የስልጣን ሽግግር በተመለከተ የወያኔ ሕገ መንግሥት አንቀጽ ክፍተት አለበት ተባለ
አቶ ዮሐንስ ወልደ ገብርኤል አዲስ አበባ በቅሎ ቤት አካባቢ ነው የተወለዱት፡፡ የመጀመርያ ደረጃና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የጨረሱት እዚህ አዲስ አበባ ነው፡፡
በ1978 ዓ.ም. አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ገብተው በ1980 ዓ.ም. በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቀዋል፡፡ በሥራው ዓለም በመጀመሪያ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሥር በሲዳሞና በዝዋይ በከፍተኛ ፍርድ ቤት ዓቃቤ ሕግነት ሠርተዋል፡፡ በመቀጠል ከ1985 ዓ.ም. በኋላ በልዩ ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት በልዩ ዓቃቤ ሕግና በረዳት የልዩ ዓቃቤ ሕግ ሹምነት ሠርተዋል፡፡ በሥነ ምግባርና በፀረ ሙስና ኮሚሽን በዓቃቤ ሕግነትና በኢትዮጵያ ጉምሩክ ባለሥልጣን የሕግ መምርያ ኃላፊና የጉምሩክ ዓቃቤ ሕግ ሆነው የሠሩ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ለ15 ዓመታት ያህል በመንግሥት ተቋማት ውስጥ በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች አገልግለዋል፡፡ ሰለሞን ጐሹ የአስቸኳይ ጊዜ የፖለቲካ ሥልጣን የአመራር ክፍተትን በተመለከተ አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- የአስቸኳይ ጊዜ የፖለቲካ ሥልጣን የአመራር ክፍተቶችን በተመለከተ በኢትዮጵያ ታሪክ የምናገኛቸው እውነታዎች ምን ያሳያሉ?
አቶ ዮሐንስ፡- የአገር መሪዎች ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ እነሱ ለተወሰኑ ጊዜያትም ቢሆን ከቢሮአቸው ሲለዩ የሚያስተዳድሩት ሕዝብ፣ የሚመሩት መንግሥት፣ ሠራዊት፣ አገር ዕጣ ፈንታው ምንድን ነው? የሚለው ሊያስጨንቀን ይገባል፡፡ በአገራችን ታሪክ የሥልጣን አወራረስ ሁልጊዜ የተረጋጋ አይደለም፡፡ ከጥንት ጀምሮ ነገሥታት በሚሞቱበት ጊዜ ሁሌም የሚከሰቱ ኹከቶች ይኖራሉ፡፡ እንደ ጥንቱ አሠራር ከሆነ ብዙ ጊዜ የሥልጣን ሽኩቻ ስለሚኖር የሥልጣን ሽኩቻውን ለማስወገድ የነገሥታት ልጆችና ልዑላን በሙሉ ይሰበሰቡና ወህኒ አምባ ወይም እስር ቤት እንዲገቡ ይደረግ ነበር፡፡ የደርግ መንግሥት ሊመጣ ሲል የአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ከሥልጣን እንደተገረሰሰ በርካታ ልዑላንና የንጉሡ ቤተሰቦች ሕፃናቱ ሳይቀሩ ወደ እስር ቤት እንዲገቡ ተደርጎ ነበር፡፡ የአገሪቱ ታሪክ በዚህ ጉዳይ ላይ ትልቅ አሻራ ጥሎ ማለፉ አይካድም፡፡ ደርግ ይህን ነገር ያደረገው የሥልጣን ሽኩቻው እንዳይመጣ ለማድረግ ነው ወይ? ለሚለው ጥያቄ መልስ መስጠት አስቸጋሪ ነው፡፡ ደርግ ዕርምጃውን ለመውሰድ የአገሪቱን ተሞክሮ እንደ ምሳሌ ወስዶ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አለ፡፡ በ1999 ዓ.ም. እስር ቤት እያለሁኝ የቀጠሮ እስረኞች ወደ ፍርድ ቤት ልንሄድ አውቶቡስ ላይ በምንሳፈርበት ወቅት አንድ በወንጀል ተከሶ የታሰረ ነጋዴ ከደርግ ሦስት ከፍተኛ አመራሮች ጋር ሲቀላለድ እሰማው ነበር፡፡ ለመሆኑ የደርግ ወራሽ ማነው? የሚል ጥያቄ ያነሳላቸዋል፡፡ ከአንዱ የደርግ አባል የተሰጠው ምላሽ “አይ ደርግ የወላድ መካን ነው፤ ወራሽ የለውም፤” የሚል ነበር፡፡ ይኼ ምልልስ ትልቅ የሕገ መንግሥት ጉዳይን ነው የሚያነሳው፡፡ ደርግ የራሱ የሆነ ሕገ መንግሥት ነበረው፡፡ ሥልጣኑ የተወረሰው ግን በሕገ መንግሥቱ መሠረት አልነበረም፡፡
