‹‹ፍቅር ማወቅ እና አለማወቅ›› የሚባል ነገር አለ? ‹‹ፍቅር ማወቅ›› የሚባል ነገር ካለስ – ኢትዮጵያውያን ፍቅር ያውቃሉ? – የዛሬ የፍቅር (የቫለንታይን) ቀን ጽሑፋችን በዚህ ዙሪያ ያጠነጥናል፡፡
መቃጠር (Dating)
“Dating” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል በአገርኛ አማርኛ እኩያ አንድ ቃል ፍቺ ይገኝለት ከተባለ – መቃጠር – የሚለው ተቀራራቢ ይሆናል፡፡ ሆኖም ‹‹አቃጣሪ›› የሚለው የቆየ ቃል የሚሰጠው አሉታዊ ትርጉም ነው፤ ሁለት ሰዎች መሐል ነገር የሚያመላልስ ማለት ሲሆን በፍቅርም ቢሆን አቃጣሪ የሚለው (በተለይም ከጥንታዊ አመጣጡ አንጻር) ቤተሰቦቻቸው ለመገናኘት ዕድሉን የነፈጓቸውን ተፋቃሪዎች በመሐል እየተመላለሰ የፍቅር መልዕክታቸውን የሚያደርስ የሚል ትርጉም ይኖረዋል፡፡ ትርጉሙን ቦርቀቅ ስናደርገው ደግሞ ሁለት ሰዎች እንዲፋቀሩ ለማድረግ በመሐላቸው የድለላ ሥራ የሚሠራ – የሚያቃጥር (dating agent) – እስከሚል ትርጉም ሊደርስ ይችላል፡፡
የፈረንጅኛውን ትርጉም ስንወስደው ደግሞ የተለየ እና አዎንታዊ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ዊኪፔዲያ ለምሳሌ ለDating የሚሰጠው ትርጉም እንዲህ ይተረጎማል ‹‹Dating is a form of courtship consisting of social activities done by two people with the aim of each assessing the other’s suitability as a partner in an intimate relationship or as a spouse. While the term has several meanings, it usually refers to the act of meeting and engaging in some mutually agreed upon social activity in public, together, as a couple.…››
ኢትዮጵያ ውስጥ አንዳንድ ዘመነኛ ከተሜዎች ካልሆኑ በስተቀር፣ መግጠም አለመግጠማችንን እናጥና ብለው ተከታታይ ቀጠሮዎች አመቻችተው፣ አንደኛ፣ ሁለተኛ፣ ሦስተኛ ቀጠሮ በ‹መቃጠር› የሚጠናኑበት እና የሚወያዩበት መንገድ አለ ለማለት ይከብዳል፡፡ አጋጣሚዎች ፈቅደው ከንፈር ለከንፈር ሲገናኙ በሚጀመር የከንፈር ወዳጅነት ድንገት ወደ‹‹ግንኙነት›› ወይም ዕውቅና ያልተሰጠው ፍቅር (affair) ይገባሉ፡፡
ይህንን የመቃጠር ልምድ ማዳበር የግንኙነት ወቅት ለሚኖሩ ክፍተቶችን ለመቀነስ ይረዳል የሚሉ ልምዱ መዳበሩን የሚያበረታቱ ሲኖሩ በሌላ በኩል ደሞ ከባሕላችን ውጪ የሆነና በእኛ ማኅበረሰባዊ ባህሪ ሊለመድምና ውጤታማ ሊሆን አይችልም በሚል ያጣጥሉታል፡፡
ፍቅረኝነት፣ ፍቅር አገላለገጽ እና “Romance”
