ኢሕአዴግ በግንባርነት ለመቀጠል ወሰነ

ከሪፖርተር

በመለስ ዜናዊ የሚመራው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ከሁለት ዓመት በፊት በሰባተኛ ጉባዔው የነደፋቸው ዕቅዶች ከሞላ ጎደል የተሳኩ መሆናቸውን አሳወቀ፡፡

ድርጅቱ አሁን ያለው የግንባርነት አደረጃጀት የላቀ ውጤት ያስገኘለት መሆኑን ስላመነበት ወደ ሌላ ደረጃ (ውህደት) የመሸጋገር ጥያቄ በስምንተኛ ጉባዔው እንደማይነሳም ታውቋል፡፡

የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሙክታር ከድር ትናንት ነሐሴ 18 ቀን 2002 ዓ.ም. ረፋድ ላይ በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ድርጅቱ ከሁለት ዓመት በፊት ባካሄደው ጉባዔ ያቀዳቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዓላማዎች ከሞላ ጎደል መሳካታቸውን ኢሕአዴግ ባካሄደው ግምገማ ማረጋገጡን አሳውቀዋል፡፡

በመጪው ዓመት መጀመሪያ ወር መስከረም በሚካሄደው ጉባዔም እነዚህን እመርታዎች አጠናክሮ ለመቀጠል የሚያስችሉ ውሳኔዎች ለማስተላለፍ መዘጋጀቱን አቶ ሙክታር ገልጸዋል፡፡ እንደ ኃላፊው ገለጻ፣ ባለፈው ወር በተካሄደው የኢሕአዴግ የአፈጻጸም ግምገማ፣ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሕገ ደንቡ በሚፈቅደው መሠረት በመጪው መስከረም ስለሚካሄደው 8ኛ ጉባዔ ዝግጅት የሚያደርግ ዓብይ ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡

ኮሚቴው ለ8ኛው የኢሕአዴግ ጉባዔ የሚያስፈልጉ ፖለቲካዊና ድርጅታዊ ዝግጅቶች እስካሁን ያጠናቀቀ ሲሆን፣ የተቀሩትም በቅርቡ ይጠናቀቃሉ ተብለው እንደሚጠበቁ ተገልጿል፡፡ ንዑስን ኮሚቴዎችም ተዋቅረዋል፡፡

በአዳማ ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው የኢሕአዴግ 8ኛ ጉባዔ፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት የድርጅቱን አፈጻጸም በተመለከተ ሪፖርት የሚቀርብ ሲሆን፣ ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ያቅዳል፣ በድርጅቱ ኦዲትና ቁጥጥር ኮሚሽንም ላይ ይነጋገራል፡፡ በጉባዔው የድርጅቱ የምክር ቤት አባላትና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፣ የድርጅቱን ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበርም ይመረጣሉ፡፡

አቶ ሙክታር፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ድርጅታቸው ኢሕአዴግ ይዟቸው የነበሩ ዕቅዶችና አፈጻጸማቸው በሁሉም ዘርፎች ከፍተኛ ስኬት መመዝገቡን መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡ ኢኮኖሚያዊ ዘርፉን በተመለከተ፣ ኢሕአዴግ የ6ኛ ጉባዔ ውሳኔዎች ተከትሎ የተመዘገበው 11 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ተጠናክሮ መቀጠሉንና እስከ አሁን ለሰባት ተከታታይ ዓመታት ተመሳሳይ ዕድገት መመዝገቡን የድርጅታቸው መስመር ትክክለኛነት የሚያረጋግጥ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በእጥፍ ያደገባቸው እነዚህ ዘመናት፣ መላው ሕዝብ የውጤቱ ተጠቃሚ መሆኑንም መረጋገጡ ኢሕአዴግ ያምናል፡፡ በዕድገቱ ቁጥር ላይ መጠነኛ ልዩነት ያለ ቢሆንም የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ የመሳሰሉ ተቋማትም ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ያለ መሆኑን ቢያምኑም፣ ዕድገቱ ሰፊውን ሕዝብ ተጠቃሚ ያደረገ ስለመሆኑ ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ በተለይ ተቃዋሚዎች ደግሞ፣ ‹‹አለ የሚባለው ዕድገት በመሬት አልታይ አለን፣ ሕዝቡ አሁንም እንደተራበ ነው›› በሚል ተደጋጋሚ ትችት ሲያቀርቡ ይደመጣል፡፡ ኢሕአዴግ ግን የኢኮኖሚ ዕድገቱ ግብርናን መሠረት ያደረገ በመሆኑ፣ በተለይ የገበሬውን ሕይወት እየቀየረ ነው የሚል ምላሽ ይሰጣል፡፡ በመንግሥት ሚድያ እንደሚገለጸው፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በርካታ ‹‹ሚሊዮነር አርሶ አደሮች›› ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እጅ ሽልማት ሲቀበሉ ተስተውሏል፡፡

