የአቶ በረከት “የኢኮኖሚ ዕድገት እያጣጣመ ያለ” ሕዝብ እና አብዮት አዳባባይ

የመንግስት ጉዳዮች ኮሙኒኬሽን ሚኒስትር አቶ በረከት ስምዖን ዛሬም እንደወትሮው ብልሀት እና መረጃ ያልጎበኘውን ዲስኩር ከማሰማት አልሰነፉም፡፡ በቱኒዚያ እና በግብፅ አደባባዮች የተስተዋለውን የሕዝብ አብዮት መነሾ ከኢትዮጵያ ኹኔታ ጋር በማነጻጸር የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሁለቱ አገሮች ሕዝቦች “በተሻለ የኢኮኖሚ እድገትና ሽግግርን እያጣጣመ ነገንም በተስፋ እየጠበቀ መኾኑን” ሲገልጹ የተለመደው የአቶ በረከት ማስተዋል የራቀው ድፍረት አብሯቸው ነበር፡፡
ለአቶ በረከት አሁን በሰሜን አፍሪካ እና መካከለኛው ምስራቅ አገራት እየተቀጣጠለ የመጣው የሕዝብ አመጽ የሚጠበቅ ነው፡፡ ነገር ግን የእርሳቸው ኢትዮጵያ “ተጨባጭ ዴሞክራሲን የተላበሰች፣ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት የተከበረባት እንዲሁም ሕዝቡ በነጻ ምርጫ የፈለገውን የሚሾምባት” የምድር ተምሳሌት ናት፡፡ እናም የሕዝብ ቁጣ “ሲያልፍም አይነካንም” አይነት መልዕክት አስተላለፉ፡፡
ንግግራቸውን ከቁም ነገር መውሰዱ ለምሁራዊ ወግ እንዲበቃ አያደርገውም፡፡ ይሁንና የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት ኾነ ብለውም ይኹን በቸልተኝነት ለኻያ ዓመታት ለዘለቀው ጉዟቸው የሚሰጡት ግምት ከእውነት መራቁ የሚመሩትን ሕዝብ እና አመራራቸው ያመጣውን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ኹነቶች ለመመዘን ያላቸው አቅም እጅጉን ዝቅ ያለ መኾኑን አመላካች ነው፡፡
የምናውቃት የአቶ በረከት ኢትዮጵያ አንድ ነች፡፡ ከቱኒዚያ እና ከግብፅ ሕዝቦች ጋራ የሚያመሳስላት በአምባገነኖች መዳፍ ሥር ለዓመታት መዳከሯ እንጂ በኢኮኖሚ መሥፈርቶች ለማወዳደር የሚያስችል ቅርርብ እንደሌለም እናውቃለን፡፡ በቀላሉ እንኳን በቅርቡ ይፋ የኾነውን የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የፈርጀ ብዙ ድህነት መለኪያ ብንወስድ 90 በመቶ ያህሉ ዜጎቿ “ድኻ” የኾኑባት አገር ከአስር በመቶ ዝቅ ያለ የድኽነት ምጣኔ ካስመዘገቡት ሁለቱ አገራት ጋር ማወዳደሩ የሚያስኬድ አይደለም፡፡ አቶ በረከት “ተስፋ የቆረጠ” ያሉት ሕዝብ ከቱኒዚያ እና ከግብፅ ይልቅ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚገኝም ግልጽ ነው፡፡
በመካከለኛ የገቢ ሰንጠረዠ የሰፈሩት የሁለቱ አገሮች ሕዝቦች የኢኮኖሚያዊ ጥያቄ ዛሬ አንድ ኢትዮጵያዊ ከሚጠይቀው የሕልውና ጉዳይ ጋር ሲነጻጸር የሰማይና የምድር ያህል ርቀት አለው፡፡ ብዙሃኑ ኢትዮጵያዊ የእለት ጉርስን መሸፈን እንደ ስኬት የሚመለከት ነው፡፡ ከእለት እለት እየባሰበት የሚመጣ የኑሮ ውድነት፣ በአመት 20 በመቶ ምጣኔ የሚደርስ ሥራ አጥነት እና በነጻነት ተንቀሳቅሶ የመስራት መብት አለመኖር ዋነኛ የፖለቲካ ኢኮኖሚው መገለጫ ናቸው፡፡ ዜጎች በእኩል ተወዳድረው ሊያገኟቸው የሚገቡ የሥራ ዕድሎች ሙሉ ለሙሉ የተዘጉና የገዢው ፓርቲ ተዋናይ መኾን ብቻውን ዋነኛ መሥፈርት የኾነባት አገር ፤ ሌሎች አገራት ከሚያስፈልጋቸው አብዮት በብዙ እጅ የላቀ አብዮት እንደሚያስፈልጋት ደጋግሞ መናገር ይቻላል።

“መለስኖሚክስ” እና “የፍቅር አዲስ ኢኮኖሚ”

