የሐሳብ ልዩነት እንደ ኃጢአት


ቤተ ክርስቲያን ይህንን ሰሞን ከዕርቅና ከፓትርያርክ ምርጫ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ወገኖችን የሐሳብ ፍጭት እያስተናገድች ትገኛለች፡፡ አንድ ሰው የቱንም ዓይነት ሐሳብ ይኑረው ለቤተ ክርስቲያን ይበጃል ብሎ ሐሳብ እስከሠነዘረ፣ ያንን ሐሳቡንም ከሸፍጥና ከሰይጣናዊ መንገድ በተለየ መልኩ ባገኘው የተፈቀደ መድረክ ላይ ሁሉ እስካንጸባረቀ ድረስ ለቤተ ክርስቲያን ይበጃል እንጂ አይጎዳትም፡፡
ቀደምት አበው የቤተ ክርስቲያንን አመራር ከግለሰባዊነት ይልቅ ለጉባኤ የሰጡበት አንዱ ምክንያት ውይይት፣ ክርክርና የሐሳብ ልዩነት እንዲኖር ብለው ነው፡፡ አንድ ሰው በተመደበበት የቤተ ክርስቲያን ኃላፊነትና በተፈቀደለት የአገልግሎት ሜዳ ውስጥ ይበጃል ያለውን ሐሳብ ማንሣት፣ ለሐሳቡም ማስረጃ አቅርቦ መከራከር፣ በስተመጨረሻም በጉባኤው ሕግ መሠረት ለጸደቀው ሐሳብ መገዛት ይጠበቅበታል፡፡

በ51 ዓም በኢየሩሳሌም የተደረገችው የመጀመርያዋ የቤተ ክርስቲያን ዓለም ዐቀፍ ጉባኤ ምክንያት በክርስቲያኖችና እነርሱንም በሚመሩና በሚመግቡ አባቶች መካከል በተነሣው የሐሳብ ልዩነት ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያን ከአይሁድ ማኅበረሰብ ወጥታ ወደ አሕዛብ መንደር ስትገባ በአሕዛብና በአይሁድ ክርስቲያኖች መካከል ከአነዋወራቸው የተነሣ የሓሳብ ልዩነት ተፈጠረ፡፡
ይህ የሐሳብ ልዩነትም በጉባኤ ኢየሩሳሌም ታይቶ በስተመጨረሻ አባቶችና መንፈስ ቅዱስ ለቤተ ክርስቲያን ይበጃል ያሉትን ውሳኔ ወሰኑ፡፡ በጊዜው ‹ብዙ ክርክር› እንደነበረ የሐዋርያት ሥራን የጻፈው ቅዱስ ሉቃስ ገልጦታል (የሐዋ 15÷7)
እንኳን ቤተ ክርስቲያንን በሚመራው ሲኖዶስ መካከል ቀርቶ በሁለትና በሦስት አባቶች መካከል አገልግሎትንና ለአገልግሎት የተሻለ የሆነውን መንገድ በመምረጥ ረገድ ልዩነት የታየበት ጊዜም ነበር፡፡ ቅዱስ ጳውሎስን ወደ ቤተ ክርስቲያን በማምጣት፣ ከሐዋርያትም ጋር በማቀራረብና በክርስቲያኖች ዘንድ የነበረውን ተፈሪነት በማስቀረት ታላቅ ሚና በተጫወተው በቅዱስ በርናባስና በሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ መካከል የሐሳብ ልዩነት ተፈጥሮ ነበር፡፡
የቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደሚነግረን የሐሳብ ልዩነቱ መነሻ ወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስን የተመለከተ ነበር፡፡ ከሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ጋር ለአገልግሎት ወጥቶ የነበረው ቅዱስ ማርቆስ አገልግሎቱን አቋርጦ ወደ እናቱ መመለስ ፈለገ፡፡ ከቅዱስ ጳውሎስ ጋር የነበረው በርናባስም እንዲመለስ ፈቀደለት፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ግን ወደ ኋላ መመለስ የለም አለ፡፡ በርናባስ ግን ይዞት ወደ ኢየሩሳሌም አደረሰው፡፡
በሌላ ጊዜ አስቀድመው በሰበኩበት ቦታ ተመልሰው ወንድሞችን ለማየት ሲመካከሩ በርናባስ ማርቆስን ለመውሰድ አሰበ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ግን አስቀድሞ ከጉዞ አቋርጦ መመለሱን አስታውሶ መሄድ የለበትም አለ፡፡ በዚህ ምክንያት በሁለቱ አባቶች መካከል ‹እርስ በርሳቸው እስኪለያዩ ድረስ መከፋፋት ሆነ› (የሐዋ15÷36-40)፡፡ ይህ በሐሳብ መለያየታቸው ግን ቤተ ክርስቲያንን ጠቀማት እንጂ አልጎዳትም፡፡ ‹አንድ ቢሆኑ ኖሮ ወንጌል ትጸናለች አትሰፋም ነበር፤ በመለያየታቸው ግን ወንጌል ሰፋች› ይላ መተረጉማ፡፡
ዮሐንስ አፈወርቅና ቅዱስ ኤጲፋንዮስ የቁስጥንጥንያዋን ንግሥት ብርክልያን በተመለከተ የተለያየ ሐሳብ ነበራቸው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ‹ብርክልያ ለምትፈጽመው ግፍ ፊት ለፊት መወገዝ አለባት› ሲል፣ ኤጲፋንዮስ ደግሞ ‹እርሷን ማውገዙ በቤተ ክርስቲያን ላይ ከባድ ፈተና ያመጣል› ብሎ ያምን ነበር፡፡ ይህ ውይይት በቁስጥንጥንያ ሲደረግ ሁለቱ አባቶች በአቋም ስላልተግባቡ እስከ መለያየት ደርሰው ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያን ግን ዛሬ የሁለቱንም አባቶች ቅዳሴ ትቀድሳለች፡፡
በ13ኛው መክዘ ቤተ ኤዎስጣቴዎሳያንና ቤተ ተክለ ሃይማኖታውያን የሁለቱን ሰንበት አከባበር በተመለከተ የተለያየ አቋም ነበራቸው፡፡ በኋላ ዘመን በጉባኤ ደብረ ምጥማቅ ወደ አንድ አቋም እስኪመጣ ድረስ ከባድ ክርክር ይደረግ ነበር፡፡ እንዲያውም በገድለ ዜና ማርቆስ እንደምናነበው በዓምደ ጽዮን አደባባይ አቡነ ኤዎስጣቴዎስና አቡነ አኖሬዎስ በጉዳዩ ሲከራከሩ በመገኘታቸው ከንጉሡ ዘንድ አቡነ አኖሬዎስ ከባድ ቅጣት ገጥሟቸው ነበር፡፡ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ መጀመርያ እስክንድርያ፣ በኋላ ኢየሩሳሌም፣ ከዚያም ቆጵሮስ፣ በመጨረሻም አርመን ሄደው ያረፉት በዚህ ክርክር ምክንያት ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያን ግን አቡነ ኤዎስጣቴዎስንም አቡነ አኖሬዎስንም ቅዱስ ብላ አክብራቸዋለች፡፡
