ግብፅ በምእራብ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የወርቅ ክምችት አገኘች
በውድነህ ዘነበ | ሪፖርተር
የግብፁ የማዕድን ኩባንያ አስኮም የሚሌኒየም ግድብ በሚገነባበት ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ ባካሄደው የወርቅ ፍለጋ ከፍተኛ የወርቅ ክምችት ማግኘቱ ተረጋገጠ፡፡ የግብፁ ኩባንያ አስኮም ከአንድ ዓመት በላይ ለሆነ ጊዜ በክልሉ 8,000 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ቦታ ላይ ወርቅና የከበሩ ማዕድናትን ሲፈልግ ቆይቷል፡፡
ከኩባንያው የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በዓረብ ኑቢያን ሺልድ ክልል ውስጥ በተለይም በምዕራብ ኢትዮጵያ ቤኒሻንጉል ክልል ውስጥ ወርቅና ከወርቅ ጋር ተቀራራቢነት ያላቸውን የማዕድናት ክምችት አግኝቷል፡፡
አስኮም በግብፅ የካፒታል ገበያ እ.ኤ.አ. በ2009 የተቋቋመ ኩባንያ ነው፡፡ በማዕድን ፍለጋና ማውጣት ሥራ ላይ የተሰማራ ኩባንያ ሲሆን አትራፊም ነው፡፡
የወርቅ ማዕድን በዚህ ክልል ያገኘው አስኮም ብቻ አይደለም በሼክ መሐመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ የተመሠረተው ማድሮክ ጐልድም የወርቅ ክምችት አግኝቷል፡፡ ሚድሮክ ጐልድ ከማዕድን ሚኒስቴር በቤንሻንጉል ክልል ቡለን ወረዳ ሞር አካባቢ ከሁለት ዓመት በፊት የወርቅ አሰሳ ፈቃድ አግኝቷል፡፡