ከጣራ እስከ ጉዛራ

(የመጨረሻው ክፍል)

የኢፋግ የባርያ ንግድ ገበያ ዋርካ

‹ላላዋቂ ፎገራ ዱሩ ነው› ሲባል ሰምታችሁ ከሆነ አሁን ስላለሁበት ቦታ እየተነገራችሁ ነው ማለት ነው፡፡ ፎገራ በደቡብ ጎንደር፣ ዓባይን ከተሻገራችሁ በኋላ ጣናን ባሻገር እያየ የሚገኝ ሰፊ ሜዳ ነው፡፡ ለዚህ ነው ‹ላላዋቂ ፎገራ ዱሩ ነው› የሚባለው፡፡ ፎገራ አለቃ ገብረ ሐናን የመሰሉ ሊቃውንትን ያፈራ ታዋቂ ቦታ ነው፡፡ እዚህ ናበጋ ጊዮርጊስ ነው አለቃ ትውልዳቸውም፣ ዕረፍታቸውም፡፡
ፎገራ ውኃ ገብ ረግረግ መሬት በመሆኑ ከአፍ እስከ ገደፉ በሩዝ ምርት ተሸፍኗል፡፡ አንዳንዶች እንዲያውም ‹ሕንድ በኢትዮጵያ› እያሉ ይጠሯታል ፎገራን፡፡ የፎገራ ገበሬ የነቃ የበቃ ገበሬ ነው፡፡ ፎገራ መንደር ውስጥ ስትገቡ የምታገኟቸው የቴክኖሎጂ ምርቶች ገጠር መሆናችሁን ያስረሷችኋል፡፡ ንግግራቸው አማርኛ፣ አለባበሳቸው ወደ ኦሮምኛ ይጠጋል፣ ፎገራዎች፡፡ በመንደሩ ውስጥ ትግርኛ፣ አማርኛና ኦሮምኛ ተቀላቅሎ ሲነገር ትሰማላችሁ፡፡

 ለምን? አትሉም፡፡ ፎገራ በጥንቱ የሲራራ ነጋዴዎች መንገድ የምትገኝ ቦታ ናት፡፡ ከጣና በስተ ሰሜንም ሆነ ከጣና በስተ ደቡብ አቋርጠው የሚያልፉ ሁሉ በፎገራ መሔዳቸው ግድ ነው፡፡ ፎገራ ደቡቡን ኢትዮጵያ ከሱዳን ገበያና ከቀይ ባሕር ወደቦች ጋር የምታገናኝ የንግድ መናኸርያ ነበረች፡፡

ልጥጥ ያለው ሜዳዋ ለአጋሰሶች አመቺ መሆኑ፣ የከብቶች መኖ ለማግኘትም ቀላል መሆኑና ውኃ በአካባቢው መኖሩ ለነጋዴዎች ምቹ የማረፊያ ቦታ አድርጓት ነበር፡፡ ከዚያም በተጨማሪ የነገሥታቱ ቤተ መንግሥቶች በአካባቢዋ በመኖራቸው ለጥበቃ የተመቸች ሥፍራም ነበረች፡፡ በጎንደር የመጀመርያው ቤተ መንግሥት የሆነው የዐፄ ሠርጸ ድንግል የጉዛራ ቤተ መንግሥትም የሚገኘው እዚያው አለፍ ብሎ ነው፡፡ 
የፎገራ ሩዝ
በሩዝ ሰብል የተሞላውን የፎገራን ሜዳ አልፋችሁ ስትሄዱ
ሀገርሽ ወዴት ነው ብዬ ብጠይቃት
ከምከም ብላ ሳቀች ነገሩ ቢደንቃት
የተባለባትን ሊቦ ከምከምን ታገኛላችሁ፡፡ እዚህ ነው እንግዲህ ኢፋግ ያለችው፡፡
ኢፋግ በጥንቲቷ ኢትዮጵያ ዋነኛ ከነበሩት የባርያ ገበያዎች አንዷ ነበረች፡፡ በምዕራብ በለሳ በኩል ወደ ሱዳን በዚያውም ወደ ግብጽና ዓረብ ሀገሮች፣ በሰሜን ደንቢያ በኩል ደግሞ ወደ ትግራይና ኤርትራ፣ በዚያውም አድርጎ ወደ ዓረቡ ዓለም ይሻገሩ ለነበሩት ባሮች አንዷ ገበያ ነበረች- ኢፋግ፡፡