ልክ እንደ‹dating› ሁሉ ‹romance› ለሚለው ቃልም ሁነኛ የአገርኛ አማርኛ ትርጉም ማግኘት አይቻልም፡፡ ‹romance› ማለት ፍቅርን መግለጫ መንገድ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ጥንዶች ፍቅረኞቻቸውን ለማስደሰት ቢፈልጉም እንኳን ፍቅረኛቸውን ለማስደሰት አቅደው የሚያደርጉበት ልምድ/ባሕል የለም ብሎ መከራከር ይቻላል፡፡ እንዲያውም ብዙዎች የፍቅር አጋራቸውን ‹‹ፍቅረኛዬ›› ነች ብሎ ማለት እያሳፈራቸው፤ በእንግሊዝኛ ‹‹ቦይፍሬንዴ/ገርልፍሬንዴ›› ማለት እየቀናቸው ነው፡፡ ያውም ይህ በከተማ ውስጥ ነው፡፡ በገጠሩ ክፍል በምስጢር ከሚጠበቅ የከንፈር ወዳጅነት ተሻግረው ለትዳር ከበቁ በኋላ ፍቅር የሚገለጸው በቁፍጥንና ነው፡፡ በሁሉም የኢትዮጵያውያን ብሔሮች እና ባሕሎች ብዙም በማይራራቅ ሁኔታ ባሎች ሚስቶቻቸውን በመቆጣጠር እና በመቆጣት የበላይነታቸውን ከማሳየት በላይ ሌላ ፍቅር የሚገልጹበት መንገድ የለም ማለት ይቻላል፡፡ ይህ ማለት ግን ፍቅር የላቸውም ተብሎ ሊተረጎም አይገባም፤ ፍቅር አላቸው ነገር ግን ፍቅራቸውን የመግለጫ መንገድ/ባሕል/ልምድ ግን የላቸውም፡፡ በተደጋጋሚ ሲገለጽ እንደሚስተዋለው ዱላ የፍቅርና ቅናት መገለጫ እየተባለ ቢነሳ አሁን አሁን ግን ጉዳዩ ወንጀል በመሆኑም ጭምር በጊዜ ሂደት ቢያንስ እንደፍቅር መገለጫነት መቆጠሩ ቀርቶአል፡፡
ማቆላመጥ
አንዱ የኢትዮጵያውያን ፍቅርን የመግለጽ ችግርን የሚያንፀባርቀው ፍቅረኞችን ለማቆላመጥ የምንጠቀምበት ቃላት ማጠር ነው፡፡ ፈረንጆቹ ‹‹honey, sweetie, baby…›› እያሉ የፍቅረኛቸው ስም እስኪረሳቸው ሲያቆለማምጡ የኛዎቹ ግን የፍቅረኛቸውን ስም እንኳ በቁልምጫ መጥራት የሚከብዳቸው ጊዜ ይስተዋላል፡፡ ስንቶች ፍቅረኞቻቸውን ‹‹ማሬ፣ ጣፋጯ፣ ፍቅሬ…›› ብለው በአደባባይ ይጠራሉ? ከጓደኞቻቸው ጋርስ በግልጽ ያስተዋውቃሉ? ብዙ ጊዜ ከወጣቶቹ አንደበት የማትጠፋው ‹‹የኔ ቆንጆ›› የምትል ቃል ራሷ፣ የወል ስም እየሆነች አጠቃቀሟ የምር ይሁን የልምድ ለመለየት ያስቸግራል፡፡
ኩራተኝነት
ኩራተኝነት በኢትዮጵያ ወንዶች ውስጥ የተለየ ለፍቅር የመመረጫ መንገድ ነው፡፡ ሴቶቹም ‹‹ኩራቱ…›› ብለው ያደንቁታል፣ ‹‹ጅንኑ…›› ብለው ይዘፍኑለታል፤ ወንዱም ያንኑ ያጠናክራል፡፡ አለዚያ ወንድ ልጅ ፍቅሩን ብሎ ጠብ እርግፍ ቢል፣ ሌላው ቀርቶ እርሷን ለመርዳት ማጀት ቢገባ ‹‹ኤጭ… እሱ ደግሞ ወንድ ነው እንዴ!? ሴታ፣ ሴት ነገር…›› ተብሎ የወንድነት ማረጋገጫውን ሊነጠቅም ይችላል፤ እሱም አይሞክረውም፡፡ ሴቶቹም ‹‹ኮስታራ ወንድ ይስበኛል›› እያሉ ያበረታታሉ ወንዶቹም ‹‹እንኳን ዘንቦብሽ…›› ዓይነት ብለው ነገሩ እንደነበረ ይቀጥላል፡፡
አበሻ ያልሆኑ ወንዶች፣ ፍቅራቸውን መግለጫ ፅጌረዳ አበባ ይሰጣሉ፣ በየሬስቶራንቱ ወንበር ይስባሉ፣ የወይን ጠጅ ብርጭቆ ይሞላሉ፣ የመኪና በር ይከፍታሉ… ወዘተ፣ ወዘተ… እስኪ ኢትዮጵያዊውን ከተሜ እንመልከተው እና ከፈረንጆቹ ኮርጆም ሆነ በራሱ በኢትዮጵያዊ መንገድ ፍቅሩን የሚገልጽበት የተለየ ልምድ የሚባለው ነገር አለ? ምንድን ነው?
