ሞትና የኢትዮጵያ መሪዎች

ቅኝት፤ መስፍን ማሞ ተሰማ

መንደርደሪያ 

ወደ መጣሁባት ምድር

እስክመለስባት በፍቅር

ሰውን ከማስደሰት በቀር

አይወጣኝም ክፉ ነገር፤

ልዕልት ድምፃዊት ብዙነሽ በቀለ ነበረች በጥዑመ ዜማ የታጀበውን ይህንን ግጥም ያንቆረቆረችው። አዎ! ሠው በምድር ቆይታው ለአምሳያው ሠው መልካም ነገሮችን አበርክቶ፤ በፍቅርና በሠላም ኖሮ ማለፍ ከቻለ እንደምን ያለፀጋና መታደል ነው?! ፀጋነቱም መልካም ምግባሩና በፍቅር የተገነባው ሰብዕናው ስሙን ከመቃብር በላይ ህያው ማድረጉ ብቻም ሳይሆን ግዑዝ አካሉ ሞትንም ድል ነስቶ ለቋሚው የህይወት መምህርና የመልካምነት ተምሳሌ ሆኖ ከዘመን ዘመን፤ ከትውልድ ትውልድ መሻገር መቻሉም ጭምር እንጂ።