እስከ መቼ ?

ይህንን ስጽፍላችሁ እጅግ አዝኜ፣ እጅግም ተናድጃለሁ፤ ወንድ መሆኔን ከጠላሁባቸው ጥቂት አጋጣሚዎች አንዱ  የዛሬው ገጠመኝ ነው፡፡
ቢሮዬ ውስጥ ቁጭ ብዬ እየሠራሁ እያለ ድንገት የጫጫታ ድምጽ ከውጭ ሰማሁ፤ መጀመርያ የሰዎች የጨዋታ ድምፅ መስሎኝ ዝም አልኩ፡፡ እየቆየ ግን ‹ጩኸት በረከተ› እኔም ነገሩ ግራ ገብቶኝ ወጣሁ፡፡ ይህ አካባቢ የወፍ ድምጽ እንኳን የማይሰማበት ጸጥታ የሞላው አካባቢ ነበርና ነገሩ እንግዳ ነው የሆነብኝ፡፡
ከወጣሁ በኋላ ያየሁትንና የሰማሁትን ግን ለማመን አልቻልኩም፡፡
እኅትና ወንድም በአንድ ድርጅት ውስጥ ይሠራሉ፤ ብዙ ጊዜ በመግባባት መንፈስ መሥራታቸው ይደንቀኝ ነበር፡፡ ሲሳሳቁና ሲጫወቱ እንጂ ሲከራከሩ እንኳን ሰምቼ አላውቅም፡፡ አሁን ያየሁት ግን በእውኔ ነው፣ በሕልሜ፣ ወይስ በፊልም የሚያሰኝ ነው፡፡

አንዲት እኅት ስቅስቅ ብላ ታለቅሳለች፣ ወንድሟም አለፍ ብሎ ‹ልቀቋት ተዋት፤ ምን ታመጣለች› ይላል፡፡ የታመ መችም መሰለኝ፡፡ እኔ ግራ እንደተጋባሁ ምክንያቱን ጠየቅኩ፡፡ በመካከላቸው በሥራ አለመግባባት ይፈጠራል፤ ታላቅ ወንድም ይበሳጭና ታናሽ እኅቱን በጥፊ ይወለውላል፡፡ ቢሮ ውስጥ፣ በቢሮ ሰዓት፣ ሰው ሁሉ እያየና እየሰማ፣ በሥራ ግንኙነት፡፡ ማመን አልቻልኩም፡፡

