‹መግደል ደስ ይለኛል›
ሰሞኑን በኒውዮርክ በበጎ ፈቃድ በተሠማሩ የእሳት አደጋ ተከላካዮች ላይ እሩምታ የከፈተው ተኳሽ ይህንን ያደረገበትን ምክንያት ‹መግደል ደስ ይለኛል› ብሎ ነበር የገለጠው፡፡ በዚያው ዕለት በአንድ የዋና ቦታ ከልጆቼ ጋር ሄጄ ነበር፡፡ በዚያ የዋና ቦታ በውኃ የሚሠራ የልጆች መጨዋቻ ሽጉጥ የያዙ ሕጻናት በገንዳው ውስጥ ገብተው ልባቸው እስኪጠፋ ይጫወታሉ፡፡
‹አይ ኪል ዩ› ይለዋል አንዱ ሌላውን፡፡
‹‹ኖ ኖ›› ይላል ተገድለሃል የተባለው፡፡
‹ኖ ኖ ዩ ኦልሬዲ ዴድ› ይላል ‹ገዳዩ›፡፡
ገርመውኝ ጠጋ አልኩና አዋራቸው ጀመር፡፡
‹‹መግደል ጥሩ ነው እንዴ ልጆች›› አልኳቸው፡፡
‹‹አይ ላይክ ኢት›› አለኝ ‹ሽጉጡን› የያዘው ልጅ፡፡
‹‹መግደል ትወዳለህ›› አልኩት፡፡ ዝም ብሎ ያየኝ ጀመር፡፡
‹‹መግደልኮ መጥፎ ነው፤ ወንጀልም ነው›› አልኩት ድምጼ ሊጠፋ ደርሶ፡፡ አንድ ሰምቼው የማላውቀውን ፊልም ጠራልኝና ‹እዚያ ላይ አላየኸውም፤ እንትና እንትናን ሹት ሲያደርገው›› አለኝ፡፡
ልጆቻችን የሚያዩዋቸው ፊልሞች፣ የሚጫወቱባቸው ‹ጌሞች›፣ የሚለብሷቸው ልብሶች፣ የሚጠቀሙባቸው ደብተሮች፣ የሚይዟቸው የምሳ ዕቃዎች ይታዩኝ ጀመር፡፡ ለእኛ ልጆች ‹ጀግና› ምንድን ነው? እነርሱ የሚያደንቁትና ቢሆኑት የሚወድዱት ምንድን ነው? አርአያቸውና አይከናቸው ማነው?
ሰው አርአያውን ወይም ጀግናውን የሚወስደው ከማኅበረሰቡ ነው፡፡ ማኅበረሰቡ ሲያደንቅለት፣ ሲያወራለት፣ ሲያሞግሰው፣ ሲዘፍንለት፣ የሰማውን፤ ብሎም እርሱ ራሱ ደጋግሞ ያየውን የሰማውንና የተከታተለውን ጀግናና አርአያ ያደርገዋል፡፡ ሰው የማያውቀውን ሰው ጀግና አያደርገውም፡፡ ስሙ ከፍ ብሎ ያልሰማውን ሰው አይከን አያደርገውም፡፡ ደጋግሞ ያላየውን ወይም ያልሰማውን ሰው አያደንቀውም፤ አይከተለውምም፡፡
ለመሆኑ አሁን ስለነማን ነው በብዛትና በስፋት እየተወራ፣ እየታየስ ያለው? ይህንን ስንመልስ የልጆቻችን ዕጣ ፈንታን ማየት እንችላለን፡፡
ስለ ዘፋኞችና የፊልም ተዋንያን፣ ስለ ኳስ ተጨዋቾችና ስለ ሞዴሊስቶች፣ በየሚዲያው ይተረካል፣ በየጋዜጣው ይጻፋል፣ በየኢንተርኔቱ ይለቀቃል፣ በየማኅበራዊ ሚዲያው ይበተናል፡፡ የበሉትና የጠጡት፣ ያወጡትና ያወረዱት፣ የለበሱትና የተጫሙት፣ ያገቡትና የፈቱት፣ የነዱትና የገዙት፣ ያጠፉትና ያለሙት ሁሉ ይዘከዘካል፡፡ የእነዚህ አካላት የየዕለት ውሏቸው እንደ ዜና መዋዕል በየቀኑ ይፈተፈታል፡፡ እንኳን ያወሩትና ያደረጉት ያሰቡትና የተመኙት ሁሉ ይቀርባል፡፡ ፎቷቸው በደብተር ላይ ይለጠፋል፣ በልብስ ላይ ይታተማል፣ በፖስተር ይዘጋጃል፣ በቦርሳ ላይ ይወጣል፡፡
ለልጆቻችን ጀግኖች ማለት እነዚህ ናቸው፡፡ ደጋግመው ሲወደሱ የሚሰሟቸው፤ ደም ከፍለው የሀገራቸውን ነጻነት ከጠበቁት ይልቅ የሀገራቸውን ሚዲያ ሳንቲም ሳይከፍሉበት የወሰዱት የልጆቻችን ጀግኖች እነዚህ ናቸው፡፡ ፎቷቸውንና ሥዕላቸውን ለማየት ሙዝየም መሄድ ከሚያስፈልጋቸው የሀገራቸው ጀግኖች ይልቅ ፎቷቸውን እንደ ልብ ደብተራቸውና ቦርሳቸው ላይ የሚያገኟቸው የልጆቻችን ጀግኖች እነዚህ ናቸው፡፡
