የሙስሊሞች እንቅስቃሴ ክፍል 2 – ምላሽ ለዶር ብርሃኑ ነጋ አማኑኤል ዘሰላም

መግቢያ

አንባቢያን ሰፊ ግንዛቤ ይኖራቸው ዘንድ፣ የሙስሊም አክራሪነት እንዴትና ከየት እንደተጀመረ፣ በአሁኑ ወቅትም በአለማችን ምን አይነት ችግር እያስከተለ እንዳለ ለማሳየት ሞክሪያለሁ። በተለይም ሳዉዲ አረቢያ ፣ ካላት የነዳጅ ክምችት የተነሳ በምታገኘዉ ፔትሮ ዶላር፣ ምን ያህል፣ ለሰብዓዊነት ክብር የሌለዉን አክራሪነት ለማስፋፋት የምትጫወተዉ አሉታዊና ሰይጣናዊ ሚና ፣ የማያሻሙ መረጃዎች በማስቀመጥ ግንዛቤ እንዲኖር ለማድረግ ሞክሪያለሁ። በክፍል ሁለት ትኩረቴን በዉጭ አገራት ካሉ የአክራሪነት እንቅስቃሴዎች አንስቼ በአገራችን እየታዩት ወዳሉት የሙስሊም እንቅስቃሴዎች እዞራለሁ።

ኦፌሴላዊ በሆነዉ የሕዝብ ቆጠራ ዉጤት መሰረት ሙስሊም ማህበረሰብ ወደ 36 ሚሊዮን ይጠጋል። በአኗር መስኪድ፣ በአዋሊያ ኮሌጅ እንዲሁም በተወሰኑ ሌሎች ቦታዎች የሚደረጉት እንቅስቃሴዎች ሙስሊሙን በሙሉ ይወክላሉ ብሎ መናገር ትንሽ ያስቸግራል። በመሆኑም የሙስሊሞች ተቃዉሞ ስል፣ የተወሰኑ ሙስሊሞችን ተቃዉሞ ማለቴ እንጂ፣ ጠቅላላ የሙስሊሙ ማህበረሰብን ተቃዉሞ ማለቴ እንዳልሆነ እንዲታወቅልኝ እፈልጋለሁ።

ኢሕአዴግና ሙስሊሞች

«ኢሕአዴግ መስኪዶችን ዘግቶ የዜጎችን የእምነት ነጻነት እየተጋፋ ነዉ» የሚል ክስ የሚያቀርቡ አሉ። በአገራችን ኢትዮጵያ ከነበሩት መንግስታት በላይ፣ የሙስሊሙ ማህበረሰብ መብት በስፋት እንዲከበር ያደረገ ፣ እንደ ኢሕአዴግ መንግስት ያለ ይኖራል ብዬ አላስብም። ከተገነቡት አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናት ጋር ሲነጻጸሩ፣ የተሰሩ አዳዲስ መስኪዶች ቁጥር እጅግ በጣም ይበልጣል። በተለያዩ የእስልምና አመት በዓሎች ወቅትም፣ ሙስሊሙ፣ በታላቁ ስታዲየምና በመሳሰሉ ሰፋፊ ቦታዎች በነጻናትና ያለ ገደብ፣ ተሰባስቦ አምልኮዉን እያደረገ ነዉ። በመስኪዶች ጸሎት እንዳያደርግ የተከለከለበትም ሁኔታ እንዳለ በመረጃ የሚያሳዩ ዘገባዎች አላነበብንም። (መስኪዶች ተቃውሞ የሚሰማባቸውም ቢሆኑም አልተዘጉም)

መረጃዎች እንደሚያሳዩት አሁን ያለው ችግር ፣ ኢሕአዴግ የሃይማኖትን መብት በመርገጡ የመጣ ችግር ሳይሆን፣ በሙስሊሞች መካከል የተፈጠረ አለመስማማት፣ ያመጣዉ ችግር እንደሆነ ነዉ።

ለመጀመሪያ ጊዜ በሙስሊሙ መካከል ችግር እንዳለ የተሰማው የአዋሊያ ኮሌጅ ተማሪዎች ተቃውሞ ባሰሙበት ወቅት ነበር። መጅሊሱ (ከፍተኛ የእስልምና ጉባኤ ምክር ቤት – በኦርቶዶክ ሲኖዶስ እንደሚባለዉ) «ከሳዉዲ የመጣ የዋሃቢዝም አክራሪነት መንፈስ እየበዛ ነው» በሚል በምርጫና በፍላጎት ላይ የተመሰረተ ለዘብተኛና ሰላማዊ የሆኑ የእስልምና አስተምህሮዎች በአዋሊያ እንዲሰጡ ወሰነ።