ሪፖርተር፡- አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ የፖለቲካ ሥልጣን አመራርን በተመለከተ ያስቀመጠው ድንጋጌ የለም የሚል ክርክር አለ፡፡
አቶ ዮሐንስ፡- አሁን ያለው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የፕሬዚዳንቱንም ሆነ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሥልጣንን በተመለከተ አንድ አጋጣሚ ቢፈጠርና ሥልጣናቸውንና ኃላፊነታቸውን በሙሉ ጤንነትና በሙሉ ብቃት መፈጸም የማያስችላቸው ሁኔታ ቢከሰት፣ ማን ተክቷቸው ይሠራል ለሚለው ጥያቄ ግልጽ ምላሽ የሚሰጥ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ ፖለቲካውን ወደ ጎን ትተነው ሕጋዊ የሆነ በቂ መልስ የለም፡፡ በነጠረና በተስተካከለ ሁኔታ ሕገ መንግሥቱ ላይ ተቀምጧል ብዬ አላምንም፡፡
ሪፖርተር፡- ክፍተቱ ለፕሬዚዳንቱም የሚሠራ ቢሆንም ሕገ መንግሥቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሰጠው ሠፊ ስልጣን አኳያ ክፍተቱ አደገኛ ነው የሚል ስጋት ያላቸው አሉ፡፡
አቶ ዮሐንስ፡- አደገኛነቱ ምንም የሚያጠራጥርና የሚያከራክር አይደለም፡፡ የውጭዎቹን አገሮች ሕገ መንግሥቶች ትተን እዚሁ አገራችን በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን የነበሩ ሁለት ሕገ መንግሥቶችን ብንመለከት፣ በ1923 ዓ.ም. እና በ1948 ዓ.ም. የወጡት ሕገ መንግሥቶች እንዲህ አይነት ክፍተቶችን ሊፈጠሩ እንደሚችሉ፣ በተለይ በከፍተኛ አስፈጻሚነት ያሉ ሰዎች ከሥራም ብዛትና እረፍት ከማጣት አኳያ፣ ሥራው በተፈጥሮው አድካሚ በመሆኑ የመታመም፣ አቅም የማነስና አቅም የማጣት ችግሮች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ከግምት ውስጥ በማስገባት ምን ዓይነት መፍትሔ መወሰድ እንዳለበት በግልጽ አስቀምጠዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት ችግሮች ባደጉና ከፍተኛ የሕገ መንግሥት ታሪክና ደረጃ አላቸው ብለን በምንወስዳቸው እንደ አሜሪካ ባሉ አገሮች ለብዙ ጊዜ ሲፈታተኑዋቸው ነበር፡፡
ለምሳሌ አሜሪካኖች በጣም ቆይተው ነው እ.ኤ.አ. በ1967 ለዚህ ችግር መፍትሔ የሰጡት፡፡ ይህም የተደረገው በሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ አማካይነት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎች በተለያዩ አገሮች የተቀረፁት ችግሮቹ በሰው ልጅ ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ መሆናቸውን በማመን ብቻ አይደለም፡፡ ጉዳቱ የአገር ስለሆነ ነው፡፡ ሕገ መንግሥት የመንግሥት አወቃቀርን፣ የሥልጣን ሽግግርን፣ የሥልጣን አወራረስን፣ ወዘተ. የሚደነግግ የበላይ ሕግ እንደመሆኑ መጠን፣ እነዚህ ጉዳዮች ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ሊደነገጉ የሚገባውም በሕገ መንግሥት ብቻ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በብዙ አገሮች ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ወይም ምክትል ፕሬዚዳንት አደጋዎች ሲከሰቱ ወይም ዋናው አስፈጻሚ ሥራውን ለመሥራት በማይችልበት ጊዜ ተክተው እንዲሠሩ የሚያስችሉ ድንጋጌዎች አሉ፡፡ በኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ሚና ለመጫወት የሚያስችለው ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ አለ?
