ለሰይጣንም የሚገባውን አትንፈጉት ! በካፋ ኃይለ የሱስ

ይህንን ጽሁፍ ከምርጫው በፊት በድረገጽ ላይ ለማስፈር አስቤ ነበር የጀመርሁት። የምርጫውን ቀን ዘንግቼ ኖሮ ልክ ስጨርስ ምርጫው በማግስቱ መሆኑን ተረዳሁ ! ዓላማዬ አንዱን ወገን ለይቼ ለመደገፍ ስላልነበር ምርጫው ቢአልፍም ይነበብ ብዬ እነሆ አሰፈርሁት።

የምርጫው ማለፍ ከጽሁፉ ውስጥ የቀነሰው ወይም የጨመረው አስተሳሰብ የለም። ያው የነበረኝን እምነት ነው ያቀረብሁት።

‘’ለሰይጣንም የሚገባውን አትንፈጉት’’ የሚለው አነጋገር ወይም ተረት በትውልድ አገሬ በኢትዮጵያ ባይለመድም ቃል በቃል ወስደን ለሰይጣን ምሱን ጭዳ እናቅርብለት አስካላልን ድረስ ከማህበረሰብ አንፃር ሲታይ ሚዛናዊና የሚገባ አስተሳሰብ ነው። በመንፈሳዊ አስተሳሰብም ቢሆን “ለሰይጣን” የሚለውን ቃል ሳናነሳ መልካም ለዋለልህ መልካም ዋልለት ከማለትም አልፎ ክፉ ለዋለብህ ደግ ዋልለት ነው የሚባለው። በግለሰቦች መካከል ይህን ለመከተል ከፍተኛ የመንፈስ ጥንካሬና ሚዛናዊነትን የሚጠይቅ ቢሆንም ሃገርን በሚመለከት ግን እያንዳንዱ ዜጋ በሃቀኝነት ቢአከብረው ይጠቅም ነበር።

በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ ያለው መንግሥትና ካድሬዎቹ እንዲሁም ተቃዋሚዎቹና ደጋፊወቻቸው በሃቅም ሆነ በቅጥፈት የሚአሰራጩት ፕሮፓጋንዳ እንደየድርሻቸው ሰሚ አያጣም:: ነገር ግን ሁለቱም ተቀናቃኞች ጥላቻንና ለስልጣን ጉጉትን መሰረት አድርገው ብቻ ስለተነሱ አንዳንድ ጉሉህ ሃቅ እየተዛባና እየተሽፈነ ከሰሚው መካከል የሚሳሳተው እንዳይበዛ ያሰጋል።

መታገልም ሆነ ማታገል መምረጥም ሆነ መመረጥ በማልችልበት፣ በገዛ ፈቃዴ በተውሁት የትውልድ አገሬ ጉዳይ ከሌሎች እንደምሰማውና በሌሎች እንደሚጻፈው በገነፈለ ስሜት የምሰጠው አስተያየት አይኖረኝም። ቢኖረኝም ሩቅ ሰፋሪ በመሆኔ ግንባር እንደተሰለፈ ታጋይ በጋለ ስሜት ብተች “ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ ነው” እንዳልባል እተወዋለሁ። ነገር ግን ከሁለቱም ተቃራኒ ወገኖች ማለት ከኢትዮጵያ መንግሥትና ከተቃዋሚወቹ፣ህዝቡን ለማሳመንና ደጋፊ ለማብዛት ስለሚደረገው ርብርብ በአየር የሚተላለፈውን ሳይና ሳዳምጥ፣ መራጭ ብሆን ኖሮ ግራ እንደሚገባኝና ሳልመርጥ እንደምቀር እየተረዳሁ ነው። በብዙ ጥረት ያዳፈንሁትን ጥላቻና ቂም ጭሬ ባራግበው እንኳን፣ በየትኛው ወገን ላይ እንደሚአተኩር እርግጠኛ አይደለሁም! (ቂምና ጥላቻ ስልም ባንዱ ወገን ላይ ብቻ ያተኮረ አይደለም!)

ለአገርና ለህዝብ ጥቅም እኔ እበልጣለሁ በማለት ሁለቱም ወገን በቅጥፈት ወይም በምኞት የሚገቡት ቃል እጅግ ብዙ ነው። መፈጸሙ ወይም አለመፈጸሙ በኋላ ነው የሚታየው። ለምርጫ በሚቀርቡት ፓርቲወች ዉስጥ ጐልተው የሚታዩት ግለሰቦች ቢገመገሙ ግን፣ አቶ መለስ ዜናዊና አቶ ግርማ ወልደጊዮርጊስ ወይስ አቶ ሰየ አብርሃና አቶ ነጋሶ ጊዳዳ ሊሻሉ ነው?

የመቶአለቃ ግርማ ከቁጥር መግባት አንባቢን ግራ ሊአጋባ ይችል ይሆናል። ሚናቸው አነስተኛ ቢሆንም ከመሰሎቻቸው ጋር በሁዋላ ስለሚጠቀሱ ነው ያነሳሁአቸው።

ዎያኔ ደርግን ድል አድርጐ አገሪቱን ከተቆጣጣረ በኋላ ለዘመናት የኖረውን የክፍላተሃገር ክልል ሽሮ በዘርና በቋንቋ በተመሰረተ ክልል ሲአደራጅ አቶ ሰየና አቶ ነጋሶ የት ነበሩ?

