የማጥቃት ዘመቻው ተጀምሯል፤ ሁሉም ለፍልሚያ ይታጠቅ!!!
የመለስ ዜናዊ አገዛዝን ለማስወገድ የሚደረገው የተባበረ የማጥቃት ዘመቻ ሚያዝያ 1 ቀን 2003 ዓም በሰሜን አሜሪካ ተጀመረ። የመለስ ዜናዊ ምስለኔዎች ሚያዝያ 1 እና 2 በሰሜን አሜሪካ የተለያዩ ከተሞች ስለ አምስት ዓመቱ “የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ” ለመስበክ እንዲሁም “በአባይ ግድብ” እንቁልልጭ ኢትዮጵያዊያንን በማማለል ገንዘብ ለመሰብሰብ ያደረጉት ሙከራ ከሽፎ የህዝባዊ አመጹ ክብሪት ተጫረ። መለስ ዜናዊ የኢትዮጵያዊያንን ትኩረት ለመሳብ ይረዱኛል ብሎ በከፍተኛ ወጪ ያዘጋጃቸው ስብሰባዎች በተገላቢጦሽ የህዝባዊው አመጹ ጅማሮ ማብሰሪያ ሆኑ።
በዋሽንግተን ዲሲ፣ ሎስአጀለስ፣ ሚኒያፓሊስ፣ ቶሮንቶ አትላንታ፣ ዴንቨር … የትግራይ ገዢ ጉጅሌ አባላትና ምስለኔዎቻቸው ለዓመታት አይተውት የማያውቁት የቁጣ መዓት ወረደባቸው። በአባይ ግድብ ዜና ይጨፍራል ያሉት ህዝብ “በባድመ፣ በምርጫ፣ በእርዳታ እህል ያልታመነ በአባይ ወንዝ ልማት አይታመንም” አላቸው። ቦንድ ለመግዛት ይሸቀዳደማል ብለው ተስፋቸውን የጣሉበት ዲያስፖራ “በላባችን ያገኘንውን ገንዘብ ለስዊዝ ባንክ አንሰጥም” አሏቸው። “አሁንስ መለስ ጀገነ” ይላሉ የተባሉ ሰዎች “የመለስ አገዛዝ በቃ!” አሉ።
ኢትዮጵያዊያን “በቃ!!! ገዬ!!! ይአከል!!! አሎኒ!!! ዲታህ!!! ወጣንደም!!! በስ!!! ጉደስ!!!” ሲሉ በአንድነት ጮኹ፤ ጨፈሩ። ቀድሞ በጋራ ተሰልፈው የጋራ ተቃውሞ በጋራ ለማሰማት ይቸገሩ የነበሩ ወገኖች በአንድነትና በጋራ “የመለስ አገዛዝ በቃን” ሲሉ መስማት ኢትዮጵያዊያን ያኮራ፤ መለስና አሽከሮቹን ግን በእጅጉ ያሸማቀቀ ክስተት ሆነ።
በግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ እምነት ሚያዝያ 1 እና 2 በሰሜን አሜሪካና የታዩት የተደራጁ ህዝባዊ ተቃውሞዎች የአገር አቀፉ ህዝባዊው ተቃውሞ መጀመሪያ ናቸው። ከእንግዲህ ድል ሳይጨበጥ ወደ ቤት መመለስ የለም። በጅማሮው እለት የታየው የአንድነትና የእልህ ስሜት ተጠናክሮ ከቀጠለ፤ በውጭ አገራት ያለው ኢትዮጵያዊ በያለበት በዚህ መልክ ከበረታ፤ ነገ ትግሉ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚዘልቅ እና ውጤታማም እንደሚሆን እርግጠኛ መሆን ይቻላል።
ከእንግዲህ የጥቃት ዘመቻችንን ለማፋፋም የወያኔ ሹማምንት ስብሰባ እስኪጠሩ መጠበቅ የለብንም። ከመለስ አገዛዝ ጋር እየነገዱ ያሉ የንግድና የኮንስትራክሽን ኩባንያዎችን፤ የትምህርት ተቋማትንና ታዋቂ ሰዎችን እያፈላለግን ከመለስ ዜናዊ አምባገነን ሥርዓት ጋር የሚደርጉትን ግንኙነት እንዲያቋርጡ ማስገደድ ይኖርብናል። መለስ ዜናዊና ወንጀለኛ ባልደረባዎቹ ለፍርድ የሚቀርቡበት ሁኔታ ማመቻቸት ይገባል። ጥቃታችንን በሁሉም መስኮች ማጠናከር ይገባናል። ከእንግዲህ ማፈግፈግ የለም። የጥቃት ዘመቻው ተጀምሯል። ሁሉም ለመጨረሻ ፍልሚያ ይታጠቅ!!!
የመለስ ዜናዊ ዘረኛ አገዛዝ በቅቶናል፤ አንገሽግሾናል!!!
በቃ!!! ገዬ!!! ይአከል!!! አሎኒ!!! ዲታህ!!! ወጣንደም!!! በስ!!! ጉደስ!!!