ኳሷ ኢሕአዴግ ሜዳ ላይ ነው ያለችዉ ! አማኑዔል ዘሰላም
ልማት ለአንድ አገር በጣም አስፈላጊ ነዉ። አገራችን ኢትዮጵያ ሰለጠኑ ከሚባሉ አገራት ጋር ስትነጻጸር ብዙ የሚቀራት ናት:: አገራችንን ከድህነት ነጻ ለማዉጣት፣ በአጭር ጊዜ ዉስጥም ወደ መካከለኛ አገራ ዉስጥ እንድትመደብ ለማድረግ፣ ኢሕአዴግ የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ አውጥቶ እየተንቀሳቀሰ ነዉ:: ይህ ኢሕአዴግ የጀመረዉን የልማት እንቅስቃሴ ከመደገፍ ባሻገር፣ ኢትዮጵያዉያን በሙሉ ባላቸው አቅምና ጉልበት የድርሻቸዉን ሊያበረክቱበት የሚገባ እንቅስቃሴ ነዉ::
አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሃይለማርያም ደሳለኝ፣ ለፓርላም ካደረጉት ንግግር፣ አንድ ግሩም አባባል አደመጥኩ። «የአይቻልም መንፈስን መስበርና የይቻላል መንፈስን በአገራችን ማምጣት አለበን» ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ:: ኢሕአዴግ ብቻዉን የሚያደርገው ሳይሆን ኢትዮጵያዊ ሁሉ በጋራ ተባብሮ የሚሰራው እንደሆነም ሳይገልጹ አላለፉም::
በአገር ዉስጥም ሆነ በዉጭ አገር የሚኖረዉ ኢትዮጵያዊ፣ የልማት እንቅስቃሴዎችን ይቃወማል ብዬ አላስብም:: አገሩን የሚወድ ኢትዮጵያዊ ሁሉ፣ ኢትዮጵያ አድጋ፣ ትልቅ ደረጃ እንድትደርስ መፈለግ ብቻ ሳይሆን መክፈል ያለበትን መስዋእትነት ለመክፈል ዝጉጁ ነዉ::
በአገር ቤት የሚኖረዉ ኢትዮጵያዊ የአንድ ወር ደሞዙን ለአባይ ወንዝ ግንባታ እንደከፈለ የሚታወቅ ነዉ:: አገር ቤት ያሉ ወገኖቻችን በተፈጠረው የዋጋ ግሽፈትና ከፍተኛ የኑሮ ውድነት፣ ኑሮን መግፋት ቢያቅታቸዉም፣ ቢያማቸዉም፣ የሚያምኑበት ጉዳይ ነዉና ካላቸዉ ከትንሹ ገቢያቸው 12% ሲሰጡ አልከፋቸውም::
እንደምንሰማዉ አገር ቤት የሚኖረው ሕዝብ፣ እንደገና ለሁለተኛ አመት የደሞዙን 12% እንዲያዋጣ ተጠይቆ እያዋጣ ነዉ:: የኑሮ ዉድነት፣ ትንሽ እንኳን ጋብ ባላለበት ሁኔታ እንደገና፣ መዋጮ በማዋጣት ችግር ዉስጥ እንዲገባ መደረጉ ተገቢ አይመስለኝም:: ሌላ አማራጭ ባይኖር ኖሮ፣ «እሺ ፣ ምንም ማድረግ አይቻልም» እንል ነበር:። ነገር ግን ሌላ አማራጭ አለ። እርሱም ማዋጣት የሚከብደዉን ሕዝብ ማስጨነቅ ሳይሆን ማዋጣት የሚችለዉን በተለይም በዳያስፖራ የሚገኘዉን ኢትዮጵያዊ በስፋትና ማሳተፍና ማንቀሳቀስ ነዉ።
«ዳይስፖራዉን ለማሳተፍ ሞክረናል፤ ከዳያስፖራዉም ብዙ ገንዘብ ሰብስበናል» የሚል ምላሽ የኢሕአዴግ ባለስልጣናት ሊሰጡ ይችላሉ። ትክክል ነዉ። በተለያዩ የአሜሪካን የአዉሮፓ ከተሞች ብዙ ገንዘብ ተሰብስቧል። ቦንድ የገዙ ዜጎች ብዙ ናቸዉ። ነገር ግን በበቂ ሁኔታ ዳያስፖራዉን በማሳመንና በማግባባት ስራ ተሰርቷል ብዬ አላስብም። ስራ ተሰርቶ ቢሆን ኖሮ ለአባይ ወንዝ ግንባታ የሚያስፈልገው ወጪ በሙሉ ይሸፈን ነበር። አገር ቤት ካለዉም ድሃ ወገናችን መዋጮ አይጠየቅምም ነበር።