በዐፄ በዕደ ማርያም ዘመን፣ እጨጌ መርሐ ክርስቶስ የደብረ ሊባኖስ አበ ምኔት እያሉ ከግብጽ የሚመጡትን ጳጳሳት በተመለከተ በደብረ ሊባኖስ ታላቅ የሊቃውንት ጉባኤ ተደርጎ ነበር፡፡ በጉባኤው ላይ ‹ኢትዮጵያውያን የራሳችንን ጳጳሳት እንሹም‹ የሚሉ ሊቃውንት ሐሳባቸውን ያቀረቡ ሲሆን፣ ‹ከግብጽ እያስመጣን እንቀጥል› ያሉ ሊቃውንትም ሐሳባቸውን አቅርበው ነበር፡፡ በወቅቱ በተደረገው ከባድ ክርክር ከአቡነ መርሐ ክርስቶስ በቀር ወደ ስድስት መቶ የሚጠጉት ሊቃውንት ‹እኛው የራሳችንን ጳጳሳት እንሹም› የሚለውን አጸደቁት፡፡ አቡነ መርሐ ክርስቶስ ግን አልተስማሙም ነበር፡፡ በመጨረሻም ንጉሡ ጉዳዩን በይደር እንዳቆዩት በዚያው ቀረ፡፡
እንዲህ እያልን ብንቀጥል በቤተ ክርስቲያን አባቶች ዘንድ ለአንድ ችግር በሚሰጥ የመፍትሔ ሐሳብ የተለያዩ አቋሞችን መያዝና፣ በዚያ አቋም መከራከርም ያለና የነበረ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
በዚህ ወቅት ግን አባቶቻችን ዕርቁንና የፓትርያርክ ምርጫውን በተመለከተ የተለያየ ሐሳብ በመስጠታቸው ምክንያት ሁሉም ከእርሱ ሐሳብ በተቃራኒው የሆኑትን ወይም ይሆናሉ ብሎ የገመታቸውን አባቶች ያወግዛል፤ ያስፈራራል፤ እንደ ኃጢአተኛ እየቆጠረም እኛ ያልነውን ካልተቀበላችሁ በቀር ሕዝብ እንዲያወግዛችሁ እናደርጋለን ይላል፡፡
ይህ ዓይነቱ አሠራር በቤተ ክርስቲያን ጉዞ ላይ ሦስት ችግሮችን ያመጣል
1.         አባቶች ሐሳብ አንሥተው ከመከራከርና ከመወያየት ይልቅ ‹ኦሆ በሃሊ› ብቻ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ነገ የሚገጥማቸውን ማንኛውንም ዓይነት ተጽዕኖ በጥብዐት ከመመከት ይልቅ በፍርኃት እሺ ብቻ ብለው እንዲቀበሉ ያደርጋቸዋል፡፡
2.       የብዙኃንን ጭቆና ያመጣል፡፡ አምባ ገነንነት ሕዝብን እንደ ገል ቀጥቅጠው፣ እንደ ሰም አቅልጠው በሚገዙ ግለሰቦች ላይ ብቻ የሚታይ አይደለም፡፡ ቡድንም፣ ማኅበረሰብም አምባገነን የሚሆንበት ጊዜ አለ፡፡ ቡድንና ማኅበረሰብ ‹ጊዜ የወለደውን፣ ሕዝብ የወደደውን› ብቻ ተቀበሉ ብሎ ግለሰቦችን የሚደፍቅበትና ነጻነታቸውን የሚነሣበት ጊዜ አለ፡፡ የአንድ ሰው ሐሳብ የሚመዘነው በሐሳብ አቀራረቡ፣ ባቀረበው ማስረጃ፣ በተከራከረበት ዐውድ፣ ብሎም በሐሳቡ መንገድ ሳይሆን ምን ያህል ሰው ተቀብሎታል በሚለው ይሆናል፡፡ እንዲህ ያለው አሠራር ለምርጫና ለሥልጣን እንጂ ለሐሳብ አይሆንም፡፡