ድርጅቱ በዴሞክራሲና በመልካም አስተዳደር መስክም፣ ከፍተኛ እመርታ ማስመዝገቡን ይገልጻል፡፡ የኢሕአዴግ ፖለቲካዊ ትንታኔ የሚያቀርበው አዲስ ራዕይ መጽሔት የሐምሌ 2000 ዓ.ም. ልዩ ዕትም የ7ኛ ጉባዔ ሪፖርት በስፋት እንደቀረበው፣ በ1997 ዓ.ም. ምርጫ ማግስት የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ መለስን ጨምሮ የኢሕአዴግ ከፍተኛ አመራሮች ከሕዝቡ ጋር ባካሄዱት ውይይት ሕዝቡ ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ቅሬታ እንደነበረው ገዥው ፓርቲ ግንዛቤ ወስዷል፡፡ በዚህ መሠረት በገጠርም ሆነ በከተማ የመልካም አስተዳደር እጦትን ለማስወገድና የዴሞክራሲ ግንባታ ለማረጋገጥ ባደረገው ጥረት ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቡን አቶ ሙክታር ይናገራሉ፡፡

በድርጅታዊና በፖለቲካዊ ጉዳዮችም ኢሕአዴግ ራሱን ከመቼውም በላይ ማጠናከሩን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ የአመራር መተካካትን ለማረጋገጥ ኢሕአዴግ ሰፊ የፖለቲካ ሥልጠና ማካሄዱ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች በአባልነት ማሰባሰብ መቻሉን እንደድርጅታዊና ፖለቲካዊ ስኬት አስቀምጧል፡፡ በአንዳንድ ወገኖችና በተቃዋሚዎች እነዚህ ከአምስት ሚሊዮን የሚበልጡ አዳዲስ የኢሕአዴግ አባላት ‹‹በጥቅማ ጥቅም የተደለሉ ናቸው›› በሚል ይተቻሉ፡፡ ኢሕአዴግ ግን ሕዝቡ የድርጅቱን መስመር እየተረዳ መምጣቱን በአንድ ወገን፣ የኢሕአዴግ ካድሬዎች የማሳመን ብቃት በሌላ ወገን፤ ውጤት አድርጎ ይመለከተዋል፡፡

ወደ ምርጫ 2002 ዓ.ም. ውጤት ከመግባታቸው በፊት አቶ ሙክታር እነዚህ ከላይ የተጠቃቀሱ እምርታዎችን አስመልክተው፣ ‹‹በአጠቃላይ ኢሕአዴግ ስኬታማ ፓርቲ መሆኑን አረጋግጧል›› ሲሉ ድርጅታቸውን አንቆለጳጵሰዋል፡፡ የምርጫ 2002 ውጤትም የእነዚህ ስኬቶች ውጤት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በመጪው ዓመት መስከረም 5 ቀን በሚጀመረው የኢሕአዴግ ጉባዔ ስለሚቀርቡ አጀንዳዎችና የሚነደፉ ቀጣዩ ድርጅታዊ ዕቅዶች ገለጻ ተከትሎ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የምርጫ 2002 ውጤት ተከትሎ በራሱ በኢሕአዴግም የታመነበት በአገሪቱ የተመሠረተው ‹‹የአውራ ፓርቲነት›› ፖለቲካ፣ የኢሕአዴግ የአመራር መተካካትና የኢሕአዴግ የውስጥ አደረጃጀት ጥያቄ ከጋዜጠኞች ከቀረቡ ጥያቄዎች መካከል ናቸው፡፡

አቶ ሙክታር፣ በተለያዩ አጋጣሚዎች ተገልጸዋል ያሉት የአውራ ፓርቲ ‹‹መድበለ ሥርዓት›› ወደ ተተካኪ ሥርዓት የሚሸጋገርበት አቅጣጫ እንደሚኖርና ተቃዋሚዎችም ፓርላማ ባይገቡም በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች በሚደረጉ ውይይቶች ተሳታፊ የሚሆኑበትና ሐሳባቸው የሚካተትበት አሠራር እንደሚኖር አስረድተዋል፡፡ አቶ ሙክታር ያብራሩት፣ የተቃዋሚዎች በአገራዊ ጉዳዮች የማሳተፍ ሐሳብ፣ ራሱ ኢሕአዴግም ያልጠበቀው የ2002 ‹‹አስገራሚ ውጤት›› ተከትሎ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተገባው ቃል ሲሆን፣ የአውራ ፓርቲ፣ አንድ ፓርቲና ተተካኪ ሥርዓት ጉዳዮች ደግሞ በአዲስ ራዕይ መጽሔት ሐምሌ-ነሐሴ 2002 ዕትም ‹‹የምርጫ 2002 ስትራቴጂካዊ ፋይዳ›› በሚል የቀረበውን የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ትንታኔ የሚያጠናክር ነው፡፡ ‹‹ተቃዋሚዎች እንደልባቸው መንቀሳቀስ የሚያስችል አስተማማኝ ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና ያለው የፖለቲካ ምኅዳር እስካለ ድረስ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት አደጋ ውስጥ አይደለም›› ብለዋል፡፡

