አባ ፊልጶስን ፍለጋ(ክፍል አራት)

ደብረ ታቦር ኢየሱስ ከሩቅ ሲታይ

click here for pdf 
ወጋችንን ደብረ ታቦር ላይ ነበር ያቆምነው፡፡ ሪቻርድ ፓንክረስት እንደሚነግሩን በአካባቢው ትውፊት መሠረት ደብረ ታቦርን መሠረቷት የሚባሉት የኦሮሞው ተወላጅና በትውልድ ሙስሊም ሆነው በኋላ ክርስትናን የተቀበሉት ራስ ጉግሳ መርሳ ናቸው፡፡ ራስ ጉግሳ 1791-1818 ዓም ድረስ አካባቢውን አስተዳድረዋል፡፡ ራስ ጉግሳ ዋና ከተማ አድርገው መጀመርያ የከተሙት ከጎንደር በስተ ደቡብ ምሥራቅ 60 ኪሎ ሜትር ላይ በሊቦ ነበር፡፡ በኋላ ግን ለተፈጥሯዊ ምሽግ ወደምትስማማው ተራራማ ቦታ ሄደው ከተማቸውን በመቆርቆር ቦታውን ‹ደብረ ታቦር› ብለው ጠሩት፡፡
ራስ ጉግሳ አብዛኛውን ዘመናቸውን ያሳለፉት፣ ብዙዎቹን ሥራ የሠሩትና በኋላም ዐርፈው በ1818 ዓም የተቀበሩት እዚሁ ደብረ ታቦር ኢየሱስ ነው፡፡ የራስ ጉግሣ ልጅ ኢማም ከአባቱ ቀጥሎ የገዛውና በመጨረሻም በ1821 ዐርፎ የተቀበረው እዚሁ ነው፡፡ ከእርሱ በኋላ ራስ ማርዬ፣ ራስ ዶሪ (እስከ 1824 ገዝተው እዚያው ዐርፈው ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ተቀብረዋል)፣ ራስ ዓሊ ዐሉላ(ታላቁ ራስ ዓሊ) በደብረ ታቦር መንበራቸውን ዘርግተው ገዝተዋል፡፡

እኤአ በ1843 ደብረ ታቦርን የጎበኛት ፈረንሳዊው ዲ አባዲ በከተማዋ ውስጥ በዚያ ጊዜ ከ1600- 1700 የሚጠጉ ቤቶች እንደነበሩ ጽፏል፡፡ የሕዝቡም ብዛት ወደ 10 ሺ ይጠጋ ነበር፡፡ ለሁለት ዐሥርት ዓመታ ያህል ደብረ ታቦር ላይ የከተሙት ራስ ዓሊ ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን በመሥራት ይታወቃሉ፡፡ በደቡብ ምሥራቅ እናቲቱ ማርያም፣ በምሥራቅ ልጅቱ ማርያም፣ በሰሜን ጠጉር ሚካኤል የሚጠቀሱላቸው ናቸው፡፡ በጎንደር ታሪክ ውስጥ በትውልድ ሙስሊም የሆኑት የኦሮሞ ሥርወ መንግሥት ታሪክ የሚጠናቀቀው ደብረ ታቦር ላይ ነው፡፡
ዐፄ ቴዎድሮስ በየካቲት 1848 ዓም መንበረ ሥልጣኑን ሲይዙ ደብረ ታቦር አንዷ የመቀመጫ ከተማቸው ነበረች፡፡ በጥር 1849 ዓም የግብጹን ፓትርያርክ አቡነ ቄርሎስን የተቀበሉት እዚሁ ደብረ ታቦር ነበር፡፡ በ1853 ዓም ከወይዘሮ ጥሩ ወርቅ ጋር የተጋቡትም እዚሁ ደብረ ታቦር ነበር፡፡ ቴዎድሮስ የውጭ ሀገር ባለሞያዎችን በመጠቀም ከደብረ ታቦር እስከ አሞራ ገደል፣ በመጨረሻው ዘመናቸውም ከደብረ ታቦር እስከ መቅደላ መንገድ አሠርተው ነበር፡፡ በከተማዋ የሚገኘውን ደብረ ታቦር መድኀኔዓለምን አሠርተዋል፡፡ ይህ ጊዜ የቴዎድሮስ ጠባይ የተቀየረበት በመሆኑ ምዕራብ ጎጃም አዴት የሚገኘውን መድኃኔዓለምን አቃጥለው ሀብቱንና ቅርሱን ለደብረ ታቦር መድኀኔዓለም በመስጠታቸው
እንግዲህ ለታቦት አልሰጥም ስለት
አዴት መድኃኔዓለም ነዶ አገኘሁት
ብላ አንዲት ሴት ገጥማለች ይባላል፤፤
ዐፄ ቴዎድሮስ ሴፓስቶፖል መድፋቸውንም ያሠሩት በደብረታቦር ከከተማው አጠገብ በሚገኘው ሰላምጌ በተባለው ቦታ ነው፡፡
እጅግ የሚያሳዝነውም ዐፄ ቴዎድሮስ ከተማዋና ለመጨረሻ ጊዜ ለቅቀው ወደ መቅደላ ሲጓዙ ወታደሮቻቸው መስከረም 30 ቀን ከተማዋን አቃጠሏት፡፡