የመጅሊሱን ዉሳኔ ጥቂት ተማሪዎች ተቃወሙ። በሙስሊሞች መካከል ችግር እንዳለ ያኔ በይፋ አወቅን። የተነሳዉን የተማሪዎች ረብሻ ለማረጋጋት ፖሊስ ጣልቃ ገባ። ጥቂት ሳምንታት እንዳለፉ «ብዙ ሙስሊሞችን እወክላለሁ፣ የብዙ ሙስሊሞች ፊርማ አለኝ» የሚል ኮሚቴ ተቋቋመ። ኮሚቴዉ ጥያቄዎች ይዞ ወደ መንግስት ሄደ፡

በኮሚቴዉ የቀረቡ ጥያቄዎች የሚከተሉት ነበሩ፡

1. ሕዝበ ሙስሊሙ የመረጣቸዉ መሪዎች በመጅሊሱ እንዲቀመጡ
2. የአሕባሽ አስተምህሮ «ከእስልምና መሰረታዊ አስተምህሮ የወጣ ነዉ» በማለት በእስልምና ተቋማት አስተምህሮ እንዳይሰጥ
3. የአዋሊያ ኮሌጅ በቦርድ እንጂ በመጅሊሱ እንዳይመራ

እንግዲህ አንድ ነገር ልብ ልንል ያስፈልጋል። ከጅምሩ አለመስማማቱ፣ ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት፣ በሙስሊሞች በራሳቸው መካከል የተፈጠረ እንጂ፣ በመንግስትና በሙስሊሙ መካከል እንዳልነበረ ነዉ። የሙስሊሙን ተቃዋሞ እመራለሁ የሚለዉም ኮሚቴ ጥያቄዎቹን ይዞ የሄደዉም፣ ወደ መንግስት ነበር።

«መጅሊሱ ብቃት የለዉም፣ እንደገና የመጅሊስ ምርጫ መደረግ አለበት» ለሚለው የመጀመሪያዉ የኮሚቴዉ ጥያቄ መጅሊሱ ተስማማ። «የአህበሽ አስተምሮ በማናቸውም የእስልማና ተቋማት መሰጠት የለበትም» የሚለዉ የኮሚቴዉ ሁለተኛ ጥያቄ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀረ። ሙስሊሙ በግዴታ እንዲማር እስካልተደረገ ድረስ «መማር የሚፈልግ ፣ የመማር መብቱ ሊጠበቅለት ይገባል» የሚል ዉስኔ ተሰጠ። የአዋሊያ ኮሌጅን በተመለከተ ፣ መጅሊሲ የበላይ ጠባቂ ሆኖ በቦርድ እንዲተዳደር ስምምነት ተደረሰ።

ኮሚቴዉና የሚደግፏቸው ሙስሊሞች በዚህ አልተደሰቱም። ምርጫ እንዲደረግ መወሰኑ ጥሩ ሆኖ ሳለ፣ ምርጫዉ የት መደረግ አለበት በሚለው ላይ አለመስማማት ተፈጠረ። የአህበሽ አስተምህሮ፣ በፍላጎትም እንኳ መሰጠት የለበትም የሚል አቋም ተያዘ። በጠረቤዛ ዙሪያ ማግኘት ያልተቻለዉን፣ በሰላማዊ ተቃዉሞ ለማግኘት የተቃዉሞ እንቅስቃሴዎች መሰማት ጀመሩ። ከዚያም ጋር በተገናኘ የኮሚቴዉ አንዳንድ አባላት ታሰሩ። ለዉይይትና ለምክክር ጊዜ ሰጥቶ ፣ ሁሉም አሸናፊ የሆኑበትን ሁኔታ ከመፍጠር ይልቅ፣ ብዙዎች ተቃዉሞ እያሰሙም፣ የመጅሊሱ ምርጫ ቀጠለ።