የአመራር መተካካትን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄም፣ የመስመር ቀጣይነትን ለማረጋገጥ ምንም ዓይነት የፖለቲካ ክፍተት ሳይፈጠር የአመራር ቅብብሎሽን ለመፍጠር መተካካቱ የተሳካ ይሆናል የሚል እምነት አላቸው፣ አቶ ሙክታር፡፡

ኢሕአዴግ ከግንባርነት ወደ ውህደት የመሸጋገር ጥያቄ የ8ኛ ጉባዔው አጀንዳ ይሆን እንደሆነ፣ በምርጫ 2002 የተገኘው አስገራሚው ውጤትም የተቃዋሚዎች ድክመት ብቻ የሚያመላክት ነው? ወይስ ኢሕአዴግ ራሱ ያመነበት ስህተት አለና በቀጣዩ ከዚህ የተሻለ ተቀባይነት ያለው ምርጫ ለማካሄድ ዕቅድ አለው? በሚል ከሪፖርተር ለቀረበው ጥያቄ ሰፋ ያለ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ኢሕአዴግ ባለፉት አምስት ዓመታት ላይ ያካሄደው ግምገማ ውጤት አወንታዊ መሆኑን ቢገልፅም፤ ‹‹እነዚህ የተገኙት ድሎች ያለ ድክመት የመጡ ናቸው ብለን አናምንም›› በማለት፣ በመጪው ጉባዔ ሰፊ ውይይት የሚያስፈልጋቸው ድክመቶች እንደሚኖሩ አመላክተዋል፡፡ ‹‹በተደጋጋሚ እንደተገለጸው፣ ኢሕአዴግ የመላዕክት ስብስብ አይደለም፣ የሰዎች ስብስብና ነውና ስህተቶች መኖራቸው አይቀርም፤›› በማለት፡፡
ኢሕአዴግ የአራት ፓርቲዎች ግንባር ሲሆን፣ ወደ ውህደት የማምራት ዕቅድ ካለውና የ8ኛ ጉባዔው አንድ አጀንዳ ይሆን እንደሆነ በተመለከተ ለቀረበ ጥያቄም፣ ‹‹እስከ አሁን ድረስ ጥያቄው ዝግ አይደለም፤ ነገር ግን አሁን እየሠራበት ያለው የግንባርነት ደረጃ የላቀ ውጤት ያስመዘገበበት መሆኑን ስለታመነበት፣ በዚሁ ለመቀጠል ወስኗል›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፤ የጉባዔው አጀንዳ እንደማይሆንም በማረጋገጥ፡፡

የኢሕአዴግ የአመራር አመራረጥ ዴሞክራሲያዊነት የጎደለው መሆኑን አስተያየት በመስጠት እያንዳንዱ አባል አመራሩን በነፃነት የሚመርጥበት መንገድ ድርጅቱ አልፈለገም ወይ? የሚለው ከሌላ ጋዜጠኛ ለቀረበው ጥያቄም፣ ‹‹ከዚህ በፊትም አባሉ አመራሩን በነፃነት ሲመርጥ ቆይቷል›› በሚል የተሰጠውን አስተያየት ያስተባበሉት አቶ ሙክታር፣ በቀጣዩም የአባሉ ነፃነት በነበረበት ይቀጥላል የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ሙስናን በተመለከተ ለተነሳው ጥያቄም፣ ድርጅቱ ‹‹ኪራይ ሰብሳቢነት›› የሥርዓቱ ዋነኛ አደጋ ነው ብሎ በግልጽ የሚያምን በመሆኑ፣ በተለያዩ መንገዶች ‹‹ሙስናን የሚፀየፍ ኅብረተሰብ እንፈጥራለን›› የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ በቀዳሚነት ሙስናን መከላከል የሚቻልበት መንገድ በመከተል፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ፣ በሙሰኞች ላይ ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ኢሕአዴግ ቁርጠኛ አቋም እንዳለው ተናግረዋል፡፡

ኢሕአዴግ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ ወደ ሶሻል ዴሞክራሲ የመሸጋገር አዝማሚያው የቀጣዩ ጉባዔ አጀንዳ ይሆን እንደሆነ ከሪፖርተር ለተነሳው ጥያቄ ኃላፊው ምላሽ ሳይሰጡ ቀርተዋል፡፡

መስከረም 5 ቀን 2003 ዓ.ም. የሚካሄደው ጉባዔ ‹‹ታሪካዊ ነው›› ያሉት አቶ ሙክታር፣ የሴቶችና የወጣቶች ሊጎች እንዲሁም ደግሞ የውጭ አገር እንግዶችና የወዳጅ ፓርቲዎች ተወካዮች በክብር እንግድነት እንደሚጋበዙ ተናግረዋል፡፡

ኢሕአዴግ በ7ኛ ጉባዔው የክብር እንግዳ አድርጎ የጋበዘው የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ አመራርን ሲሆን፣ ከአሜሪካና ከአውሮፓ የተጋበዘ ከፍተኛ ባለሥልጣን እንዳልነበር ይታወሳል፡፡