አትርፍ
click here for pdf
ሰውዬው ምንም ነገር የማይጠግብ ነው ይባላል፡፡ ሁሉንም ነገር የርሱ ብቻ በማድረግ የሚረካ፡፡ መደመርና ማባዛት እንጂ ማካፈልና መቀነስ ያልተማረ፡፡ አንድን ነገር በመጠቀም ሳይሆን አንድን ነገር የራስ በማድረግ ብቻ የሚረካ፡፡ አንዳንድ ሰው ገጥሟችሁ አያውቅም፡፡ ኮሚቴ ከተቋቋመ እርሱ፤ ቢሮ ከተመሠረተ እርሱ፡፡ ሹመት ከመጣ እርሱ፤ ፊልድ የሚወጣ ከሆነ እርሱ፤ ስብሰባ ከተጠራ ራሱ፤ አበል ያለው ሴሚናር ካለ እርሱ፤ የውጭ ዕድል ከመጣ ራሱ፤ ልምድ ልውውጥ ከመጣ እርሱ፤ ድግስ የሚያ ዘጋጅ ኮሚቴ ከተቋቋመ እርሱ ጥልቅ የሚል ሰው አልገጠማችሁም? እንደዚያ ዓይነት ማለት ነው፡፡
ሰውዬው ምንም ነገር የማይጠግብ ነው ይባላል፡፡ ሁሉንም ነገር የርሱ ብቻ በማድረግ የሚረካ፡፡ መደመርና ማባዛት እንጂ ማካፈልና መቀነስ ያልተማረ፡፡ አንድን ነገር በመጠቀም ሳይሆን አንድን ነገር የራስ በማድረግ ብቻ የሚረካ፡፡ አንዳንድ ሰው ገጥሟችሁ አያውቅም፡፡ ኮሚቴ ከተቋቋመ እርሱ፤ ቢሮ ከተመሠረተ እርሱ፡፡ ሹመት ከመጣ እርሱ፤ ፊልድ የሚወጣ ከሆነ እርሱ፤ ስብሰባ ከተጠራ ራሱ፤ አበል ያለው ሴሚናር ካለ እርሱ፤ የውጭ ዕድል ከመጣ ራሱ፤ ልምድ ልውውጥ ከመጣ እርሱ፤ ድግስ የሚያ ዘጋጅ ኮሚቴ ከተቋቋመ እርሱ ጥልቅ የሚል ሰው አልገጠማችሁም? እንደዚያ ዓይነት ማለት ነው፡፡
እኔ የምለው በውጭም ሆነ በውስጥ ፓርቲ፣ ድርጅት፣ ማኅበር፣ ሸንጎ፣ በተቋቋመ ቁጥር ብዙ ጊዜ የማያቸው ተመሳሳይ ሰዎችን ነው፡፡ እዚያኛው የነበሩት እዚህኛውም ይመጣሉ፤ ለዚህኛው ቡድን ቋሚ ተሰላፊ የነበሩት እንደገና ለዚያኛው ቡድን ይሰለፋሉ፡፡ ለዚያኛው ፓርቲ ላንቃቸው እስኪቀደድና ሆዳቸው እስኪደርቅ ሲሟገቱና እርሱን ያልደገፈ የማርያም ጠላት ሲሉ የነበሩት እንደገና እዚህኛው ገብተው እንደዚያው ይላሉ፡፡ እነዚህ የእግር ኳስ ተጫዋቾች እየተሸጡና እየተዛወሩ ለሌላ ቡድን እንደሚጫዎቱት እነዚህም ተሽጠውና ተዛውረው መጫወት ጀምረው ይሆን እንዴ? እንዴው ሁሉም ቦታ መግባት ያስፈልጋል ማለት ነው?