አቶ ዮሐንስ፡- በፖርላሜንታሪያዊ ሥርዓት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት ደግሞ ፕሬዚዳንቱ ዋና አስፈጻሚ ነው፡፡ ዋና አስፈጻሚው ሊታመም፣ አቅም ሊያጣ ወይም ሥራ መሥራት የማይችልበት ሁኔታ ሊያጋጥመው፣ እንዲሁም በሞት ሊለይ ይችላል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ሲከሰቱ ማን ነው ተክቶ ዋነኛውን ኃላፊነት የሚወስደው? አሜሪካ ለምሳሌ ለምክትል ፕሬዚዳንቱ ሥልጣኑን ሰጥታለች፡፡ በሌሎች አገሮች ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ ለፓርላማው አፈ ጉባዔ ሥልጣን የሚሰጡ አገሮችም አሉ፡፡
በኢትዮጵያ ይህን ዓይነቱን ክስተት የሚያስተናግድ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ የለንም፡፡ ዋናው አስፈጻሚ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሚያግዝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አለ፡፡ በሕገ መንግሥቱ ተዘርዝሮ የተቀመጠ ሥልጣን ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አልተቀመጠም፡፡ ይልቁንም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተለይቶ የተሰጠውን ሥራ እንደሚያከናውን ነው ሕገ መንግሥቱ የሚገልጸው፡፡ በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማይኖርበት ጊዜ እሱን ተክቶ እንደሚሠራም ተደንግጓል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተለይቶ የተሰጠው ሥራ ካለ እሱን ይሠራል፡፡ ተጠሪነቱም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው፡፡ ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣኑን በውክልና ለይቶ ባልሰጠበትና ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሌለበት ሁኔታ እንዴት ተክቶ ሊሠራ እንደሚችል ግልጽ አይደለም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጊዜያዊ ወይም ቋሚ ሕመም ቢያጋጥመው ማን ተክቶት ይሠራል ለሚለው ጥያቄ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 75 ክፍተት አለው፡፡
በተጨማሪም የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሻሿም ልክ እንደ ሌሎቹ ሚኒስትሮች ነው፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት ነው የሚሾመው፡፡ እንዲያውም የሌሎች ሚኒስትሮች ቢሮዎች ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍ ያለ ኃላፊነት ይሰጣቸዋል፡፡ ለዚህም ይመስለኛል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሙሉ ጊዜ ሥራ እንዲኖረው በማሰብ ሌሎች ሚኒስትር መሥሪያ ቤቶችን እንዲመራ የሚደረገው፡፡ የመጀመርያው መከላከያ ሚኒስትር፣ ሁለተኛው የግብርናና የገጠር ልማት ሚኒስትር፣ ሦስተኛውና የአሁኑ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደግሞ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርን እንዲመሩ የተደረገውም ለዚህ ይመስላል፡፡
ሪፖርተር፡- የሚኒስትሮች ምክር ቤት ተጠሪነት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው፡፡ የሚዋቀረውም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ የፖለቲካ ሥልጣን አመራር ክፍተት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢፈጠር የምክር ቤቱ ሚና ምንድን ነው? ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ህልውና ውጭ ምክር ቤቱ ሥራውን መቀጠል ይችላል?