በዚያ ዘመን ነፍስ ያወቀ ሁሉ እንደማይረሳው አቶ ሰየ የኢትዮጵያ የመከላከያ ሚንስትር ሆነው ለኢትዮጵያውያን ሁሉ ሳይሆን ለዘረኞች ብቻ አጋር የነበረውን ሰራዊት ሲመሩና የዘረኝነቱን ፖሊሲ በሃይል ሲአስከብሩ፣ አቶ ነጋሶ ደግሞ የኢትዮጵያ ፕሬዘዳንት ተብለው ያለአድልኦ ለመላው ኢትዮጵያ እርቅና ሰላምን በመምከር ፈንታ በጠባብ ብሔረተኝነት ተተብትበው እነአቶ ታምራት ላይኔና አድርባይ መሰሎቻተው ያላዝኑት የነበረውን የዘረኛ ፕሮፓጋንዳ ሲአስተጋቡ የነበሩ ሰው ናቸው። እነዚህ ሁለት የተቃዋሚው ክፍል ታላላቅ መሪወች ዛሬ ለጥቅም ሲሉ ኮቶቻቸውን ገልብጠው ኢትዮጵያዊ ለሆነ ፓርቲ የጌታአዳር ቢገቡም ቀድሞ የነበራቸው የዘረኝነት አቋም ላለመለወጡ ሊያስወግዱት ያልቻሉትን ጠባብ ብሄረተኝነት በማንፀባረቅ ዘራቸውን ለየፓርቲአቸው ስም ተቀጽላ አድርገው ከተሰለፉ ፓርቲወች ጋር ማበራቸው ራሱ ማስረጃ ነው። ታዲያ አቶ መለስን ጠላሁ በማለት ብቻ ለነዚህ ሁለት ሰዎች እንዴት ይጨበጨባል! በአገሪቱ ጨርሶ ሰው ከጠፋ ለአቶ መለስ ልቦና ስጥልን ብሎ እየጸለዩ ባሉበት እንዲቆዩ መመኘት ይሻል ይሆናል እንጅ ለለየለት ወንጀለኛ ምህረት ቢደረግለትም የፖሊስ ሠራዊቱ አዛዥ ይሁን አይባልም !

የኢትዮጵያ ህዝብ ጥላቻና ቂሙን ቶሎ የመርሳት ወይም ያለቦታው የማዋል ባህሪ አለው።

ፀሃዩ ንጉሥ ! ሲላቸው ኖሮ ሌባ ! ሌባ ! እያለ ወደ እስር ቤት የላካቸውን ንጉሠ ነገሥት፣ የኮለኔል መንግሥቱ አገዛዝ ሲአንገፈግፈው “ ተፈሪ ማረኝ !” እያለ ናፈቃቸው !

“ በሮቼን ጨርሼ ልጆቸን ሳስማማ፤
ወያኔ ደረሰች በነጠላ ጫማ፤ “ ብሎ እየዘፈነ፣ ነፃ አውጪ አድርጐ የተቀበለውን መንግሥት ብዙ ወራት ሳይቆይ ከደርግ ያልተለየ የጭካኔና የአምባገነንነት ፀባዩን ሲአመጣ ህዝቡ እንደልማዱ ያለፈውን ቂም ረሳና ‘’ መንጌ ማረኝ “ ማለት ጀመረ! ምናልባት’’ መሌ ማረኝ ‘’ የሚልበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? ይህን ጉድ ለመስማት ብቻ ተቃዋሚወቹ ወየው ባሸነፉ!

ሌላው የተለመደ ባህሪ አድርባዩንና ቀጣፊውን ፈጥኖ ይቅር ማለት ነው!
ወያኔ እንደገባ በኤርትራ መገንጠልና በአሰብ ወደብ መታጣት በመቆርቆር በየስብሰባው ለሚነሱ ጥያቄወች ከአቶ መለስ ይልቅ በቁጣ በመንጨርጨር መልስ ይሰጡ የነበሩት አቶ ታምራት ላይኔና ሌሎች፣ ዳዊትና እንድርያስ የተባሉ ሁለት ሰወች ነበሩ። እነዚህ ሰወች ዛሬ ስማቸው በክፉ ብዙም አይነሳ። አሳዳሪው ለዘብ አድርጐ የሚጠቁመውን ተቀብሎ ጌታውን ለማስደሰት በበለጠ ቁጣ ከሚንጨረጨርና አግንኖ ከሚቀጥፍ፣ ለማጣ አድርባይ፣ ያው የአድርባዩ ጌታ አይነተኛው ጠላት ይሻላል!
ከሁሉም አሳፋሪና ቅሌት ሆኖ የታየው አድርባይነት ደግሞ ፣በቅርቡ የሃገሪቱ ፕረዘዳንት አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ጌቶቻቸውን ያስደሰቱ መስሏቸው ያለ ምክንያትና ያለቦታው የዘላበዱት ቅጥፈት ነው!