ምነው እዚህም እዚያም ድስት ጥልቅ ትያለሽ? ብለው ማማሰያን ቢጠይቋት «ባክህ እኔ ያልገባሁበት ወጥ አይጣፍጥም ብዬ ነው» አለች አሉ፡፡
የአንዳንድ ሰዎች የማዕረግ ስም ለምን የሚረዝም ይመስላችኋል? ያገኙትን ሁሉ ስለሚጠቀልሉኮ ነው፡፡ አንዳንዱስ ሕግ ወይም መመሪያ ወይም ደግሞ የመምረጫ መመዘኛ፤ አለያም ደግሞ የዕድገትና የደመወዝ ደረጃ ማሻሻያ እንዲያወጣ ሲመደብ ሕጉንና መመሪያውን ለርሱ በሚሆን ልክ የሚሰፋ ሰው አልገጠማችሁም? «3 ዓመት እንዲህ በተባለ የሥራ መደብ ላይ የሥራ ልምድ ያለው፤ ከአለቃው ጋር አራት አገር የተጓዘ፤ ቢያንስ በስድስት አገራዊ ስብሰባዎች የተካፈለ፤ ታላላቅ ባለ ሥልጣናትን የመቀበል ልምድ ያለው፤» እያለ የወጣውን መመዘኛ ስታዩት «እንዲህ ባለ የመኖርያ አድራሻ የሚኖር» የሚልና «የሸሚዝ ቁጥሩ ይህንን ያህል የሆነ» የሚል ብቻ ሲቀር ሌላው ሁሉ እርሱ ብቻ የሚያሟላው ይሆንላችኋል፡፡
ስኳሩንም፣ በርበሬውንም፣ ጤፉንም፣ ጨውንም፣ ዘይቱንም ካልሰበሰበና በመጋዝኑ ካላከማቸ የማይረካ ሰውስ አላያችሁም? አከማችቶ አከማችቶ ሕዝቡ ሲቸገር ሲያይ የሚደሰት? የሕዝቡን ችግር የገቢው ምንጭ አድርጎ በነፍስ ዋጋ እየቸረቸረ ገንዘብ ብቻ በመሰብሰብ የሚረካ? እንዲህ ያለው ስግብግብኮ እርሱ አይበላም፤ ሰውም አያበላም፤ ገንዘብ ብቻ እንደሰበሰበ ይሞትና የገዛ ልጆቹ ተካፍለው ሲበትኑት ታያላችሁ፡፡ ያደለው እንደ ቢልጌት ድርጅት አቋቁሞ ድኻውን ይረዳል፡፡ ያላደለው ደግሞ እንደዚህ ሰውዬ ሲያከማች ብቻ ይኖራል፡፡ የእርሱ ዓላማ ማከማቸት እንጂ መጠቀምና መጥቀም ስላልሆነ ከርሱ በላይ ችግረኛ የለም፡፡
ታድያ ይኼ ሰው ሰፊ የሆነ መሬት ነበረው፡፡ ነገር ግን በዚያ የመሬት ይዞታው ሊረካ አልቻለም፡፡ ዓለምን ጠቅልሎ የመያዝ ምኞት ነበረው፡፡ ልክ ቆንጆና ታዋቂ የሆነችን ሴት ሁሉ የራሱ ለማድረግ ሲኳትን እንደሚውል ቅንዝረኛ ስግብግብ፡፡
አንድ ቀን እርሱ መሬቱን ሲያሳርስ አንድ ጠቢብ ሰው በዚያ ሲያልፍ አገኘው፡፡ ብዙ ሰዎች ጠቢቡን ሰው ይከተሉት ነበር፡፡ ከተለያየ ችግራቸው ያላቅቃቸው ዘንድ፡፡ ይኼ ባለ መሬት ሰውዬ ሁኔታውን ሲያይ እርሱም ወደ ጠቢቡ ተጠጋ፡፡ ይኼኔ ጠቢቡ ተገረመ፡፡
«ደግሞ አንተ ምን ሆንክ? ይኼንን ሁሉ መሬት ታሳርሳለህ፤ እስኪ መሬትህን ተመልከተው? ለመሆኑ ልኩን ታውቀዋለህ? አንተም ከእነዚህ እኩል እኔ ጋ ምን አመጣህ?» አለው የዋሑ ጠቢብ፡፡ ለምን የዋሕ አልኩት መሰላችሁ፡፡ አባባ ታምራት ጋር ድንጋዩን ወርቅ አድርግልን እያሉ ይማልሉ የነበሩት እነማን እንደነበሩ ያልሰማ ጠቢብ በመሆኑ ነው፡፡ ዛሬም በየጠንቋዩ ቤት ሀብት ፍለጋ የሚጋፉት ችግረኞች እንዳልሆኑ ያላየ ጠቢብ ነው፡፡ ድኻው ድንጋይ እየጠረበ፤ መንገድ እያጸዳ፣ የሰው ልብስ እያጠበ፤ የጉልበት ሥራ እየሠራ፤ በሰው ቤት ተቀጥሮ፤ ዘበኛ ሆኖ ኑሮን ለማሸነፍ እየታገለ ነው ወዳጄ፡፡
