«የምርጫውን ውጤት ሕዝቡ ተቀብሎታል» አምባሳደር ቡዝ
እስክንድር ነጋ (አዲስ አበባ)
ቻይና ሰራሽ እስክሪብቶዬን ከገዛኹት ሁለት ቀናት እንኳን አላስቆጠርኹም፡፡ ገና ከወዲሁ እየተቆራረጠ ግን ትዕግስቴን እየተፈታተነው ነው፡፡ በዘመኑ የአራዳዎች ዘይቤ «ሙዴ» ሊበላሽ አፋፍ ላይ እየተንገዳገደ ነው፡፡
በሌላ በኩል፣ የአምባሳደር ቡዝ ቃለ–ምልልስ አለብኝ፡፡ ለሁለተኛ ሳምንት መዝለቁ ምቾት አልሰጠኝም፡፡ አቦ! ስንት የሚፃፍለት ነገር እያለ! ስለሚሊኒየሙ ግድብ ምን ተነካ? የእኔንም ሆነ የብዙ ሰዎችን ስሜት እየኮረኮረ ያለ ጉዳይ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ብቻውን እየጋለበው ነው፤ እያተረፈበትም ነው፡፡ ቅዳሜና እሁድ በአሜሪካ ስለተደረጉት ፀረ–ኢሕአዴግ ሰላማዊ ሰልፎች አንዲት ጦማር ብሰንቅ ነፍሴ በደስታ ትውተረተር ነበር፡፡ የብዕሬ ቱሩፋት የሚሊዮኖችን የታፈነ ስሜትም ትኮረኩር ነበር ብዬ አስባለኹ፡፡