ለሕዝበ ሙስሊሙ ጥያቄዎች መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ መሪዎች ፖሊስ ጣቢያ ተይዘው ተለቀቁ

ኡስታዝ አቡበከርና ኡስታዝ አህመዲን ዛሬ ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ተኩል አካባቢ ዘነበ ወርቅ እየተባለ በሚጠራው ሠፈር በመኪና እየተጓዙ ሣሉ ተይዘው ለአራት ሰዓታት ያህል እሥር ቤት ውስጥ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡

በጉዞ ላይ ሣሉ በአንዲት የግል ሠሌዳ ባላት ተሽከርካሪ ውስጥ የነበሩ የሲቪል ልብስ የለበሱ ሰዎች አስቁመዋቸው ወደራሣቸው መኪና ካስገቧቸው በኋላ ወደአዲሱ የአዲስ አበባ ፖሊስ ሕንፃ እንደወሰዷቸው ገልፀዋል፡፡

እዚያ እንደደረሱም በተናጠል ሁለት ሰዓት ለሚሆን ጊዜ በሁለት ባዶ ክፍሎች ውስጥ ካስቀመጧቸው በኋላ እንደዚያው በተናጠል ወደቢሮ እየጠሩ “እኛ የመጣነው ካንተ ጋር ልንወያይ አይደለም፤ ማስጠንቀቀያ ልንሰጥህ ነው፤ እየሆነ ባለው ሂደት ውስጥ ሁለን ነገር የምታደርገው አንተ ነህ፤ የምታደርገውን ነገር ሁሉ እናውቃለን፤ ከተቃዋሚዎች ጋርም ግንኙነት እንዳለህ እናውቃለን፤ ሁሉም መረጃ አለን፤ የምታደርጉትን፣ ሕዝብን በሕዝብ ላይ የምትቀሰቅሱትን፤ ዓላማችሁ ዕምነት አይደለም፤ ፖለቲካ ነው” እንዳሏቸው አመልክተዋል፡፡

ሊሰሟቸውም ፍቃደኛ አለመሆናቸውንና የሚሰጧቸውም “የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ” መሆኑን፤ “ከእናንተ ጋር ፍርድ ቤት በመመላለስ የምናጠፋው ጊዜ የለም፤ የራሣችንን እርምጃ እንወስዳለን” ያሏቸው መሆኑን ሁለቱም በየራሣቸው ተናግረዋል፡፡

በኋላም ከቀኑ ሰባት ሰዓት አካባቢ ቀደም ሲል በእሥረኛ ደንብ መሠረት የወሰዱባቸውን የግል ንብረቶቻቸውን መልሰውላቸው እንደለቀቋቸው አመልክተዋል፡፡

ከተያዙበት ጊዜ ጀምሮ ሰዎቹ ካሣይዋቸው ማመናጨቅ፣ የኃይል ቃላትና ማስጠንቀቂያዎች ሌላ የደረሰባቸው የአካል ጥቃት አለመኖሩን ኡስታዝ አቡበከርና ኡስታዝ አህመዲን አመልክተዋል፡፡

ዝርዝሩን የያዘውን ከሁለቱም ጋር የተደረገውን ሙሉ ቃለምልልስ ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡

(ገፁ ሲከፈት የተደራረቡ ወይም የተረበሹ ድምፆችን የሚሰሙ ከሆነ ከማጫወቻዎቹ አንደኛውን ብቻ አስቀርተው የቀሩትን ያቁሟቸው፡፡)