መጋረጃው ያልተነሳ ተውኔት፣ ያልተፈታ እንቆቅልሽ! በልጅግ ዓሊ

ግን መጋረጃው ያልተነሳ ተውኔት ፣ ያልተፈታ፣እንቆቅልሽ አለውና ጨለማ፣
ነፋስ – እሳተ ገሞራን ሊታቀፍ ይቻላልና ጠፍ ባድማ፣
ዐይን ያለው ይይ !
ልብ ያለው ያስተውል !
ጆሮ ያለው ይስማ !

ደበበ ሰይፉ ለራስ የተጻፈ ደብዳቤ

በደርግ ዘመን የነበረችውን እናት ሃገራችን ኢትዮጵያ እንሽጣት ብለን ብንስማማ ስንት ብር ነበር የምታወጣው? በሻዕብያ ክብሩ ተዋርዶ ያ ሁሉ መከራ የደረሰበት የኢትዮጵያ ሠራዊት ስንት ብር ነበር የተሸጠው? በአዲስ አበባ ለማኝ ሆኖ ክብሩ እንዲዋረድ የተደረገው ሠራዊት ስንት ብር ነበር ያወጣው? አየር ኃይል ፣ ባሕር ኃይል . . . ሌሎቹም የሠራዊቱ ክፍሎች ስንት ብር ነበር ሊሸጧቸው የተስማሙት? ያ ሁሉ ጀኔራል፣ ያ ሁሉ መኰንን ከኛ ጋር ይሞታሉ ብለው ያሰቧቸው መሪዎቻቸቸው ስንት ብር ነው ያተረፉባቸው?

በኢሳት ቴሌቪዥን ሰሞኑን በተከታታይ ይቀርብ የነበረውን የቀድሞው የኢሠፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የነበሩት<<የጓድ ካሣ ከበደን>> ቃለ መጠይቅ የመጨረሻውን ክፍል ከሰማሁ በኋላ የተሰማኝ ይህ ነበር።

የደርግ የመጨረሻ ቀናት ምሥጢር አሁኑም ገና የተዳፈነ፣ መጋረጃው ያልተነሳ ተውኔት ነው። ለኢትዮጵያ ሕዝብ ድብቅ የሆኑ ግን የሃገሪቷን ሁኔታ እስከናካቴው የለወጡ ያልተፈቱ እንቆቅልሾች አሉት። የዚህ ተከታታይ ቃለ መጠይቅ የመጨረሻ ክፍል ፍንትው አድርጎ ያሳየን በሃገራችን ላይ ምን ያህል ክህደት እንደተፈጸመባት ነው። ያም ብቻ አይደለም፣ የደርግ ሹማምንት እንደገና ወደ ሥልጣን ለመመለስ የሚደረገውን ትግል እንደቀጠለ መሆኑንም አስገንዝቦናል። ማን ከማን ጋር እንደተሰለፈም ሰምተነዋል። የተውኔቱ መጋረጃው ሙሉ በሙሉ እንዳልተከፈተ ደግሞ ግልጽ ነው።

የኢትዮጵያ ሠራዊት ገና ከቀበሮ ጉድጓዱ ሳይወጣ አዲስ አበባ ላይ መሪዎቹ ሃገሩን ሊሸጡ በገንዘብ ይደራደሩ እንደነበር ከቃለ መጠይቁ ተረድተነዋል። በዚህ ድርድር ውስጥ የግል ኪስ መዳበር ፣ የራስን ቆዳ ማዳን እንጂ የሃገሪቱ፣ የሠራዊቱ የወደፊት ዕጣ አልተካተተም። የአሜሪካን ዶላር የተመደበለት የፈላሻዎች ሕይወት መትረፍ እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝብ ምን ወደፊት ሊገጥመው እንደሚችል ያሰበበት አልነበረም። ዛሬ በካሳ ከበደ የተሰጠው ቃለ መጠይቅ ምንም እንኳን አሁንም በውሸት የታጠረ ቢሆንም ሃገራችን ላይ የተፈጸመው ክህደት ክብደቱ ምን ያህል እንደሆነ ጭላንጭል አሳይቶናል።