በስማዳ መንገድ የሚገኙ ቋጥኞች

ደብረ ታቦር የዐፄ ዮሐንስ አራተኛም ከተማ ነበረች፡፡ ነገር ግን የቀድሞ ነገሥታት የነበሩበትን አካባቢ ትተው ‹ሠመራ- መረጣት› በተባለው አካባቢ አዲስ ከተማ ቆረቆሩ፡፡
ዐፄ ዮሐንስ ራስ አዳልን ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ብለው በጥር 1873 ዓም በጎጃም ላይ ያነገሡዋቸው ደብረ ታቦር ላይ ነበር፡፡ አቡነ ጴጥሮስ፣ አቡነ ሉቃስና አቡነ ማርቆስ የተባሉት ግብጻውያን አባቶች በደብረ ታቦር ተቀምጠው ነበር፡፡ እንዲያውም አቡነ ማርቆስ ዐርፈው በ1874 ዓም የተቀበሩት እዚያው ነው፡፡ ስለ ከተማዋ አስደናቂ ታሪክ ልቡ ይበልጥ ለማወቅ የፈለገ ቢኖር የሪቻርድ ፓንክረስትን The History of Däbrä Tabor (Ethiopia): Bulletin of the School of Oriental and African Studies, University of London, Vol. 40,No. 2 (1977), pp. 235-266) ቢያነብ ይበጀዋል፡፡
አሁን ከተማዋን እንልቀቅና ወደ ስማዳ እናምራ፡፡ መንገዱ ወደ ስማዳ እስኪገነጠል ድረስ አስፓልት ነው፡፡ ወደ ስማዳ ከተገነጠለ በኋላ ግን ‹ማሩኝ› የሚያሰኝ ኮረኮንጅ ነው፡፡ ደግነቱ በመንገድ ላይ ብዙ የሚታይ ነገር አለው፡፡ የዝማሬ መዋሥዕቱን ማስመስከሪያ ዙር አምባን በሩቁ ትሳለማላችሁ፡፡ ቅዱስ ያሬድ ከዐፄ ገብረ መስቀልና ከአቡነ አረጋዊ ጋር ወደ ቦታው መጣ፡፤ ቦታውን ወደዱት ነገር ግን የመውጫው ነገር ቸገራቸው፡፡ ያን ጊዜ መልአከ እግዚአብሔር ‹አባ ሆይ ዙርና ወደ ተራራ ውጣ› ስላላቸው ቦታው ‹ዙር አባ› መባሉን የአካባቢው ትውፊት ይናገራል፡፡ እልፍ ስትሉ ደግሞ ከሁለት መቶ ዓመታት በላይ እድሜ ያለው የቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን እንደ ዙር አምባው ሁሉ ተራራ ላይ ከነ ሙሉ ግርማ ሞገሡ ይታያችኋል፡፡

የቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን

በመንገድ ላይ ተፈጥሮን እንድታደንቁ የሚያደርጓችሁ የቋጥኝ ተራሮች አትለፉኝ አትለፉኝ ይላሉ፡፡ ስማዳ የጤፍ ሀገር ነው፡፡ ዛሬ በአዲስ አበባና በአካባቢው የተወደደው የአድአ በርጋ ነጭ ማኛ ጤፍ መነሻው ስማዳ ነው፡፡ ዐፄ ምኒሊክ ለቤተ መንግሥታቸው የሚሆን ነጭ ጤፍ ቢያጡ ከስማዳ አስመጥተው በአድአ በርጋ ስለዘሩት ይኼው ጤፉም ለምዶ ቀረ፡፡ የስማዳ ጥንታዊው ታዋቂ ማኛ ጤፍ ‹ስይት› ጤፍ ይባላል፡፡ ችግሩ በአንድ ቦታ የሚበቅለው መጠን አነስተኛ በመሆኑ ለቅንጦት እንጂ ለአዘቦት አይሆንም አሉ፡፡

መሪጌታ ሐረገ ወይን

በመንገዳችን ላይ በላይ ጋይንት ወረዳ ውስጥ የምትገኘውን ወለላ ባሕር ከተማን እናገኛታለን፡፡ እዚያ ደግሞ የታወቁት ሊቅ መሪጌታ ሐረገ ወይን ይገኛሉ፡፡ መሪጌታ ሐረገ ወይን እግዚአብሔር ጸጋ የሰጣቸው የታሪክ ሊቅ ናቸው፡፡ ከመቄት በታች ያለውን ሀገር በተመለከተ የማያውቁት ነገር የለም፡፡ የእያንዳንዱን ጎጥ ታሪክ ያውቁታል፡፡ እጅግ የሚገርመው ደግሞ ታሪኩን እንዳይረሱት በደብተር ላይ ጊዜ ሲያገኙ ይጽፉታል፡፡ 

ዕድሜ ጠገቧ የመሪጌታ ሐረገ ወይን ደብተር

እርሳቸው እንደነገሩን ከሆነ አካባቢውን ከግራኝ ጥፋት በኋላ ያቀኑት በፄ ሠርጸ ድንግል ዘመን ወደ አካባቢው የመጡ አራት ቅዱሳን ናቸው፡፡ ዐፄ ሠርጸ ድንግል ወደ ጎንደር ሲሻገሩ አራት ሊቃውንትን አመጡን አአራት ቦታ መደቧቸው፡፡ አባ መሰንቆ ድንግል(ለቤተልሔም)፣ አባ ለባዌ ክርስቶስ(ለዙር አምባ)፣ አባ ብእሴ እግዚአብሔር (ለገርባ ማርያም)ና አባ ተክለ ወልድ(ለደብረ ማርያም)፡፡ በሌላ ታሪክ ላይ እነዚህ አባቶች የመጡት ከጉራጌ ምሁር ኢየሱስ መሆኑን ይገልጣል፡፡ 
መሪጌታ ሐረገ ወይንን ስለ አቡነ ፊልጶስ ስለ ጌርጌስና ደብረ ሐቃሊትም ጠየቅናቸው፡፡ እርሳቸው የማያውቁት ነገር የለምና፡፡ ‹ወገዳን አልፋችሁ ሂዱ ሁሉንም እዚያ ታገኙታላችሁ› አሉን፡፡ እኛም መስቀላቸውን ተሳልመን ጉዟችንን ቀጠልን፡፡ የስማዳ ወረዳ ዋና ከተማ ወገዳ ስንደርስ እኩለ ቀን ነበር፡፡ እኔና ሙሉ ቀን ወደ ወረዳው ቤተ ክህነት አመራን፡፡ የወረዳው ሊቀ ካህናት በደስታ ነው የተቀበሉን፡፡ ደብዳቤያችንን ተመልከተው እርሳቸው የወረዳውን መስተዳድር ለማነጋገር ሄዱ፡፡
ከወረዳው መስተዳድር አብረውን የሚጓዙ ሁለት ፖሊሶችን ማስፈቀዳቸውንና ነገ በጠዋት ብንነሣ የተሻለ መሆኑን አስታወቁን፡፡ እኛም ለረዥም መንገድ ስለተጓዝን ማረፉን ወደድነው፡፡ በከተማው የተሻለ ነው የተባለው ሆቴል ውስጥ ሃያ ብር ከፍለን አደርን፡፡ ከተማዋ በጸጥታ የተሞላች ናት፡፡ ከእኛ ሆቴል ጀርባ ግን አንድ ጅብ የሚያህል ማይክራፎን ተከፍቶ አገሩን ያተራምሰዋል፡፡ ከምሽቱ አራት ሰዓት በሁለት የእንግሊዝ የእግር ኳስ ቡድኖች መካከል የሚካሄደውን እግር ኳስ እያስተዋወቀ ነው፡፡ ቦታ ሳይሞላባችሁ ግቡ ይላል፡፡ ቤቱ የኳስ ማሳያ ቤት መሆኑ ነው፡፡ ወደ አምስት ሰዓት ላይ እርሱም ጸጥ አለ፡፡ እኛም ተኛን፡፡

