አባት ሀገር (የመጨረሻ ክፍል)
የሚወዱትን ሰው አጥቶ በብቸኝነት መኖር ከተስፋ ይልቅ በትዝታ ውስጥ እንድንኖር የሚያደርግ ነው፡፡ በማኅበረሰባችን ባህል የቤት ውስጥ ሥራዎች የሚባሉትን በአብዛኛው የሚሸፍኑት ሴቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ሴቶች የተማሩም ቢሆኑ ወይም ያልተማሩ፣ ሠራተኞችም ቢሆኑ ወይም የቤት እመቤቶች የቤት ሥራ ይቀርላቸው ይሆናል እንጂ የቤት አስተዳደር አይቀርላቸውም፡፡ እነዚህ ሴቶች ሊቃውንትም ቢሆኑ ወይም ሳይንቲስቶች፣ የሀገር መሪዎችም ቢሆኑ ወይም የታወቁ ሃሳብ አመንጭዎች የቤት ውስጥ ጭቅጭቅ ግን አይቀርላቸውም፡፡ ጓዳ የራሱ ሳይንስ አለው፡፡ የጓዳ ሳይንስ እስከዛሬ በየትኛውም ትምህርት ቤት አይሰጥም፡፡ የጓዳ አስተዳደር በየትኛውም የአስተዳደር ትምህርቶች ውስጥ አልተካተተም፡፡
ይህ ነው እንግዲህ ለአባቴ የመጀመርያው ፈተና፡፡ ጓዳውን ማስተዳደር፡፡ በቤታችን ውስጥ እናታችን ካረፈች በኋላ ሦስት ዓይነት የቤት ሠራተኞችን አይተናል፡፡ የመጀመርያዎቹ ቤቱን ‹‹የወንድ ቤት ነው›› ብለው የሚያስቡና መደፋፋት፣ ማባከንና ማዝረክረክ ይቻላል ብለው የሚገምቱ ናቸው፡፡ ወንድ ጓዳ ድረስ አይዘልቅም፤ የተጠየቀውን ይሰጣል፣ ግዛ የተባለውን ይገዛል፤ ለምን አለቀ፣ መቼ አለቀ፣ እንዴት አለቀ አይልም ብለው የሚያስቡ ዓይነት ናቸው፡፡
መጀመርያ አካባቢ አባቴም እንደሚሉት ነበር፡፡ እየቆየ ግን ወገቡን መያዝ ጀመረ፡፡ ቀድሞ የእናቴ ደመወዝና ትከሻ ይሸፍኗቸው የነበሩ ቀዳዳዎች ሁሉ መታየት ጀመሩ፡፡ እርሱም ራሱ በነገሩ ውስጥ ሲገባበት ግራ ይገባው ጀመር፡፡ ለሁለት ሕጻናትና ለአንድ አባወራ እንዴት አንድ ሊትር ዘይት በሦስት ቀን ብቻ እንደሚያልቅ ሊገባው አልቻለም፡፡ ‹‹ወጡ በዘይት ብቻ ቢሠራ እንኳን ይህንን ያህል ሊፈጅ አይችልም›› ማለት ጀመረ፡፡ ነገር ግን ሠራተኛ አሰናብቶ ሠራተኛ ማግኘት፣ እስኪገኝም የኛ መንገላታት እያሳሰበው ሁሉንም ይሸከመው ነበር፡፡ አንዳንዴ ሲመርረው ‹‹ወይ እናት ስንቱን ተሸክመሽው ኖረሻል›› ይልና ዕንባው ዱብ ዱብ ይላል፡፡
ሁለተኛዎቹ ሠራተኞቻችን ደግሞ ጥሩዎች ናቸው፡፡ ለእኛ ያዝኑልናል፡፡ እንደ እናት ለመሆን ይሞክራሉ፡፡ የአባታችን ሁኔታ ያሳዝናቸዋል፡፡ ችግሩ ኀዘናቸው ከልክ ያልፍና ‹አምጵ› እያሉ ከንፈራቸውን ሲመጡለት ይናደዳል፡፡ እርሱ የሚረዳውና የሚረዳው እንጂ የሚያዝንለት አይፈልግም፡፡ ችግሩ ደግ ሠራተኞቻችን አይበረክቱም፡፡