የታወቀው የሙዚቃ ሰው ዶክተር ጥላሁን ገሠሠ ከዚህ አለም በሞት ሲለይ ለቤተሰቡ በተላኩትና ቀብሩ ላይ በተነበቡት የሃዘን መግለጫወች፣ የአቶ መለስ ዜናዊ የሃዘን መልዕክት የደብዳቤ አፃፃፍን ስራት በተከተለ ደብዳቤ፣ ሟቹን አድንቀው፣ ሃዘናቸውን ሲገልፁ፣ አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ግን እጅግ በሚአሳፍር ሃሰተኝነት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ከአማርኛ በቀር በሌላ ብሔረሰብ ቛንቛ እንዳይዘፈን የተከለከለ ነበር፣ ሲሉ ዋሽትው፣ ዘረኝነት የማይቃጣው፣ የመንግሥት ተቀጣሪና፣ እውነተኛ ኢትዮጵያዊ፣ የነበረው አቶ ጥላሁን፣ የቛንቛ ጨቛኙን መንግሥት ተጋፍጦ በኦሮምኛ እንደዘፈነ ለማስመሰል ሞከሩ! ይህ ቅጥፈት የተሰነዘረው ዶክትር ጥላሁን በህይወት በነበረበት ጊዜ ቢሆን ኖሮ ምን ያህል ባዘነ! እነ አቶ ወሰኑ ዲዶ እነ አቶ አርጋው በዳሦ ወ፣ዘ፣ተ በህዮት ቢኖሩ እኒህን አሳዛኝ ፍጡር ምንኛ በናቋቸው! አቶ መለስ ራሳቸው በዚአንጊዜ ምንም ልጅ ቢሆኑ ‘’ እመበቴ ማሪያም እሰይ ተመስጊና፤ አባ ጠቅል ኃይሌ ኃያል ዝንጉሥና ‘’ እየተባለ በትግራይ ብሄረሰብ ቛንቛ በሬዲዮ ሲዘፈን ስለሰሙ የቀጠሯቸውን ፕሬዘዳንት ሳይታዘቧቸው አልቀሩም! አንባቢ እንዲአነፃፅራቸው የሁለቱም የሃዘን መግለጫወች ቀጥሎ ያሉት ነበሩ. . . .

ለተከበራችሁ የክቡር፣ ዶክተር፣ አርቲስት፣ ጥላሁን ገሠሠ ቤተሰቦች፣

አዲስ አበባ፣

ጉዳዩ፥ በዶክተር፣ አርቲስት፣ ጥላሁን ገሠሠ ሞት የተሰማኝን ጥልቅ ሃዘን ስለመግለጥ።

ክቡር ዶክተር፣ አርቲስት፣ ጥላሁን ገሠሠ በኢትዮጵያ ህዝቦች ሁለንተናዊ ህዮት ዙሪያ ከግማሽ ምዕት ዓመት በላይ በማዜም ከአንድ ዜጋ የሚጠበቀውን ሃላፊነት የተወጣ ጀግና ነው። በዚህ ተግባሩ ከግል ህይወቱ ይልቅ ላገሩና ለህዝቡ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል። ሙዚቃውን በካሴት በማሳተም ብቻ ሳይወሰን በተለያዩ ያገሪቱ ክፍሎችና በውጭ አገር በአካል በመዘዋወር የኢትዮጵያን ገፅታ በመገንባት ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ለሃገሩ አበርክቷል።
ክቡር ዶክተር፣አርቲስት፣ጥላሁን ገሠሠ፣ በሙዚቃው፣ ያለፈውን፣ የአሁኑንና መጭዉን ትውልድ ያገናኘ ዝነኛ ሙዚቀኛ ነው።
ስለልማት፣ ስለማህበራዊ ኑሮ፣ ስለኢኮኖሚ ወ፣ዘ፣ተ፣ ያቀነቀናቸው ዜማወች፣ ዜጐች ለልማት እድገት እንዲተጉ፣ መልካም ስነምግባር እንዲገነቡ፣ ስለአገራቸው እንዲአስቡ፣ ትምህርት ሰጥቷል። ለወደፊትም ትምህርት ሆኖ ይኖራል። በዚህ ተግባሩ በሙዚቃው መስክ ኢትዮጵያ በአፍሪቅና በአለም ደረጃ ታዋቂ እንድትሆን አድርጓል።
ኢትዮጵያ የብዙ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች፣ ሃገር ብትሆንም፣ በብሔረሰቦች ቋንቋወች ማዜም በተከለከለበት ዘመን እንኳን፣ የኦሮምኛ ዜማ በማቀንቀን አሁን በሃገራችን ለሚታየው፣ ሁሉም ብሔር፣ ብሔረሰብና ህዝቦች፣ በቋንቋቸው የመጠቀም መብት ፈር ቀድዷል። በመሆኑም ወጣቱ ትውልድ የዚህን ኩሩና ጀግና አርቲስት ፈለግ በመከተል እና የሱን ታሪክ ደግሞ በማንሳት የዜግነት ግደታቸውን ይወጣሉ የሚል ዕምነት አለኝ። የክቡር አርቲስት ዶክተር ጥላሁን ገሠሠ ከዚህ አለም በሞት መለየት ሃዘኑ የቤተሰቡ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝቦች ጭምር ነው። እሱ ቢአልፍም ሥራው ለዘላለም ስለሚኖር መፅናናት ይገባናል።
በክቡር፣ አርቲስት፣ዶክተር ጥላሁን ገሠሠ ከዚህ አለም በሞት መለየት የተሰማኝን ጥልቅ ሃዘን በኢትዮጵያ ፈደራላዊ፣ ዴሞክራሲአዊ፣ ሪፐብሊክ መንግሥትና በራሴ ስም እየገለጥሁ ለቤተሰቦቹ ብርታትና መፅናናትን እመኛለሁ።
ከሰላምታ ጋር
ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ
የኢትዮጵያ ፈደራላዊ፣ ዴሞክራሲአዊ፣ ሪፐብሊክ ፕረዜዳንት
____________________________