እነዚህ በየጠንቋዩ ቤት የምታያቸው አብዛኞቹ ምንም ሳይለፉ ሺውን መቶ ሺ፤ ሚሊዮኑን ቢሊዮን፤ ምድር ቤቱን ፎቅ፤ የጭልፋውን በአካፋ ማድረግ የሚፈልጉትኮ ናቸው፡፡
የባንኩን ቁልፍ ለኛ
ዘበኛው ይተኛ
ሊሉኮ ነው የሚያድሩት፡፡ የሌላውን አስዘግተው የራሳቸውን ብቻ ሊያስከፍቱ፤ ሌላውን አክስረው ራሳቸውን ብቻ ሊያስተርፉ ነውኮ የሚያደገድጉት፡፡ የዋሕ ጠቢብ፡፡
«ግንኮ የኔ ከሆነው የኔ ያልሆነው ይበልጣል» አለ ባለ መሬቱ፡፡
«ሕይወት እንደዚያ ነዋ፡፡ አንድ ሰው እርሱ ከያዘው ይልቅ ያልያዘው ካልበለጠ ሕይወት አትጣፍጥም፡፡ አታጓጓም፤ ሥራ ሥራ፣ ልፋ ልፋ የሚል ጉጉት አይኖርም፡፡ ሰው የደከመው፣ የተፈላሰፈውና የሠለጠነውኮ ከሚያውቀው የማያውቀው፣ ከደረሰበት ያልደረሰበት፣ ከቻለው ያልቻለው፣ ካገኘው ያላገኘው፣ የርሱ ከሆነው ያልሆነው በመብለጡ የተነሣ ነው፡፡ እንዳንተ ያሉ ሰዎች ዕድገትንና ሥልጣኔን ይገድሏቸዋል፡፡» አለው፡፡
ባለ መሬቱ ብዙም በመልሱ አልረካም፡፡ ትክክለኛ መልስ እንጂ የሚያረካውን መልስ አላገኘም፡፡ ለባለ ሀብቱ በትክክለኛ መልስና በሚያረካ መልስ መካከል ልዩነት አለ፡፡ ትክክለኛ መልስ ማለት «አምስት በጎች ለአምስት ሰዎች ሲካፈሉ ስንት ይደርሷቸዋል?» ሲባል «አንዳንድ» የሚለው ዓይነት ነው፡፡ ይህ ግን አርኪ መልስ አይደለም፡፡ አርኪ መልስ የሚሆነው «ለባለመሬቱ አራት በጎች ይደርሱትና ቀሪዎቹ አራት ሰዎች ግን አንዱን በግ አርደው ይካፈላሉ» የሚለው ዓይነት ነው፡፡
«ይሁን እሺ፤ ግን አሁን ካለኝ መሬት በተጨማሪ ብዙ መሬት እፈልጋለሁ፡፡ ይኼ እነ እገሌ እነ እገሌ እነ እገሌ የሚያርሱት መሬት፤ እዚያ ወንዙ ዳር፣ ተራራው ሥር፣ ከሸለቆው ማዶ ያለው ሁሉ መሬት የእኔ እንዲሆን እፈልጋለሁ» አለው፡፡
ጠቢቡ ተገረመ፡፡ «ይህንን ሁሉ መሬት ለምን የራስህ ታደርገዋለህ? ሌሎቹ ሰዎችስ? ሕይወትኮ መልካም የምትሆነው በመካፈል እንጂ በማከማቸት አይደለም፡፡ አንተ የምትዘራውን ሌሎች ካልገዙህ፣ ሌሎች የሚዘሩትን አንተ ካልገዛህ ምን ዋጋ አለው፡፡ እርሱን ተወው ቢያንስ የምትፎካከረው ሰው ካላገኘህ አንደኛ መውጣትህን በምን ታውቃለህ? አላየህም እንዴ ሯጮች እንኳን በደንብ ለመሮጥና ሪከርድ ለመስበር ሲሉ ሌላ አሯሯጭ ቀጥረው ከእርሱ ጋር ይፎካከራሉ፡፡ ያለ ተመጣጣኝ ፉክክር ሕይወት ደስታ አታገኝም፡፡? አለና መከረው፡፡ ይህ ግን ትክክለኛ መልስ እንጂ የሚያረካ መልስ አልነበረም፡፡
