የዘንድሮ የፋሲካ ዓውደ ዓመት ገበያ በርካታ ሸማቾችን የተፈታተነ ነው
(ሪፖርተር) — የዘንድሮ የፋሲካ ዓውደ ዓመት ገበያ በርካታ ሸማቾችን የተፈታተነ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የሳምንቱ መገባደጃ ድረስ እንደ ወትሮው የሞቀ ገበያ አልተስተዋለም፡፡ በተለይ የቅቤ ዋጋ ከመጠን በላይ መናር ተጠቃሽ ይሆናል፡፡
የዘይት፣ የስኳር፣ በቅርቡም የዱቄት ዋጋ መወደድና የአቅርቦት እጥረት ሲያጉላላው የነበረው ሸማቾች፣ ለዓውደ ዓመት የሚፈልጋቸውም ዕቃዎች ዋጋ ማሻቀብ የዘንድሮን የበዓል ገበያ አቀዛቅዞታል፡፡ በተለያዩ ገበያዎች መመልከት እንደተቻለውም በቅቤ ዋጋ መጨመር ምክንያት አብዛኛው ሸማች ግማሽ ኪሎና ከዚያ ያነሰ መጠን ለመግዛት መገደዱንም ታዝበናል፡፡ በግና ዶሮ ለመግዛት የወጡ ሸማቾች በዋጋ ጭማሪው እየተደናገጡ በአብዛኛው ሳይገዙ ሲመለሱ ይታዩ ነበር፡፡ የሚገዙትም ቢሆኑ በዋጋው መናር በጣም ሲማረሩ ይታያሉ፡፡