በእስራኤሎች እንደ ምሥጢር የማይቆጠረውና ለእነርሱ የጀግንነት፣ ለእኛ ደግሞ የክህደት ታሪክ የሆነው የአደባባይ ምሥጢር ሆኗል። ኦፕሬሽን ሰሎሞን(operation solomon) በሚባለውንና በ1991 እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ቤተ እስራኤሎችን (ፈላሻዎችን) ወደ እስራኤል ለመውሰድ በተደረገው እንቅስቃሴ ቀንደኛ ተሳታፊ የነበሩ የውጭ ሃገር ዜጎች ግማሾቹ መጽሐፍ ሲጽፉ፣ ሌሎቹ ደግሞ ቃለ መጠይቅ እየሰጡ ነው። አንዳንዶች ደግሞ ምንም ሳይናገሩ ከዚህ ዓለም አልፈዋል።

በወቅቱ የዚህን አስከፊ የክህደት ወንጀል በደንብ የሚያውቁ፣ በኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም በሠራዊቷ ላይ በደረሰውን ግፍ ቀጠጥተኛ ተሳታፊነት የነበራቸው፣ ሁለት ግለሰቦች ሁኔታውን ምንም ሳያጋልጡ አልፈዋል። አንደኛው የወያኔ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበረው መለስ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የደርግ የስለላ ሚኒስተር የነበረው ተስፋዬ ወልደ ሥላሴ ነው ። የእነዚህ ግለሰቦች ማለፍ አንዳንድ የተውኔቱን ተሳታፊዎች ዳግም ወደ መድረክ ብቅ እንዲሉ ገፋፍቷቸዋል። ቢሆንም እውነቱን ደብቀው መቆየት ይችሉ ይሆን?

ይህንን የሃገራችንን አስከፊ ትዝታ በሚመለከት በብዙ ጸሐፊዎች ተጽፈው ለንባብ የበቁትን ጽሁፎች ስንመለከት ሃገራችን ዛሬ ለደረሰባት መከራ ለንዋይና ለሥልጣን ያደሩ ግለሰቦች ታላቅ አስተዋጽዖ ማድረጋቸውን እንረዳለን። ዛሬ እንደ ጀግና በአንዳንድ <<ነፃ>>ጋዜጠኛ ነን በሚሉ አሳታሚዎች የሚሞካሸው መንግሥቱ ከሃገሪቷ ቤተመንግሥት የነበረውን ወርቅ ዘርፎ እንደሄደ በዚያን ወቅት የእርሱን ወደ ዚምባቡዌ ሽሽት ያዘጋጁ የውጭ የስለላ ድርጅት አባሎች በሰጡት ቃለ መጠይቅ በግልጽ አስቀምጠውታል።

Stephen Spector በጻፉት <> – በተሰኘው መጽሐፍ ውስጥ ይህ የክህደት ተግባር በሰፊው የተገለጸ ሲሆን፣በሴራው ውስጥ ተሳተፋ የነበሩትን እማኞችም ምሥክርነት ተመዝግቧል። በዚህ ተግባር ላይ የተሳተፉ የተለያዩ ድርጅቶች ለጸሐፊው በሰጡት ፍቃድ፣ በተለይም በኒውዮርክ የሚገኘው JDC (American Jewish joint distribution committee) የሚባል ድርጅት ምስጋና ይግባውና የተሰበሰቡትን ዶክመንቶች በመፍቀዱ ምክንያት ይህ ደባ ለአንባብያን እይታ ሊጋለጥ በቅቷል።

