝ ሁለት ነገር ነው፡፡ በአንድ በኩል ደንበኞቻቸውን ለይተው ማወቃቸው፡፡ ማክበራቸው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ደስታቸውንና ትርፋቸውን ማካፈላቸው፡፡ የስጦታው ማነስና መብዛት ለእኔ ቁም ነገር የለውም፡፡ ትልቁ ቁም ነገር ማሰቡ ነው፡፡ መክበሩ ነው፡፡ ዋጋ መስጠቱ ነው፡፡
አባድሮች ለሁላችንም አርአያ የሚሆን ሥራ አሳይተዋልና ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ ‹ካልፈለግከው ተወው› በሚባልበት ሀገር ደንበኛን ‹እንፈልግሃለን› የሚል ሲገኝ ምስጋና ይገባዋል፡፡ አባድሮች እናመሰግናለን፡፡