ጌታችን በዚህ ምድር ሲያስተምር ከጠቅላላው ሕዝብ አምስት ገበያ ሰምቶታል፤ ከሰማው አምስት ገበያ ሕዝብ መቶ ሃያው ተቀብሎታል፡፡ ከመቶ ሃያውም አንዱ ይሁዳ ከድቶታል፡፡ የጌታችንን መዋዕለ ሥጋዌ ምን ያህል ሰው ተቀበለው? በሚለው የምንመዝነው ቢሆን ኖሮ ማናችንም ክርስቲያን ባልሆንን ነበር፡፡
3.       የሓሳብ ክርክር ወርዶ ወደ ግለሰባዊ ክርክር ይገባል፡፡ ሰው መመዘን ያለበት በአቋሙ ነው፡፡ ክርክር ሊደረግበት የሚገባውም አቋሙ ነው፡፡ ተክለ ሰብእናው አይደለም፡፡ ሐሳብ የሚፈራና ሐሳብን የሚሞግት ዐቅም የሌለው ብቻ ነው ተክለ ሰብእና ላይ የሚንጠለጠለው፡፡ ሰው ‹ሐሳብህ ትክክል አይደለም› እንጂ ‹እንዴት እንደዚህ ታስባለህ?› ሊባል አይቻልም፡፡ ያውም ደግሞ ለሕዝብ በኦፊሴል ክፍት ባልሆነ የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ውስጥ ዘልቆ ገብቶ እገሌ ለምን ይህንን ሐሳብ ሰጠ፣ እገሌስ ለምን ይህንን ተናገረ፣ እገሌስ ለምን እንደዚህ ያስባል፣ እገሌስ ለምን ዝም ይላል እያሉ መክሰስና መውቀስ ከማሸማቀቅ ያለፈ ዋጋ አይሰጥም፡፡
በሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የምርጫ ሕግ የፖፑ ምርጫ እስኪጸድቅ ድረስ የሲኖዶሱ አባላት ከማንም ጋር እንዳይገናኙ፣ መግለጫ እንዳይሰጡና፣ በሌሎች ጫና ውስጥ እንዳይገቡ የሚደረገው በነጻነት የመሰላቸውን ሐሳብ አቅርበው መከራከርና መወያየት እንዲችሉ ለማድረግ ነው፡፡ በኛ ዘንድ ግን ይህ ዓይነቱ አሠራር ባለመኖሩ ‹የፓርላማ አባላት እንኳን በጉባኤያቸው ላይ በሚሰጡት ሐሳብ አይከሰሱም› በሚባልበት ዘመን አባቶች በጉባኤያቸው በሰጡት ሐሳብ ምክንያት ይዘለፋሉ፤ ይከሰሳሉ፤ ማስፈራርያም ይደርሳቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የሚቀርቧቸው ሰዎች ‹ምን አስጨነቀዎት፤ ለምን ዝም አይሉም፤ ለምን ይወጋሉ› እያሉ ‹እምነ ተናግሮ ይኼይስ አርምሞ› እንዲሉ ያደርጓቸዋል፡፡ ይህ ሁኔታ ዛሬ የአንዳንዶቻችንን ሐሳብ ለማራመድ ጠቅሞን ይሆናል፡፡ ነገ ግን ልማድ ሠልጥኖ ሕግ ይሆንና ጥቂት ክፉዎች ብዙኃኑን እንዲዘውሩት ያደርጋል፡፡
በአንድ እግር ኳስ ሜዳ ላይ ተመልካቾች፣ ተጨዋቾች፣ ዳኞችና ረዳት ዳኞች ይኖራሉ፡፡ የተጨዋቹ ድርሻ መጨዋት ነው፡፤ ሕግና ደንቡን ጠብቆ መጨዋት፡፡ የተመልካቹ ድርሻ መደገፍ ነው፡፡ ሕግና ደንቡን ጠብቆ መደገፍ፡፡ የረዳት ዳኞቹ ድርሻ ማመልከት ነው፡፡ ሕጉም ‹ለዳኛው ያመለክታል› ነው የሚለው፡፡ የዳኞቹ ድርሻ ደግሞ መወሰን፡፡ ተመልካችም፤ ተጨዋችም፣ ረዳት ዳኛም ሊወስኑ አይችሉም፡፡ ሊወስን የሚችለው ዳኛው ነው፡፡ ማመልከት፣ ማሳየት፣ መጠቆም፣ ሐሳብ መስጠት ግን ይችላሉ፡፡ ዳኛው ሲወስን ግን ሁሉ ይጸናል፡፡