ለባለመሬቱ «እገሌና አንተ ብትወዳደሩ ማን ያሸንፋል?» ለሚለው ጥያቄ ትክክለኛ መልስ «በሚገባ ሮጦ መሥመሩን ቀድሞ ያለፈ» የሚለው ነው፡፡ ይህ ግን አርኪ መልስ አይባልም፡፡ አርኪ መልስ የሚሆነው «ሮጦ አንደኛ ማን ወጣ የሚለው ሳይሆን እንዲያልፍ መደረግ ያለበት ማነው? በሚለው ላይ ቀድሞ በመወሰን በሚገኘው ውጤት አሸናፊው ይታወቃል» ከተባለ ነው፡፡ ይኼ ይህንን ሰውዬ ብቻ ሳይሆን ጨረታ የሚጫረቱ፣ ምርጫ የሚወዳደሩ ሰዎችንም ሊያረካ የሚችል ይሆናል፡፡
ጠቢቡ ሰው በጣም አዘነ፡፡ ለሌሎቹ ሰዎች ለሕይወታቸው የሚሆን የችግራቸውን መፍትሔ ሰጥቶ አሰናብቷቸዋል፡፡ የቀረው ይሄ ባለ መሬት ብቻ ነው፡፡ «የምትፈልገው ምን ያህል መሬት ነው?» አለና ጠቢቡ ጠየቀው፡፡ ባለ መሬቱ ልኩን መናገር ከበደው፡፡ ምናልባት በአካባቢው ያለው መሬት ከዚያ ከበለጠሳ? ረዥም ጊዜ ወሰደ፡፡ ጠቢቡ ረፈደበት፡፡
«ወዳጄ እኔ አንድ መፍትሔ ልስጥህ፡፡ ከዚህ እኔና አንተ ከቆምንበት ዛፍ ጠዋት ጀንበር ስትወጣ ተነሣና ብትፈልግ ሩጥ ብትፈልግ አዝግም፡፡ በእግርህ የረገጥከው መሬት ሁሉ ያንተ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ጀንበር ከመጥለቋ በፊት እዚህ ዛፍ ሥር መድረስ አለብህ፡፡ በል ቻው» አለውና ጠቢቡ ሄደ፡፡
ሰውዬው በደስታ ሰከረ፡፡ ማታ ራቱን በደንብ በላ፡፡ ሚስቱ ስንቁን አዘጋጀችለት፡፡ በእግሩ በአካባቢው ወዲህና ወዲያ በማለት ጥንካሬውን ፈተነ፡፡ ያስከነዳል፡፡ ዕንቅልፍ በዓይኑ አልዞረም፡፡ ልቡ ብቻ በአካባቢው ሲዞር አደረ፡፡ አሥር ጊዜ በግድግዳው ጭንቁር እያጮለቀ ጀንበር መውጣት አለመውጣቷን ሲያይ አደረ፡፡
አይነጋ የለም ነጋ፡፡
እኩል ነው ከጀንበሯ ጋር የወጣው፡፡ ሮጠ፤ ሮጠ፤ ሮጠ፤ ሮጠ፡፡ አስደሳችና አጓጊ ይሆነውን የመሬቱን መልክዐ ምድር እያየ ይህንንም ያንንም ለመጠቅለል ሮጠ፡፡ አንዱ ቦታ ሲደርስ ሌላ ይታየዋል፤ ያንን ሲያዳርስ ያላዳረሰው ይበልጥበታል፡፡ እርሱን አዳርሳለሁ ብሎ ሲሄድ ከዚያ የበለጠ ያገኛል፡፡ ይህንንማ መተው የለብኝም ብሎ ያንን በሩጫ ሲያዳርሰው ከርሱ ይበልጥ የተዋበ ያያል፡፡ ምን ያድርግ፡፡ ብቻ ሮጠ፤ ሮጠ፤ ሮጠ፤ ሮጠ፡፡