ለአርቲስት ዶክተር ጥላሁን ገሠሠ ቤተሰቦች፣
አዲስ አበባ
የአርቲስት ዶክተር ጥላሁን ገሠሠ ዜና እረፍትን በሚመለከት የተሰማኝን ጥልቅ ሃዘን ስገልጥ በታላቅ አክብሮት ነው።
አርቲስት ዶክተር ጥላሁን ገሠሠ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ለመላው አለም በማስተዋወቅ ረገድ በህይወት ዘመኑ ላበረከተው አስተዋፅኦ ሃገራችን በእጅጉ ከምትኮራባቸው ስመጥር ሰዎች ዘንድ የሚቆጠርና በሃገራችን ሙዚቃ እድገት ላይ ቀዳሚና ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው ታላቅ ሰው ነው።
አርቲስቱ በህይወት ዘመኑ ለአገሩ በጎ አሳቢ፣ ለኢትዮጵያ ልማትና እድገት በዘርፉ የሚጠበቅበትን ሚና የተጫወተ፣ አንጋፋ ሰው ነው።
አርቲስቱ በህይወት ዘመኑ ያበረከተው አስተዋፅኦ ለሌሎች አርቲስቶች አራዓያ መሆን የሚገባው ነው
ለአርቲስቱ በተሰቦችና ዘመድወዳጆች፣ መፅናናትን እመኛለሁ።
ከሰላምታ ጋር

መለስ ዜናዊ
የ ኢ፣ፌ፣ ዴ፣ ሪ፣ ጠቅልቅይ ሚንስትር

እንግዲህ አገሪቱን በዘርና በቋንቋ የከፋፈሉትና ቀንደኛ ዘረኛ የተባሉት ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ፣ ባለፉት ዘመናት፣ ነበረ፣ የሚባለውን የዘር ጭቆና ዋሽተው ለማጋነን ሳይሞክሩ፣ ፕሬዜዳንት ግርማ፣ በእሳቸው ዘመን የነበርን ገና ሳናልቅ የአሁኑን ትውልድ ዋሽተው ለማሳሳት መሞከራቸውና ከሳቸው በፊት ፕሬዜዳንት የነበሩትም የአቶ ነጋሶ ጊዳዳ ዘረኝነት ሲታይ ሁለቱም ለአገሪቱ ፕረዜዳንትነት የተመረጡት ሰወች ለምርጫ የተመዘኑት በጥሩ ኢትዮጵያዊነት ሳይሆን በአክራሪ ዘረኝነታቸው መሆኑን ያስረዳል። እነዚህ ስልጣን ለሌለው ስም ብቻ ሲሉ በስተርጅና ህሊናቸውን የሸጡ ሰወች የኢሉአባቦርንና የበቾን ኦረሞ ህዝብ እንደማይወክሉ ተስፋ አለኝ።

እስቲ ደግሞ አቶ መለስ ዘናዊን ከአንድ ሌላ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ጋር እናነፃፅራቸው።

ዶክተር ብርሃኑ ነጋ፣ ‘’ በጠበንጃ ስልጣን የያዘ መንግሥት ያለ ጠበንጃ አይወገድም ’’ በሚል ይመስላል ‘’በሁሉም መንገድ እታገላለሁ!’’ በማለት እየፈከሩ ነው። ግልጥ መልስ እንዲሰጡ ተደጋግሞ ቢጠየቁም፣ ‘’በሁሉም መንገድ እንታገላለን’’ ከማለት በቀር፣ እሸፍታለሁ ለማለት አልደፈሩም። ሆኖም፣ የጦር ሰፈራቸውን በኤርትራና በዩናይትድስተትስ አድርገው፣ በአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ድጋፍ ተዋግተው ኢትዮጵያን ነፃ ለማውጣት መመኘታቸው የአደባባይ ምስጢር ነው። ትንሽ ግራ የሚአጋባው ግን በዚአው ኤርትራ ባለው የዶክተር ብርሃኑ ጦር ሰፈር አጠገብ ሌሎች ሁለት ድርጅቶች፣ በአቶ ኢሳያስ እየተረዱ ኢትዮጵያን ነፃ ለማውጣት ሳይሆን ከኢትዮጵያ ንፃ ለመውጣት እየተንቀሳቀሱ ነው!

ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ያሉት እውነትነት አለው!
በጠበንጃ ሃይል ዙፋን ላይ የተሰቀለ መንግሥት፣ አምባ ገነን ከሆነ በእርግጥ ያለ ጠበንጃ ሊወርድ አይችልም።
በአንድ በኩል ደግሞ አቶ መለስ ስለዚሁ ጉዳይ አንስተው ሲናገሩ ያሉት፣ ዕውነትንት አለው!
አቶ መለስ እንዳሉት፣መሪወች በመራራው ትግል ሳይሳተፉ እሩቅ በምቾት ተቀምጠው ሌሎችን ተዋጉ ማለት ከትግል ስልትም ሆነ ከሞራል አንፃር አሳፋሪ ሙከራ ነው!

ግራ በሚገባ አነጋገር፣ አቶ ብርሃኑ ነጋ፣ አሜሪካ ተቀምጠው፣ በአቶ ኢሳያስ ድጋፍ ኢትዮጵይያን ንፃ ሲአወጡ፣ አቶ ኢሳያስን አጋር አድርገው ከኢትዮጵያ ነፃ እንወጣለን የሚሉትን ድርጅቶች፣ እንዲሁ በአቶ ኢሳያስ እየተረዱ አሜሪካ ወይም አስመራ ተቀምጠው ሊአስወጉ ነው? ሲአስቡት ራስ ያዞራል! ምናልባት አቶ መለስ፣ እሳትና ጭድን ምሳሌ አድርገው የተናገሩት በሚገባ ሳይገልፀው አልቀረም። ባንድ የጦር ሰፈር፣ባንድ የአገራቸው ጠላት የሚደገፉት ሶስቱም ድርጅቶች፣ፕሮግራማቸው ቢታይ፣ በእውነትም እሳትና ጭድ ናቸው። ወናፉን የጨበጠው ደግሞ ዋናው የኢትዮጵያ ጠላት፣ ኢሳያስ አፈዎርቂ መሆኑን የኢትዩጵያ ህዝብ ሊገነዘበው ይገባል።

አማራጭ ሲጠፋ፣ ወቅቱን የጠበቀ የትጥቅ ትግል በቁምነገር ከተያዘ አያዋጣም አይባልም። ኢሳያስን አምኖ የሚሞከረው ግን ታላቅ ሞኝነት ብቻ ሳይሆን ፅረ ኢትዮጵያዊነት ነው!

የአሁኖቹ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶች የትግል ብርታት፣ እርስ በርስ ሲናቆሩ ነው እንጅ እንቃወማለን በሚሉት መንግሥት ላይ ምንም ፋይዳ ሰርቶ አያውቅም።
የትጥቁ ትግል ወትሮ ቀርቷል! አመችው የሰላማዊ ትግልም ቀጥሎ አመለጠ! በግንቦት7፣ ያ ሁሉ ንፁህ ዜጋ፣ ከመሪዎቹ አንድም አብሮት ሳይኖር ያለርህራሄ ከመጨፍጨፉ በፊት የድርጅቶቹ መሪወች፣ ህሊና ቢኖራቸው ኖሮ፣ የተቆጣውን ህዝብ አባብለውና አረጋግተው፣ ያገኙትን ወንበር ይዘው ፓርላማ በመግባት የሰላም ትግል ቢቀጥሉ ኖሮ፣ እስካሁን ድረስ የወያኔ መንግሥት፣ ወይ ይስተካከላል፣ አለዚያ መፈረጃ ሆኖ ይወድቅ ነበር። አላማቸው በጥድፊያ ስልጣን ለምያዝ ብቻ፣ ስለነበር፣ ለህዝብ እልቂት ምክንያት ሆነው እነሱም የመታሰር እጣ ደረሳቸው። ከተፈቱም በኋላ ህብረት መስርተውና ተጠናክረው ሰላማዊ ብልሃት በመፍጠር ፈንታ፣ ተፈረካክሰው፣ ድንጉጦቹ፣ አገር ጥለው በመሰደድ ከሩቅ ሲአናፉ፣ ቆራጦቹ ደግሞ ፣ አገር ሳይለቁ፣ ግን ያለ ብልሃት ሰላማዊ ትግሉን ቀጠሉ። ብዙ የህሊናም ሆነ የአካል መጉላላትም እንደየቆራጥነታቸው እየተመዘነ ደረሰባቸው። ከሁሉም ቆራጧ ወይዘሪት ብርቱካን ግን በውጭም በውስጥም ያሉት ቢከፋፈሉት ለሳምንት ሊሸከሙት የማይችሉትን መራራ ስቃይ ከተሸከሙት ረጅም ጊዜ ሆነ። የኒህን ቆራጥ ሴት ስቃይ፣ በውጭ አገሮች ተበታትኖ ምንም ሳይጐድልበት በነፃነት የሚፈነድቀው አበሻ፣ መፈክር አንግቦ በመሰለፉ፣ ሻማ አብርቶ በመንጫጫቱ፣ ከልብ ተገንዝቦታል ለማለት ያዳግታል።