ከባሕርዳር ወደ ጎንደር የሚወስደውን መንገድ ተከትላችሁ፣ የፎገራን ሜዳ ካለፋችሁ በኋላ፣ ወደ ግራ ስትታጠፉ የኢፋግ ከተማ ትታያችኋለች፡፡ ወደ ውስጥ የሚያስገባው መንገድ አመቺ ነውና ባጃጆች እንኳን ሳይቀሩ ይጎበኟታል፡፡ ከተማውን በስተቀኝ አቋርጣችሁ ስታልፉ የምታገኙት ዕድሜ ጠገብ ዋርካ ነበር ዋነኛው የባርያ ገበያ ማዕከል፡፡
ዙርያውን በቤቶች ተከብቦ ዛሬ ተንቆ የተቀመጠው ዋርካ ለብዙዎች የሀብት ማከማች ለብዙዎች ደግሞ የልቅሶና የዋይታ ቦታ ነበረ፡፡ እንዲህ ዓይነት ታሪኮቻችን በሚገባ ተመዝግበውና ተጠብቀው መቆየታቸው ካለፈው ስሕተታችን እንድማር፣ እንዳንደግመውም ያደርገናል፡፡ እኛ ግን እንደዚያ አንመስልም፡፡ የኢፋግን የባርያ ገበያ ታሪክ ረስተነው ዛሬ በዘመናዊ ባርነት እኅቶቻችን እየተሸጡ የጥንቶቹ ባሮች ይሄዱባቸው ወደነበሩት ሀገሮች በመሔድ ላይ ናቸው፡፡
እዚያ በዋርካው አካባቢ ያገኘኋቸውን የሀገር ሽማግሌ ‹ኢፋግ ማለት ምን ማለት ነው?›› ብዬ ጠየቅኳቸው፡፡ እርሳቸውም ‹‹‹ይፋ ግፍ› ማለት ነው›› አሉኝ፡፡ እንዴት? ስል ነገሬን አስረዘምኩ፡፡ እርሳቸውም እንዲህ ተረኩልኝ፡፡ ‹‹በድሮ ጊዜ እዚህ ገበያ ላይ ከየሀገሩ በባርያ ፈንጋዮች እየተያዙ ባሮች ለገበያ ይመጡ ነበር፡፡ ታድያ ከመጡ በኋላ እንዳያመልጡ እዚህ ዋርካ ሥር ከዋርካው ጋር ታሥረው ቆመው ይውላሉ፡፡ ገዥውም እየመጣ እያየ መርጦ ይገዛ ነበር፡፡ ታድያ አንድ ክፉ ሰው ባሮችን ሰብስቦ በገመድ አሥሮ ሲያመጣ አንዱ ባርያ በረኃብ መንገድ ላይ ይሞትበታል፡፡ ጨካኝ ስለነበር ባርያውን ከመቅበር ይልቅ አብሮ አሥሮ አመጣውና እዚህ ዛፍ ሥር አቆመው፡፡ በኋላ ገዥ መጥቶ አሥሩንም ባሮች ገዝቶ ገንዘቡን ከሰጠ በኋላ ባሮቹን በገመድ እየጎተተ ሲወስዳቸው ያ ባርያ ዝንጥፍ ብሎ ወደቀ፡፡ እንዲህ ያለ ግፍ በአደባባይ ስለተሠራባት፣ ሬሳ ስለተሸጠባት ይፋግ ተባለች›› አሉኝ አዛውንቱ፡፡
በአካባቢው ስትቆሙ በዚያ ዘመን ሰው በሰው ላይ ሲሠራ የኖረው ግፍ በዓይነ ኅሊናችሁ ይመጣባችኋል፡፡ ሰው ሰውን ሲሸጥ፣ ሰውም ሰውን ሽጦ ሲተዳደር፡፡ ግን የባርያ ንግድ ቆሟል? ይህንን ነበር እኛ ስንጠያየቅ የነበረው፡፡ የገበያ ቦታውንና አሠራሩን ቀይሯል? ወይስ ቆሟል?