ጀንበር በስተ ምዕራብ ማቆልቆል ጀመረች፡፡ የሚገርመው ነገር እስካሁን ካየውና ከረገጠው መሬት ይልቅ ይህ አሁን የሚያየው በለጠበት፡፡ ተራራው፣ ከተራራው ሥር የሚፈልቀው ምንጭ፤ ጫካው፤ በጫካው ውስጥ የሚሰማው የወፎች ዝማሬ፡፡ እንዴት ይተወው፡፡ ሮጠ፤ ሮጠ፤ ሮጠ፤ ጀንበርም ወደ ምዕራብ ታሽቆለቁላለች፡፡ «ጥቂት ጊዜ አለኝ ቢያንስ ያንን ጫካ መጠቅለል አለብኝ አለ» የያዘውን ስንቅ እንኳን የሚበላበት ልብም ጊዜም አላገኘም፡፡ በከዳ ጉልበቱ ሮጠና እንደምንም ብሎ ጫካውን አዳረሰው፡፡ ጀንበሯ ግን ከቅድሙ በበለጠ ፍጥነት ወደ ምዕራብ መስኮቷ ልትገባ እየፈጠነች ነው፡፡
አሁን ሁሉንም ማዳረስ እንደማይችል ገባው፡፡ ከዚያ ይልቅ ትልቁ ፈተናው ጀንበሯ መስኮቷን ከፍታ ከመግባቷ በፊት ወደዚያች ዛፍ ለመመለስ መቻሉ ነው፡፡ ሩጫውን ወደ ዛፏ አደረገ፡፡ ከዛፏ እዚህ ለመድረስ ከዐሥር ሰዓት በላይ ወስዶበታል፡፡ አሁን በሁለት ሰዓታት ውስጥ እዚያች ዛፍ ላይ መድረስ ተመኘ፡፡
ጉልበቱ እየከዳው፤ አንጀቱም በረሃብ እየተሳበ፤ ጀንበሯም ከርሱ በበለጠ ፍጥነት እየተሽቆለቆለች ተጓዘ፡፡ ራሱን ማዞር፤ ሆዱን ማጥወልወል፤ ጉልበቱን ማሣሠር ጀመረው፡፡ እንዲያም ሆኖ ሮጠ፡፡ አሁን ፉክክሩ ከጀምበሯ ጋር ነው፡፡ «ምናለ እንደ ኢያሱ ፀሐይ ለማቆም በቻልኩ» አለ በልቡ፡፡ ያ የቆሎ ተማሪ ትዝ አለው፡፡
የቆሎው ተማሪ የሚካኤል ዕለት አሥራ ሁለት ቦታ ድግስ ተጠራ፡፡ ግን አሥራ ሁለት ቦታ ማዳረስ አይችልም፡፡ የገጠር መንደር እዚህና እዚያ ማዶ ነውና፡፡ ወዴትኛው ድግስ መሄድ እንዳለበት መወሰን አቅቶት መሐል መንገድ ላይ ቆሞ ሂሳብ መሥራት ጀመረ፡፡ እዚህ ብሄድ እዚያ ይሄና ያ ይቀርብኛል፡፡ እዚያ ብሄድ እዚህ ይሄና ያ ይቀርብኛል፡፡ እያለ እያሰበ መወሰን ቢያቅተው «ምናለ ለዛሬ ሚካኤል ከአሥራ ሁለት በበታተነኝ» አለ ይባላል፡፡
ሰውዬው እየተንገዳገደ ይሮጣል፡፡ ጀንበር ግን በኩራት ወደ ቤቷ ትገሠግሣለች፡፡ እርሱ የተነሣባትን ዛፍ በዓይኑ እንኳን ለማየት ገና አልደረሰም፡፡ እጅግ ርቆ መሄዱን ያወቀው አሁን ነው፡፡
ደከመውና ወደቀ፡፡ የማይደከማት ጀንበር ግን ሄደች፡፡
ወድቆ እየተሳበ ለመጓዝ ሞከረ፡፡ ግን አቃተው፡፡ ልቡ እንደ ገጠር ወፍጮ ዷዷዷ እያለች ትመታለች፡፡ እንደምንም ኃይል ሰብስቦ ተነሣና አንድ ሁለት ርምጃ ተራምዶ ለመጨረሻ ጊዜ ወደቀ፡፡ ትንፋሹ ለመጨረሻ ጊዜ ወጣች፡፡ ልቡ ቆመ፡፡ ጀንበርም ጠለቀች፡፡
ሠፈር ጎረቤቱ ተጯጩኾ በስንት ፍለጋ ጅብ ሳይበላው አገኘው፡፡
በማግሥቱ እየተለቀሰ በሦስት ክንድ ከስንዝር መሬት ውስጥ ተቀበረ፡፡ ያንን ሁሉ መሬት ያካተተው ሰውዬ ይህቺ ቁራጭ መሬት ብቻ የርሱ ሆነች፡፡ ማካፈል አቅቶት ሁሉንም አስረከበ፡፡
ሐራሬ፣ ዚምባቡዌ፡፡