የደከሙለትና አሁንም የሚሰቃዩለት ፓርቲአቸው፣ ተበጣብጦና ደጋፊወቻቸው እንደአውሬ ሲባሉ መስማት፣ በኢትዮጵያ አዲስ ነገር አይደለምና እንደ ቀላል ብንቆጥረው፣ አንዲት ልጃቸው ስታድግ አለማየታቸው፣ እናታቸውን ተንከባክበው ለመጦር አለመታደላቸው፣ እንዲሁም የወጣትነት ዘመናቸው በእስር ቤት ማለፉ፣ በወይዘሪት ብርቱካን ላይ የሚአደርሰውን የመንፈስ ጭንቀት(የአካል ምቾት ማጣቱን ብንተወው!) አንድም ደጋፊ ሊሰማው፣ ወይም፣ ሊረዳው አይችልም! ቢረዳው ኖሮ፣ በብልግና አፃፃፍና አነጋገር፣ ዋጋ በሌለው ሰልፍና ጫጫታ፣ ጠላቶቻቸውን እልክ ከማጋባት፣ በጨዋነት፣ በጐ በመመካከር፣ ይቅርታ የሚአገኙበትን መንገድ መፈለጉ እስታሁን ውጤት ባመጣ ነበር! ጀግና የተጠማ ህዝብ፣ የራሱን ፈሪነት መሸፈኛ አድርጐ ጀግናን ማሞካሸት ይውዳል እንጅ፣ የራሱን አገር ሰወች እንደማያውቅ ሁሉ ባለበት አገር የዴሞክራቲክ ምብት ተጠቅሞ ቢንጫጫ፣ እስሩን ያጠብቀዋል እንጅ አያላላውም! ይልቅስ ሁሉም በጥሞና ለያለበት አገር መንግሥታት፣ ያገሩን ሰወች ጠባይና ባህል እያስረዳ፣ ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት መውጫ ሳያጣ፣ ሽንፈት ሳይሰማው፣ ርህራሄ የሚቸርበትን መንገድ፣ ወይዘሪት ብርቱካንም፣ ከባድ ሽንፈት ሳይሰማቸው፣ ይቅርታ የሚአገኙበትን መንገድ፣ መፈለግ ሳያዋጣ አይቀርም ነበር። ከመሰረቱ ይሄ ቢደረግና ወዘሪት ብርቱካን ቢፈቱ ኖሮ፣ ወይም ከጅምሩ ባይታሰሩ፣ ፓርቲአቸው ሳይበጣበጥ፣ እሳቸውም ባላቸው ተወዳጅነት በምርጫው ታልቅ ተስፋ ይኖራቸው ነበር። ይህ ሁሉ አልፏል፣ ግን የሳቸውን ስቃይ ለማቅለልና የፖለቲካ ፓርቲአቸውም እንዲአንሰራራ ከተፈለገ የውይዘሪት ብርቱካን ጉዳይ በብልሃት መያዝ ይኖርበታል።

ሻማ አብርቶ በመማጠንና፣ በሰላማዊ ሰልፍ ተቀስቅሶ፣ ማንም መንግሥት፣ በሰው አገር ጣልቃ ገብቶ፣ወይዘሪት ብርቱካንን በኃይል ለማስፈታት የሚሞክር አይኖርም። ሞኞቹ ብቻ ሳይሆኑ፣ እብዶቹም፣ ይህንን አይስቱትም። ኃያላን መንግሥታትም ቢሆኑ፣ በሰው አገር ጉዳይ ጣልቃ ገብተው፣ ግለሰብን ለመርዳት ወይም ለውጥ ለማምጣት የሚችሉት፣ ያለውን መንግስት በመለመን ብቻ ነው።

እኔ ከሞትሁ ሰርዶ አይብቀል፣ ባዮቹ ደግሞ፣ ኃያላን መንግሥታት፣ ላለው መንግሥት የሚሰጡትን እርዳታ፣ እንዲአቆሙ ይመኛሉ! የእርዳታው መቆም ቀርቶ፣ መቀነስ እንኳን፣ ወገናቸውን ምንያህል፣ እንደሚጐዳ፣ ሳያውቁት ቀርተው ሳይሆን፣ የየግል ቂምና ጥላቻቸው ከረካ፣ ኢትዮጵያ እንዳለች ብትመድም፣ ግድ ስሌላቸው ነው። እንደዚህ ያሉቱ ናቸው የወይዘሪት ብርቱካንን ስቃይ የሚያራዝሙት።

በይፋም ሆነ፣ በውስተታዋቂ፣ ለዘር የተሰለፉ ፓርቲወች፣የተባበሩበት፣ ዋናው ተቃዋሚ ድርጅት፣ መድረክ፣ ምርጫ አሸንፎ፣ ሥልጣን ቢይዝም ሆነ፣ ወይም ሽንፈትን በጥሞና ተቀብሎ፣ በተቃዋሚነት ቢቀጥል፣ ዋናው አጠያያቂ ጉዳይ፣ የራሱ ህልውና ነው። ከጅምሩ፣ ከልብ በኢትዮጵያዊነት ሳይሆን፣ የየዘር ባንዲራውን በልቡ ቀርጾ የተሰለፈ በመሆኑ፣ እንደየዘሩ እንዳይበታተን ያሰጋል።

ዋናው አስጊ ጉዳይ ደግሞ፣ ተቃዋሚወቹ፣ ዘንቦ ተባርቆ፣ ቢመረጡ፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ፣ የገቡትን ቃል፣ አፈፃፀም ላይ ነው።

