ከአንድ ዘር የተውጣጣ የገዢ መደብ ለመፍጠር ሌት ከቀን የሚሰራው የወያኔ ቡድን ለኢትዮጵያችን መልካምን ለማድረግ አይቻለውም!
ከዝግጂት ክፍላችን
በዘረኛውና አምባገነናዊው የወያኔ አገዛዝ ቁጥጥር ስር የምትገኘው አገራችን ኢትዮጵያ ከሰሞኑ ብዙ የድህነት ሽልማቶችን ተቀብላለች።
ዴሞክራሲ እና እኩልነትን የማስፈን ጭንብሎቹ የወደቁበት ዘረኛ አገዛዝ ህልውናውን ለማስጠበቅ ሲል “ልማት ልማት” የሚለውን ዘፈን መዝፈን እና ማስዘፈን ከጀመረ እንደሰነባበተ እናውቃለን። በተለይም የምርጫ 97 ሽንፈቱን ተከትሎ ክፉኛ የታመመው አገዛዝ አገሪቱ የሌላትን እና በየመንግስት ባንኩ ጥረው ግረው ያገኙትን ገንዘብ ካስቀመጡ ኢትዮጵያውያን የበዘበዘውን ገንዘብ በንግድ ድርጂት ስም ላስመዘገባቸው የራሱ ድርጂቶች በማበደር አዲስ አበባን ህንፃ በህንፃ ካደረገ በኋላ፤ እነዚህ ሰው ሰራሽ የድንጋይ ክምሮች የአንድን አገር እድገት ለብቻቸው የሚገልጹ ይመስል፤ እንደ ልማት ማስረጃ አድርጎ ሲያስነግርላቸው እንደቆየ እናውቃለን።
ዘረኛው አገዛዝ ፈርዶበት ግን የሰለጠኑ አይኖች ሞልተው ኖሯል፤ ከህንፃዎቹ በስተጀርባ እየሄዱ የሚፈትሹ እየተበራከቱ መጡ። ወያኔ የእድገት ወሬውን የሚያቆመው ከተቀቀሉ ቁጥሮች በተሰራ መሰረት ላይ መሆኑም ተጋለጠ። ይሁን እንጂ “የሌባ አይነ ደረቅ መልሶ ልብ ያድርቅ” እንዲሉ…እርቃኑን በመውጣቱ መግቢያ ጉድጓድ ያጣው አገዛዝ ባልሞት ባይ ተጋዳይነት የልማት ከበሮውን ማስደለቁን ቀጥሎበታል።
ከኢትዮጵያ ህዝብ በተዘረፈ ገንዘብ ከርሳቸውን እየሞሉ በአለማችን አራት ማእዘናት ተሰራጭተው ያሉ የወያኔ ጭፍሮችም ውሸት ሲደጋገም እውነት ይሆናል በሚል እምነት “እድገት እድገት እድገት” እያሉ ይዘምራሉ። የወያኔ የእድገት ወሬ በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ዘንድ እንደ ቀልድ የሚታይ ጉዳይ ነው። ከጥቂት አመታት በፊት በግ እያረደ የሚፈስከው ቤተሰብ ሁለት ኪሎ ስጋ መግዛት ተስኖት እራሱን ሲያገኝ፤ ሽሮም ብትሆን በየቀኑ በልቶ ማደርን የለመደው ደግሞ ምግብ በፈረቃ መብላት እንደጀመረ እያወቀው “ልማት” የሚሉት ነገር ተቃራኒ ትርጉም ከሌለው በስተቀር ስላቅ እንደሆነ ደህና አድርጎ ያውቀዋል።
ከደጋፊዎቹ እና አድርባዮች በስተቀር የወያኔን የልማት መዝሙር ተቀባብለው ሲዘምሩ የከረሙት ጥቂት የዋሆች እና አይናቸውን ጨፍነው ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ አገዛዙን ለመደገፍ የሚፈልጉ አንዳንድ አገራት እና አለማቀፍ ተቋማት ናቸው። አሁን አሁን ግን አለማቀፉ ማህበረሰብ አይኑን እንደጨፈነ መቀጠል ወደማይችልበት ደረጃ ላይ እየደረሰ ነው። የወያኔን የተቀቀሉ ቁጥሮች እያጋለጡ ያሉ አንዳንድ ምእራባውያን ተመራማሪዎች ብቅ ብቅ እያሉ ሲሆን፤ ይህ ደግሞ በዚሁ የሚቆም አይሆንም። የዘረኛው አገዛዝ ዴሞክራሲያዊነት ሃሰት መሆኑ ተጋልጦ አብዛኛው አለማቀፍ የመረጃ አውታር እንዳውገዘው ሁሉ የኢኮኖሚ ውሸቱም ሙሉ በሙሉ እርቃኑን የሚወጣበት ቀን እየተቃረበ ነው።
አገራችን ኢትዮጵያ በወያኔ አገዛዝ ቁጥጥር ስር በአለማችን ላይ እጅግ ደሃ ከሚባሉት አገራት ውስጥ አንዷ እንደሆነች በቅርብ ጊዜ ካሳዩት ሪፖርቶች ውስጥ አንዱ እንግሊዝ አገር በሚገኘው ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ትብብር ተዘጋጅቶ ይፋ የተደረገው ነው።