ምንም ያህል ብናውቅ፣ ምንም ያህል ብንራቀቅ፣ ምንም ያህል ሐሳብ ቢኖረን፣ ምንም ያህል ሐሳባችን ትክክልም ቢሆን፣ ምንም ያህል ብንጽፍና ብናትም፣ የኛ ድርሻ ሐሳብ ማቅረብ ነው፡፡ ሐሳባችን ሊሰማ በሚችልበት መንገድ ማቅረብ፡፡ መወሰን ግን የኛ ድርሻ አይደለም፡፡ መወሰን የቅዱስ ሲኖዶስ ድርሻ ብቻ ነው፡፡ አንድ ቡድን በዳኛው ውሳኔ ላይስማማ ይችላል፡፡ ነገር ግን የመቀበል ግዴታ አለበት፡፡ ቅሬታ ማቅረብ ይችላል፤ ነገር ግን ለርሱም ሥርዓት አለው፡፡ አንድ ምእመንም በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ላይስማማ ይችላል፡፡ ነገር ግን የመቀበል ግዴታ አለበት፡፡ ቅሬታ ሊኖረው ይችላል፡፡ ነገር ግን ሐሳቡን ማቅረብ ያለበት በሕግና በሥርዓት ብቻ ነው፡፡
በቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ላይ በሚቀርብ አጀንዳ መልካም ነው ያሉትን ሐሳብ ያቀርቡ፣ ለሐሳባቸውም ይከራከሩ ዘንድ የስብሰባው ሥነ ሥርዓት ሕግ ይፈቅድላቸዋል፡፡ ያ ሐሳብ በኛ መመዘኛ አይጠቅም ይሆናል፡፡ ግን መብታቸው ነው፡፡ ማንኛውም በጎ ሐሳብ መብትን እስከ መከልከል ከሔደ በጎነቱ አበቃለት ማለት ነው፡፡
ሌላው ቀርቶ ‹ፓትርያርክ ሊሆኑ ይፈልጋሉ› እየተባሉ የሚታሙት አባቶች እንኳን የሚወጣውን መመዘኛ እስካሟሉና ሥርዓቱን እስከጠበቁ ድረስ ፓትርያርክ ሊሆኑ መፈለጋቸው ነውሩ ምንድን ነው? በቅርቡ በግብጽ ቤተ ክርስቲያን በተደረገው ምርጫ ከስድስት በላይ አባቶች ራሳቸውን ለዕጩነት አቅርበው አልነበር እንዴ? ቅዱስ ጳውሎስስ ‹ማንም ኤጲስ ቆጶስነትን ቢፈልግ መልካሙን ሥራ ይመኛል› ብሎ አስተምሮ የለም እንዴ? (1ኛጢሞ 3÷1) እነዚህን አባቶች መውቀስ የምንችለው ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ከተጓዙ ብቻ ነው፡፡ ለምን መንፈሳዊ ሹመት ፈለጋችሁ? ብለን ዘራቸውን፣ ብሔረሰባቸውንና ተክለ ሰብእናቸውን ልንወቅስ አንችልምኮ፡፡ መሆን የለባችሁም ስንል መከራከር ያለብን በሕጉና በሥርዓቱ መሠረት እንጂ ‹እንዴት እንዲህ ይላሉ› በሚል መሆን አይችልም፡፡ ያውም ደግሞ ከጥርጣሬና ከወሬ በቀር ምንም ማስረጃ በሌለው ነገር፡፡ 
