የዶቼ ቬለ መታፈን በኢትዮጵያ
የዶቸ ቬለ የፕሮግራሞች የበላይ ሐላፊ ክርስቲያን ግራምሽ የኢትዮጵያ መንግሥት የዶቸ ቬለ ሥርጭት ከእወካ ነፃ መሆኑን እንዲያረጋግጥ ጠይቀዋል።
የዶቼ ቬለ የአማርኛ ሥርጭት ባለፉት ጥቂት ቀናት ዉስጥ አልፎ አልፎ ግን ሆን ተብሎ እየታፈነ ወይም ጃም እየተደረገ መሆኑንን የጣቢያዉ የቴክኒክ ባለሙያዎች አስታወቁ።የሥርጭቱን አድማስና ጥራት የሚከታተሉት የቴክኒክ ባለሙያዎች እንዳሉት የአማርኛዉ ዝግጅት የሚሠራጩባቸዉ የሞገድ መስመሮች በፈረቃ በሚመስል መልኩ እየታፈኑ ነዉ።ዶቸ ቬለ እርምጃዉን ተቃዉሞታል።የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ግን ስርጭቱ ሆን ተብሎ ሥለመታፈኑ የምናዉቀዉ ነገር የለም ብለዋል።ነጋሽ መሐመድ ዝር ዝር ዘገባ አለዉ።
የተለያዩ አድማጮች ከተለያዩ አካባቢዎች በላኳቸዉ የSMS መልዕክቶች የዶቸ ቬለ ሥርጭት አንዳዴ ሙሉ በሙሉ፥ ሌላ ጊዜ በከፊል፥ አልፎ አልፎ እያሰለሰ እንደሚታፈን፥ ወይም በስርጭቱ መሐል ያልተለመደ ባዕድ ረባሽ ድምፅ እንደሚገባበት በተደጋጋሚ እያስታወቁን ነበር።የዶቸ ቬለ የሥርጭትና የሞገድ መስመሮች ጥራት ክፍልም ይሕኑ ነዉ ያረጋገጠዉ።
የክፍሉ የቴክኒክ ባለሙያዎች ባደረጉት ክትትል መሠረት ቢያንስ በሁለት የሞገድ መስመሮች የሚተላለፈዉ የአማርኛ ሥርጭት ሆን ተብሎ መታፈኑ ወይም መታወኩ ተረጋግጧል።የቅርቡ አብነት የትናንቱ ሥርጭት ነዉ።የቴክኒክ ክፍሉ እንዳረጋገጠዉ ትናንት ከተለያዩ የማሰራጪያ ሞገዶቻች አንዱ ከ11 ሠዓት ከ14 ደቂቃ እስከ 11 ሠዓት 38 ደቂቃ ድረስ፥ ሁለተኛዉ ደግሞ ከ11: 14 ደቂቃ እስከ 11 ከ33 ደቂቃ ድረስ ታፍኖ ወይም ጃም ተደርጎ ነበር።
ስርጭቱ የሚታፈነዉ ወይም የሚታወከዉ ከኢትዮጵያ አካባቢ እንደሆነ ባለሙያዎቹ ጠቁመዋል። የዶቸ ቬለ የፕሮግራሞች የበላይ ሐላፊ ክርስቲያን ግራምሽ የኢትዮጵያ መንግሥት የዶቸ ቬለ ሥርጭት ከእወካ ነፃ መሆኑን እንዲያረጋግጥ ጠይቀዋል።
«ይሕ አዲሱ እርምጃ ዶቸ ቬለ ሚዛኑን የጠበቀ ፖለቲካዊ፥ ምጣኔ ሐብታዊ እና ማሕበራዊ ጉዳዮችን የሚዳስስ መረጃ ለኢትዮጵያና ለአካባቢዋ አድማጮች እንዳያሰራጭ ያደናቅፈዋል።ሥለዚሕ የኢትዮጵያ መንግሥት የዶቸ ቬለ የአጭር ሞገድ መስመሮች ከእወካ ነፃ መሆናቸዉን እንዲያረጋግጥ እጠይቃለሁ።»
የዶቸ ቬለ የአማርኛ ሥርጭት ሆን ተብሎ ሲታፈን ወይም ሲታወክ ያሁኑ የመጀመሪያዉ አይደለም። በቅርቡ ብቻ በሁለት ሺሕ አመተ-ምሕረት ለተከታታይ ወራት እና ባለፈዉ አመት ግንቦት ወር አካባቢም ታፍኖ ነበር።በዚያን ወቅት ለደረሰዉ አፈና ለፕረስ ነፃነት የሚሟገቱ ወገኖች ባንድ ወይም በሌላ መልኩ የኢትዮጵያ መንግሥትን ወቅሰዉ ነበር።
የኢትዮጵያ መንግሥት የያኔዉን ወቀሳ አልተቀበለዉም ነበር። አሁንም የኢትዮጵያ የመገናኛ ወይም የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መስሪያ ቤት ምክትል ሐላፊ አቶ ሽመልስ ከማል «ዶቸ ቬለ አልታወከም» ብለዋል።
የዶቼ ቬለ የቴክኒክ ባለሙያዎች እንደሚሉት ሰሞኑን የደረሰዉ አፈና፥ እወካ ወይም ጃሚንግ ከዚሕ ቀደም ከደረሰዉ ጋር ተመሳሳይ ነዉ።የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ምክትል ሐላፊ አቶ ሽመልስ ከማል ግን መጀመሪያ አጣሩ ነዉ ያሉት።
ዶቸ ቬለ የአማርኛዉ ክፍል ዝግጅቶቹ ከአድማጮቹ እንዲደረስ ወትሮ ከሚታወቁት የአጭር የሞገድ መስመሮቹ በተጨማሪ በሁለት አዳዲስ ሞገዶችም እያሰራጨ ነዉ።
ነጋሽ መሐመድ
ሒሩት መለሰ