የአህበሽ አስተምሮን በተመለከተ

በአህበሽ አስተምሮ ዙሪያ ቅር የተሰኙ የሙስሊም ተቃዋሚዎች «የአህበሽ አስተምህሮ በግድ እንድንማር እየተደረግን ነዉ» በሚል መጅሊሱን ብቻ ሳይሆን ኢሕዴግን ከሰሱ። አህበሽን የሚያወግዙ የተለያዩ ጽሁፎች በየድህረ ገጹ ተለቀቁ። አህበሽ ጸረ-እስልምና ፣ ከዉጭ የመጣ መጤ ትምህርት እንደሆነም በስፋት መነገር ጀመረ።

እስልምና አንድ ሆኖ፣ በአምልኮ ስርዓት እንዲሁም በቁራን ዉስጥ ባሉ አንዳንድ ሱራዎችም(ምእራፎች) አተረጓጎም ዙሪያ የሚለያዩ የተለያዩ አስተምህሮዎች አሉ።

ለምሳሌ የዋሃቢዝም አስተምህሮን ካየን ፣ በመጀመሪያዉ ክፍል ጽሁፌ በስፋት ለማሳየት እንደሞከርኩት፣ በአገራችን የተለመደው የመዉሊድ ባእል እንዳይከበር ይከለክላል። ሴቶች በሕይወት እያሉ እንዲገነዙ ያስገድዳል። እስላማዊ የሻሪያ መንግስት መቋቋም አለበት ይላል።

ወደ አህበሽ አስተምህሮ ስንሄድ መዉሊድን ማክበር አይከለክልም፤ ሴቶች ሙሉ ለሙሉ በሕይወት እንዲገነዙ አያዝም፣ ሙስሊሙ ከሌሎች አምነቶች ጋር ተከባብሮ መኖር አለበት ይላል፤ የእስላማዊ ሻሪያ መንግስትም እንዲቋቋም አላማዉ አያደርግም።

የአህበሽ አስተምሮን የጀመሩት የሐረር ተወላጅ የሆኑት ኢትዮጵያዊዉ አብዱላ አል ሃሪሪ ናቸዉ። ስለዚህ አህበሽ ስሙ እንደሚገልጸዉ ከሃበሻ (ኢትዮጵያ) የተነሳ አስተምህሮ ነዉ። በአገራችን ያሉ ሙስሊሞች ከሌሎች እምነት ተከታዮች ጋር በሰላም ተከባብረዉ የኖሩ እንደመሆናቸው፣ ያንን የመቻቻልና የመከባበርን መንፈስ ያንጸባረቀ እንደ ሊባኖስ ባሉ፣ በርካታ እምነቶች ባሉበት አገር፣ በስፋት ተቀባይነት ያለዉ፣ በተለይም ከዋሃቢዝም በተቃራኒዉ የቆመ አስተምህሮ ነዉ።

ከሳዉዲ ለመጣዉ አክራሪ የዋሃቢዝም አስተምህሮ፣ ተቃዉሞ ከሚያሰሙ የሙስሊም ወገኖች አካባቢ፣ ብዙ ተቃውሞ አንሰማም። ነገር ግን መሰረቱ ከኢትዮጵያ የሆነዉን (ወይንም በኢትዮጵያዊ የተጀመረ) የአህበሽን አስተምሮ ላይ ይሄን ያህል ጠንካራ ተቃዉሞ ለምን ሊኖራቸዉ እንደቻለ ግን በራሱ የሚያነጋግር ነዉ።

እንደዚያም ሆነ፣ የአህበሽን አስተምህሮ አለመቀበል የማንም ሙስሊም ሙሉ መብት እንደሆነ አምናለሁ። ዜጎች እንኳን የአንድ እስልምና አስተምህሮ አለመቀበል ቀርቶ፣ ከእስልማና ወደ ክርስትና፣ ወይንም ወደ ሌላ እምነት የመሄድ ሙሉ መብት አላቸው። ስለዚህ ኮሚቴው «የአህበሽ አስተምህሮን አንፈልግም» ማለቱ ሊያስወቅሰዉና ሊያስኮንነው ፣ ሽብርተኛም ሊያስብለው አይገባም።

ነገር ግን ኮሚቴው «እኛ የማንፈልገው ትምህርት ስለሆነ፣ ሌሎች ቢፈልጉም መማር የለባቸውም » በማለት ማክረሩ ተቀባይነት ሊኖረዉ አይገባም።

