ከዘር ወደ ኢትዮጵያዊነት ፖለቲካ – ምክር ለኢሕአዴግ (ግርማ ካሳ)
በምርጫ ዘጠና «ይህ ሕዝብ የሚፈልገዉ የመጣህበትን መሰረት አይደለም። የመጣህበትን ብሄር አይደለም። የምትሰራለትን ስራ ነዉ» የሚለዉ፣ አቶ በረከት ስምኦን ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር ካደረጉት ቃለ ምልልስ የተቀነጨበ ግሩም አባባል ነዉ። ከአንድ ከኢሕአዴግ አመራር አባል ብዙ ጊዜ የማንሰማው አባባል !!!
ከአንድ አመት በፊት ለሶስት ሳምንታት አሜሪካን ለመጎብኘት የመጣ፣ አንድ ሰዉ በወቅቱ ያስደሰተኝ፣ አንድ ወሬ አወጋኝ። አቶ መለስ የሚመሩት የኢሕአዴግ ማእከላዊ ኮሚቴ ይሁን ጠቅላላ ጉባኤ፣ ስብሰባ አድርጎ በነበረ ወቅት የሆነ ነገር ነዉ። ከስብሰባው መካከል ከዚህ በፊት ተነስተዉ የማያውቁ ጥያቄዎች መጠየቅ፣ ቀርበው የማያውቁ አስተያየቶች መሰጠት ጀመሩ። «ለምን የብሄር ብሄረሰብ እና የዘር ነገር ላይ እናተኩራለን ? ሕዝቡ ይሄን አይፈልግም። አንድነትን ነዉ የሚፈልገዉ ? ለምን የስራ ሃላፊነት በሞያ ብቃት ሊሆን ሲገባዉ በዘር ይሆናል ? ለምን ብቃት ያላቸው ኢትዮጵያዉያን ከዚህ ብሄር አይደላችሁም ተብለው በአንዳንድ ክልሎች እንዳይሰሩ ይታገዳሉ ? ይሄን ኢሕአዴግ ማስተካከል አለበት …ወዘተረፈ » የሚሉ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ነበሩ ሲቀርቡ የነበሩት።
ታዲያ አሁን አቶ በረከት «ይህ ሕዝብ የሚፈልገዉ የመጣህበትን መሰረት አይደለም። የመጣህበትን ብሄር አይደለም። የምትሰራለትን ስራ ነዉ» ሲሉ ገረመኝ። «ከአንድ አመት በፊት የደረሰኝ መረጃ ትክክለኛ ነበር ማለት ነዉ?» ብዬ እራሴን ጠየኩ።
ይሄ ብቻ አይደለም። የአቶ መለስ ወዳጅ እና ልዩ አማካሪ የነበሩ፣ በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ለኢሕአዴግ ተሟጋችና «ጠበቃ» ተብለው ይቆጠሩ ከነበሩ ጥቂት ግለሰቦች መካከል በቀዳሚነትና በዋናነት የሚጠቀሱ አሜሪካዊዉ ፖል ሄንዚ ነበሩ። እኝህ ሰው በምርጫ ዘጠና ሰባት ወቅት በኢትዮጵያ የተፈጠረዉን ሁኔታ ከግምት ዉስጥ በማስገባት፣ ኢሕአዴግን የመከሩት አንዳንድ ምክሮች ነበሩ።
«ከ1991 በሁዋላ የተፈጠረዉ የፖለቲካ ስርዓት ብዙ ያልተጠና (Ad Hoc) እና ደርግ ሲወድቅ የነበረዉን ሁኔታ ያንጸባረቀ ነበር። ነገር ግን የማይቀየርና የማይሻሻል ተደርጎ ሊወሰድ አይገባዉም። ለምን ብዙ ጠቃሚ ያልሆኑ ሁኔታዎች እንዲከሰቱ አድርጓል» በማለት ነበር ፓል ሄንዝ የጻፉት።
ጠቃሚና አላስፈላጊ ካሉዋቸው ነጥቦች መካከል፣ በኢሕአዴግ ስርአት ከመጠን ያለፈ ጊዜና ጉልበት ለብሄር ብሄረሰቦች በደልና ብሶት መሰጠቱ እንዲሁም የትኩረት አቅጣጫዉ ከልክ ባለፈ መልኩ በብሄር ብሄረሰብ ወይንም በዘር ላይ መሆኑ ይገኙበታል።
በዚህም ምክንያት ፕል ሄንዝ ፣ ኢሕአዴግ በዘር ላይ ከማተኮር በአንድነት ላይ ማተኮር እንዳለበት፣ በዘር ላይ የተመሰረቱ ድርጅቶች ግንባር መሆኑ ቀርቶ፣ የኢትዮጵያዉያንን በሙሉ ጥቅም ለማስጠበቅ የቆመ አንድ ሕብረ ሄራዊ ፓርቲ ቢሆን መልካም ሊሆን እንደሚችል ነበር የገለጹት።
“If a majority of EPRDF leadership agrees that the entire party structure of Ethiopia should be changed, they would be well advised to pre-empt Kinijit by announcing the transformation of EPRDF into a party with a new name and new character. Among names that could be considered most appropriate might simply be “Ethiopian Democratic Party (EDP)” which would declare adherence to a platform for protecting the unity and integrity of the country, furthering its development and modernization in all respects with a firm commitment to democracy. ” ነበር ያሉት እኝህ ምሁር።