“መልቲ ዳይሜንሺናል ፖቨርቲ ኢንዴክስ” ወይም ዘርፈ ብዙ የድህነት መመዘኛ የሚባለውን አዲስ ዘዴ በመጠቀም በተደረገው በዚህ ጥናት፣ 90 በመቶ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ደሆች እንደሆኑና ይህም በክፋቱ ከአለም ሁለተኛ ደረጃ መያዙን አስታውቋል። አንደኛውን ደረጃ የያዘችው ምእራብ አፍሪካዊቷ አገር ኒጀር ስትሆን መንግስት አልባዋ ሶማሊያ እንኳን በየአመቱ አስር በመቶ እድገት ተመዝግቦባታል ተብሎ መለስ ዜናዊና ጭፍሮቹ ከሚነግሩን ኢትዮጵያችን ተሽላ ተገኝታለች።
ከዚህ ቀደም በስራ ላይ ይውሉ የነበሩ የድህነት መመዘኛዎች፣ የግለሰቦችን የቀን ገቢ ብቻ ከግምት ውስጥ የሚያስገቡ ሲሆኑ፤ አዲሱ መመዘኛ በሰው ልጅ ህይወት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሊያደርሱ የሚችሉ ዘርፈ ብዙ ጉድለቶችን ከግምት የሚያስገባ ነው። ከነዚህም ውስጥ የትምህርትና የጤና ጥበቃ ሁኔታ፤ እንዲሁም የአጠቃላይ ኑሮ ደረጃን ይለካል። በዚህ መሰረትም፥ ከአስር ኢትዮጵያውያን ዘጠኙ ድሆች ናቸው ሲል ሪፖርቱ ደምድሟል።
ጥናቱን ያካሄደው ተቋም ለምርምሩ የተጠቀመው ዳታ ወይም መረጃ የዛሬ አምስት አመት የተሰበሰበ መሆኑንም ገልጿል። ባለፉት አምስት አመታት፣ በተለይም ከምርጫ 97 በኋላ የወያኔ አገዛዝ ስራ ላይ ያዋለውን ሃላፊነት የጎደለው የገንዘብ ፖሊሲ ተከትሎ፣ ቁጥራቸው የማይታወቅ ኢትዮጵያውያን ቀድሞ ከነበረው ወደ ባሰ ድህነት መሸጋገራቸውን ከግምት ውስጥ ስናስገባ፣ ይህ ድህነት በምን ያህል እጅ እና በምን ያህል ጥልቀት ጨምሮ ይሆን ብለን መጠየቃችን አይቀርም።
ኒውስዊክ የተባለው ታዋቂ የአሜሪካ መጽሔት ባለፈው ሳምንት ባወጣው ሪፖርት ደግሞ ለነዋሪዎቻቸው በሚሰጡት ምቾት እና እድል ላይ አንድ መቶ የአለም አገራት አወዳድሮ ኢትዮጵያን 94ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል።
መጽሔቱ፥ “ዛሬ ብትወለድ፥ የትኛው አገር በጤና፣ በደህንነት፣ በብልጽግና፣ እና በእድገት የተሞላ ኑሮ እንዲኖርህ ከፍተኛውን እድል ይሰጥሃል?” የሚለውን ጥያቄ ይዞ በመነሳት ንጽጽሩን እንዳካሄደ ገልጿል። ትምህርትን፣ ጤናን፣ የኑሮ ጥራት ደረጃን፣ የኢኮኖሚ ተወዳዳሪነትን፣ እና የፖለቲካ ሁኔታን እንደማነፃጸሪያ ነጥቦች ተጠቅሟል። ለምሳሌ የኑሮ ጥራት ደረጃን ለመመዘን ከተጠቀመባቸው ቁልፎች ውስጥ አንዱ “በቀን ከሁለት ዶላር በታች” የሚያገኙ ዜጎች ቁጥር ሲሆን፤ 77.57% የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ከዚህ እንደሚመደቡ አስረድቷል። ይህ ሪፖርት አገራቱን ለማነፃጸር የተጠቀመው መረጃ እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር 2008 እና 2009ን የሚሸፍን እንደሆነም ታውቋል።
በዚህ ሪፖርት መሰረት የምግብ ዋስትና እጥረት የከፋ ደረጃ ላይ ካለባቸው አስር የአለም አገሮች ውስጥ ኢትዮጵያ አንዷ ነች።