አቶ ዮሐንስ፡- የሚኒስትሮች ምክር ቤት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ሥልጣን ተክቶ ሊሠራ የሚችልበት የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታዎች ይኖራሉ፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ምን ዓይነት እንደሆነ በሕገ መንግሥቱ ተካቷል፡፡ አሁን የምንነጋገርበት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም የፕሬዚዳንቱ መታመም፣ አቅም ማጣት፣ መደበኛ ሥራን ለመሥራት አለመቻል፣ በሞት መለየት፣ ወዘተ. በዚያ ውስጥ የሚካተቱ አይደሉም፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደ አንድ አካል የጠቅላይ ሚኒስትሩን ኃላፊነት ተክቶ መሥራት ስለመቻሉ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ እንደዚያ አይታየኝም፡፡ ሊሆን የሚችለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሥራ ላይ ካለው አብዛኛውን መቀመጫ ከያዘው ፓርቲ በጊዜያዊነት አሊያም በቋሚነት ለመተካት፣ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመምረጥ፣ ኃላፊነቱን ለማሸከምና ሥልጣን ለመስጠት መሥራት ይኖርበታል፡፡
ሆኖም የተሻለው አማራጭ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ማድረግ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ማሻሻያ ሲደረግለት ፋታ የማይሰጡ አጣዳፊ ጉዳዮችንም ማስተናገድ ይቻላል፡፡ በመሀል ላይ የሚኖሩ ክፍተቶች ሁልጊዜም ኢ-ሕገ መንግሥታዊ የሥልጣን ሽግግርን ሊጋብዙ ይችላሉ፡፡ በአንቀጽ 9(3) ላይ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ የሥልጣን ሽግግር በከፍተኛ ሁኔታ ተከልክሏል፡፡ ነገር ግን ሕገ መንግሥቱ ሊሸፍናቸው በማይችሉ ክፍተቶች ላይ የሚከሰቱ የሥልጣን ሽግግሮች መፍቻ ቁልፍ የለውም፡፡ ብዙ አገሮች እንደዚህ ዓይነት ችግር ገጥሟቸዋል፡፡ መፍትሔ የሚሆኑ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎችንም እንዲቀርፁ አስገድዷቸዋል፡፡ አሜሪካ እ.ኤ.አ. በ1967 ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ከማድረጓ በፊት የዚህ ዓይነት ድርጊቶችን በተደጋጋሚ አስተናግዳለች፡፡ ለምሳሌ በአንድ ወቅት ለአንድ ወር ብቻ የሠራ ፕሬዚዳንቷ በአጋጣሚ በሞት ተለይቷል፡፡ ምክትል ፕሬዚዳንቱ የቀረውን ጊዜ በፕሬዚዳንትነት ቢጨርሰውም የሥልጣን ሽግግሩ ሕገ መንግሥታዊ አልነበረም፡፡ ፕሬዚዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ ከሞቱ በኋላ ነው ችግሩ መፍትሔ እንዲሰጠው ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያው የተደረገው፡፡ በፖላንድ ባለፈው ዓመት በተከሰተው የአውሮፕላን አደጋ 96 ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ፕሬዚዳንቱን ጨምሮ ሲያልቁ፣ አገሪቷ በፍጥነት ሌላ መንግሥት በመመሥረት ሥራው የቀጠለው የፖላንድ ሕገ መንግሥት ችግሩን የሚቀርፍ ድንጋጌ ስለነበረው ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ፓርላሜንታሪያዊ ሥርዓት የምትከተል አገር በመሆኗ ፓርላማው የሚፈጠሩ ክፍተቶችን ለመሸፈን ይችላል የሚል አስተያየትም ይሰነዘራል፡፡