በጨዋ ደንብ መለያየት (Silent breakup)
‹መለያየት› በየትኛውም ዓለም ላሉ ጥንዶች ከባድ ነው፡፡ ለምሳሌ ጥቃት አድራሾች በርካቶች ናቸው፡፡ በምዕራቡ ዓለም ዝነኞች ሲያገቡ ‹‹ብንለያይ የፍቅር ሕይወታችንን እንዳትጽፍበት/ፊበት›› ተባብለው ይፈራረማሉ፡፡ ወጣቷ ዘፋኝ ቴይለር ስዊፍት ለኒውስ ዊክ በሰጠችው ቃለምልልስ ‹‹ፍቅረኞቼ ስንለያይ እባክሽ አትዝፈኚብኝ›› ይሉኛል ብላለች፤ በርግጥ ከጆናስ ብራዘርስ ባንድ ታላቅየው ጋር በነበራት የፍቅር ግንኙነት እና መለያየት ዙሪያ እሷም፣ እነርሱም ዘፍነውባታል፡፡
ለኢትዮጵያውያን ግን መለያየት ከሁሉም የባሰ በጣም ከባድ የቤት ሥራ ነው የሚመስለው፡፡ ምዕራብ አገራት ውስጥ ሳይቀር ሚስቶቻቸውን የገደሉ ኢትዮጵያውያን እና ፍቅረኞቻቸውን የቀጡ ሰዎች ቁጥር ተመሳሳይ በደል ከፈፀሙ የአገራቱ ነዋሪዎች ቁጥር የሚበልጥ ይመስላል – በዜና እንደምንሰማው፡፡ በአገራችንም ከማስፈራራት፣ ማሳደድ እና ጥፊ በተረፈ እስከ ጩቤ መማዘዝና አሲድ መረጫጨት መለያየትን እየተከሉ የሚመጡ ነገሮች ሆነዋል፡፡ እርግጥ ነው እነዚህኞቹ ከቁጥራቸው አንፃር ብዙውን ሊገልፁ ባይችሉም፣ በከፊልም ቢሆን መከሰታቸው አሳፋሪ ነው፡፡
ከዚህ በተረፈ እኛም አገር በመለያየት ዙሪያ ከጓዳ ለሕዝብ የበቁ ብዙ ታሪኮች አሉ፡፡ የዘፋኟ የሃይማኖት ግርማ ባል መጽሐፍ ጽፏል፤ ገጣሚው ኤፍሬም ስዩምም እንዲሁ ‹‹ፍቅር እዚህ ቦታ ፈገግ ብሎ ነበር›› በማለት በቀድሞ መድብሉ ያሞገሳትን ‹‹ሶሊያና›› የተባለች ሴት፣ መልሶ ረግሟታል፡፡
ትዕግስት እና መቻቻል የሚባል ነገር – በተራ ጥንዶች መለያየትም ላይ አይስተዋልም፡፡ ጫጫታ ይበዛበታል፤ ወዳጅ ጓደኛ ይነካካበታል፣ ሮሮ እና ብሶት ይስተጋባበታል – እስከድብድብም ሊደርስ ይችላል፡፡ ሴቷም በራስዋ ወንዱም በራሱ ከባቢ የግንኙነቱን ጉድፎች የአጋራቸውን ችግሮች ይናገራሉ፡፡ በጣም የተለየ ሁኔታ ካልተፈጠረ በስተቀር አብዛኛው ግንኙነት ሲጠናቀቅ ለወደፌት ሰላምታ ያህል እንኳን የሚሆን ትእግስት አይቀራቸውም፡፡ ተለያይተው ጓደኛ የሚሆኑ ጥንዶች ከስንት አንድ ናቸው፡፡
የፍቅር ቀንና ፍቅርን ማወቅ
እነዚህን እና የመሳሉትን ተያያዥ ጉዳዮች ስንመለከት ኢትዮጵያውያን የቫላንታይን ቀንን ዓይነት በዓላትን የምናከብርበት የባሕል መቆሚያ ሊያጥረን ይችላል፡፡ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን (በተለይ ለዚህ የተፈጠሩ የሚመስሉ ኤፍኤሞች) ስለበዓሉ አከባበር ሲያነሱ መጤ ባሕል ነው፣ የእኛ አይደለም፣ የምዕራባውያን ተጽእኖ ነው የሚሉ ቀላል መከራከሪያዎችን ከማንሳት ውጪ የባሕላችን መሠረታዊያንን እና ልምዳችንን እንዲሁም የፍቅር መግለጫ መንገዶቻችንን ለውይይት አንስተው ግን አይስተዋሉም፡፡