በግልጥ በሚታይ መልኩ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከ97 ምርጫ በኋላ “ልማታዊ መንግስት” የሚል ጽንሰ ሐሳብ ወደ ፖለቲካቸው ሲያስገቡ ኢኮኖሚውን ለማገዝ አዲስ መላ አስከትለው ነበር፡፡ ኢኮኖሚውን ለማገዝ ያመጡት መላ ከምርታማነት ጋር በቀጥታ የተያያዘ አልነበረም፡፡ ይልቁንም ምርታማነት ያልነካቸውን “የምርታማነት ወሬ” በብዛት እና እስኪያሰለች ለሕዝቡ ማድረስ፡፡ ከምንም ተነስቶ የሚያሰግር የኢኮኖሚ መረጃ ይበተናል፡፡ በየትኛውም ጊዜ ቢኾን ከመንግስት የሚወጡ መረጃዎች ታሽተውና ለፖለቲካ ፍጆታ በሚውል መልኩ ተሰልተው ይለቀቃሉ፡፡ ስለዚህም ባለፉት ስድስት አመታት ኑሮ አሽቆለቆለም፤ ተመነደገ የቁጥር መረጃዎች እንዳሰገሩ አሉ፡፡
ይህ የአቶ መለስ “ብልሃት” ማለትም የተሳሳተ የኢኮኖሚ ፖሊሲን በሚፈበረኩ አዎንታዊ መረጃዎች “ማከም” ግን የዓለም አቀፍ ተቋማትን የሚደናግረውን ያህል ከመረጃዎቹ ይልቅ ኢኮኖሚውን ለሚኖረው ማኀበረሰብ የሚያደናግሩ አልነበሩም፡፡ ኑሮን ሲኖረው መረጃዎቹን ሳይሆን ምርቱን የሚናፍቀው ሕዝብ የመለስ ኢኮኖሚን ፉርሽ መኾኑን ይናገራል፡፡
ከወራት በፊት ድምጻዊት ፍቅር አዲስ ነቃዓጥበብ የብር ዶላርን የመመንዘር አቅም መውደቅን ተከትሎ የአንድ ብር ቄጤማ ገበያው ለማዘጋጀት ፍቃደኛ አለመኾኑን ተገንዝባ የሰነዘረችው ጥያቄ በሚያሰግሩ ምትሃት ቁጥሮች “ሐልዮት” የቆመውን “የመለስ ኢኮኖሚ” ገመና የሚገልጥ ነበር፡፡ በወቅቱ ፍቅር አዲስ “ዶላር እና ቄጤማ ምን አገናኛቸው?” ስትል ነበር የጠየቀችው፡፡ ይህ “የፍቅር አዲስ ኢኮኖሚ” የተንዛዛ እና የሚያምታታ ሕልዮት የለውም፤ ነገር ግን በተምታቱ የኢኮኖሚ መረጃዎች የተውሸለሸለው ኢኮኖሚ አቶ መለስ እና አቶ በረከት ከሚያስቡት በላቀ መልኩ ምን ያህል ማህበረሰቡ እየተገነዘበው እንዳለ ነው የሚያሳየው፡፡
ሰሞነኛውም የአቶ በረከት “የኢኮኖሚ ዕድገትን እያጣጣመ ያለ” የተባለ ሕዝብ የአቶ መለስንም ኾነ የፍቅር አዲስ ኢኮኖሚ ያውቃቸዋል፡፡ የመለስ ኢኮኖሚ “በምትሃት ቁጥሮች” ነገር ግን የፍቅር አዲስ ኢኮኖሚ ደግሞ በሚጨበጥ የገበያ መስተጋብር እንደሚገለጥ ያውቀዋል፡፡ ይህም ስሌት ነው ከአብዮት አደባባይ እና ከጣህሪር አደባባይ የትኛው እንደሚርቅ በግልጽ የሚያሳየው፡፡

አቶ በረከት የዘነጉት ነገር . . .?

አቶ በረከት ያነሷቸውን ፖለቲካዊ ጉዳዮች ወደ ጎን ብንላቸው ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች ብቻቸውን አብዮት አደባባይን የበለጠ ቅርብ እና የሚናፈቅ ያደርጉታል፡፡ ዋጋ እየተተመነለት ለኪሳራ የሚዳረገው ነጋዴ፣ ክፍያው እና ድካሙ የማይመጣጠንለት ምንደኛ፣ በምርጥ ዘር እና በማዳበሪ እዳ ኑሮው የተጎሳቆለበት አርሶ አደር፣ ነገ የስራ ዋስትና የሌለው ተማሪ እና ሌሎች የማህበረሰቡ አካላት የግብጽ ዜጎች ጣህሪርን ለነጻነት ከሚናፈቁት በላይ አብዮት አደባባይን ይናፍቃሉ፡፡
አቶ በረከት ግን ይህ የነጻነት ናፍቆት አልገባቸውም ወይም እንዲገባቸው አልፈልጉም፡፡ ማህበረሰቡም እርሳቸው ከሚያስቡት በላቀ የኢኮኖሚውን መረጃ ከኑሮው ምዕራፍ እየገለጠ እንደሚያነብ ዘንግተውታል፡፡ የእርሳቸው መዘንጋት ግን አብዮት አደባባይን ሩቅ፣ ጣህሪርን ግን ቅርብ አያደርግም፡፡