የጉዞ ማስታወሻ፤ መቐለን በአንድ ቀን
ከአዲስ አበባ ብዙም ርቆ የማያውቅ ሰው ሃያ ኪሎ ሜትር ሲራመድም ቢሆን የጉዞ ማስታወሻ ይጽፋል፡፡ እኔም የዛሬ ሁለት ዓመት እጄን ይዛ ጎንደርየወሰደችኝ ወዳጄ፣ ዛሬ (ኅዳር 12፤ 2005) ደግሞ መቐለ ወሰደችኝ፡፡ ጉዞዬ ረዥም ነው፤ ገና አክሱም ላሊለባላና ሌሎች ጥቃቅንና አነስተኛ ቦታዎችን እጎበኛለሁ፡፡ ይህንን ያህል ካስቀናኋችሁ ይበቃል፣ አሁን በጥቅሉ ላስነብባችሁ አቅጄ የነበረውን የጉዞ ማስታወሻ አላስችል ስላለኝ አመሻሹን የማደሪያዬን መስኮት ሰብሮ የዘለቀ፣ ምንጩ ግን ያልታወቀ ዋይፋይ ተጠቅሜ ጻፍኩት፡፡
ለመናዘዝ ያክል፤ መቐለን ሳስብ መጀመሪያ የሚመጣብኝ ነገር ሕወሓት ነው፡፡ እንዴያው እንዲሁ… ትንሽ ስጋ እንደመርፌ ትወጋ… የሚለው አባባል በራሱ ኢሕአዴግ ለመቐሌ ሳያዳላ አይቀርም የሚል ጥርጣሬ ሽው እንዲልብኝ አድርጎ ነበር… ነበር ያልኩት ያለነገር አይደለም፡፡ የመሐመድ ሰልማን ተወዳጅ መጽሐፍ ፒያሳ ‹አደይ መቐለ› ባለው ትረካው ነገሩን ሁሉ ድባቅ መትቶታል፡፡ መቐሌ የምስኪኖች እና አቧራ የዋጣት ከተማ ናት ብሎ ነበር ልበል?!
መቐለ ስገባ ግን ያልጠበቅኩት ነው የገጠመኝ፡፡ ሲጀመር ስፋቷ እንደዚህ አልመሰለኝም ነበር፤ ከሌሎች የክልል ከተሞች አንጻር መቐለ ሰፊ ነች፡፡ ሲቀጥል፣ አቧራ የለባትም – መሐመድ መቼ እንዳያት እኔ እንጃ እንጂ እኔ በተንቀሳቀስኩባቸው ቦታዎች ሁሉ ውስጥ ለውስጡ ሳይቀር ለዓይን በአማረ የኮብል ስቶን ድንጋይ የተነጠፈች ከተማ ነች – አደይ መቐለ፡፡ እኔ እኮ አቧራ ሲባል የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ ጅማሄጄ ያየሁትን ዓይነት መስሎኛል፡፡
ወደ መቐለ የተጓዝነው በሰላም ባስ ነበር፡፡ ሰላም ባስ ዕድሜ ለፉክክር – የስካይ ባስን የመሳሰሉ አዳዲስ ባሶችን በአገልግሎት ላይ ያዋለው በቅርቡ ነበር፤ እናም ምቾቱ እምብዛም አልተጓደለብንም፡፡ የመቐለ መንገድ በተለይም ወደትግራይ ክልል እየተቃረብን በመጣን ቁጥር የተራራው ነገር እያስገረመኝ ነበር፤ እያስገረመኝ ብቻ ሳይሆን እያሳሰበኝም ጭምር፡፡ ኢትዮጵያ ይሄን ሁሉ ተራራ ተሸክማ ምን ታደርገዋለች? ወይ አርሳው ቀለብ አታመርት፣ ወይ አፍርሳው ከተማ አትቆረቁርበት – ይሄ ‹‹ጋራ ሸንተረርሽ›› እያልን የምንዘፍንላት ዘፈን ልክ ‹‹ድንግልናሽ›› እያልን ምንም ያልተሠራባት፣ ያልተበላባት መሆኑን በተዘዋዋሪ እንምንናገረው ይሆን?