በሌላም በኩል ደግሞ አሁን በቤተ ክርስቲያን በተፈጠሩ ጉዳዮች ላይ ከኛ የተለየ ሐሳብ ሠንዝራችኋል እየተባሉ የሚወቀጡም አካላት አሉ፡፡ በአንድ በኩል ‹አቡነ መርቆሬዎስ ከነ ሙሉ ሥልጣናቸው ወደ መንበራቸው ይመለሱ› የሚሉ አሉ፡፡ በሌላ በኩል ‹አዎ ይመለሱ፤ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያኒቱ በእንደራሴ ትመራ› የሚሉም አሉ፡፡ ‹የለም ዕርቁም ይቀጥል፤ ቤተ ክርስቲያንም ስድስተኛውን ፓትርያርክ ትምረጥ፤ እርሳቸውም መጥተው በክብር ይኑሩ› የሚሉም አሉ፡፡
እነዚህ ሁሉ ወገኖች ለቤተ ክርስቲያን ብለው ሐሳባቸውን እስከሰጡ ድረስ ሊወገዙ፣ ሊኮነኑና ሊብጠለጠሉ አይገባም፡፡ ሐሳባቸውን በማስረጃና በተጠየቅ መሞገት ግን ይቻላል፡፡ የኔ ሐሳብ ከአንተ ይሻላል ብሎ የሚሻልበትን መንገድ ማሳየት ይቻላል፡፡ ያኛው ሐሳብ ስሕተት ነው ብሎ ስሕተት የሆነበትን ምክንያት ማመልከት ይቻላል፡፡ የሁሉም ነገር ማሠርያው ግን ኃላፊነትና ሥልጣን የተሰጠው አካል ውሳኔ ነው፡፡ እርሱም ቅዱስ ሲኖዶስ፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ እኔ የምፈልገውን ካልወሰነ በቀር ‹መንግሥት ተጭኖት ነው፣ ሥልጣን ተፈልጎ ነው፤ ዘር ነው፣› እያሉ የውግዘት ጋጋታ ማዝነብ በተመልካች ወንበር ላይ ተቀምጦ የዳኛ ፍርድ እንደመስጠት ያለ ነው፡፡ ‹ከእኔ ጋር ያልሆነ ሁሉ ከጠላቴ ጋር ነው› የሚለው የቀዝቃዛው ጦርነት አሠራር ዛሬ የሚሠራ አይደለም፡፡
ይልቅ አባቶቻችን ሆይ
ተከራከሩ፣ በሓሳብ ተፋጩ፣ መንፈሳዊነትን ባልዘለለ መንገድ ልዩ ልዩ ሐሳቦችን አቅርባችሁ በዚያው በሲኖዶሳችሁ ውስጥ ተከራከሩ፡፡ ሐሳባችሁ የምንደግፈውም ይሁን የምንቃወመው፤ የምንፈልገውም ይሁን የምንጠላው እናንተ ግን ለእግዚአብሔር፣ ለሕግና ለኅሊናችሁ ታማኞች ሆነችሁ በጎ ነው ባላችሁት፣ ቤተ ክርስቲያንን ይጠቅማል ባላችሁት ሐሳብ ተከራከሩ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ብዙኃን ግለሰቦችን እንደሚጨቁኑ አስቡ፡፡ ሴትዮዋ ‹አፍ ያለው ያግባሽ ከብት ያለው› ስትባል ‹አፍ ያለው ያግባኝ፣ በአፉ ከብቱን ያመጣዋል› ያለችው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ሐሳባችሁን በሕግ፣ በማስረጃና በተሻለ ሓሳብ እንጂ በጩኸት ብዛት አትቀይሩ፡፡ የተጮኸለት ሁሉ ትክክለኛ አይደለም፤ ስሕተትም አይደለም፡፤ ዕድለኛ ሐሳብ ነው እንጂ፤ ያልተጮኸለትም ስሕተት አይደለም፤ ትክክለኛም አይደለም፣ ዕድለ ቢስ ሐሳብ ነው እንጂ፡፡
ይልቅ ቤተ ክርስቲያን ትጠቀም ዘንድ ተለያይታችሁ ተከራከሩ፤ አንድ ሁናችሁ ግን ወስኑ፡፡