እንዳይበረክቱ የሚያደርጓቸው ዕድርተኞቻችን ናቸው፡፡ በሠፈራችን የወንድና የሴት ዕድር አለ፡፡ የወንድ ዕድር ገንዘብ ከመክፈል፣ ድንኳን ከመጣልና ማታ ማታ ካርታ እየተጫወቱ ከማምሸት በቀር ሌላ ጣጣ የለበትም፡፡ የሴት ዕድር ግን እንጀራ መጋገር፣ ወጥ መሥራት፣ ማስተናገድ፣ ንፍሮ መቀቀል፣ ፍራሽ ዘርግቶ ድንኳን ውስጥ መቀመጥ፣ ቡና ማፍላት አለበት፡፡ በዚህ ሁሉ መካከል ደግሞ ሐሜቱ አለ፣ ጠቡ አለ፣ መተቻቸቱ አለ፤ መነቋቆሩ አለ፡፡ አሁን እናቴ ካረፈች በኋላ የሴት ዕድሩ ጉዳይ የአባቴ ጣጣ ሆነ፡፡ የግድ ዕድሩን ለመሳተፍ በእናቴ ምትክ የቤት ሠራተኞቻችን እየሄዱ ሽንኩርት እንዲከትፉ፣ ሥጋ እንዲዘለዝሉ፣ ወጥ እንዲሠሩ፣ አንዳንዴም እንዲያስተናግዱ ይደረጋል፡፡ አንዳንዶቹ ሠራተኞቻችን እንደ መዝናኛ ስላዩት አያማርሩም፡፡ ደጋጎቹ ግን አይፈልጉትም፡፡ ሁለት ልቅሶ ከሠሩ በኋላ ይሄዳሉ፡፡
ሦስተኛዎቹ ሠራተኞቻችን ለፈተና የሚመጡ ናቸው፡፡ እንዲያውም አንድ ቀን የቤት ሠራተኛ የሚያመጡልን የሠፈራችን ሴትዮ እኛ ቤት ውስጥ መሆናችንን ሳያውቁ ‹‹እንግዲህ ዕወቂበት፤ ካወቅሽበት የቤት እመቤት ትሆኛለሽ፤ ካላወቅሽበት ደግሞ አንቺም እንደሌሎቹ ትወጫለሽ›› ሲሉ ሰምቻቸዋለሁ፡፡ መመርያው አልገባኝም ነበር፡፡ በኋላ ነው የተረዳሁት፡፡ ማታ ማታ ቤቱን የፋሽን ትርዒት ማሳያ ታደርገዋለች፡፡ ሽቱ ተቀብታ፣ ገላዋን ታጥባ፣ ስስ ልብስ ትለብስና ሳሎን ትቀመጣለች፡፡ ነገር ዓለሟ ሁሉ አልገባኝም፡፡
አባቴ ደግሞ እኛን የቤት ሥራ ማሠራት፣ ራት አብልቶ ማስተኛት ስላለበት ከሥራው ሮጦ ቤት ነው የሚመጣው፡፡ ቤት ሲገባ ሽቱዋ ያውደዋል፡፡ አባቴ ወንድ ነው፡፡ ይህንን አትርሱ፡፡ ያውም ገና በወጣትነቱ የሚወዳትን ሚስቱን ያጣ ወንድ፡፡ አንዳንድ ጊዜ እኔን ይዞኝ ወጥቶ በረንዳ ላይ እናመሻለን፡፡ ከራሱ ጋር እየታገለ መሆኑን ዐውቃለሁ፡፡ አባቴ ሌሊት ሌሊት ውኃ የመጠጣት ልማድ አለው፡፡ ማታ ከመተኛቱ በፊት በራስጌው ውኃ ይደረግለታል፡፡ ይህችኛይቱ ልጅ ግን ሆን ብላ ሲተኛ ጠብቃ መኝታ ቤቱ ትሄድና ውኃውን ታስቀምጣለች፡፡ ሁለት ጊዜ ከተኛ በኋላ በር እንዳትከፍት ሲነግራት ሰምቻለሁ፡፡ ነገር ግን አላቆመችም፡፡