ዋሃቢዝም የሰዎችን ምርጫ አያከብረም። አንድ ሙስሊም ክርስቲያን ከሆነ መገደል አለበት ነዉ የሚለዉ። ከዋሃቢዝም ዉጭ ሌላ የእስልምና አስተምህሮ በምንም አይነት መሰጠት የለበትም ማለት ብቻ ሳይሆን፣ ሌላ አስተምህሮ የሚቀበሉትን ጸረ-አላህ እና ጸረ-እስልምና አድርገዉ በመቁጠር እንዲጠፉ ያስተምራል። ታዲያ በአህበሽ ላይ ይሄን አይነት ጠንካራ አቋም መያዝ፣ በዋሃቢዝም የአክራሪነት መንፈስ መያዝ ተደርጎ በአንዳንዶች ቢወስድ ስሀትት ነዉ ሊባል ይችላልን?

አገር የጋራ ሃይማኖት የግል ነዉ። ሌላዉን እስካልነካ ድረስ፣ ማንም የፈለገዉን መማር፣ የፈለገዉን መቀበል፣ የፈለገዉን መምረጥ ይችላል። አህበሽ መማር የፈለገ እንዳይማር ማንም ሊከለክለው አይገባም። መማር የማይፈልግ ደግሞ በግድ እንዲማር መገደድ የለበትም።

ያሉት መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ ማንም ሙስሊም በግዴታ አህበሽን ሆነ ሌላ አስተምሮ የተማረበት ሁኔታ ያለ አይመስለኝም። በኢሕአዴግ ሸምጋይነት በመጅሊሱና በኪሚቴዉ መካከል በተደረገዉ ውይይት ወቅትም ግልጽ የተደረገው፣ የአህበሽ አስተምህሮ በፍቃደኝነት እንዲሰጥ ነዉ። ስለዚህም «በግድ መጤ ኃይማኖት እንድንማር እየተደረግን ነዉ» የሚባለው ክስ ትንሽ ዉሃ የሚቋጥር አይመስለኝም።

መጅሊሱ እንዴት ይመረጥ?

ሌላዉ የአለመስማማት ምክንያት የሆነዉ የመጅሊሱ ምርጫ ነዉ። «ምርጫዉ እንዴት ይካሄድ ?» የሚለዉ ትልቅ ዉዝግብን አስነሳ። በየቀበሌዉና በየወረዳዉ ሙስሊሞች ተወካዮቻቸውን እንዲመርጡ፣ መጅሊሱ ሲወስን፣ የሙስሊም ተቃዋሚዎችን የሚመራዉ ኮሚቴ «ምርጫዉ መደረግ ያለበት በመስኪዶቹ ዉስጥ ነዉ» የሚል አቋም ያዘ። «ምርጫችን በመስጊዳችን» የሚል መፈክርም መስማት የጀመርነዉ በዚህ ምክንያት ነዉ።

ምርጫዉ በመስኪዶች ከተደረገ፣ በዋና ዋና መስኪዶች በብዛት ይገኛሉ የሚባሉት ዋሃቢስቶች መጅሊሱን የመቆጣጠር አቅም ይኖራቸዋል። በየወረዳዉ ከተደረገ ደግሞ፣ በአብዛኛዉ ሱፊ የሆነዉ ለዘብተኛዉ ሙስሊም መጅሊሱን ሊቆጣጠር ነዉ። ፍጥጫዉ እንግዲህ እዚህ ላይ ነዉ።

መጅሊሱ በየወረዳው ምርጫ ይደረግ ብሎ ሲወስን «ከመስኪድ በጣም ርቀው ወይንም መስኪዶች የሌሉባቸው ቦታዎች የሚኖሩ ፣ በተለያዩ ምክንያቶች መስኪድ መምጣት የማይችሉ (ወራቸው የደረሰ ሴቶች ….) ሙስሊሞች በምርጫዉ እንዲሳተፉ ያደርጋል» በማለት ነበር።

ሙስሊም ተቃዋሚዎች ግን «በየወረዳዉ ከሆነ የምርጫ ማጭበርበር ይኖራል። በመስኪዶች ግን፣ ምርጫዉን በቅርበት ለመከታተል ይቀላል። ስለዚህም ምርጫዉ በመስኪድ መሆን አለበት» በሚለው አቋማቸው ጸኑ። በአዋሊያ ኮሌጅ ፣ በአኗር መስኪድ አካባቢ ሰላማዊ ተቃዉሞዎቻቸዉንም ማሰማት ጀመሩ። ከመስኪድ በመዉጣት፣ በመርካቶ አካባቢ ጩኸታቸውን ለማሰማት በሞከሩበት ጊዜ፣ የፌደራል ፖሊስ ጣልቃ ገባ። የኮሚቴ መሪዎችም በብዛት ተይዘው ታሰሩ።