መቐለ የገባነው በማግስቱ ጠዋት ሁለት ሰዓት ነበር፡፡ (የመጀመሪያውን ቀን አላማጣ ላይ ማደር ነበረብን፤) እንደገባን መዝናኛ ቁርስ ቤት የተባለ የከተማዋ ዝነኛ ቤት ውስጥ የከተማዋን ዝነኛ ቁርስ በላን – ፋታ፡፡ ከዚያ ጉዞ ወደ አፄ ዮሓንስ 4ተኛ ቤተ መንግሥት፡፡
በነገራችን ላይ የመለስ ፎቶ መቐለን እንደአዲስ አበባ አላጥለቀለቃትም፡፡ ይህንን ቀድሞ መቐለ ደርሶ የተመለሰ አንድ ወዳጃችንም አጫውቶን ነበር፡፡ ምክንያቱ ምንድን ነው ለሚለው ጥያቄዬ መልስ ያገኘሁ የመሰለኝ የቴክኖ ሞባይል ማስታወቂያ አንድ ሕንፃ ግድግዳ ላይ በትልቁ በእጅ ተስሎ ስመለከት ነው – ይመስለኛል መቐለ ውስጥ የቢልቦርድ ማተሚያ የለም – ቢኖርም ውድ ነው፡፡
የአፄ ዮሓንስ ቤተመንግሥት በእድሳት ላይ በመሆኑ በርቀት ከማየታችን በቀር፣ የተመለከትነው በፎቶ ነበር፡፡ ፎቶው ላይ ድንጋዩ እንደጎንደር ቤተመንግስቶች ተክቦ ስናይ ‹‹ታዲያ የሚታደሰው ለምን በሲሚንቶ ይለሰናል?›› ብለን ጠየቅን፡፡ ‹‹ቤተ መንግሥቱ በፊት የተለሰነ ነበር፣ ደርግ ነው ልስኑን ያፈረሰው›› አሉን፤ ‹‹ደርግ ቤተ መንግሥቱን በካምፕነት ተጠቅሞበት›› እንደነበርም ነገሩን፡፡ ሙዚየሙ ውስጥ ከአፄው ዙፋን፣ ባለወርቅ ‹ምላጭ› መሳሪያዎች እና የፈረስና በቅሎ ኮርቻዎች በቀር ሌሎቹ የራስ ጉግሣ እና ሌሎችም መሣፍንቶች ቁሳቁሶች ናቸው፡፡ ስለዚህ የእዚህንኛው ሙዚየም ጉብኝታችን ረዥም ሰዓት ሊፈጅ አልቻለም – ጉዞ ወደ ‹ሓውልቲ› – የሰማዕታት መታሰቢያ ሐውልት እና ሙዚየም፡፡
የሰማዕታቱ መታሰቢያ
የሰማዕታቱ ሐውልት ያለበት ጊቢ ውስጥ አርብ እና ቅዳሜ ብቻ ፊልም የሚያሳይ የማቲ መልቲፕሌክስ ሲኒማ ቤት እና የሰማዕታቱ መታሰቢያ ሙዚየም አለ፡፡ ወደሙዚየሙ ገባን ሙዚዬሙ በአቅርቦቱ በአራት ቢከፋፈልም በይዘቱ ግን ፎቶ እና መገልገያ ቁሳቁሶች የሚታዩበት ነው፡፡ የሚገርሙ ጥንታዊ መሳሪያዎች (ጦርነቱ የተካሄደው በምንሊክ ጊዜ ነው እንዴ – የሚያስብሏችሁ)፣ የሬዲዮ ማሰራጪያዎች፣ ሌሎች ቁሳቁሶች እና በርካታ ተራኪ ፎቶዎች ሙዚየሙ ውስጥ ይገኛሉ፡፡
ፎቶዎቹን ስመለከት ሆነ ብዬ እፈልግ የነበረው የአቶ ስዬን እና የአቶ መለስን ፎቶ ነበር፡፡ ብዙዎቹ ታጋዮች ተሰብስበው፣ አፈር ለብሰውና እና ተጎሳቁለው (እየተሳሳቁም፣ በሥራ ላይ ተሰማርተውም ቢሆን) በጋራ የተነሷቸው ፎቶዎች ውስጥ መለስ የሉም፡፡ መለስ ፌስቡክ ላይ ከምናውቃቸው አንዳንድ የብቻዎቻቸው ፎቶዎች እና ከሁለት ስብሰባዎች ውስጥ በቀር ሌላ ቦታ የለም፡፡ አቶ ስዬ ግን ከናካቴው የሉም፡፡ ሌላው የገረመኝ ግን የ1977 የምሁራን ስብሰባ የተባለ ፎቶ ላይ የአቶ በረከት ስምኦንን ፎቶ ማየቴ ነው፡፡ እዚያ ውስጥ ከአቶ በረከት ያቺ ፎቶ በቀር ሁሉም ሰዎች የሕወሓት እና የሕወሓት ብቻ ናቸው፡፡
‹የትሮይ ፈረስ› የሚል መጽሐፍ ላይ አንድ ኤርትራዊ ምሑር ‹ለኤርትራ ሕዝብ የሚበጀው ሰላምና ዕርቅ ነው› በሚል የጻፉትን መጽሐፍ ሽፋን መሳሪያ ባፍጢሙ ተደፍቶ አበባ በቅሎበት ነበር፤ የዚህን መጽሐፍ ምላሽ መለስ ‹የኤርትራ ሕዝብ ትግል ባፍጢሙ አይደፋም› በሚል ሲጽፉ ጠብመንጃውን በሽፋን ገጻቸው አቃንተውታል ሲል አስነብቦናል፡፡ ያቺን የመለስ ምላሽ የተባለችውንም መጽሐፍ ስመለከታት ሰውነቴን ብስጭት ውርር ሲያረገኝ ታወቀኝ፡፡ ዘራፍ አይባል ነገር፡፡
በወዳጆቻችን እዩ የተባልነውን ሁሉ ጊዜ በሚፈቅድልን መሠረት አዳረስነው፤ ከሁሉም ደስ የሚለው ግን የከተማዋ ሕዝብ መስተንግዶ ነው፡፡ ፈገግታውን የማይሰስት ሰው ያለበት ከተማ የሚጎበኝ ባይኖረውም ሳያውቁት ይናፈቃል:: እኔ ግን በማለዳ ወደአክሱም መጓዜ ነው – ስለአክሱም ቆይታዬ የምጽፈው ነገር እንደሚኖረኝም አትጠራጠሩ::