የሌሊት ጉዞ

ከሌሊቱ ዐሥር ሰዓት ተነሣን፡፡ የወረዳው ሊቀ ካህነት ከአንድ ሌላ አባት ጋር ቀድመው ደርሰዋል፡፡ አንደኛው የፖሊስ አባልም መጥቷል፡፡ አንደኛው ግን አልመጣም፡፡ በሞባይል ስልኩ ሲደወል ዝግ ነው ይላል፡፡ ለሠላሳ ደቂቃ ያህል ጠበቅነው፡፡ ምንም ነገር ስለ እርሱ ማወቅ አልቻልንም፡፡ በመጨረሻ አንደኛውን ፖሊስ ብቻ ይዘን በፒክ አፕ መኪናችን ጉዞ ጀመርን፡፡ የወገዳን ከተማ ለቅቀን አሥር ኪሎ ሜትር ያህል እንደሄድን መኪናዋ ማቃሰት ጀመረች፡፡ 

ፀሐይ በስማዳ ተራሮች ብቅ ስትል

መንገዱ ድንጋዮች ወጣ ወጣ ብለው የተቀመጡበት እንጂ መንገድ ሆኖ የተሠራ አይመስልም፡፡ ከጎማዋ ቁመት የማይተናነስ ድንጋይ መሐል ላይ ቁጭ ብሎ ‹እስኪ የምታደርጉትን አያለሁ› ይላል፡፡ ከዚያ በላይ ደግሞ መንገዱ ተራራማ ነው፡፡ 

ውጭ- አልወጣም

ድንበሩ ሂጅ ይላል መኪናዋ ‹እንዴት አድርጌ› ትላለች፡፡ እኛ እንጨነቃለን፡፡ በዚህ መሐል የቀረው ፖሊስ ደወለ፡፡ ‹በእግሬ እየመጣሁ ነው ጠብቁኝ› አለ፡፡ ‹ባትልስ የት ይደረሳል› እያልን፣ መኪናችንንም እየገፋን ጠበቅነው፡፡ እውነትም ቆፍጣና ፖሊስ ነው ሮጦ ደረሰብን፡፡ እንደደረሰ ‹እንዴት ይቺን መኪና ይዛችሁ ትመጣላችሁ› ብሎ ሊውጠን ደረሰ፡፡ ‹ዕራቁቱን ለተወለደ ልጅ ደበሎ መቼ አነሰው› አለ የሀገሬ ሰው፡፡

ሂጂ- አልሄድም

መኪናዋ ስንገፋት፣ ስትገፋን ጥቂት ከሄደች በኋላ ‹ከዚህ በላይ በምንም ዓይነት አልንቀሳቀስም› አለች፡፡ ብንገፋት፣ ብንጎረጉራት ወይ ፍንክች፡፡ ሁላችንም በየድንጋያችን ተቀመጥን፡፡ ምን እናድርግ? እንሂድ ወይስ እንቅር? ያንን ሁሉ ለፍተን ጫፍ ላይ ስንደርስ ልንሸነፍ ? ምንስ አማራጭ አለን ?
 (ይቀጥላል)