በተጋለጠው ደባ ውስጥ ዋና አቀነባባሪ <<ጓድ ካሣ ከበደ ተሰማ>> መሆናቸውም በሰፊው ተጠቅሷል። እሳቸውም በአሁኑ ወቅት ባገኙት አጋጣሚ እውነቱን በማወላገድ አዲስ ስብዕና ለመላበስ ጥረት እያደረጉ ነው። በዚህም ምክንያት ለኢሳት በአራት ተከታታይ ፕሮግራም ቃለ መጠይቅ ሰጥተዋል። <<ጓድ ካሣ ከበደ>> የኢሠፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የፓርቲው የውጭ ጉዳይ ሃላፊ የነበሩ ሲሆን በደርግ መውደቂያ ሰሞን ከፍተኛ የሃገሪቷ ባለሥልጣን ነበሩ። ደርግ ሥልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ የአረመኔው የመንግሥቱ ኃይለማርያም የቀኝ እጅ ሆነው አገልግለዋል። በሃገሪቱ ውስጥ ለተፈጸሙት በደሎች በቀጥታም ይሁን በተጓዳኝ ተጠያቂነት አለባቸው። በአሁኑ ወቅት በሰሜን አሜሪካ ኗሪ ናቸው።( ይህንንም ቢሆን በዚሁ ደባ ምክንያት የተሸለሙት ነው) በተለይ ከእስራኤላውያን ጋር የቅርብ ግንኙነት ስለነበራቸው የቤተ እስራኤሎቹን ሽያጭ በሚመለከት ቀጥተኛ ተሳትፎ አድርገዋአል።

<< ጓድ ካሣ>> ለኢሳት ይህንን በሚመለከት የሰጡት ቃለ መጠይቅ ብዙ ሃሰትን ያካተተ ነው። በዚህ ቃለ መጠይቅ በግል ያገኙትን የነዋይ ጥቅም እንደ ዋዛ አልፈውታል። በድርድሩ ወቅት ቤተሰቦቻቸውን ቀድመው በማሸሽ እሳቸውም ከአንደኛው የእስራኤል ዲፕሎማት ከሃገር ለመውጣት መዶላታቸውን ክደው ሳይታሰብ የተሳካ ለማስመሰል ጥረዋል። እስካሁንም ለመንግሥቱ ኃይለማርያም ያላቸውን ታማኝነት አረጋግጠዋል። ከእስራኤል የተገኘውን የኢትዮጵያውያን ፈላሻዋች << ሽያጭ>> ገንዘብ (35 ሚሊዮን ዶላር) ለግላቸው ለማድረግ የግላቸውን የባንክ ቁጥር መስጠታቸውን ሳይናገሩ አልፈውታል። በተለይ በደርግ መንግሥት ውስጥ በግላቸው በምንም ወንጀል ተጠያቂ እንዳልሆኑ በተካኑበት ራስን የማዳን ጥበብ ተጠቅመው ሊያስረዱ ቢጥሩም፣ እውነቱ ግን ለአረመኔው መንግሥቱ የግል አማካሪና ለአገዛዙም ፈላጭ ቆራጭ እንደነበሩ ይታወቃል። ስለ << ጓድ ካሣ >> ጠባይ ከውጭም ይሁን ከሃገር ውስጥ ብዙ ምስክርነት ተገኝቷል።
በተለይ አብረዋቸው የሠሩ አሜሪካውያንና እስራኤላውያን ስለ እሳቸው ሲያስረዱ፡ – ከላይ በተጠቀሰው መጽሐፍ፡ -ገጽ 33 ላይ ።

Kassa’s tactics vexed and occasionally enraged the Israelis, some of whom later called him a liar. “Kassa never tells the truth” said one. He can lie to your face”. Another more diplomatically, said that he had never known anyone who related to the truth in quiet the way that kassa did.

ካሣ የሚጠቀምባቸው ዘዴዎች እስራኤላውያን ባለስሥልጣናትን የሚያስቆጣ አንዳንዴም ከአቅም በላይ የሆነ ንዴት ውስጥ የሚከት ነበር። አንዳንዶቹ በኋላ ውሸታም ብለው እስከመጥራት ደርሰዋል። አንድ ባለስልጣን <<ካሣ በምንም ዓይነት እውነት አይናገርም። ፊትህም ላይ መዋሸት አይከብደውም>> ብሎ እስከመናገር ደርሷል። ሌላው ባለሥልጣን ለስለስ ባለ አቀራረብ እንደ ካሣ ከእውነት ጋር የሚያደርገው ዝምድና አስገራሚ የሆነ ሰው አጋጥሞት እንደማያውቅ ተናግሯል።