አቶ ዮሐንስ፡- ፓርላማው እንኳን በግልጽ ያልተሰጠውን ሥልጣን ቀርቶ ዋነኛ የሆነውን አስፈጻሚውን የመቆጣጠር ሥልጣኑን እኮ በውክልና ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አሳልፎ የሰጠ የመንግሥት አካል ነው፡፡ አዋጅ ቁጥር 691/2002 በአንቀጽ 34 ላይ የአስፈጻሚ አካላትን ተቋማት ማቀላቀል፣ ማፍረስ፣ ለሁለት መክፈል፣ ተጠሪነታቸውን መቀያየር ሥራ ከፓርላማው ወደ አስፈጻሚ አካልም ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት በውክልና እንዲዘዋወር አድርጓል፡፡ አቅሙ ቢኖረው ለምን አሳልፎ ይሰጣል? ለምክር ቤቱ ከተሰጠ ያው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሰጠ ማለት ነው፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሌላ ጠቅላይ ሚኒስትር የመምረጥ ሥልጣን ሊኖረው ይችላል፡፡ ነገር ግን ሥራውን በአግባቡ እየሠራ ያለና ክፍተቶችን በሚገባ የሚሸፍን ተቋም ስለመሆኑ ግን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡
ሪፖርተር፡- ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ሳይደረግ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ችግር ቢፈጠርና ምርጫ ሳይደረግ ጊዜ ቢቆጠር ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ውጭ እንደ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔና የመሳሰሉ አካላት በጊዜያዊነት ሥልጣን ሊይዙ ይችላሉ የሚል አስተያየት አለ፡፡
አቶ ዮሐንስ፡- የትኛው ባለሥልጣን ጠቅላይ ሚኒስትሩን ተክቶ የመሥራት ብቃት አለው የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችል መረጃ የለኝም፡፡ ሕገ መንግሥቱ ግን በግልጽ ለአንዳቸውም ሥልጣን አይሰጥም፡፡
ሪፖርተር፡- ኢሕአዴግ ከአራት ዘውግ ተኮር ፓርቲዎች የተውጣጣ ግንባር ነው፡፡ ክፍተቱ የተለያዩ ዘውግ ተኮር የሥልጣን ፉክክርን አይጋብዝም ወይ? ለዚህስ በብሔር ላይ የተመረኮዘው የፌዴራል ሥርዓት ክልሎችን ወደ ፉክክሩ እንዲገቡ አያደርግም ወይ?
አቶ ዮሐንስ፡- በብሔር ላይ የተመረኮዘውን የፌዴራል ሥርዓት እንደ ችግር አላየውም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በቋንቋው፣ በሃይማኖቱ፣ በጦርነቱ፣ በሰላሙ፣ በደስታው፣ በፍቅሩ፣ ወዘተ. በጣም የተሳሳረና የተገመደ ሕዝብ ነው፡፡ ይኼ የአመለካከት ጉዳይ ነው፡፡ በደቡብም፣ በምሥራቅም፣ በምዕራብም፣ በሰሜንም ያለው ሕዝብ ለበርካታ ሺሕ ዓመታት መስተጋብር የፈጠረ ስለሆነ፣ ያለውና የነበረው ፖለቲካዊ አሰላለፍ በሕዝቡ ውህደትና አንድነት ላይ ችግር ያመጣል ብዬ አላስብም፡፡
ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአገልግሎት ዘመናቸውን ለመጨረስ ባይችሉና ሌላ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመምረጥ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቢገደድ፣ ሁለተኛው ምርጫ ከመጀመርያው የተለየ ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ አለ?