አንድ ቀን እኔ ከትምህርት ቤት ግማሽ ቀን ተምሬ ተመለስኩ፡፡ እኒያ ሠራተኛ የሚያመጡልን ሴትዮና ሠራተኛችን በረንዳ ላይ ቡና ይጠጣሉ፡፤ መኛታ ቤቴ ገብቼ ዘጋሁት፡፡ ሲያወሩ ግን በመስኮት ይሰማኛል፡፡ ሴትዮዋ ሠራተኛችንን ይመክሯታል፡፡ የቤት ሠራተኛ ሆነው ገብተው በዚያው ሚስት ስለሆኑ ሴቶች ታሪክ ያጫውቷታል፡፡ ዓላማዋ ገባኝ፡፡ አባቴ ሲመጣ ነገርኩት፡፡ እንደ ልጅ ሳይሆን እንደ እኩያ እኅቱ ነበርና የሚያወራኝ እርሱም እንደገባው ነገረኝ፡፡ ከሁለት ቀን በኋላ እንድትሄድ ተደረገ፡፡
እኒያ የሠፈራችን ሴትዮ ተናደዱ ‹‹አያያዙን አልቻልክበትም፤ በየሳምንቱ እያስወጣችሁ እኔ ከየት አመጣለሁ፡፡ አያያዝ ማወቅ ያስፈልጋል፤ ሲቀጥሩ እንደ ሠራተኛ ሲያኖሩ እንደሚስት ሲሉ አልሰማህም›› አሉና ተቆጡ፡፡
አባቴን የቤት ሠራተኞቹ ብቻ አልነበሩም የተፈታተኑት፡፡ የገዛ ጓደኞቹም ደጋግመው ፈትነውታል፡፡ እርሱ የእኛ ነገር ነው የሚያሳስበው፡፡ በእናታችን አለመኖር በጣም እንደተጎዳን አድርጎ ያስባል፡፡ ጭንቀቱ ጉዳታችን እንዳይሰማን ለማድረግ ነው፡፡ ቤት በጊዜ ከገባ ታናሽ ወንድሜን ሽኮኮ አድርጎ እኔን ያዝልና ያጫውተናል፡፡ የቤት ሥራዬን አብሬው እሠራለሁ፡፡ ቅዳሜና እሑድ አውጥቶ ያዝናናናል፡፡ ልብሳችንን በማሽን ራሱ ያጥባል፤ ይተኩሳል፡፡ በቦርሳዬ የያዝኩትን ምግብ ራሱ ይከታተላል፡፡ ገላችንን የሚያጥበን እርሱ ነው፡፡ አልጋችንን የሚያነጥፈው እርሱ ነው፡፡ ተነጥፎ ካገኘው እንኳን እንደገና ገልጦ ያየዋል፡፡ ሰውነታችን የተኮሰ ወይም የከሳ ከመሰለው ሮጦ ወደ ሐኪም ቤት ነው፡፡ እንዲያውም ጭንቀቱን ያየው የሕጻናት ሐኪሙ ‹‹መጀመርያ ይደውሉልኝና ተነጋግረን ይመጣሉ›› ባይለው ኖሮ በየሦስት ቀኑ እዚያው ይገኝ ነበር፡፡
ይህንን ቤት ቤት የሚል ጠባዩን ግን ጓደኞቹ አልወደዱለትም፡፡ ‹‹ሴቶቹ ወንድ በሆኑበት ዘመን እንዴት ወንዱ ተመልሰህ ሴት ትሆናለህ›› ብለውታል፡፡
ከእነርሱ ጋር ወጥቶ ማምሸት እንዳለበት ደጋግመው መክረውታል፡፡ ሆን ብለው በመሥሪያ ቤቱ መስክ እንዲወጣ አድርገውታል፡፡ እንዳይቀየሙት ብሎ እንድ ቀን አብሯቸው ቢያመሽ በሚጠጣው ቢራ ውስጥ አንዳች ነገር አድርገው ዕንቅልፍ ዕንቅልፍ ሲለው አልጋ ይዞ እንዲያድር አድርገውታል፡፡ የሚስቱ ሐሳብ ይለቀው መስሏቸውም