የአባይን ግድብ ለመገንባት ወደ አራት ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል። በሰሜን አሜሪካ ብቻ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ወደ አንድ ሚሊዮን ይደርሳል ተብሎ ይገመታል። በዉጭ ያለነዉ አንድ ሚሊዮኖቻችን በሰዓት 5 ዶላር ብቻ ነዉ የሚከፈልን ብለን ብንወስድ፣ የአመት ደሞዛች ወደ 10000 ዶላር ይደርሳል። አገር ቤት መዋጮ እንዲያዋጣ ሕዝቡ ከተጠየቀዉ 12% በታች፣ 10% ለኢትዮጵያ ልማት ብንመድብ፣ በአመት አንድ ቢሊዮን ዶላር በቀላሉ ማሰባሰብ እንችላለን። በአራት አመት ዉስጥ ለአባይ ግድብ ግንባታ የሚያስፈልገዉን በሙሉ፣ የአለም ባንክ ወዘተረፈ የመሳሰሉትን ሳንለምን፣ ኑሮ የከበደዉንም አገር ቤት ያለዉን ሕዝባችንንም ሳናስጨንቅ፣ ማሟላት ተቻለ ማለት ነዉ። እንግዲህ ሂሳቡን በግልጽ አስቀጬዋለሁ። ፍላጎቱና መግባባቱ ካለ ፣ አቶ ኃይለማርያም እንዳሉት በርግጥ እንችላለን። አዎን ይቻላል።
ትልቁ ጥያቄ መግባባቱና መስማማቱ ላይ ነዉ። በቅርቡ አምባሳደር ግርማ ብሩ ዋሺንገትን ዲሲ ከሚገኝ የሃገር ፍቅር ራዲዮ ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ ሲቋጩ የተናገሩትን ልጥቀስ።
«አንድ አገር ነው ሊኖረን የሚችለዉ። ሰው በምርጫ አይደለም በአንድ አገር ዉስጥ የሚወለደው። ያቺን ያለችንን አገር፣ በክብር ለመጠበቅ እንድንችል፣ ሁሉ ልዩነቶቻችንን አቻችለን፣ የአገራችን መሰረታዊና ብሄራዊ ጥቅም የሚመለከቱ ጉዳዮች ሲኖሩ፣ አንደ አንድ መቆም አለብን» ነበር ያሉት አምባሳደሩ።
በዉጭ አገር የሚኖረዉ አብዛኛዉ ኢትዮጵያዊ ከኢሕአዴግ የሚፈልገዉ ኢሕአዴግ አገር ቤት ያለዉን ሕዝብ እንዲያከብርና የሕዝቡን ጥያቄና ፍላጎት እንዲያሟላ ነዉ። አገር ቤት ባሉ እሥር ቤቶች የሕሊናና የፖለቲካ እሥረኞች ከሌሉ፣ ኢትዮጵያዉያን በነጻነትና ያለ ፍርሃት በአገራቸው የመናገር፣ የመሰብሰብ፣ የማምለክ ነጻነታቸው ከተረጋገጠ፣ በባለስልጣናቱም ሆነ ከባለስልጣናቱ ጋር ዝምድናና ግንኙነት ባላባቸው ግለሰቦች የሚፈጸሙበትን ግፎች አቤት የሚልበት ነጻና ገለልተኛ የፍርድ ስርዓት ከተዘረጋ፣ በዉጭ ያለዉ ኢትዮጵያዊ ተቃዉሞም ሆነ ቅሬታ የሚያሰማበት ምንም ምክንያት አይኖረም።
ኢሕአዴግ በዉጭ አገር የሚኖረዉን ኢትዮጵያ በስፋት ለማቀፍ ይችል ዘንድ፣ ሊያደርጋቸው የሚገባ ተግባራት አሉ። እነርሱ እጅግ በጣም ጥቂትና ቀላል ናቸዉ። በዋናነት አምባሳደር ግርማ ብሩ እንዳሉት የመተማመን፣ የመቻቻልና የመከባበርን መንፈስ እንዲሰፍን ማድረግ ነዉ። ኢሕአዴግ የሚደግፉትን ብቻ ይዞ መሄድ ሳይሆን፣ አገርን በጋራ አንድ እርምጃ ለማስኬድ ሲባል፣ የማይደግፉትንና የሚቃወሙትን ማቅረብ መቻል ያለበት ይመስለኛል።
ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለማርያም ደሳለኝ ለፓርላማ ባደረጉት ንግግር የፓርቲዎች የምክር ቤት አባል ከሆኑ (የምርጫ ስነ ምግባር ኮዱን ከፈረሙ) የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር አገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ዙርያ እንደሚነጋገሩ ግልጽ አድርጓዋል። የምርጫ ስነ ምግባር ኮዱን ያልፈረሙ እንደ መድረክ ያሉ፣ የድርጅቶች ስብሰብ ከሆኑ ጋር ግን ለመነጋገር የኢሕአዴግ ፍቃደኛት እንደሌለ አስረድተዋል። ይህ ትልቅ ስህተት መሰለኝ። ኢሕአዴግ መንግስት ነዉ። መንግስት ደግሞ ያኮረፉትን፣ ያመጹትን ወደ ሰላም የማምጣት ትልቅ ሃላፊነት አለበት። ኢሕአዴግ ጠንካራ ከሚባሉ ተቃዋሚዎች ጋር አልነጋገርም ካለ፣ የመከባበሩንና የመቀራረቡን መንፈስ አደፈረሰው ማለት ነዉ።
ሌላዉ ብዙዎቻችን እንደምናወቀዉ ሽብርተኞች ተብለው የታሰሩ በርካታ ወገኖቻችን አሉ። ጋዜጠኛ እስክንደር ነጋ፣ አቶ አንድዋለም አራጌ፣ አቶ በቀለ ገርባ ፣ እህት ርዮት አለሙ የመሳሰሉ ዜጎች በቃሊቲ እሥር ቤት ይገኛሉ።
ከአቶ እስክንደርና ከአቶ አንዱዋለም ጋር ጥሩ ቀረቤታ አለኝ። ብዙ ጊዜ በስልክና በኢሜል እንገናኝ ነበር። እግዚአብሄርን የሚፈሩ፣ በምንም መልኩ ፣ በማንም ላይ ጉዳት እንዲደርስ የማይፈልጉ፣ ከራሳቸዉ ጥቅም ይልቅ የሕዝብን ጥቅም ያስቀደሙ ሰላማዊ ሰዎች ናቸዉ። ግንቦት ሰባት አባል ናችሁ ተብለዉ ተከሰዋል። ግንቦት ሰባት የተሰኘውን ድርጅት እንኳን ሊደግፉ፣ በዉጭ ባሉ ሜዲያዎች የግንቦት ሰባት «የሰላማዊ ትግል አይሰራም» ፖለቲካን በይፋ የተቃወሙ ናቸዉ። እነዚህን ወገኖችን ሽብርተኞች ናቸው ብሎ መፈረጅ በጣም አሳዛኝ ከመሆኑ የተነሳ ማንም የማይቀበለው ነዉ። እነርሱን ባሰሯቸው ባለስልጣናትም ላይ ጤናማ ያልሆነ አመለካከት እንዲኖረን ያደረገና የሚያደርግ ነው።ጎጂ ነዉ።
በቅርቡ ለአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ፣ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ እነ እስክንደር ነጋን «ሁለት ባርኔጣ እያደረጉ የሽብር ሥራ ላይ የተሰማሩ» ሲሉ እንደከሰሷቸው አንብቢያለሁ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምን አይነት መረጃ ይዘው ይሄን ሊሉ እንደቻሉ ሊገባኝ አልቻለም። አቃቢ ሕግ ያቀረባቸው የቪዲዮ መረጃዎች ሁሉ ሳይቀሩ፣ የነ እስክንድርን ሰላማዊነት ነዉ ያረጋገጡት። ዉጭ አገር ላሉ ሜዲያዎች በሰጡት ቃለ ምልልሶች፣ ከሰላማዊ ትግል ዉጭ ሌላ ነገር እንደማያዋጣና እንደማይደግፉ ነዉ እነእስክንድር በግልጽ ያሰቀመጡት። የጻፏቸዉን ጽሁፎች፣ አገር ቤት በሚታተሙ ጋዜጦችና በይፋ በሚነበቡ ድህረ ገጾች አወጡ እንጂ፣ በሚስጠር ያቀባበሉትና የበተኑት አመጽ የተሞላበት ጽሁፎች የሉም።