በፕል ሄንዝ አስተያየት ላይ የራሳቸዉን ተጨማሪ አስተያየት የሰጡት በዉጭ አገር የሚኖሩ አቶ ሳሙዔል ገብሩ ሲጽፉ «The notion of placing one’s ethnic affiliation above one’s status as being an Ethiopian has plagued the country’s political development. Ethiopians tend to declare each other as either “the oppressed” or “the oppressor” without recognizing that at one point in our history we were all oppressed and oppressors » በማለት የአቶ ፖል ሄንዚ አስተያየቶች ይጋራሉ።
ኢሕአዴግ፣ ከአራት በዘር ላይ የተደራጁ ድርጅቶች ስብሰብ መሆኑ ከበፊትም እንደማይዋጥላቸው የገለጹት አቶ ሳሙኤል «I would rather have the EPRDF as a political party and that be it. Too much concentration on one’s ethnicity further divides Ethiopia’s unity» ሲሉ ኢሕአዴግ ማሻሻያዎች እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዉም ነበር::
እንግዲህ ኢሕአዴግ በምርጫ ዘጠና ሰባት የተመለከተዉን የሕዝቡን ስሜት አስተዉሎ፣ ኢትዮጵያዉያን የተዋለዱ፣ የተደባለቁ፣ ለመቶ አመታት ተከባብረዉ ተዋደዉ የኖሩ መሆናቸዉን ተረድቶ፣ እንዲሁም እንደ ፖል ሄንዝና እና አቶ ሳሙኤል ገብሩ ያሉ ያቀረቡትን አስተያየቶች ከግምት በማስገባት፣ ደረጃ በጠበቀ መልኩ ኢትዮጵያዉያንን በሚያስተሳሰርና በሚያቀራረብ አጀንዳዎች ዙርያ መስራት ብዙ ይጠበቅበታል።
እርግጥ ነዉ እንደምንሰማዉ በቅርብ ጊዜ ዉስጥ ሕወሃት፣ ኦህዴድ፣ የአማራዉና የደቡብ ድርጅቶች እንደሚዋሃዱ ነዉ። ነገር ግን ከአራት ድርጅቶች ግንባርነት ወደ አንድ ፓርቲ መዞር በራሱ መሰረታዊ ለውጥ ሊሆን አይችልም።
መሰረታዊ ለዉጥ ማለት እነ ፓል ሄንዚ እንደመከሩት ኢሕአዴግ የአገሪቷን በዘር ላይ ያተኮረ ሕገ መንግስት እንዲሻሻል በማድረግ ዙሩያ ቀዳሚ በመሆን እንቅስቃሴዎች ሲጀምር ነዉ።
አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስተር ሃይለማሪያም ደሳለኝ፣ አቶ መለስ ዜናዊ የነበራቸዉን ፖሊሲዎች እንደማይለዉጡ እየነገሩን ነዉ። እርግጥ ነዉ በሶማሊያ በሱዳን የሚደረጉ የኢትዮጵያ ጥረቶችን፣ አባይን በመገንባት እንዲሁም ሌሎች በርካታ የልማት እንቅስቃሴዎችን በማስፈጸም ዙሪያ የአቶ መለስን ጅማሮዎች መቀጠሉ ተገቢ ነዉ።
ነገር ግን፣ የአቶ መለስን ዜጎችን በፍርደ ገምድልነት የማሰርና ዜጎችን በሽብርተኝነት የመፈረጅ ፣ ነጻ ጋዜጦችን የመዝጋት፣ የዴሞክራሲ ተቋማት በአንድ ፓርቲ ቁጥጥር ዉስጥ እንዲሆን የማድረግ የመሳሰሉ የአቶ መለስ የተሳሳቱ ፖለቲካዎችን እና አሰራሮችን መቀየርና መለወጥ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ እነ ፕል ሄንዚ እንደመከሩት ጠቃሚ የፌዴራልም ሆነ የክልል ሕገ መንግስቶች ላይ ማሻሻያዎች ማድረግ ይኖርባቸዋል።
እርግጥ ነዉ አቶ በረከት እንዳሉት «ይህ ሕዝብ የሚፈልገዉ የመጣህበትን መሰረት አይደለም። የመጣህበትን ብሄር አይደለም። የምትሰራለትን ስራ ነዉ» ። የዚያኑ ያህል ደግሞ ይህ ሕዝብ የሚያገለግለዉና የሚያከብረዉ መሪና ደርጅት ነዉ የሚፈልገዉ። አዲሱ የአቶ ኃይለማርያም ኢሕአዴግ የአቶ መለስ ኢሕአዴግ የጀመራቸዉን ጥሩ ስራዎች ያዝ ፣ ጎጂ የሆኑትን ደግሞ ጣል አድርጎ ሕዝቡ የሚፈልገዉን አይነት ድርጅት ቢሆን፣ ለኢሕአዴግም ለኢትዮጵያም የሚጠቅም ነዉ ባይ ነኝ።
እንግዲህ እግዚአብሄር አራት ኪሉ ላሉቱ ማስተዋልና ልቦና ይስጣቸው !