ከበሮ በሰው እጅ ያምር፣ ሲይዙት ያደናግር፣ የሚለው ተረት፣ እንዳይመጣ ያሰጋል።

ዴሞክራሲ፣ እንደየህዝቦች፣ ንቃተ ህሊና፣ በሂደት እየተለመደ የሚዳብር እንጂ፣ በችሮታ የሚሰጥ አይደለም። በተለይ አሁን፣ አገሪቱ በዘር ተከፋፍላ፣ የኢትዮጵያ ህልውና በሚንገዳገድበት ዘመን፣ የዴሞክራሲ መብት፣ መረን ከመለቀቅ የሚለይበትን፣ የንግግርና የፅሑፍ ነፃነት፣ ከብልግና አፃፃፍና ከህገወጥ ዘለፋ፣ የተለየ መሆኑን፤የመሰብሰብና የመደራጀት መብት፣ ከፅረ ሰላም መደራጀትና፣ ከፅረሰላም ስብሰባወች ጋር ግንኙነት እንደሌለው፣ ህዝቡ እንዲማርና እንዲለምድ፣ መጣር ያስፈልጋል።

ደርግ፣ ያለምንም ደም፣ኢትዮጵያ ትቅደም፣ ሲል፣ መጀመሪያ ከልቡ ነበር።

በሃያኛው ምቶ ክፍለዘመን፣ ድሮ በቀረ፣ ፍፁም በሆነና፣ ሕግ በማይዳኘው፣ ንጉሣዊ አገዛዝ፣የሚማቅቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ እልል ብሎ ይቀበለኛል፣ የሚል ተስፋ ነበረው። በየስፍራው፣ ተቃዋሚ እየተነሳበት፣ የሚጨብጠውን ሲአጣ፣ በዚያ ላይ ደግሞ፣ የኰለኔል መንግሥቱ ፈሪነትና የተፈጥሮ እርኩስ ጠባይ ሲጨመርበት፣ ያለምንም ደም ሲል የነበረው ደርግ፣ የኢትዮጵያውያን ደም፣ እንደ ጎርፍ እንዲዎርድ ምክንያት ሆነ።

ወያኔ ግን፣ ገና ሲነሳ፣ የያዘው አላማ፣ በቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተቀባይነት እንደማይኖረው፣ ስለጠረጠረ፣ ተዘጋጅቶ ነው የመጣው። መላ ኢትዮጵያን፣ በዘርና በቋንቋ፣ከፋፍሎ በመከለል፣ መጀመሪያ፣ ጠንካራ ደጀን ያደረገውን የትግራይን ክፍለሃገር፣ ከጎንደርና ከወሎ፣ ለም፣ መሬት ቆርሶ ካሰፋና ካጠናከረ በኋላ፣ ሌላው ክልል፣ ቢበጣበጥም፣ ቢጨቆንም፣ በፈደራላዊ አሰራር በየራሱ ዘር መሪነት ስር ስለሆነ፣ ወያኔን አያሳማም፣ ብሎ አሰበ። የፌደራሉ መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ ሲያስፈልግም፣ዉሳኔው፣ ሁሉም ክልሎች የሚሳተፉበት ስለሚሆን፣ አሁንም ወያኔ ብቻውን፣ ሊታማ አይችልም። ግን መታማቱ፣ አልቀረም። የፌዴራሉ መንግሥት፣ ዉሳኔ ቢሆንም፣ ያው አቶ መለስ ናቸው የሚታሙት! የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ በተለይ ተቃዋሚው ክፍል፣ በፓርላማ ውስጥ የድጋፍ ድምፅ በሰጡት አድር ባዮች ላይ አይጨክንም! አንድ መሪ፣ የህዝብ ተወካዮችን ውሳኔ አምኖበት በማፅደቁ፣ ሊታማ አይገባም። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ፣ ዉሳኔው ትክክል ቢሆንም እንኳን፣ ተቃዋሚ ፓርቲወች፣ የመለስ ዉሳኔ! በሚል ብቻ ይነቀፋሉ። ኢትዮጵያውያን፣እንደባህል የያዙት አንድ ክፉ ጠባይ አለ! ብዙውን ጊዜ፣ የሚአምኑበትና በልባቸው የሚአደንቁት ጉዳይም ቢሆን፣ እኔ በተናገርሁት፣ እኔ ባደረግሁት ኖሮ በሚል ቅናት ብቻ ይቃወሙታል። ለምሳሌ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት፣ በሶማልያ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት ሲወስን፣ በውጭ ያለው ተቃዋሚ፣ ገና ጉዳዩን ሳይመረምር ተንጫጫ! ጣልቃ አልገባም ቢልም ኖሮ የዚያኑ ያህል መንጫጫቱ አይቀርም ነበር! ይህን የሚአረጋግጥው፣ የኢትዮጵያ ሠራዊት፣ ግዳጁን ፈፅሞ ወደአገሩ ሲምለስ፣ ተቃዋሚወቹ፣ ፈረጠጠ እያሉ ተሳለቁ። ወደሶማሊያ ለመዝመት፣ በተወሰነበት ሰሞን፣ ስለ ጉዳዩ፣ አንዲአብራሩ፣ የአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ፣ የጋበዛቸው አንድ የኢትዮጵያ ተወላጅ ፕሮፌሰር፣ ከሙያ አንፃር ያብራራሉ ብየ በጉጉት ስጠብቅ፣ ገና ንግግራቸውን ሲጀምሩ፣ ‘’ መቸም፣ ፓርላማው እንዲወስን ያደረጉት አቶ መለስ ናቸው. . . .’’ ብለው ስለጀመሩ፣ ምሑርነታቸውን በመናቅ፣ ማዳመጡን ተውሁት! በዚአው ሰሞን በጀርመን ሬድዮ ሌላ ፕሮፌሰር፣ስለዚሁ ጉዳይ ሲአብራሩ፣ የሽሪያ ህግ በሶማሊያ መቋቋም ኢትዮጵያን እንደማይጐዳ ለማስገንዘብ፣ ‘’. . . የሸሪያ ህግ፣ ለምን ያሰጋናል፣ በሳኡዲ አረቢአም አለ . . .’’ ብለው ሲጀምሩ፣ የአሁን ዘመን ፕሮፌስሮችን ታዝቤ ነገሩን ተውሁት።