ኢሕአዴግ በመጅሊሱ የርሱ ሰዎች እንዲመረጡ ሊያደርግ አይችልም የሚል አስተያየት የለኝም። እንደተባለው ምርጫዉ ሊጭበረበርም ይችላል። ነገር ግን በመስኪድ መደረጉ ደግሞ፣ የባሰ ጸረ-ዴሞክራሲያዊና የአብዛኛዉን ሙስሊም ፍላጎት ያላንጸባረቀ ምርጫ የሚሆንበትን ሁኔታ ይፈጥራል። በመስኪድ አካባቢ ያሉ ጥቂቶች፣ አብዛኛዉ ሙስሊም ሳይመርጣቸው፣ መጅሊሲን በአቋራጭ ሊቆጣጠሩ ይችላሉ። በተለይም ደግሞ ዋሃቢስቶች መጅሊሱን ከተቆጣጠሩ፣ በሳዉዲ አረቢያ እንደምናየዉ፣ በእስላማዊ ተቋማት በሙሉ፣ እንደ ሳዉዲ አረቢያ ባሉ አገራት በስፋት የሚሰጠው አይነት የአክራሪነት ትምህርት ሊስፋፋ ይችላል። ሙስሊሙ ማህበረሰብ ሰላማዊ የሆኑ፣ በመቻቻልና በመከባበር ላይ ያተኮሩ የእስልምና አስተምህርዎች እንዳያገኝ፣ እርስ በርሱ የበለጠ እንዲከፋፈል፣ ከሌሎች እምነቶች ተከታይች ጋር ፊት ለፊት እንዲላተም ያደርጋል። ይህ ደግሞ የአገራችንን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ነዉ።

ዶር ብርሃኑ ነጋ እንዳሉት፣ አሁን ያለዉ ችግር የጥቂት ሙስሊሞች ተቃዉሞ የመብት ጥያቄ ሳይሆን የሌላዉን መብት የመርገጥ ጥያቄ ነዉ። አህበሽ በግድ ተማሩ አልተባሉም። ነገር ግን መማር የሚፈልግ ሌላ ሙስሊም «አህበሽን መማር የለበትም ነዉ» እያትባለ ያለው። በወረዳቸው መመረጥ መምረጥ ይቻላሉ። ያንን መብታቸዉን ማንም አልነፈጋቸውም። ምርጫዉ እንዳይጭበረበር ከተፈለገ ደግሞ ፣ ምርጫዉ ትክለኛ የሚሆንበትን ሃሳቦች በማቅረብ በጋራ መስራት ሲኖርባቸው፣ ምርጫዉ በመስኪድ ካልሆነ በሚል፣ በተለያዩ ምክንያቶች መስኪድ መምጣት የማይችለው ሙስሊም እንዳይመርጥ እያከላከሉት ነዉ። ይህ ደግሞ ለማንም የሚበጅ አይደለም።

የመፍትሄ ሃሳቦች

እንግዲህ ያለውን ችግር ባሉኝ ግንዛቤዎች በዚህ ሁኔታ ለማሳየት ከሞከርኩ ፣ ከዚህ ቀጥሎ እንዴት መቀጠል ያስፈልጋል በሚለዉ ጥያቄ ዙሪያ አንዳንድ ሃሳቦችን ላቅርብ።

እንደሚታወቀዉ በርካታ ሙስሊሞች እየታሰሩ ነዉ። ችግሮች እየለዘቡ ሳይሆን እየከረሩ ነዉ የመጡት። የሚያሳዝነው ደግሞ ይሄን ችግር ለማስፋት የሚሞክሩ ዉጭ አገር የሚቀመጡብ አንዳንድ የፖለቲካ ደርጅቶችና ሜዲያዎች መኖራቸው ነው።