ከዚህ እንደምንመለከተው ካሣ ውሸት መናገር የለመደባቸው፣ አልፎም ተርፎም ባሕሪያቸው መሆኑን ነው። ብዙዎቹ በዚህ እንቅስቃሴ የተሳተፉ ዲፕሎማቶች ይህንኑ መስክረዋል። ለኢሳት በሰጡት ቃለ መጠይቅ የምንረዳው ራሳቸውን ንፁህና ምንም ወንጀል ያልሠሩ አድርገው ሌሎችንን ለመወንጀ ፍላጎት ነው። በተለይ እስራኤሎች በደርግ መጨረሻ የገንዘብ ሚኒስትር የነበረውን ሰው በሃሰት ሲወነጅሉ እጅ ከፍንጅ ይዘዋቸዋል።

በዚሁ መጽሐፍ ውስጥ በገጽ 34 ላይ እንዲህ ይላል፡ –

ዩሪ ሉብራኒ (Uri Lubrani) የተባለ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የእስራኤል አምባሳደር የነበረ ሰው በዚሁ መጽሐፍ ገጽ 34 ላይ ስለ ካሣ ብልጣ ብልጥ ነጣቂ ቀበሮና ስግብግብ እንደነበረ አውቃለሁ ብሎ ተናግሯል።

<< I also always knew that he was a wily fox and greedy >>
ይህንን << ጓድ ካሣን >> የተጠናወታቸውን የሥልጣንና የንዋይ ፍቅር የውጭ ሰዎች ምስክርነት ብቻ ሳይሆን ውስጥ በሃገር ውስጥ የነበሩ ሌሎች ጓዶቻቸውም ቀደም ብለው አጋልጠውታል።

እንግዲህ ከዚህ በመነሳት በኢሳት የተላለፈው<<የጓድ ካሣ>> ቃለ መጠይቅ ተአማኒነት አጠያያቂ የሚያደርገው ይህ የመዋሸት ጠባይ አሁን እየቀጠለ መሆኑን ስንመለከተው ነው። ይህ ሁሉ እንቅስቃሴ <<ጓድ ካሣ ከበደ >> አሁን በኢሳት እንደሰጡት ለሃገር ሲሉ የደከሙበት ሳይሆን ከግል ንብረት ማካበት ጋር የተያያዘ ለመሆኑ ብዙ ማስረጃ ማቅረብ ይቻላል። ለማስረጃ ያህል <<ጓድ ካሣ>> በዚህ አስከፊ በሆነው የክህደት ተግባር ውስጥ ምን ያህል በነዋይ እንደተደጎሙ ማስረዳት ይቻላል። እሳቸውም ቢሆኑ በጥሬ ገንዘብ ያገኙትን ካዱ እንጂ በአሜሪካ ሃገር የተደላደለ ሥራና መኖሪያ ከሃገር ሽያጩ እንዳገኙ አልደበቁም።

ይህንን በሚመለከት በዚሁ መጽሐፍ ገጽ 121 ላይ እንዲህ ተቀምጧል።

Kassa then told Jackson that his “personal situation” was solved. It was in deed! Numerous sources confirm that, without checking with the Israelis, Jackson had offered kassa a $3.4 million cash side deal on behalf of Nate Shapiro and AAEJ. Using the rough figure of 17000 Jews, this amounted to a $200 – a head- personal payment to kassa upon completion of the airlift, in addition to the larger sum being negotiated.

ካሣ ለጃክሰን << የግል ችግሩ>> መፍትሔ እንዳገኘ ነግሮታል። በእውነትም ከሆነ ከብዙ ምንጮች የተገኘው መረጃ ጃክሰን ሌሎቹን ሳያማክር 3.4 ሚሊዮን ዶላር በጎን በ ኔት ሻፐሮና የሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ አይሁዶች ድርጅት (Nate Shapiro and AAEJ ስም ቃል ገብቶለታል። ይህ ሂሳብ የሆነውም በግለሰብ 200 ዶላር ሲሆን ከ17000 ፈላሻዎች የሚገኝ ነው። ገንዘቡም የሚገኘው የፈላሻዎቹ ጉዞ ከተጠናቀቀ በኋላ ከዚህ በፊት ከተስማሙት 35 ሚሊዮን ዶላር በተጨማሪ ይሆናል።