የኢፋግ ከተማ
የኢፋግን ከተማ ተሰናብተን ጉዟችን ወደ አዲስ ዘመን ከተማ ሆነ፡፡ አንዳንዶች ይህቺ ከተማ ‹አዲስ ዘመን› የተባለችው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ‹አዲስ ዘመን› ከመባሉ በፊት ነው ይላሉ፡፡ እንዲያ ከሆነ አዲስ ዘመኖች የቅጅ መብት ጥያቄ ማንሣት አለባቸው፡፡ የጎንደሩ ደብረ ብርሃን ሥላሴ ከሰሜን ሸዋው ደብረ ብርሃን ሥላሴ ‹ደብረ ብርሃን ሥላሴ›› የሚለውን ስም ሲወስድ ዐፄ ኢያሱ አድያም ሰገድ ለሰሜን ሸዋው ደብረ ብርሃን ሥላሴ ሁለት ሺ  መክሊት ወርቅ ከፍለው ነበር ይባላል፡፡ እንግዲህ ለአዲስ ዘመኖች መከራከርያ ማቅረቤ ነው፡፡
አዲስ ዘመን ከተማ ጥንት አሁን በነበረችበት ቦታ ላይ አልነበረችም ይባላል፡፡ የተመሠረተችው አሁን ጣራ ገዳም ካለበት ተራራ ሥር ነበር አሉ፡፡ ታድያ የከተማዋ ሴቶች ውኃ ሊቀዱም ሆነ እንጨት ሊሠብሩ እዚህ ተራራ ሥር ይመጣሉ፡፡ ወደ ገዳሙም ክልል ይገባሉ፡፡
ከእነዚህ እንጨት ሰባሪ እኅቶች መካከል አንዷ አንድ ቀን ወደ ገዳሙ ክልል ገብታ በነበረ ጊዜ ምናምን አደናቅፏት ከአንዱ የገዳሙ ሰው ጋር ትሰናከላለች፡፡ የገዳሙ ሰውም በፈጸሙት ድርጊት ተፀፅተው ራሳቸውን በሾተል ጃንደረባ ያደርጋሉ፡፡ ነገሩም ለገዳሙ መነኮሳት ኀዘን ይሆናል፡፡ መነኮሳቱ ነገሩን ይወያዩበትና ወደ አካባቢው ገዥዎች ያመራሉ፡፡ ‹‹ችግሩ እየተከሰተ ያለው ገዳምና ከተማ አብረው በመሆናቸው ነውና ከተማው ይነሣ›› ብለው ይጠይቃሉ፡፡ አገር ገዥዎቹም ጥያቄያቸውን ተቀብለው ከተማዋን ከጥንቱ ቦታዋ በማንሣት ዛሬ ያለችበት ቦታ ተከሏት፡፡ ስሟንም ‹‹አዲስ ዘመን›› አሏት ይባላል፡፡
እስኪ አዲስ ዘመንን እንለፋት፡፡
ወደ ጉዛራ ቤተ መንግሥት መግቢያ
ጉዟችንን ወደምናጠናቅቅበት እንፍራንዝ ወደሚገኘው ወደ ጉዛራ ቤተ መንግሥት፡፡ ጉዛራ ማለት በግእዝ መሰባሰቢያ ቦታ፣ የጉባኤ ቦታ ማለት ነው፡፡ ወደ እንፍራንዝ ከተማ ከመድረሳችሁ በፊት ወደ ቀኝ ስትመለከቱ ጉዛራን በጉብታው ላይ ጣናን ፊት ለፊቱ እያየ ታገኙታላችሁ፡፡ በመግቢያው ላይ ያለው ሰሌዳም ይህንኑ ይነግራችኋል፡፡ የአካባቢው ሰዎች በመኪና መግባት እንደሚቻል ይናገራሉ፡፡ እኛ ግን የገባነው በእግራችን ነው፡፡ እየታጨዱ ባሉት እርሻዎች መካከል እያቆራረጣችሁ ዙርያ ጥምጥም የሆነውን መንገድ መከስከስ ነው፡፡
