ድልድይ በመደርመሱ የባህር ዳር ጐንደር የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ተስተጓጐለ

ከሪፖርተር

ከባህር ዳር ወደ ጐንደር በሚወስደው መንገድ እንፍራንዝ የሚባለው ወንዝ ላይ የተገነባው ድልድይ በደረሰበት የመደርመስ ጉዳት የትራንስፖርት እንቅስቃሴ መስተጓጐሉ ተገለጸ፡፡ በአካባቢው የነበሩ የዓይን እማኞች እንደጠቆሙት፣ በድልድዩ ላይ በአንድ ወገን በተፈጠረ መደርመስ ካሳለፍነው እሑድ ጀምሮ በባህር ዳርና በጐንደር ከተሞች መካከል ግንኙነት እንዲቋረጥ አድርጓል፡፡

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የኢንፎርሜሽንና የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በድልድዩ ላይ የደረሰው ጉዳት የተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ እንዳያስተጓጉል በተለዋጭ መንገድ እንዲጠቀሙ እየተደረገ ነው፡፡

ጉዳት የደረሰበትም ድልድይ ቢሆን አነስተኛ ተሽከርካሪዎች እየተሸጋገሩበት የሚገኝ በመሆኑ፣ ተፈጥሮ የነበረው፣ ችግር ለጊዜውም ቢሆን መፍትሔ ማግኘቱን ይጠቁማሉ፡፡
የትራፊክ እንቅስቃሴው ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ተስተጓጉሎ የነበረው የተለዋጭ መንገዱ የሚያልፍበት ቦታ ላይ ከፍተኛ ጐርፍ ስለነበረ ነው ብለዋል፡፡ ይሁንና የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት፣ ድልድዩ ለጊዜው ምንም ዓይነት ተሽከርካሪዎችን እያስተናገደ አይደለም፡፡

ድልድዩ ረዥም ዕድሜ ያለውና ያረጀ በመሆኑ፣ መንግሥት በበጀት ዓመቱ እንደገና እንዲገነቡ በዕቅድ ከያዛቸው ድልድዮች መካከል አንዱ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡

ሃያ ሜትር ርዝማኔ ይኖረዋል የተባለው አዲስ ድልድይ እስኪገነባ ድረስ ግን፣ በጊዜያዊነት የብረት መሸጋገሪያ ድልድይ እንዲሠራ በመወሰኑ፣ የብረት ድልድዩ ግንባታ ግብዓቶች ወደ አካባቢው እየተጓጓዙ መሆኑንም አቶ ሳምሶን ገልጸዋል፡፡