እነዚህ የልጆቻችን ጀግኖች በተሠማሩበት ሞያ ጎበዞችና ታዋቂዎች ቢሆኑም ገልበጥ ተደርገው ሲታዩ ግን አንዳንዶች ሌላ ገጽታም ደግሞ አላቸው፡፡ ያገባሉ ይፈታሉ፣ ይማግጣሉ፣ ይቀብጣሉ፣ አደንዛዥ ዕፅ ይጠቀማሉ፣ እሥር ቤቶችን በተደጋጋሚ ይጎበኛሉ፣ የዘረኝነት ስድብ ይሳደባሉ፣ ይደባደባሉ፣ ያልተፈቀደ መሣርያ ይይዛሉ፣ ሕጻናትን ያባልጋሉ፣ ለፍቅረኞቻቸው ታማኝ አይሆኑም፡፡ ስለ እነርሱ ሲተረክ ግን ይኼ ሁሉ ይነገራል፤ ይዘከዘካል፤ ይተነተናል፡፡ ‹ታዋቂው እገሌ› እየተባለ አስነዋሪውም ነገር አብሮ ይነገርለታል፡፡ ልጆቻችንም ይህንን ይሰማሉ፡፡ ለእነርሱ የሚያደንቁት ሰው ያደረገው ሁሉ የሚደነቅ፣ የሠራው ሁሉ ትክክል፣ የፈጸመውም ሁሉ ሊከተሉት የሚገባ አድርገው ይወስዱታል፡፡
አሁን ልጆቻችን ጀግኖቻቸውን የሚወስዱት ከኢንተርኔት፣ ከፊልምና ከሚዲያ ነው፡፡ ከተረቶች፣ ከቀድሞ ታሪክና ከማኅበረሰባዊ ክዋኔዎች ጀግኖችን የሚወስዱበት ዕድላቸው እየተሟጠጠ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሳይንቲስቶች፣ ደራስያን፣ የሀገር መሪዎች፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣ ለሰው ልጅ ደኅንነት በጎ የሚያደርጉ ሰዎች፣ የፈጠራ ባለሞያዎች፣ አዳዲስ ነገሮችን የሚያገኙ አሳሾች፣ ለሀገራቸውና ለሕዝባቸው ነጻነትና መብት የተሠው አርበኞች፣ እውነትንና መረጃን ፍለጋ ሕይወትን የሚከፍሉ ሰማዕታት ጋዜጠኞች፣ የሚዲያዎችን ውቃቤ መሳብ አልቻሉም፡፡ ስለእነዚህ እናቅርብ ብለው የሚነሡ ሚዲያዎችንም ስፖንሰር የሚያደርጋቸው የለም፡፡ የሚዲያ ባለቤቶችም ‹›ገንዘብ አታመጡም› ብለው ፊታቸውን ያዞሩባቸዋል፡፡
በአንድ ወቅት የእንግሊዟ ልዕልት ዲያናና የካልካታዋ ቅድስት ማዘር ቴሬዛ ተከታትለው ይህችን ዓለም ተሰናበቱ፡፡ የዓለም ሚዲያዎች ሰፊውን ሽፋን የሰጡትና ብዙ ሰዎችም መስማት ይፈልጉ የነበሩት ስለ ልዕልት ዲያና ነበር፡፡ ልዕልት ዲያና አሟሟቷ አሳዛኝ ቢሆንም ለሰዎች ልጆች በሰጡት ክብርና ፍቅር፣ አገልግሎትና ደግነት ግን ማዘር ቴሬዛ ከልዕልት ዲያና ይበልጡ ነበር፡፡ በልዕልት ዲያና ሞት ከተጎዱትም በላይ በማዘር ቴሬዛ ሞት የተጎዱት ይበልጡ ነበር፡፡ ነገር ግን የልዕልት ዲያና ጉዳይ የማዘር ቴሬዛን መሞት እንኳን እስከ ማስረሳት ደርሶ ነበር፡፡