ይህንን ያለው ብሪታንያ በሚገኝ እና ሜፕልክሮፍት በተባለ ድርጅት፣ ከተባበሩት መንግስታት የአለም የምግብ ፕሮግራም ጋር በመተባበር፣ የሚዘጋጀው አመታዊ የምግብ ዋስትና አደጋ መለኪያ ሪፖርት ነው። ሪፖርቱ ወደ ድምዳሜ ለመድረስ አስራ ሁለት መመዘኛዎችን የሚጠቀም ሲሆን፤ ከነዚህም ውስጥ የእህል ምርት፣ የነፍስ ወከፍ ገቢ፣ የግብርና እና የማከፋፈያ መሰረተ ልማት አውታሮች ጥራት፣ ግጭቶች፣ እንዲሁም የመንግስት ብቃት የሚሉት ይገኙበታል። በዚህም አኳኋን በአለም ላይ አደገኛ የምግብ ዋስትና እጥረት ካለባቸው አገሮች ውስጥ ኢትዮጵያን ስድስተኛ ደረጃ ላይ አኑሯታል።
ይህ ሪፖርት የተሰራው ወያኔ የሚያወጣቸውን የእህል ምርት ቁጥሮች ተጠቅሞ ይሁን አይሁን ግልጽ አይደለም። ተጠቅሞ ከሆነ አደጋው የከፋ እንደሆነ መገመት ይችላል። ምእራባውያን ተመራማሪዎች ጥያቄዎች እያነሱ ያሉበት ዋና ጉዳይ ወያኔ በግብርናው ዘርፍ አለ የሚለው እድገት እና የሚሰጠው ቁጥር ነው።
በሌላም በኩል ጋላፕ የተባለ የጥናት ተቋም ባሰባሰበው መረጃ መሰረት እድሉ ቢቀርብላቸው 46 በመቶ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን ጥለው እንደሚሄዱ ገልጿል። አንዳንዶች ይሄ ከእውነተኛው ቁጥር እጅግ ያነሰ ነው ይላሉ።
የአንድን አገር ውስጣዊ ሁኔታ ከሚገልጹ ነገሮች ውስጥ አንዱ ሰዎች ወደ ውስጥና ውጪ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ነው። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎች አገር ጥለው የሚሰደዱ ከሆነ፣ በዛ አገር ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እንዳሉ ጠቋሚ ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው የፖለቲካ አፈና እና ድህነት የተነሳ ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ኢትዮጵያውያን በየአመቱ ቀዬያቸውን እየጣሉ እንደሚሰደዱ ይታወቃል። የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን በሰኔ ወር ባወጣው ሪፖርት፥ እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር በ2009 ብቻ 42500 ኢትዮጵያውያን በተለያዩ አገራት የፖለቲካ ጥገኝነት እንደጠየቁ መግለጹ ይታወሳል። ይህ ቁጥር እንግዲህ የፖለቲካ ጥገኝነት የጠየቁትን ብቻ የሚያካትት ነው። ስራ ፍለጋ ወደተለያዩ አገራት ህጋዊ እና ህገ-ወጥ በሆነ መንገድ የሚሰደዱትን አያካትትም።
ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በአገራቸው ይመሩት የነበረው ኑሮ ምን ያህል እንዳንገሸገሻቸው የሚታወቀው ደግሞ ሌላ አገር ለመድረስ ሲሉ ሊያልፉበት የሚፈቅዱት መከራ ነው። የተሻለ ኑሮን ተስፋ እስካዘለ ድረስ ምንም አይነት መከራ ይሻላል ብለው የወሰኑ ይመስላሉ። ኑሮ በኢትዮጵያ ተስፋና ደህንነት የለውምና፤ ወደ ጣሊያን ለመሻገር በእግር ሲኳተን አሸዋ ውስጥ ሰጥሞ መቅረት ይሻላል።
በየቀኑ ዜና ለሚከታተል ሰው፥ በሆነ አገር ስለሚንከራተቱ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የሚከተለውን መስማት የተለመደ ነው።