እስከሚገባኝ ድረስ፣ በፍርድ ቤት አቃቢ ሕግ ባቀረባቸዉ መረጃዎች ሁሉ በግልጽ የተረጋገጠው፣ እነ እስክንድር አንድ ባርኔጣ ብቻ እንዳደረጉ ነዉ። እርሱም ነጭ የሰላም ባርኔጣ። አቶ ኃይለማርያም በዚህ ጉዳይ ላይ፣ ከእዉነት የራቀ ጠቃሚ ያልሆኑ አባባሎችን በመሰንዘር ከኢትዮጵያዉያን ጋር ብዙ ባይቀያየሙ ይሻላል።
እንግዲህ በነ እስክንድር ላይ እየተደረገ ያለዉ አሳዛኝ ክስተት ነዉ ሌላዉ በዋናነት የመቀራረብንና የመግባባትን መንፈስ እያደፈረሰ ያለዉ።
እርግጥ ነዉ ምንም ነገር ይምጣ በኢሕአዴግ ላይ በጭራሽ ቀና አመለካከት የሌላቸው፣ ኢሕአዴግ እንዲጠፋ የሚፈልጉ ጥቂት ወገኖች ይኖራሉ። አንዳንዶች ጭራቅ ከሚባለዉና ከመረብ በስተሰሜን ያሉ ወገኖቻችን ደም ከሚጠጣዉ ከሻእቢያ ጋር በመተቃቀፍ፣ ለሰላምና ለእርቅ የሚደረጉ ጥረቶች ላይ ዉሃ ለመከልበስ የሚሞክሩ አሉ። እነዚህ ኃይሎች «ኢሕአዴግ አይለወጥም። ኢሕአዴግ እነ እስክንድርን አይፈታም፣ በሕዝቡ ላይ የፍርሃት ቀንበር ጭኖ በኃይል መግዛት ነዉ የሚፈልገዉ። በኃይል ኢሕአዴግን አስገድዶ ማንበርከክ፣ አሊያም ከናካቴዉ ማስወገድ ነዉ የሚያስፈልገዉ» ይላሉ።
ይህ አይነት አመለካከት ያላቸው ወገኖች እጅግ በጣም ጥቂቶች ናቸዉ። በዳያስፖራ ተቀባይነት የሌላቸው ከመሆናቸዉም በተጨማሪ ፣ የፖለቲካ ክስረት እንደደረሰባቸው አለም የሚያውቀዉ ነዉ። እነዚህን በመፍራትና እንዲሁ በመደናበር ኢሕአዴግ ዱላውን ሰላማዊ ዜጎች ላይ ማሳረፍ የለበትም። አብዛኛዉ በዳያስፖራ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ፣ በልማቱ እንቅስቃሴ ኢሕአዴግን መደገፍ የሚፈልግ፣ ነገር ግን ኢሕአዴግ በሚወስዳቸው አላስፈላጊ፣ መቀራረብን በሚያደፈርሱ የፖለቲካ ዉሳኔዎች ያዘነ፣ ያኮረፈና የተቆጣ ነዉ።
እንግዲህ ኢሕአዴግ ከእልህና ከግትርነት ፖለቲካ ወጥቶ ለአገር የሚበጀዉን ነገር ማድረግ ይጠበቅበታል። አገራችን ኢትዮጵያ ትላልቅ ፈተናዎች ከፊቷ ተደቅነዋል። የተጀመሩ በርካታ የልማት እንቅስቃሴዎች መቀጠል አለባቸዉ። እንደ ግብጽ ያሉ አገራት መቼም ስላማይተኙልን የአገራችን አንድነት ከመቼዉም በበለጠ መጠናከር አለበት። በኤርትራ በኩል ያለዉን ችግር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍታት ያስፈልጋል። «no Peace, no war» የተባለዉ ፖሊሲ ሰዉነታችን ላይ መግል ይዘን እንድንኖር ያደረገ ፣ መቀየር ያለበት ፖሊሲ ነዉ። በመሆኑም የግዴታ ኢትዮጵያዉያን መቻቻል መቀራረብና መያያዝ አለብን። ይሄም እንዲሆን በዋናነት ኢሕአዴግ ነዉ ትልቅ ሚና ሊጫወት የሚችለዉ። ኳሱ ኢሕአዴግ ሜዳ ላይ ነዉ።
