የሁለት ሐውልቶች ዕጣ 3

የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ችግርን ለመቅረፍ እንዲያስችል በሚዘረጋው የቀላል ባቡር መሥመር ዝርጋታ ምክንያት የብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ሐውልት እንደሚነሳ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አስታወቀ፡፡ 
አቶ አበበ ምህረቱ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የኮምኒኬሽን አገልግሎት ክፍል ኀላፊ የሐውልቱ መነሳት ያሰፈለገበት ዋነኛ ምክንያት ምን እንደሆነ ሲገልጹ “በቀላል ባቡር መስመር ዝርጋታ ምክንያት መንገዱ ከዳግማዊ አፄ ምኒልክ አደባባይ ጀምሮ ወደ አውቶቡስ ተራ የሚወስደው መንገድ አትክልት ተራ ድረስ ባቡሩ በዋሻ ውስጥ ነው የሚያልፈው፡፡ በተጨማሪም የባቡሩ መስመር ከምኒልክ አደባባይ ወደ ሽሮ ሜዳ ይዘረጋል፡፡ እንደሁም ከአውቶቡስ ተራ ወደ ቅድስት ልደታ ለማርያም የሚታጠፈው መስመር መነሻም ነው፡፡ 
ስለዚህ በአሁኑ ወቅት ከማዘጋጃ ቤት አጥር ጀምሮ ወደ ትግበራ የተገባበት ሁኔታ ላይ እንገኛለን፡፡ ሥራው ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ሀውልት ሲደርስ ስዊድን አገር የሚገኘውና ከፍተኛ ልምድ ያለው ዓለም አቀፍ አማካሪ ድርጅት ሥራውን በበላይነት የሚቆጣጠረው ሲሆን በሚያስመጣቸው ባለሙያዎች አማካይነት በክብርና በጥንቃቄ ሐውልቱን አንሰቶ የዋሻው ግንባታ እንደተጠናቀቀ አንዲትም ሣ/ሜትር ሳይዛነፍ እንደነበረ በቦታው ላይ በክብር እንዲያስቀምጥ ይደረጋል፡፡ ሐውልቱ የሀገር ቅርስና ሀብት ነው፤ ለዚህም ከፍተኛ ጥንቃቄ የተሞላበት ሥራ ይሰራል፡፡” ብለዋል፡፡