በዚያ ቀን አንዲት ሴት አብራው እንድታድር አድርገዋል፡፡ አባቴ ግን የሚቀየር ሰው አልሆነም፡፡ አዘውትሮ ሐዲስ ዓለማየሁን ይጠቅሳቸዋል፡፡ ደራሲ ሐዲስ ሚስታቸው ካረፈች በኋላ ለምን ሌላ እንዳላገቡ ሲጠየቁ ‹‹እርሷ ቀለበቴን እንዳደረገችው ወደ መቃብር ሄዳለች፤ እኔም ቀለበቷን እንዳደረግኩት እሄዳለሁ›› ብለው ነበር፡፡ ይህ ለአባቴ ትልቅ መመርያው ሆኗል፡፡ ‹‹እኔኮ ባለትዳር ነኝ፤ ከሚስቴ ጋር በተለያየ ቦታ እንኖራለን እንጂ አልተፋታንም፡፡ ባል አሜሪካ ሚስት ኢትዮጵያ ይኖሩ የለም እንዴ! እርሷ በሰማይ እኔ በምድር እየኖርን ነው፡፤ እንድ ቀን እንገናኛለን፡፡ ስንገናኝ ምን እንድላት ነው የምትፈልጉት?›› ይላቸዋል፡፡
ታናሽ ወንድሜንኮ እያዘለ ነበር የሚያስተኛው፡፡ ያውም በልጅ አንደበቱ ‹‹እማዬስ›› እያለ እያስጨነቀው፡፡ የሚመልሰው መልስ እያጣ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ‹‹እማዬ ካላበላችኝ አልበላም›› ይለዋል፡፡ ፊቱን በዕንባ እየታጠበ መልሱ ይጨንቀዋል፡፡ በተለይማ ትምህርት ቤት መሄድ ሲጀምር ‹‹እንደ ልጆቹ የእኔ እናት ለምን አታደርሰኝም›› ይለዋል፡፡ አንድ ፈጣን የሆነ የሠፈራችን ልጅ አለ፡፡ ከወንድሜ ጋር አብረው ነው የሚማሩት፡፡ እንድ ቀን ‹‹እናትህኮ ሞታለች›› አለው፡፡ ‹‹ውሸትክን ነው፤ ለሥራ ውጭ ሀገር ሄዳ ነው፤ ትምጣለች›› ሲል ወንድሜ መለሰለት፡፡ ‹‹ኧ-ራ፣ እናቴ ነግራኛለች ሞታለች፤ የተቀበረችው ደግሞ ገብርኤል ነው›› አለው፡፡ ወንድሜ እየተንቀጠቀጠ ነበር ከትምህርት ቤት የተመለሰው፡፡ እንደመጣ የመኝታ ክፍላችንን ገብቶ ዘጋው፡፡ እኔና ሠራተኛችን ብናንኳኳ ሊከፍት አልቻለም፡፡
ሲጨንቀን አባታችንን ጠራነው፡፤ እርሱ ደግሞ ሲደነግጥ ጊዜ ጓደኛውን ለምኖ በመኪናው ይዞት መጣ፡፡ ቢያንኳኳ ሊከፍትለት አልቻለም፡፡ በመጨረሻ በሩን ሰብሮት ገባ፡፡ አንድ ጥግ ላይ ተቀምጦ ያለቅሳል፡፡ አባቴ እንኳን ይህንን አግኝቶ እንዲያውም ዕንባው ቅርብ ነው፡፡ አብሮት አለቀሰ፡፡ እንኳንም ከጓደኛ ጋር መጣ እንጂ የትኛውን እናባብል ነበር፡፡ ጓደኛው እንደምንም ብሎ አረጋጋው፡፡ ‹‹እናቴ ሞታለች አይደል?›› ሲል አባቴ የሚፈራውን ጥያቄ ጠየቀው፡፡ አባቴ መልሱን አጥቶት ዝም አለ፡፡ ‹‹ንገረኝ›› አለው፡፡ ‹‹ለምን ጠየቅከኝ›› አለው አባቴ፡፡ ‹‹ኤርምያስ እናትህ ሞታለች አለኝ›› አለና አለቀሰ፡፡