1. ኢሕአዴግ የታሰሩ የፖለቲካ እሥረኞችን በሙሉ መፍታት አለበት። የነ እስክንድር ጉዳይ በይግባኝ የተያዘ ነዉ። እነ እስክንድርን የከሰሰው ፌደራል መንግስቱ እንደመሆኑ የጠቅላይ ሚኒስተሩ ካቤኔ አባል የሆኑት፣ የፍትህ ሚኒስትሩ፣ ክሱ እንዲነሳ ማድረግ ይችላሉ። ይግባኙን የሚያየው ፍርድ ቤት ከአቃቤ ሕግ ተቃዉሞ እስካልሰማ ድረስ የመከላከያ ጠበቃዎችን መከራከሪያ አድምጦ በቀላሉ እስረኞችን ሊፈታ ይችላል። አራት ነጥብ። «በፍርድ ቤት ጉዳይ ዉስጥ መግባት አንፈልግም» የሚል ምክንያት ሊሰጥ አይችልም። እነ እስክንደርን የከሰሰው የሥራ አስፈጻሚዉ አካል ነዉ።የሥራ አስፈጻሚዉ አካልም አዲስ መረጃ በማግኘት ይሆኑ በተለያዩ ምክንያቶች ክሱን በማናቸዉም ጊዜ ሊያነሳ ይችላል።
2. መድረኩ የስነ-ምግባር ኮዱን ቢፈርም መልካም ነበር። የአመራር አባላቱ በሰከነ መልኩ ትኩረት ሰጥተዉበት ለሰላምና ለእርቅ የደርሻቸውን ያደርጋሉ ብዬ አስባለሁ። በኢሕአዴግ ዘንድ ግን መድረኩ ፈረመም አልፈረመም ቅድመ ሁኔታዎች ማስቀመጥ የለበትም። ለኦብነግ ያሳየዉን ለመድረኩ የማያሳይበት ምንም ምክንያት የለም። በመሆኑም ኢሕአዴግ ከመድረክ ጋር የገባዉን እልህ አቁሞ፣ ለአገርና ለሕዝብ ሲል ለመቀራረብና ለእርቅ ቦታ መስጠት አለበት። አብረዉ በጋራ የአገርን ችግር በመፍታቱ ዙሪያ ከሌሎች እንደ ኤደፓ ካሉ ድርጅቶች ጋር ሆነዉ መነጋገር አለባቸው።
3. የመልካም አስተዳደር፣ የዲሞክራሲ ስርዓት እንዲሰፍን ለማድረግ ኢሕአዴግ ቁርጠኝነቱን ማሳየት ይኖርበታል። ከምርጫ ዘጣና ሰባት በፊት የታየ መልካም ጅማሮ ነበር። ወደዚያ መመለስ ያስፈልጋል። ከምርጫ ዘጠና ሰባት በኋላ የተፈጠሩ ችግሮች እንዳይፈጠሩ ደግሞ ከላይ እንደገለጽኩት፣ አሉ ከሚባሉ በአንጻራዊነት ጠንካራ ከሚባሉ እንደ መድረክ ካሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በቅንነት እንደ ወንድማማቾች መነጋገር ያስፈልጋል።
4. የኢሕአዴግ ባለስልጣናት በሚሰጧችው ቃለ መጠይቆችና ንግግሮች መጠንቀቅ ያለባቸው ይመስለኛል። በአገራችን ብዙ ቁስል ያለባቸው በርካታ ወገኖች አሉ። አንዱ የሌላዉን ስሜት መጠበቅ መቻል አለብን። በተለይም በአመራር ላይ ያለን ሰዎች፣ የምንናገራቸው በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ እንደሚሰሙት ተረድተን፣ በተቻለ መጠን የሚያንጽ፣ የሚያቀራረብ፣ የሚያበረታታ ቃላት እንጂ የሚያፈርስ፣ የሚያቃቅርና ሌላዉን የሚያዋርድ ቃላቶች ከአንደበቶቻችን ባይወጡ መልካም ነዉ።
በርግጥም አቶ ኃይለማርያም እንዳሉት ብዙ ነገሮች እንደ አንድ ሕዝብ ማከናወን እንችላለን። የታቀዱትን ብቻ ሳይሆን ከታቀዱት ዉጭ የማድረግ አቅምና ጉልበት ኢትዮጵያዉያን አለን። ከማንም ሕዝብ አናንሰም። የጎደለንና ያጣነዉ ፍቅር ነዉ። እንግዲህ የፍቅር አምላካ እግዚአብሄር ልባችንን ለፍቅር፣ አይሞሮዋችን ለጥበቡ ይከፍትልን።