ሙስሊሙ ማህበረሰብ መረዳት የሚኖርበት፣ እንደ ዶር ብርሃኑ ነጋ ያሉ የፖለቲካ መሪዎች፣ የሙስሊሙን ጉዳይ እያነሱ፣ እየለጠጡ የሚያወሩት፣ የሙስሊሙን እንቅስቃሴ ለፖለቲካ ፍጆታ ሊጠቀሙበት ስለፈለጉ እንጂ፣ ሙስሊሙን ለመጥቀም አስበው እንዳልሆነ ነዉ። ትግሉን ወደፊት የሚወስድ፣ የሚያንጽ፣ የሚገነባ፣ ሰላምና እርቅን የሚያመጣ፣ የሰለጠነ፣ በእዉነት ላይ የተመሰረተ፣ ተስፋ የሚሰጥ ፖለቲካ ሲያራምዱ አናያቸውም። ለችግሮች መፍትሄ ሲያስቀመጡ አናያቸዉም። ፖለቲካቸዉ ጨለምተኝነት የሞላባትና መካረርን የሚያመጣ ነዉ።

ሙስሊሙን ለመጥቀም የሚፈልግ አካል፣ በዋናነት ይዞ የሚንቀሳቀሰው አጀንዳ ፣ «በሙስሊሙ አካባቢ ያለው ችግር ፣ በሙስሊሙ ማህበረሰብ እራሱ በሰላም ይፈታ» በሚለው የሰላም አጀንዳ ላይ ነዉ።

ሙስሊም አይደለሁም። የክርስትና እምነት ተከታይ ነኝ። ክርስቲያኖች የሙስሊሙን እንቅስቃሴ እንዲደግፉ የሚጠይቅ ጥሪ ስለቀረበ ነዉ አስተያየቴን ለመስጠት ችየተነሳሁት። እኔ በሙስሊሞች ቦታ ብሆን፣ የምፈልገዉና የምመኘዉ፣ ነገሮች እንዲከሩ ሳይሆን እንዲለዝቡ፣ ችግሮችም በሰላምና በዉይይት እንዲፈቱ ነዉ። በመሆኑም ሊጠቅሙ ይችላሉ የምላቸዉን አንዳንድ ምክሮች እንደሚከተሉት በትህትና አቀርባለሁ፡

1. በየአርቡ፣ የጸሎት ቦታ በሆኑ መስጊዶች፣ ተቃዉሞዎች ማሰማቱ፣ የዜጎች ሕገ መንግስታዊ መብታቸው ቢሆንም፣ ምን ጥቅም ሊያመጣ እንደሚችል ግን አላውቅም። ይልቅስ ቢጫ ወረቀት ሳይሆን ነጭ ወረቀት በማዉለብለብ ፣ በእርጋታና በቅንነት ከመጅሊሱ ጋር መነጋገሩ አይበጅምን? በኢትዮጵያ ኦርቶዶስ ቤተ ክርስቲያን፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን አንድነት ለመጠበቅ፣ አባቶች በቅንነት ላይ ያተኮረ ዉይይት አያደረጉ ነዉ። ይህ አይነቱ ቅንነት ያለበት ምክክርና ዉይይት ነዉ ሙስሊሞች ማድረግ ያለባቸው የሚመስለኝ። «እኛ ያልነው ካልሆነ» የሚል ያከረረ አቋም ብዙም ሊያስኬድ አይችልም። በሳዉዲ አረቢያ ሊሰራ ይችላል። በኢትዮጵያ ግን አይሰራም።

2. መስኪዶች የጸሎት ቦታዎች ናቸው። ከጊዜ ወደ ጊዜ፣ ከጸሎት ቤትነት ወደ ተቃዉሞ ማድረጊያ ቦታነት እየተቀየሩ ነዉ። ይህ ከቀጠለ፣ ወደፊት የሰፋ ችግር ሊያስከትል ይችላል። በመሆኑም ለመስኪዶች ሊሰጥ የሚገባው ክብርና ጥንቃቄ ሊሰጥ ይገባል ባይ ነኝ።

3. ከሳዉዲ አረቢያ ጋር ግንኙነት ያላቸው፣ በብዙ ገንዘብ እየተደገፉ፣ የዋሃቢስት አክራሪነት ትምህርቶችን ለማስፋፋት የሚሰሩ ብዙዎች አሉ። እነዚህ አክራሪነትን ሲያስፋፉ የነበሩ ወገኖች፣ ከሞላ ጎደል፣ ላለፉት ሃያ አመታት፣ የኢሕአዴግን መንግስት ቡራኬ አግኘተው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ናቸዉ። የአቶ ጁነዲን ሳዶ ባሌበትን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል። በመሆኑም ለአክራሪነት መስፋፋት ኢሕአዴግ በተወሰነ ደረጃ ሃላፊነት መዉሰድ ይኖርበታል እላለሁ።