በመሰረቱ፣ ጉዳዩ ስለሸሪያ ህግ መቋቋም ሳይሆን፣ የትና፣ ማን እንዳቋቋመው ነው ኢትዮጵያን የሚአሳስባት።

የቅርብ ጎርቤት በሆነችው፣ በሶማሊያ፣ የሰከነና፣ በመልካም ጉርብትና የሚያምን፣ መንግሥት ካልተመሰረተ፣ ምንጊዘም ለኢትዮጵያ ጠንቅ ሊሆን ይችላል። የታላቋ ሶማሊያ ምኞት አሁንም ያልጠፋ ከመሆኑም በላይ፣ የኢትዮጵያ ቀንደኛ ጠላት ኢሳያስ አፈወርቂ፣ ለሚሸርበው ደባ፣ ሶማሊያን፣ሌላ ግንባርና የጦር ሰፈር አድርጐ ነው የሚቆጥራት።

ይህ ሁሉ ሃቅ እያለ፣ በአለም በታወቀው የሃይማኖት አክራሪና ሽብር ፈጣሪ፣ በአልቃይዳ፣ የተደገፈ ድርጅት፣ ከኢትዮጵያ ጋር መልካም ጉርብትና የሚፈልገውን ሕጋዊ መንግሥት ገልብጦ ስልጣን ሲይዝ፣ የኢትዮጵያ ጦር ገብቶ አሸባሪወቹን ተቋቁሞ፣ ሕጋዊዉን መንግሥት ወደ ነበረበት በመመለሱ፣ አቶ መለስን የሚነቅፍና የሚኮንን ሰው፣ የስልጣን ጉጉት ያሳበደውና፣ ፀረ ኢትዮጵያ የሆነ ሰው ብቻ ነው!

ስለዚህ ነው፣ ሰይጣን የምለውን ገና ባልወስንም፣ ለአቶ መለስ ዜናዊ በአንዳንድ ትግባራቸው፣ የሚገባቸውን፣ ክብርና ምስጋና አትንፈጓቸው፣ የምለው።
ከማጠቃለሌ በፊት፣ ዘንቦ ጠባርቆ፣ ተቃዋሚው ፓርቲ ቢአሸንፍ፣ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ምን ያህል ጐጂና፣ አሰቃቂ እርምጃ ለመውሰድ ቃል እንደገባ፣ ማሳሰብ እወዳለሁ።

አርሶ አደሩ የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ለመኖር ነው የሚአርሰው፣ ቢባልም፣ በልቶ ያድራል፣ የአየሩ ጠባይ ባልታወከበት ዘመንም፣ እንደአቅሙ፣ ከመክበር ይደርሳል። መሬቱን መሸጥ መለወጥ መከልከሉም፣ በገንዘብ ተደልለው፣ ከሸጡ በኋላ፣ ገንዝቡ ከቁምነገር ሳይውል ቢባክን፣ የልጅ ልጅ ዞሮ መግቢያና፣ በልቶ ማደሪያ የነበረውን፣ መሬት ሲአጡ፣ ዕጣቸው፣ ለማኝና ወጀለኛ፣ መሆን ብቻ ነው። በዝርዝሩ ላይ ለማተት፣ ብዙ ገፅ ስለሚፈጅ፣ ገበሬው ወደ ከተማ ከተሰደደ ብኋላ፣የሚአጋጥመውን፣ አሰቃቂ ኑሮ፣ በብራዚል፣ ከቅርብ ጐረቤትም፣ በኬንያ፣ የደረስርውን ፣መመልከት ይበቃል።

መሬቱ በውርስ በተከፋፈለ ቁጥር የያንዳንዱ ድርሻ ማነሱ አይካድም። ለዚህ መፍትሄው ይህን የሚአስቀር የውርስ ህግ ማውጣት እንጅ ገበሬው በሃብታሞች እየተደለለ መሬቱን ሸጦ ወደ ከተማ እንዲሰደድና የኢትዮጵያ መሬት እንደፊውዳል ዘመን በትቂት ባልፀጋወች ብቻ እንዲያዝ መመኘት ብዙ መስዋእት የተከፈለበትን የመሬት ይዞታ ትግል መቀልበስ ይሆናል.

የኢትዮጵያ፣ አርሶአደር፣ መሬቱን፣ ይሽጥ፣ ይለዉጥ፣ ማለት፣ ታላቅ፣ ጨካኝነት ነው !