የመማር ጥቅም ምንድን ነው?
መማር ሰርተፊኬታችንንና ደመወዛችንን ብቻ ነው እንዴ የሚቀይረው?
አሁንም ወንድ ማለት ለመማታት ሥልጣን ያለው ፍጡር ማለት ነው?
ታላላቆች ታናናሾችን ከታናሽነት በላይ ማየት የሚችሉት መቼ ነው?
የወንዶች ትምክህት የሚለቅቀው መቼና በምን ዓይነት የትምህርት ደረጃ ነው?
አንድ መዓት ጥያቄዎች ነበር የመጡብኝ፡፡ እኔ ወደ ክርክራቸው ፍሬ ነገር አልገባም፤ በጭቅጭቁ ውስጥ ማን ነበር ጥፋተኛው? የሚለው ውስጥም አልነከርም፡፡ በምንም መንገድ ግን ማንም ማንንም እኅት በተናደደና ባልተግባባ መጠን፣ ቱግ ባለና የተበለጠ በመሰለው ጊዜ፣ ስሜቱን መቆጣጠር ባቃተውና እሳት በላሰ ቁጥር መምታት ግን አይችልም፡፡ ፈጽሞም አይችልም፤ ከዚህ የበለጠ እንስሳነትም የለም፡፡ ሰው ማለት የሚያስብ እንስሳ ነው፡፡ ማሰብ ከሰው ሲጠፋ ግን ሰው እንስሳነቱ ብቻ ይቀራል፡፡
 እኅቶቻችን የጉልበታችን ማሳያዎች አይደሉም፤ እኅቶቻችን የጡንቻዎቻችን መፈተሻዎች አይደሉም፤ እኅቶቻችን የእልሃችን መወጫዎች ፈጽሞ አይደሉም፡፡ እኅቶቻችን ሃሳብ ባነሰን ቁጥር ዐቅማችንን የምናሳይባቸው የቦክስ መለማመጃዎች አይደሉም፡፡
ክርክር፣ ውይይት፣ ሽምግልና፣ ካልተቻለም ደግሞ ሕጋዊ አሠራር እያለ አንዲት እኅት በቢሮዋ፣ በገዛ ወንድሟ የምትደበደብ ከሆነ፤ በቤታቸው ላሉት እኅቶቻችንማ ዋስትናቸው ምንድን ነው? አንድ ወንድ በቢሮ ውስጥ ለመደባደብ ካላፈረ፣ በድብቅ ቦታ ወይም በመኝታው ውስጥማ የፈለገውን ለማድረግ ምን ይፈራል? አንድ ወንድ እኅቱን ታናሽ በመሆኗ ምክንያት ብቻ ጡጫ ከሰነዘረ ሚስቱ እጣ ፈንታዋ ምንድን ነው?
ይህች እኅት ባለ ትዳር፣ ለብዙ ዓመታት የሠራች፣ የተማረች ወይዘሮ ናት፡፡ የተማረና ለብዙ ዓመታት የሠራ ወንድምም አላት፡፡ ይህ ሁሉ ግን የወንዶችን ጡጫ ከመቀበል አላዳናትም? ታድያ አንዲት እኅት ለመከበርና ለመታፈር ከዚህ በላይ ምን ማድረግ ትችላለች?
ጡጫ መሰንዘር የአእምሮ ታናሽነት ማሳያ ነው፤ ጡጫ መሠንዘር የጥበብ መጉደል ምልክት ነው፤ ጡጫ መሠንዘር ሃሳብ አልባነት ነው፤ ጡጫ መሠንዘር በውይይትና ክርክር ለመርታት አልችልም ብሎ ቀድሞ መሸነፍ ነው፡፡ ስሜትን ለማሸነፍ የማይችሉ ሰዎች የመፍትሔ አቅጣጫ ነው -ጡጫ፡፡
ብዙዎቻችን የተማርነው ወጥተን ለመቀጠር የሚያገለግለንን ብቻ ነው፡፡ በተማሩት ትምህርት አመለካከታቸው የተለወጠ ሰዎች ዕድለኞች ናቸው፡፡ ‹ደመወዛቸው የዶክተር አመለካከታቸው ግን የኋላ ቀር› የሆኑ አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ሲቪያቸውና ማንነታቸው አብሮ የማይሄድላቸው ናቸው፡፡ የቤት ቀጋ የውጭ አልጋ የሚሏቸው ዓይነት፡፡ ገና አእምራቸው ወፍሮ ጡንቻቸው ያልረገበ ዓይነት፡፡ ደበበ ሰይፉ ‹ጥሬ ጨው ጥሬ ጨው ጥሬ ጨዋዎች፣ መሰለቅ፣ መደቆስ ገና ሚቀራቸው› የሚላቸው ዓይነት፡፡
‹የተማረ› ወንድም ለእኅቱ የውርደት መንሥኤ መሆን አልነበረበትም፤ የትንሣኤዋ ፋና ወጊ እንጂ፤ ኮሌጅ መበጠስና ሰውን በቡጢ መበጠስ አብረው ከተጓዙ ትምህርት የገንዘብ ኪሣራ እንጂ የእእምሮ ልማት መሆኑ ያበቃለታል፡፡
በተደፈሩ ሴቶች ላይ ጥናት ያደረጉ አካላት ኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኞቹ ሴቶች በተላይ ሕፃናት ሴቶች የሚደፈሩት በቅርብ ቤተሰቦቻቸው ወይም ጎረቤቶቻቸው መሆኑን ይገልጣሉ፡፡ የዚህም አንዱና ዋናው ምክንያት ነገሩ ስለሚሸፋፈንና ከቤተሰብ ውርደትና ክብር ጋር ስለሚያያዝ ነው፡፡ ይኼም ነገር ነገ ‹ታድያ ወንድምሽ አይደል? የታላቅ ወንድም ደንቡ ነው› በሚሉ ቤተ ሰቦች ወይም ሽማግላች ቀልድ እንደሚኮላሽ አስባለሁ፡፡
ግን እኅቶቻችን ከቤት እስከ ቢሮ እየተጠቁ፣ ያውም በዘመዶቻቸውና በባሎቻቸው፣ በወዳጆቻቸውና በቀራቢዎቻቸው እየተዋረዱ እስከ መቼ? ያውም በ21ኛው መክዘ፡