አባቴ የሚያደርገው ጨነቀው፡፡ ምን ይበለው፡፤ አሁን ከእውነት ጋር ተፋጠጠ፡፡ ጓደኛው እውነቱን እንዲነግረው አበረታታው፡፡ አባቴ ተረጋጋና እውነቱን መናገር ጀመረ፡፡ እናታችን ምን ዓይነት እናት እንደነበረች፣ እንዴት ልትሞት እንደቻለች፣ አሁን በገነት እንዳለች፣ ወደፊት እንደሚገናኙ ለመናገር ሞከረ፡፡ ወንድሜ በትንሽ ልቡ ያዳምጠው ነበር፡፡ ከዚያም ይዞን በጓደኛው መኪና ወጣ፡፡ ከዚያ ቀን ጀምሮ ለወንድሜ በጣም ይሳሳለት ነበር፡፡ ከሠፈር ልጆች ጋር እንዳይገኛኝ ብሎ ሌላ ትምህርት ቤት አስገባው፡፡
እንዲያውም እኛ ራሳችን ለአባታችን ፈተና ነበርን፡፡ ይህን ለምን በላህ፣ ይህን ለምን ጠጣህ፣ ይህን ለምን ለበስክ፡፡ ትታመማለህ፣ ትሞትብናለህ፣ እንዲህ ትሆናለህ ፣ እንዲያ ትሆናለህ እያልን ነጻነቱን የሚገፍ ቁጥጥር እናበዛበት ነበር፡፡ እርሱም እኛን ለማስደሰት ነጻነቱን ሳይቀር ይሠዋልን ነበር፡፡ አሁን ሳስበው ይቆጨኛል፡፡
እኔን ሴት አድርጎ ያሳደገኝ አባቴ ነው፡፡ ስለ ሴትነት፣ ስለ ወጣትነት፣ ስለ ፍቅረኛ፣ ስለ የወር አበባ፣ ስለ ሞዴስና ስለ ሌላውም ቁጭ አድርጎ ያስተማረኝ አባቴ ነው፡፡ አባቴ ለእኔ አባቴም፣ እናቴም፣ ጓደኛዬም፣ መምህሬም ነው፡፡ እጅግ ሩኅሩኅ፣ ለልጆቹ የሚያስብ፣ ለልጆቹ ራሱን የሠዋ፣ መልካሙን የወጣትነት እድሜውን ለእኛ ለልጆቹ ሲል እንደ ሽማግሌ ያሳለፈ፤ ሰፍሳፋና ጭንቀታም ነው አባቴ፡፡ እኔ ውስጥ እርሱ አለ፡፡ በራሴ እንድተማመን፣ የማስበውን እንድሆን፣ በትክክለኛውም መንገድ እንድጓዝ፣ ዛሬም በፊታችሁ እንድቆም ያደረገኝ ነው አባቴ፡፡ ልጅ ለማሳደግ ሲል ልጅ ሆኗል፡፡ ሴት ልጅን ለመቅረጽ ሲል ሴት ሆኗል፡፡ ቤቱን ለማስተዳደር ሲል እማወራ ሆኗል፡፡ ለኛ ሲል ጨዋታውን፣ ዕድገቱን፣ ጓደኞቹን፣ የውጭ ዕድሎቹን፣ የትምህርት ዕድሎቹን፣ የዝውውር ዕድሎቹን ሁሉ አምክኗል፡፡
ለዚህ ነው፡፡ ይህች ሀገር ‹‹እናት ሀገር›› እንደምትባለው ሁሉ ‹‹አባት ሀገር››ም መባል አለባት ብዬ የምከራከረው፡፡ በአዳራሹ የነበረው ሰው ሁሉ ማራቶናዊ በሆነ ጭብጨባ አጀባት፡፡
© ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት የወጣ ነው፤ በተመሳሳይ ሚዲያ መጠቀም አይፈቀድም