አንድ ምሁር በገበሬው ፊት

አንድ በእርሻ ላይ የሚሠራ ዪኒቨርሲቲ መምህር በገበሬው ዙርያ ጥናት ለመሥራት ወደ ገጠር ወጡ፡፡ የአካባቢው የገበሬዎች ማኅበርም በአካባቢው የሚኖሩትን ገበሬዎች ለጥናቱ እንዲተባበሩ ለማድረግ ስብሰባ ጠራ፡፡ ምሁሩም ከገበሬዎቹ ፊት ለፊት ተቀመጡና ስለመጡበት ሥራና ከገበሬዎቹ ስለሚጠበቁ ነገሮችም ማብራራት ጀመሩ፡፡
‹‹ጉድ አፍተርኑን፤ እዚህ የመጣነው ፍሮም ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ ከእናንተ ጋር ሚት ማድረጋችን ጉድ ኦፖርቹኒቲ ነው፡፡ ኦፍ ኮርስ እዚህ ለመምጣት ያሰብነው ቢፎር ኤ ይር ነበር፡፡ በት አንዳንድ ፕሮሲጀሮችን ለማሟላት ሃርድ ስለሆነብን ትንሽ ሌትሆነናል፡፡ ሶሪ፡፡
‹‹የኢትዮጵያ ሜይን ኢንካሟ አግሪካልቸር መሆኑን አንደርስታንድታደርጋላችሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ አግሪካልቸር ዋን ኦፍ ዘ ሜይን የሰው ልጆች አንሸንት አክቲቪቲዎች ነው፡፡ ኢንኢትዮጵያ ደግሞ ሎንግ ሂስትሪ አለው፡፡ በት አግሪካልቸራችን አንደር ደቨሎፕ ሆኗል፡፡ ፋርሚንጋችን ፑር ነው፡፡ አክቲቪቴያችን ሌበረስ ነው፡፡ ገበሬው ሳይንቲፊክ ዌይ አይጠቀምም፡፡ ፋርሚንጋችን ሜካናይዝድ አይደለም፡፡ ገበሬው ኢንፎርሜሽን እንደልቡ አያገኝም፡፡ 

ናው እኛ ሪሰርች የምንሠራበት ኤርያገበሬው ሃው ካን አቺቭ ዘኒው ቴክኖሎጂ በሚለው ዙርያ ነው፡፡ ከእናንተ ፉል ፓርቲሲፔሽን እንፈልጋለን፡፡ አይ ሆፕ ኮኦፐሬቲቭ ትሆናላችሁ፡፡ ያዘጋጀናቸው ኩዌሽነሮች አሉ፡፡ ለእነዚህ ኩዌሽነሮች ኢንፎርሜሽን ትሰጡናላችሁ፡፡ ከእናንተ መካከል ራንደምሊ ኢንፎርማንቶችን እንወስዳለን፡፡ ሳም ኦፍ ዩ ሳትመረጡ ብትቀሩ ደስፐሬት እንዳትሆኑ፡፡ ኢን አዘር ዌይ እናገኛችኋለን፡፡

እነዚህን ኢንፎርሜሽኖች ወሰደን ዳታዎቹን የእናንተን ላይፍለማስተካከል እንጠቀምበታለን፡፡ ኢሪጌሽን ላይና አኒማል ሀዝባንደሪ ላይ ለመሥራት እየተዘጋጀን ነው፡፡ አፍተር ዛት ደግሞ ሌሎች ላይ እንሄድባቸዋለን፡፡
ታንክ ዩለትብብራችሁ፡፡
ገበሬዎቹ አላጨበጨቡም፤ ራሳቸውንም አልነቀነቁም፡፡
የገበሬ ማኅበሩ ሊቀ መንበር ‹‹እስኪ ጥያቄ ያላችሁ?›› አሉ፡፡ ገበሬዎቹ ዝም አሉ፡፡ ሊቀመንበሩ ደጋግመው ቢጎተጉቱም ገበሬዎቹ ጸጥ አሉ፡፡ በመካከል አንዲት እናት ተነሡና፡፡
‹‹እስኪ የመጡት ሰውዬ ይናገሩና እንጠይቃለን›› አሉ፡፡
ሊቀ መንበሩ ግራ ገባቸውና ‹‹እርሳቸውማኮ ተናገሩ›› አሉ፡፡
‹‹እኛ ግን አልሰማናቸውም›› አሉ እኒያ እናት፡፡
‹‹ታድያ እስካሁን ምን ያደረጉ ነው የመሰላችሁ›› አሉ ሊቀ መንበሩ፡፡
‹‹እኛማ በማናውቀው ቋንቋ የመክፈቻ ጸሎት እያደረሱ ነው የመሰለን›› አሉ፡፡
(መስከረም 17 ቀን በአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ ቀርቦ በነበረ ዝግጅት ከኢትዮጵያ የመጡ ምሁር በአማርኛ ማስረዳት ሲያቅታቸው ጋዜጠኛውም በአማርኛ ሲተረጉም ለተሰማው ነገር መታሰቢያ ነው)
ቺካጎ፣ ኤሊኖይስ