ቤተ ክህነትና ቤተ መንግሥት
click here for pdf
ብዙ ጊዜ መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው ሲባል፤ ለዚህም ሕግ ሲጠቀስ እሰማለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ግን የሚናገረው ከዚህ በተቃራኒው ነው፡፡ ቤተ መንግሥትና ቤተ ክህነት አንድ መሆናቸውን፡፡ እንኳን በደስታ በኀዘን እንደ ማይለያዩ፡፡
ንግሥት ዘውዲቱና አቡነ ማቴዎስ ሁለቱም የተወደዱ ነበሩ፡፡ ሁለቱም ሞተው ተለቅሶላቸው ተቀበሩ፡፡ ሁለቱም ሲሞቱ የሰው እጅ አለበት ተብሎ ታምቷል፡፡ ሁለቱም በኣታ ተቀበሩ፡፡
ዐፄ ኃይለ ሥላሴና አቡነ ቴዎፍሎስ ሁለቱም የለውጥ አራማጆች ተብለው በአዲሱ ትውልድ መጀመርያ ተመሰገኑ፡፡ ሁለቱም በኋላ ላይ ከደርግ ጋር ተጣሉ፡፡ ሁለቱም ታሠሩ፡፡ ሁለቱም ባልታወቀ ሁኔታ ተገደሉ፡፡ የሁለቱም መቃብር ለ17 ዓመታት ሳይታወቅ ኖረ፡፡ ሁለቱም ኢሕአዴግ ከገባ በኋላ ዐፅማቸው ወጥቶ ተቀበረ፡፡
መንግሥቱ ኃይለ ማርያምና አቡነ መርቆሬዎስ ሁለቱም የብሔራዊ ሸንጎ አባላት ነበሩ፡፡ ሁለቱም ኢሕአዴግ ሲገባ ከሥልጣን ‹‹ወረዱ››፡፡ ሁለቱም ከሀገር ወጡ፡፡ ሁለቱም በሕይወት ኖረው በቦታቸው የተተኩት ሲሞቱ አዩ፡፡
መለስ ዜናዊና አቡነ ጳውሎስ ሁለቱም ከ1983 ዓም በኋላ ወደ ሥልጣን መጡ፡፡ ሁለቱም በአንድ ሰሞን በሆስፒታል ዐረፉ፡፡ ሁለቱም ከእነርሱ በፊት የነበሩት መሪዎች ሳይሞቱ ቀድመው ሞቱ፡፡ በአቡነ ጳውሎስ ቀብር ላይ ጊዜያዊው ጠቅላይ ሚኒስትር ተገኙ፤ በመለስ ዜናዊም ቀብር ላይ ጊዜያዊው ፓትርያርክ ይገኛሉ፡፡
እና ቤተ ክህነትና ቤተ መንግሥት የተለያዩ ናቸው ያለው ማነው?