ከላይ እንደተመለከተው ካሣ ከበደ በእያንዳንዱ ፈላሻ ስም ሁለት መቶ የአሜሪካ ዶላር የተቀበሉ ሲሆን ባጠቃላይ 3.4 ሚሊዮን ዶላር አግኝተዋል። እንግዲህ ከዚህ በላይ እንደምንመለከተው ያ ሠራዊት ፣ ያ ሕዝብ የተሸጠው በዚህና በሌሎች ገና ወደፊት በሚገለጡ ገንዘብ ነው። ገና ሠራዊቱ ትጥቅ ባልፈታበት ወቅት አንዳንድ የደርግ ባለስልጣኖች ከወያኔ መሪዎች ባነሰ ሁኔታ የሃገራቸውን ጉዳይ ችላ በማለት ለንዋይ መራወጣቸው በምዕራብያውያን ዲፕሎማቶች ትዝብትን አትርፎላቸዋል።

ካሣ ከበደ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ላይ ይህ የፈላሻዎችን ወደ እስራኤል የመውሰድ ጉዞ በ35ሚሊዮን ዶላር ክፍያ መሆኑን አምነዋል። ግን እሳቸው እንደሚሉት እሳቸው የታገሉት ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው ያሉት ሃሰት ነው። የተሠራው ሻጥር ግን ግልጽ ነው። ገንዘቡን ለማዛወር የባንክ ቁጥር በተጠየቀ ጊዜ ከካሣ ከበደ የተሰጠው የባንክ ቁጥር የኢትዮጵያ መንግሥት ሳይሆን የግላቸው ነበር። ምስክሮቹ እንዲህ ብለው ጽፈውታል።

በዚሁ መጽሐፍ ገጽ 161 ላይ እንዲህ ይላል፡ –

The real problem was that the number was not an official government account at all. Rather it was for a private individual account, as half a dozen highly placed Israeli and American sources later confirmed.
The account number revealed the bearer’s name Barack told me. In view of the legal implications, however, he refused to disclose the name – though he did say that it was Ethiopian. “It can be published in ten years he said.

Since kassa had supplied the bank account number earlier that day, suspicion fell on him. A senior Israeli official who played a principal role in operation Solomon told me with certainty that Kassa was the one trying to take the $ 35 million.
ዋናው ችግር ገንዘቡ እንዲተላለፍ የተሰጠው የባንክ ቁጥር የግል እንጂ የኢትዮጵያ መንግሥት ያልተያዘ መሆኑ ነበር። ይህንንም ከግማሽ ደርዘን በላይ የሆኑ የታመኑ የአሜሪካና የእሥራኤል ምንጮቸች በሚገባ አረጋግጠዋል።

የተሰጠው የባንክ ቁጥር የባለቤቱን ስም ይዟል። በማለት ባራክ ነገረኝ። የሚስከትለውን ሕጋዊ ችግሮች በመፍራት የባንኩ ቁጥር ባለቤት ስም ከመናገር ተቆጠበ። ነገር ግን ኢትዮጵያዊ መሆኑን አረጋግጧል። ቀጠል አድርጎም በአስር ዓመት ውስጥ በግልጽ ሊወጣ ይችላል ብሏል።

ካሣ ነበር በዚያኑ ዕለት የባንኩን ቁጥር የሰጠ በመሆኑ ጥርጣሬው ሙሉ በሙሉ በእሱ ላይ ወድቋል። ለብዙ ዓመታት በሥልጣን ሆኖ ያገለገለ እስራኤላዊ በእርግጠኝነት ካሣ 35 ሚሊዮን ዶላሩን ሊወስድ ሲጥር እንደነበር ነግሮኛል።

ለዛሬው እዚህ ላይ ላብቃና በሚቀጥለው ስለ መንግሥቱ ወደ ዝምባቡዌ መሄድ ከዛ ጋር ተያይዞ ስለተደረገው ክህደት የተጻፈውን ለማቅረብ እሞክራለሁ።
ስለ ኢትዮጵያ የሚያስብ በሰላም ይክረም !
ይቀጥላል።
[email protected]
01/12/2012