ከባህር የወጣች አሳ
ተስፋዬ ገብረአብ
ብርድ እንዳገረጣት – እንደ ወይራ ቅጠል፣
ድምፁ እንደሚሰማው፣ እንደ ክረምት ማዕበል፣
በምልምል ግንድ ላይ፣ አንድ ዘለላ ቅጠል፣ ሆኜ የአሸንቋጦ፣
ነፋስ አወዛውዞ፣ ሊጥለኝ ነው ቆርጦ፣
(ግጥም – አሌክሳንድር ፑሽኪን)
– አያልነህ ሙላቱ እንደተረጎመው –
ከፖቶማክ ወንዝ ዳርቻ ከሚገኘው ሬስቶራንት በረንዳው ላይ ተቀምጣለች። ይህ ዋሽንግተን ዲሲ ነው። ወንዙን የተሻገረ ግን ቨርጂኒያ ገባ ማለት ይሆናል። ዓይኖቿን አሻግራ ወንዙን በዝምታ ስታጤነው ቆየች። ከመኖሪያዋ ርቃ ወደዚህ ሬስቶራንት የመጣችው ብቻዋን መሆን በመፈለጓ ነበር። ያዘዘችውን የሎሚ ጭማቂ ቀመስ አደረገችለት። እና እጇ ላይ ሲታሽ የከረመውን የቾምስኪ መጽሐፍ ለማውጣት ቦርሳዋን ስትከፍት አንድ መልከቀና ጎረምሳ በቀጥታ ወደሷ ሲመጣ ተመለከተች። በፈገግታ እንደተዋጠ እጁን ዘርግቶ ሰላምታ አቀረበላት። አላወቀችውም። ቢሆንም እሷም ፈገግ ብላ የተዘረጋላትን እጅ በትህትና ጨበጠች።