በሑመራና በሱዳን ግዛት በእርሻ ሠራተኞች መካከል በተፈጠረ ግጭት በርካታ ሰዎች ሞቱ
(The Reporter) — በትግራይ ክልል በሑመራ ጠረፍና በሱዳን ግዛት ውስጥ በአረም ሥራ ላይ በተሰማሩ ሠራተኞች መካከል በተቀሰቀሰ አካባቢን መሠረት ያደረገ ግጭት ምክንያት በርካታ ሰዎች መሞታቸው ታወቀ፡፡ በአካባቢው የሚገኙ የሪፖርተር ምንጮች እንደጠቆሙት፣ ከሐምሌ አጋማሽ ጀምሮ ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በመጡ ሠራተኞች መካካል በተከሰተው ግጭት ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ ጉዳትም ደርሷል፡፡ ምንጮች እንደሚሉት፣ ከዚህ በፊትም እንዲህ ዓይነት ግጭት አልፎ አልፎ የሚከሰት ሲሆን፣ አሁን በተለይ በጎንደርና በወሎ ተወላጆች መካከል የተፈጠረው ግጭት አካባቢያዊ ስሜትን እየያዘ መጥቷል፡፡
ግጭቱ የሚከሰተው በመቧደን መሆኑን፣ በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ያለው ችግር በፀጥታ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት መረጋጋት ቢችልም፣ በሱዳን ግዛት ውስጥ ባሉት ሠራተኞች መካከል የተፈጠረው ግጭት ግን እየቀጠለ መሆኑ ተስምቷል፡፡
እንደ ምንጮች ጥቆማ፣ ከሐምሌ 18 ቀን 2004 ዓ.ም. ሃያ አራት ሰዎች በግጭቱ ሕይወታቸው ሲያልፍ፣ ነሐሴ 7 ቀን 2004 ዓ.ም. ላይ በተፈጠረው ተመሳሳይ ግጭት ደግሞ ቁጥራቸው ወደ አሥራ አንድ የሚጠጋ ሰዎቸ ሞተዋል፡፡ በርካታ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ሁኔታውን በመጣራት ላይ ነው፡፡ የማይካራ ቀበሌ (ሑመራ ወረዳ) የፀጥታ ኃላፊ የሆኑት አቶ ሳሙኤል ተፈሪ ለሪፖርተር በስልክ በሰጡት ማብራሪያ፣ እንዲህ ዓይነት ግጭት የተለመደ ቢሆንም ባለፈው ዓመት በሽማግሌዎች አማካይነት ለማስታረቅ በተደረገው ጥረት ችግሩ ተወግዶ ነበር፡፡ አቶ ሳሙኤል የሟቾቹን ቁጥር ምንጮች ከተናገሩት በታች መሆኑን የገለጹ ሲሆን፣ ነሐሴ 7 ቀን በተፈጠረው ግጭት የስምንት ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ፣ ከዚያ በፊት ከአሥራ አንድ በላይ ሰዎች መሞታቸውን አረጋግጠዋል፡፡
ግጭቱ የሚከሰተው በአብዛኛው በሠራተኞች መካከል መሆኑን፣ በወሎና በጎንደር ተወላጆች መካከል አካባቢን መሠረት ያደረገ እየሆነ መምጣቱ አምነዋል፡፡ በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ያለው ችግር በመከላከያ፣ በፖሊስና በሚሊሽያ ኃይሎች አማካይነት በቁጥጥር መዋሉን የሚገልጹት ኃላፊው፣ አስቸጋሪ የሆነባቸው ሱዳን ግዛት ተሻግረው በመሥራት ላይ በሚገኙ ዜጎች መካከል ያለው ግጭት መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ‹‹ሱዳን ግዛት ውስጥ ገብተን ማረጋጋት ተቸግረናል፤›› ብለዋል፡፡
ኃላፊው ግጭቱን በማስነሳት ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሠራተኞችን ቁጥር ባይገልጹም፣ 400 ያህል ሰዎች በማይካራ ቀበሌ በሚገኘው ዋልታ አዳራሽ ውስጥ ታሰሩ መባሉን ስህተት መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ምንጮች እንደሚሉት ግን በዋልታ አዳራሽ ከ400 በላይ ሠራተኞች ለሳምንታት የታሰሩ ሲሆን፣ በአማራ ክልል በተጠርጣሪዎች የትውልድ አካባቢ ኃላፊዎች ጋር በተደረ ምክክር ወደ ትውልድ ስፍራቸው ተወስደው ጉዳያቸው እንዲጣራ እየተደረገ ነው፡፡
በሑመራ አካባቢ የጥጥ፣ የሰሊጥና የማሽላ ሰፊ ኢንቨስትመንት ሲኖር፣ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ ሠራተኞች በአረምና በተጓዳኝ በሌላ የእርሻ ሥራዎች ተሰማርተው እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