4. በመስኪዶች ሰላማዊ ተቃዉሞ ማሰማት፣ የመጅሊስ አመራሮች እንዲለወጡ መጠየቅ «ሽብርተኛ» ሊያሰኝ አይገባም። በመሆኑም ከሳዉዲ አረቢያ ጋር ግንኙነት የሌላቸዉ፣ የዋሃቢዝም አክራሪነትን ማስፋፋታቸዉን የሚያሳይ መረጃ ያልተገኘባቸው፣ በአዋሊያና በመስኪዶች ሕገ መንግስቱ የሚፈቅድላቸውን ተቃዉሞ በማሰማታቸው ብቻ የታሰሩ፣ ሰላማዊ ሙስሊም ወገኖቻችን ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ መፈታት አለባቸው። እነርሱን በማሰር የሚገኝ አንዳች ጥቅም የለም። ዜጎች ተቃዉሞ ስላሰሙ የሚታሰሩበት አሰራር መቆም አለበት። ኢሕአዴግ በዚህ አንጻር ከኃይል እርምጃዎች ተቆጥቦ፣ ማስተዋል ያለበት እርምጃ እንዲወስድ እመክራለሁ።

5. የኢሕአዴግ መንግስት ለአመታት በሳዉዲ አረቢያ የተደገፈ አክራሪነት ሲያስፋፋ ዝም ማለቱ ስህተት እንደነበረ ተረድቶ፣ ከዚህ በኋላ በተለያዩ ስሞች ፣ ከሳዉዲ አረቢያ የሚመጡ ገንዘቦችና እርዳታዎች ላይ የጠበቀ ክትትል ሊያደርግ ይገባዋል። ሳዉዲዎች ፣ ግብጾች የመሳሰሉ አገራት፣ ኢትዮጵያዉያን ተከባብረን፣ ተዋደን፣ ተቻችለን በሰላምና በፍቅር እንድንኖት አይፈልጉም። ታሪካዊ ጠላቶቻችን ናቸው። በመሆኑም ዉስጥ ዉስጡን ኢትዮጵያን እንዲያደሙ ሊፈቀድላቸው አይገባም።

6. ኢሕአዴግ፣ መጀመሪያዉኑ ሕግና ስርዓትን ከማስጠበቅ ዉጭ፣ በመጅሊሱና በሙስሊም ተቃውሚዎች መካከል፣ ለማስታረቅም ቢሆን፣ መግባት አልነበረበትም። እነርሱ እራሳቸዉ ከተሰማሙ መልካም፣ ካልሆነ ግን «ፍርድ ቤት ሄዳችሁ በዚያ ችግራችሁን ፍቱ» ብሎ ፣ አርፎ መቀመጥ ነበረበት። ስለሆነም መንግስት ከሙስሊሞች ጉዳይ እራሱን ሙሉ ለሙሉ ማውጣት አለበት።

7. እርግጠኛ ነኝ የተከበሩ፣ በሁሉም ተሰሚነት ያላቸዉ፣ ሙስሊም አባቶች ይኖራሉ። ከነዚህ አባቶች የተወጣጣ አንድ የሙስሊም አስታራቂ ኮሚቴ ይቋቋም። በመጅሊሱና በሙስሊም ተቃዋሚውች መካከል ያሉት ችግሮች ፣ ሁሉም አሸናፊ በሆኑበት፣ በኢትዮጵያዊ ጨዋነት መንገድ ለመፍታት ይንቀሳቀሱ።

8. ክርስቲያኑ ማህበረሰብ በሙስሊሙች ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት መሞከር የለበትም። ሙስሊሞች የራሳቸዉን ችግር እራሳቸው ነዉ የሚያውቁት። እኛ ከዳር ሆነን ብዙ በማናውቀዉና በማንረዳዉ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ገብተን፣ አንዱ ቡድን ደግፈን ሌላዉን የምንቃወምበት ምንም ምክንያት የለም። በመሆኑም እንደ ዶር ብርሃኑ ነጋ ያሉ ጥቂቶች፣ ክርስቲያኑ እንዲነሳ ያቀረቡት ጥሪ፣ «ቦታ ሊሰጠው አይገባም። ጎጂም ነው» እላለሁ።