አቶ ዮሐንስ፡- ገዥው ፓርቲ በሕገ መንግሥቱ በተገለጸው መሠረት ከፍተኛ መቀመጫ አለው፡፡ ፓርላማው የሚወስነው ውሳኔ የፓርቲውን አቋም የሚያንፀባርቅ ነው የሚሆነው፡፡
ሪፖርተር፡- ሕገ መንግሥቱ ኢሕአዴግ ካለው ፍፁም የበላይነት አኳያ አልተፈተነም የሚሉ ኃይሎች አሉ፡፡ ውሳኔዎች በድርድር እንዲያልቁ የሚያደርጉ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችሉ አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቢኖሩ አንቀጽ 75ን ጨምሮ በርካታ የሕገ መንግሥቱ አንቀጾች ይፈተኑ ነበር በሚለው አስተያየት ይስማማሉ?
አቶ ዮሐንስ፡- የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ላለፉት 17 ዓመታት የቆየ ነው፡፡ በአንፃራዊነት አስቀድሞ ከነበረው የደርግ ሕገ መንግሥት በተሻለ የተረጋጋ ሥርዓት ፈጥሯል፡፡ የተቋቋሙት ተቋማት ሥር እንዲይዙ ለማድረግ በቂ ጊዜ ነበረው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ተፈትኗል አልተፈተነም ለማለት ያሉትን ድንጋጌዎች መመርመር ይጠይቃል፡፡ ከሥልጣን ሽግግርና አወራረስ ጋር በተያያዘ ግን በእኔ እምነት የሌሎች ፖርቲዎች ተሳትፎ ይብዛም ይነስም በፓርላማ ደረጃ ነበር፡፡ ገዥውን ፓርቲ መገዳደር የሚችል ቁጥር ይዘው ግን አያውቁም፡፡ ሕገ መንግሥቱ አልተፈተነም ለማለት በጣም ይከብዳል፡፡ አሁን እየተነጋገርን ያለው ጉዳይ ግን እስካሁን እንደ ችግር ታይቶ ውይይት አልተደረገበትም፡፡ እናም አንቀጽ 75 አልተፈተነም ሊባል ይችላል፡፡
ሪፖርተር፡- ሁሉም የቀደሙት የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥቶች እንዲረቀቁ ካስቻሉዋቸው መንግሥታት የተሻለ ዕድሜ አልነበራቸውም፡፡ የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት ከኢሕአዴግ ዘመን የመሻገርና በሌሎች መንግሥታት ሥራ ላይ የመዋል ዕድል አለው?
አቶ ዮሐንስ፡- ሁሉም ሕገ መንግሥት የመንግሥትን አደረጃጀትንና የሥልጣን አወራረስን ማዕከል ተደርጎ ነው የሚወጣው በዋናነት፡፡ በ1948 ዓ.ም የወጣው የተሻሻለው የአፄ ኃይለ ሥላሴ ሕገ መንግሥት አንድ የሆነ አደጋ ቢፈጠር ወራሾቹ እነማን እንደሆኑ በዝርዝር የሚተነትን ድንጋጌ ነበረው፡፡ ደርግ ይህን ድንጋጌ አግዶት ነበር፡፡ በሕገ መንግሥቱ ወራሽ ተደርገው የተቀመጡት ልዑል አልጋ ወራሽ ሥልጣኑን እስሚይዙ ድረስ (በወቅቱ ታመው ስለነበር ሥልጣን መያዝ የሚችሉበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ በተጨማሪም ውጭ አገር ነበር የነበሩት) ሥልጣን መያዙን በመጀመሪያ ደንግጎ ነበር፡፡ በኋላ ላይ ያው ይህንንም ድንጋጌ ሽሮታል፡፡ ሕገ መንግሥት የአገርን ተጨባጭ ሁኔታ፣ የሕዝቡን ሁኔታ፣ ትስስር፣ አኗኗር፣ ወግ፣ ባህል፣ ልማድ፣ ታሪክ፣ ወዘተ. አገናዝቦ መውጣት ይኖርበታል፡፡ ይኼንን ያገናዘበ ሕገ መንግሥት ከሕዝቡና ከአገሪቱ ጋር ዘላቂ ነው የሚሆነው፡፡ ከዚህ ጋር ተገናዝቦ ያልውጣ ሕገ መንግሥት ዘላቂነት ላይኖረው ይችላል፡፡
ሪፖርተር፡- ይፋ በሆነው የመንግሥት አቋም የኢፌድሪ ሕገ መንግሥት እስካሁን ምንም ዓይነት ማሻሻያ አልተደረገበትም፡፡ ምሁራን በእርግጥ በሕገ መንግሥት ማሻሻያነት የሚጠቅሷቸው ምሳሌዎች አሉ፡፡ ለምሳሌም ከብሔራዊ ሕዝብ ቆጠራ፣ ከግብር ሕግ፣ ከሕገ መንግሥት ቀን ጋር የተያያዙትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ገዢው ፓርቲ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይን ለምንድን ነው የሚፈራው?