ለዚህ ነው እኛ ወላጆች ‹በትምህርት ጎበዝ መሆን አለብህ፣ ማጥናት አለብህ፣ አንደኛ መውጣት አለብህ፣ ሳይንቲስትና ሐኪም፣ ጎበዝ ነጋዴና መምህር፣ የሀገር መሪና ተመራማሪ፣ መሆን አለብህ› እያልን ልጆቻችንን የምንመክራቸው ምክር አንጀታቸው ጠብ ሊል ያልቻለው፡፡ እኛ ሁኑ ስለምንላቸው ነገሮች ከእኛ ውጭ ማን ሲያወራ ሰምተው ያውቃሉ? ለአንድ ሐኪም ሦስት ሺ ብር ለእንድ የፊልም ተዋናይ ደግሞ ሦስት ሚሊዮን ብር፣ ለአንድ ሳይንቲስት አምስት ሺ ብር ለአንድ ተጨዋች ግን ሃምሳ ሚሊዮን ብር ሲከፈለው እያዩና እየሰሙ ‹ማን ፉል አለ›፡፡ ለሀገሩ ድንበር ከተዋጋው ይልቅ ስለውጊያው ፊልም የሠራው ታዋቂ ሲሆን እያዩት፣ ላቦራቶሪውን ዘግቶ የካንሰር መድኃኒት ለማግኘት ከሚኳትነው ይልቅ ስለ ካንሰር የዘፈነችው ስትደነቅ እያዩ፤ ምን አድርጉ ነው የምንላቸው፡፡
ይኼ መሣርያ ይዞ የሚተኩሰው፣ የኼ እንኳን እንትናን አናቱን የበረቀሰው፣ ይኼ እንኳን ተገለባብጦ ተራራውን ያለፈው፣ ኧረ ማነው እንኳን እቴ ይኼ በካራቴ ሰዎቹን የረፈረፋቸው እርሱኮ ነው የምናምንና የምናምን ሽልማት አሸንፎ ሚሊዮኖች ሲያጨበጭቡለት፣ ሚሊዮን ብሮች ሲጎርፉለት፣ ሚሊዮን ወንዶች ሲሞቱላት፣ ሚሊዮን ሰዎች የፌስቡክና የትዊተር ገጽዋን ሲጎበኙላት የምንሰማው፡፡ አሁን ማ ይሙት የአንስታይን ፎቶ ያለበት ቦርሳ፣ የሞዛርት ሥዕል ያለበት ደብተር፣ የጋሊሊዮ ምስል ያለበት ምሳ ዕቃ፣ የሐዲስ ዓለማየሁ ሥዕል ያለበት ቲሸርት፣ የቶማስ ኤድሰን ሥዕል ያለበት ፖስተር፣ የምኒሊክ ሥዕል ያለበት እስክርቢቶ አግኝተን እናውቃለን? ልጆቻችንስ ይዘው ያውቃሉ?
ታድያ ‹መግደል እወዳለሁ› ቢሉ ምን ይፈረድባቸዋል፡፡ በየቤታችን የገጠምናቸው ዲሾች በየቀኑ ‹ጀግና ገዳዮችን› ሲያሳዩዋቸው አይደል እንዴ የሚውሉት፡፡ በገዛ ገንዘባችን፣ በገዛ ዲሻችን፣ በገዛ ቴሌቭዥናችን እነርሱ አይደሉ እንዴ ሳይከፍሉ አድናቂ እያፈሩበት ያሉት፡፡ ‹በገዛ ዳቦዬ ልብ ልቡን አጣሁት› አለ ያገሬ ሰው፡፡ በተለይማ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የልጆቻቸውን ጭቅጨቃ ለመገላገል ቴሌቭዥን ላይ አፍጥጠው እንዲውሉ ፈርደውባቸዋል፡፡
‹እዚያ ምን ወሰደህ› አትሉኝም፡፡ እዚሁ በየልጆች ማጫወቻውኮ ልጆቹ ተኩሰው እንዲጫወቱ የተዘጋጁ ብዙ ‹መግደያዎች‹ አሉ፡፡ በልደት ቀናቸውም ሽጉጥና መትረጊስ ገዝተው ‹እንኳን ለዚህ አደረሰህ› የሚሉ ወዳጆችም አሉ፡፡ በየሞባይላችንም የተኩስ መለማመጃ ‹ጌሞች› ሞልተዋል፡፡
እና ‹መግደል ደስ ይለኛል› የሚል ትውልድ ብናፈራ ምን ይገርማል፡፡ ይኼው በስለት ሚስቶቻቸውን ከሚወጉት ጀምረን እንደ ጦርነት ፊልም በቦሌ ጎዳና በመትረጊስ ሚስቶቻቸውን እስከሚረፈርፉት ድረስ አፍርተናል፡፡ አንበሳ ገዳይ፣ ነበር ገዳይ፣ ዝሆን ገዳይ፣ ቀጭኔ ገዳይ ዛሬ ተለውጠው፣ ዘምነው ዘምነው ሚስት ገዳይ፣ ባል ገዳይ፣ ልጅ ገዳይ፣ ወላጅ ገዳይ ሆነው ከመጡ ‹መግደል ያባቴ ነው ጠላትን ማደን› ብለን መዝፈን ሲያንሰን ነው፡፡
© ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት የወጣ ነው