ቀኑን ላለማበላሸት ግንኙነቶች ችግሮቻቸውን ዋጥ የሚያደርጉበት፣ በአቻ ሴቶች መካከል ቀኑን አከባበር አስመልክቶ ውድድር ቢጤ ውስጥ የሚገቡበት፣ አልፎ አልፎም ለቀኑ ሲባል ብቻ ለሰዓታት የሚቆዩ ግንኙነቶች የሚፈጠሩበት የመኝታዎች (የኪራይ) ዋጋ በጣም የሚወደድበት ቀን እንደሆነ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡
ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ደግሞ የፍቅረኞች ቀን አከባበር ከሚገባው በላይ አትኩሮትን እየሳበ ነው፡፡ በተለይ ጉዳዩ ‹‹በኤፍኤሞች አየር ሰዓት ማሟያ›› እና ‹‹የኢንተርኔት ትርጉም ማንበቢያ›› ከሆነ ወዲህ ቀላል የማይባል የወጣቱ ክፍል ባይፈልግ እንኳን ጉዳዩን ከትኩረቱ ማስወገድ እንዳይችል አድርጎታል፡፡ ይህ የባሕላችን የፍቅርን መግለጫ እጥረት መገለጫ እንዲሁም ሁሉም የሚያከብረው ኢ-ሃይማኖታዊ በዓላት/ፌስቲቫሎች እጥረት ሆኖ ሊቆጠርም ይችላል፡፡
ይህ ቀናት የማክበር ሰበብ ፍለጋ ምናልባትም ከፍቅር ባሕላችን አንጻር ፍቅራችንን የምናከብበት ሌላ ቀን ስለሌለን (ዓመቱን ሙሉ ተኮሳትረን ከርመን) ዕድሉንም የመጠቀም አዝማሚያም ይሆናል፡፡ ፍቅረኞች የፍቅረኞች ቀንን ያክብሩ፡፡ ፍቅርን የመግለጽ ባህልም ያዳብሩ፡፡ አትኩሮቱን ገደብ መስጠት ግን ከሚዲያዎቻችንም ሆነ ከእኛ የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡ ለማይገባቸው ጉዳዮች ከአቅም በላይ አትኩሮት መስጠት በቀኑ ማግስት የምንጋፈጠውን ግላዊም ሆነ ማኅበራዊ እውነታ ካለመቀየሩም በተጨማሪ አትኩሮት የሚገባው ጉዳይ ላይ አትኩሮታችንን በሚገባ እንዳንሰጥ እንዳያግደን ያሰጋል፡፡ ቢያንስ፣ ቢያንስ በዕለቱ ስለፍቅር እና የፍቅር ግንኙነትን ተከትሎ ስለምንተገብራቸው ባሕላዊ ድርጊቶቻችን በጎነት እና መሻሻል ስለሚያስፈልጋቸው ልማዶች እያወጋን ብናሳልፈው፣ ዕለቱ ዋጋ-ቢስ ከመሆን ይተርፋል፡፡
—
ማሳሰቢያ፡- ይህ ጽሑፍ የተጻፈው ስለብዙኃኑ እንጂ ስለአንዳንድ የተለዩ /ወጣ ያሉ/ ኢትዮጵያውያን አይደለም፡፡ አስተያየት ሰጪዎችም ራሳቸውን ሳይሆን ብዙኃኑን እና ባሕሉን እያሰቡ ቢሆን ይመረጣል፡፡