አቶ ዮሐንስ፡- ሕገ መንግሥት አገርና ሕዝብን ለማስተዳደር የሚቀረፅ ሰነድ ነው፡፡ ትልቅ ሰነድ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ሰነዶች የሕዝቡን ታሪክ፣ ወግ፣ ባህል፣ እምነትና ልማድ በሙሉ አካተው አገሪቱ የምትመራበት ዋነኛ ትልቁ ሰነድ ነው፡፡ ይኼን የሕግ ሰነድ በየጊዜው የሕዝቡንና የአካባቢውን ተጨባጭ ሁኔታ በማገናዘብ መለወጥና ማስተካከል የማይቻል ከሆነ ዕጣ ፈንታው አደገኛ ነው የሚሆነው፡፡ ሕገ መንግሥት ማሻሻል እጅግ አስቸጋሪና ከበድ ያለ ዕርምጃ ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም እንደ ሌሎች ሕጎች ለማሻሻል ቀላል አይደለም፡፡ ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻል የሚያስፈልጉ ዕርምጃዎች፣ ድምጾች፣ ውሳኔዎች እንደ ሌሎች የበታች ሕጎች አይደሉም፡፡ በዚህም ምክንያት በጣም አስጨናቂ ሊሆን ይችላል፡፡ ቢሆንም ግን መሻሻል በሚያስፈልግበት ሁኔታ፣ ጊዜና ወቅት መሻሻል ደግሞ ይኖርበታል፡፡ ይኼ ጥያቄ የሕግ የበላይነት ጥያቄ ነው፡፡ አስፈላጊዎቹን ማስተካከያዎች ማድረግና ዝግጁ ሆኖ ማቅረብ ካልቻለ ውጤቱ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡
የኢፌድሪ ሕገ መንግሥት ከወጣ በኋላ እንዳልከው ሙከራዎች ተደርገዋል እንጂ በተጨባጭ የተከናወነ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ አልነበረም፡፡ ውሳኔ ለመስጠት የሚወስደው ጊዜ ውስብስብነትና አስቸጋሪነት ሊሆን ይችላል የሕገ መንግሥት ማሻሻያ እንዳይደረግ የሚያደርገው፡፡ ዞሮ ዞሮ ሌላ አማራጭ ዘዴ የለም፡፡ ሕገ መንግሥት ሳይሻሻል በአማራጭ የሚከናውን ተግባር በሕገ መንግሥቱ መስተካካል፣ መደንገግና መከናወን ያለበት ትልቅ የአገር ጉዳይ ከሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ውጪ በሌሎች ሕግጋት ማስተካከል የሚቻል አይደለም የሚሆነው፡፡ ይኼ የሕጎችንና የሥልጣንን እርከን የሚያፋልስ ነው የሚሆነው፡፡ በሌሎችም አገሮች የዚህ ዓይነት አስጨናቂ ሁኔታዎች ቢፈጠሩም ዞሮ ዞሮ ግን ማሻሻል በሚገባው ጊዜ ተገቢው ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ እንዲሻሻል የተደረጉባቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡ በዚህ ሕገ መንግሥት ላይ የጨመረ ወይም የቀነሰ ተብሎ ልክ እንደ ወንጌል ወይም እንደ ቁርዓን የሚነገር ሰነድ አይደለም፡፡ የሕግ ሰነድ ነው፡፡ ሕዝብና አገር የሚተዳደርበት ነው፡፡ የሃይማኖት ድርሳን አይደለም፡፡ ተግባራዊ የሚሆን፣ የሚፈጸምና ሌሎችንም ሕጎች የሚገዛ ሕግ ስለሆነ መስተካከል ባለበት ጊዜ መስተካከል አለበት፡፡
ሪፖርተር፡- አንቀጽ 75 አሁን ያለውን ይዘት ከመያዙ በፊት የሕገ መንግሥት አርቃቂው ቡድን ያቀረበው ሌላ አማራጭ አልነበረም?