በየእለቱ ሊባል በሚቻል ሁኔታ የዜና ድረ-ገፆች ሲከፈቱ የሚታዩት ርእሶች፥ “ወደ የመን ሊያቋርጡ ሲሞክሩ የነበሩን ኢትዮጵያውያን ተሸክማ የነበረች ጀልባ ሰጠመች፤ የግብጽ ፖሊስ ወደ እስራኤል ለማቋረጥ ሲሞክር የነበረን ኢትዮጵያዊ ተኩሶ ገደለ፤ ከሁለት ሺህ የሚበልጡ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በታንዛኒያ እስር ላይ ይገኛሉ፤ ኢትዮጵያውያን ኢራቅ ውስጥ ስራ ይፈልጋሉ፤ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በደቡብ አፍሪካ ተደበደቡ፤ ኢትዮጵያዊት ሰራተኛ በአንድ የመካከለኛ ምስራቅ አገር ተገደለች፤ የመን 150 ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ወደ አገራቸው መመለሷን እና የኬንያ ፖሊስ በአንድ ቤት ውስጥ ታጭቀው የነበሩ 90 ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ማሰሩን ገለጸ የሚሉ እና የመሳሰሉት ናቸው።”
የወያኔ ባለስልጣናት እና ደጋፊዎች አገራቸውን ጥለው የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያንን በተመለከተ አስተያየቶች ሲሰጡ፥ ‘’ሆዳቸውን በፈረንጅ ምግብ መሙላት አምሯቸው ነው’’ ይላሉ። ‘’እድገት አምጥተናል፣ ሚሊዮኔር ገበሬዎች አፍርተናል’’ የሚሉን ሰዎች ዞር ብለው በቂ ምግብ አገር ቤት እንደሌለ በማመን እራሳቸውን የሚያጋልጡበት ምክንያት ግልጽ ባይሆንም፤ ምግብ ፍለጋ የትም መሄድ ግን ሃጢያት አይደለም።
ምግብ ከሶስቱ የሰው ልጆች መሰረታዊ ፍላጎቶች ውስጥ አንዱ ነው። የሰው ልጅ እነዚህን ፍላጎቶቹን ለማሟላት ነፍሱን እና ክብሩን እስካልሸጠ እና ሌሎችን እስካልጎዳ ድረስ ምግብ ፍለጋ መሰደድ ወንጀልም ሃጢያትም አይደለም። የሚያሳፍረው ግን ዜጎች ምግብ ፍለጋ ጥለዋት ይሚሄዷትን አገር ሃብትና ገንዘብ ለግል ጥቅማቸው እየቦጠቦጡ ስደትን ማባባሱ ነው።
ዋናው ጥያቄ መሆን ያለበት ኢትዮጵያ ውስጥ ለምን በቂ ምግብ የለም የሚለው ነው? ኢትዮጵያ ውስጥ በቂ ትምህርት ለምን የለም? በቂ ስራስ ለምን የለም? በቂ እድልስ ለምን የለም? ፖለቲካዊ መብትስ ለምን አይከበርም?
እነዚህን ጥያቄዎች ለአገራችን የሚወግን እና ከህዝብ የፈለቀ፤ በህዝብ ለህዝብ የተሰራ ስርአት እስኪኖረን ድረስ መልስ አናገኝላቸውም ብቻ ሳይሆን መጠየቅም አንችልም። ሲጀመር ሊዘርፍ፣ ሊያስር፣ ሊገድል እና ሊያጠፋ ከመጣ ዘረኛ አገዛዝ ተጠያቂነትንም ሆነ ማንኛውንም አዎንታዊ ነገር መጠበቅ የዋህነት ነው። በወያኔ አገዛዝ ስር ልማት አለ የሚለው የአገዛዙ ወሬ ሃሰት መሆኑን ለማሳየት ብለን እንጂ ይህን ሁሉ የዘረዘርነው፤ ከዚህ አገዛዝ መልካምን ነገር እንጠብቃለን ለማለት አይደለም። ለዚህም ነው መከራችንና ስቃያችን እንዲያበቃ በተባበረ ክንድ ለዚህ ሰቆቃ የሚዳርጉንን ዘረኞች በትግላችን ማስወገድ ቅድሚያ ሊሰተው የሚገባ ነው የምንለው።
ጅቦች የበጎች እረኞች እንዲሆኑ ተፈጥሯቸው እንደማይፈቅድላቸው ሁሉ፤ ከአንድ ዘር የተውጣጣ የገዢ መደብ ለመፍጠር በርትተው የሚሰሩት የወያኔ መሪዎችም ለኢትዮጵያችን መልካምን ለማድረግ አይቻላቸውም!