ከአስፓልቱ የአንድ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ያለው የጉዛራ ቤተ መንግሥት የጎንደር መንግሥት መሥራች በሚባሉት በዐፄ ሠርጸ ድንግል (1556-1589 ዓም) ዓም አማካኝነት የተሠራ ነው፡፡ ንጉሡ በቦታው ቤተ መንግሥቱን እንዲያንጹ ያደረጓቸው የተለያዩ ምክንያቶች አሏቸው፡፡ ወደ ሰሜን የሚሄደው የንግድ መሥመር በዚያ የሚያልፍ መሆኑ፤ ጣና ሐይቅ ከፊቱ የተንጣለለ መሆኑ፤ አካባቢው ደጋ መሆኑና ከወባ በሽታ ነጻ መሆኑ፤ አካባቢው በእህል ምርት የታወቀ መሆኑ፣ ዋናው የወርቅ ገበያ ለነበረው ፋዞግ ቅርብ መሆኑና ሌሎችም ነበሩ፡፡
ቤተ መንግሥቱ የጎንደርን ቤተ መንግሥት መልክ ይዞ በጉብታ ላይ የታነጸ ነው፡፡ ፎቅና ምድር ቤት የነበረው ይህ ቤተ መንግሥት የንጉሡን እልፍኝ፣ የፍርድ አደባባይ፣ የግብር አዳራሽ፣ ማዕድ ቤትና ሌሎችንም ክፍሎች ይዞ ነበር፡፡ ቤተ መንግሥቱ ከድንጋይና ከእንጨት የተገነባ ሲሆን ከጎንደር ቤተ መንግሥት የሰባ ዓመት ቅድሚያ እንዳለው ይነገራል፡፡
የሚገርመው ነገር በጎንደር ዘመን የተሠሩት አብያተ መንግሥት ‹ጎ› የሚለውን ስም ተከትለው የተሠሩ መሆናቸው ነው፡፡ ጉዛራ፣ ጎርጎራ፣ ጎመንጌ፣ ጎንደር፡፡ ለምን ይሆን? ብዬ ጠይቄ ነበር፡፡ በቀድሞ ጊዜ ‹ጎ ይነግሥ› የሚል ንግር ስለነበረ ነው ብለውኛል፡፡ 
የጉዛራ ቤተ መንግሥት ከሩቁ ሲታይ
የጉዛራ ቤተ መንግሥት እንደሌሎቹ ሁሉ በሚገባ አልተያዘም፡፡ ራሱን ጠብቆ ለ400 ዓመታት ቢቆይም ከአሁን በኋላ እገዛ ሳያስፈልገው አይቀርም፡፡ ቤተ መንግሥቱ ከዛሬ ሃያ አምስት ዓመታት በፊት ከዚህ የተሻለ ይዞታ ላይ እንደነበር የአካባቢው ሰዎች ይናገራሉ፡፡ በአካባቢው የተደረገው የኢሕአዴግና የደርግ ውጊያ በቤተ መንግሥቱ ላይ የመፈራረስ አደጋ አስከትሎበታል፡፡ አሁን ያለውም ከዚያ የተረፈው ነው፡፡ 
ጉዛራ ቤተ መንግሥት ግድግዳ
ከጉዛራ እንውጣ፤ እናንተንም አካባቢውንም ተሰናብተን ወደ ጎንደር እናቅና፡፡ ሌላ ጊዜ ከዓባይ እስከ ደሴ በምሥራቅና ምዕራብ ጎጃም በኩል፣ በደቡብ ጎንደር ስማዳን አልፈን፣ በጨጨሆ በኩል በመቄት ወጥተን ዋድላና ደላንታን አቋርጠን ተመልሰን አዲስ አበባ የገባንበትን የ1700 ኪሎ ሜትር ጉዞ እተርክላችኋለሁ፡፡ እስከዚያው ደኅና ሰንብቱ፡፡