አቡጊዳ – ፌዴሬሽኑ ከዚህ በፊት ብርቱካንን የክብር እንግዳ እንድትሆነ የወሰነዉን ዉሳኔ በድጋሚ አጸና !
የሰሜን አሜሪካ የስፖርት ፌዴሬሽን ቦርድ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ አትላንታ በሚደረገዉ የስፖርት ዝግጅት ላይ የክብር እንግዳ እንዲሆኑ ከዚህ በፊት የወሰነዉን ዉሳኔ በድጋሚ አጸናዉ።
ቦርዱ ወ/ት ብርቱካን የክብር እንግዳ እንድትሆነ ከወሰነ በኋላ፣ ጥቂት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴዉ አባላት፣ ከድርጅቱ ሕገ ደንብ ዉጭ፣ የቦርዱ ዉሳኔ እንደተለወጠና ወ/ት ብርቱካን የስፖርት ዝግጅቱ የክብር እንግዳ እንደማይሆኑ የሚገልጡ መግለጫዎችንና ቃለ መጥይቆችን ይሰጡ እንደነበረ፣ በዚያም የተነሳ ከኢትዮጵያዉያን ከፍተኛ ተቃዉሞ እንደተነሳ ይታወቃል።
በተለይም በአትላንታ የሚኖሩ የሲቪክ ማሃበራት መሪዎችና ታዋቂ ኢትዮጵያውያን፣ የቦርድ አባላትን ሲያነጋገሩና የተፈጠረዉ ዉዝግብ በዉይይት እንዲፈታ ዉስጥ ዉስጡን ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ የነበረ ሲሆን፣ በተለይም ቦርዱ እንደገና ተሰብስቦ በድርጅቱ ሕገ ደንብ መሰረት ዴሞክራቲካሊ ዉሳኔዎችን ካላሳለፈ፣ ፌዴሬሽኑ ትልቅ ችግር ዉስጥ እንደሚገባ ያስጠነቅቁ እንደነበረ ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸዉ የደረሰን ዜና ያመለክታል።
«ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የክብር እንግዳ ትሁን አይደለም የምንለዉ። ነገር ግን ወ/ት ብርቱካን የክብር እንግዳ እንድትሆን በስብሰባ፣ በድምጽ እንደተወሰነዉ ሁሉ፤ ቦርዱ ተሰብስቦ ድምጽ ሰጦ የወሰነዉን ዉሳኔ መሻር ሳይሽር ዉሳኔዉ ሊገለበጥ አይችልም። ጥቂቶች ፣ በምን ሁኔታ እንደተረገ በማይታወቅበት ሁኔታ፣ የቦርዱ አባላት ሳያውቁት፣ በቦርዱ ስም ውሳኔዎችን መወሰን አልነበረባቸዉ» ያሉን አንድ የአትላንታ ነዋሪ፣ ጉዳዩ የሕግና የተጠያቂነት ጉዳይ እንደሆነ አስረድተዋል።
ከብዙ ጠንካራ የቦርድ አባላት ግፊት በኋላ፣ ቦርዱ ቅዳሜ ኤፕሪል 16 ቀን ስብሰባ ያደረገ ሲሆን ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የክብር እንግዳ እንድትሆን ከዚህ በፊት በወሰነዉ ዉሳኔ ዙሪያ፣ በሰፊዉ ዉይይት እንዳደረገ ምንጮቻችን ይገልጻሉ። የቦርድ አባላት እያንዳንዳቸዉ በድጋሚ ድምጽ እንዲሰጡ ተጠይቀዉ፣ ከዚህ በፊት የወሰኑትን ዉሳኔ በድጋሚ በማጽደቅ፣ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የፌዴሬሽኑ የክብር እንግዳ ሆነዉ እንደሚጋበዙ አረጋግጧል። ምንጮቻችን እንደዘገቡት፣ ቦርዱ ዉሳኔዉን የወሰነዉ በሙሉ ድምጽ ሲሆን፣ ስብሰባዉም በሰላም በፍቅር በወንድማማችነት፣ ይቅር በመባባል እንደተጠናቀቀ ለማወቅ ችለናል።
የፌዴረሽኑ ቦርድ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን የክብር እንግዳ እንድትሆን ቢጋብዝም ለትምህርትና ለሕክምና በአሜሪካን አገር የሚገኙት ወ/ት ብርቱካን፣ ግብዣዉን ይቀበሉት አይቀበሉት ግን ገና የሚታወቅ ነገር የለም። ወ/ት ብርቱካን ለሃያ ወራት ከፍተኛ የአካልና የስነ ልቦና ቶርቸር ከደረሰባቸዉ በኋላ፣ የግላቸዉን ጊዜ መዉሰድ እንደሚፈልጉ ማሳወቃቸዉ፣ ከአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበርነታቸዉም በፍቃዳቸዉ መልቀቃቸው ይታወሳል።