አቶ ዮሐንስ፡- አንድ የተለየ ቡድን በዚህ መንገድ እንዲቀረጽ አድርጓል ብዬ አላምንም፡፡ ከአንዳንድ ሰዎች ጋር የሐሳብ ልውውጥ ሳደርግ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማይኖሩበት ጊዜ›› የሚለው የአንቀጽ 75 ክፍል በሰፊው ሊተረጎም እንደሚገባ ይከራከራሉ፡፡ በመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ አንድ አደጋ ቢከሰት ሥራን በአግባቡ የማከናወን ሁኔታ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ አለው ብለው ያስረዳሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ወዲያው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተክቶ ይሠራል ሲሉም ይገልጻሉ፡፡ ለእኔ ይኼ አያሳምነኝም፡፡ ‹‹አለመኖር›› ጊዜያዊ አልያም ቋሚ ሊሆን ይችላል፡፡ ‹‹አለመኖር›› ያለውን ሕጋዊ ትርጉም ካየን ግን ቋሚ ወይም ዘላቂ ሥራ ማከናወን አለመቻልን የሚጨምር አይደለም፡፡ በአንድ ቦታና አካባቢ ከመኖርና ካለመኖር ጋር የተያያዘ ትርጉም ነው ያለው፡፡ ለአጭር ጊዜ ወይም ለረዥም ጊዜ በአንድ አካባቢ አለመኖርን የሚያሳይ ነው፡፡ በሕመም ሥራን መሥራት አለመቻል በዚህ ውስጥ የሚካተት አይደለም፡፡ በቦታው ባይኖርም ካለበት ቦታ ከወከለው አካል ሪፖርት የሚቀበልና ውሳኔ የሚወስንን አካል ነው የሚመለከተው፡፡
ሪፖርተር፡- ከአስቸኳይ ጊዜ የፖለቲካ ሥልጣን አመራር ክፍተት ጋር በተያዘ ትልቁ ስጋት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሲቪል ተቋማት ብቻ ሳይሆን የወታደራዊ ኃይሉም አዛዥ የበላይ ናቸው፡፡ ጦር ኃይሉ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከሥልጣን ሽግግር ጋር በተያያዘ ትልቅ ሚና ያለው ነው፡፡ ይህ ክፍተት ቀዳዳ ሊከፍት አይችልም?
አቶ ዮሐንስ፡- በፖለቲካው ማን አቅምና ጥንካሬ አለው? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ለጉዳዩ ቅርብ አይደለሁም፡፡ ያለ ጥርጥር ሠራዊትን የሚመራው ዋና አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው፡፡ የመከላከያው ሠራዊት ሚኒስትር ሲቪል መሆን እንዳለበት ሕገ መንግሥቱ አስቀምጧል፡፡ የዚህ ዓይነት ተፅዕኖዎችን ለመከላከል ይመስላል፡፡ ባልተለመደ ሁኔታ አንቀጽ 9(3) ላይ በሕገ መንግሥቱ ካለው የሥልጣን አወራረስ ውጭ የሚያዝ ሥልጣን ኢ-ሕገ መንግሥታዊ መሆኑን የደነገገው እነዚህን ስጋቶች ለማስወገድ ይመስለኛል፡፡ ቢያንስ በሕግ ደረጃ ይኼን እንደ ስጋት አላየውም፡፡